Sunday, 25 December 2016 00:00

ጄቲቪ እና ካሌብ ፊልም ፕሮዳክሽን እየተወዛገቡ ነው

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(5 votes)

ጄቲቪ ኢትዮጵያ እና ካሌብ ፊልም ፕሮዳክሽን፤“ሻሞ” በተሰኘው ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ሰበብ እየተወዛገቡ ነው፡፡ ካሌብ ፊልም ፕሮዳክሽን፤“የድራማው 3 ክፍል ከእውቅናዬ ውጪ ተላልፏል”ብሏል፡፡ ጄቲቪ በበኩሉ፤ ‹‹ውንጀላው የጣቢያውን
መልካም ስም ለማጥፋት የተወጠነ ሴራ ነው›› ሲልአስተባሏል፡፡ ዘወትር እሁድ በየሳምንቱ 4፡30በጄቲቪ የሚተላለፈውን “ሻሞ” ድራማ፤ በተከታታይ ለ18 ሳምንታት ለእይታ ሲያቀርብ የነበረው ካሌብ ፕሮዳክሽን፤ “ጄቲቪ ከስምምነትና ከውለታ ውጭ ጉዳት
አድርሶብኛል›› ብሏል፡፡ ጄቲቪና ካሌብ ፊልም ፕሮዳክሽን በተዋዋሉት መሰረት፤ ለድራማው ስፖንሰሮችን ጣቢያው ሊያመጣ
ቃል ቢገባም ይሄን ባለማድረጉ የፊልም ፕሮዳክሽኑ የራሱን የማስታወቂያ ኤጀንቶች አቋቁሞ ማስታወቂያና ስፖንሰር
ለማምጣት ሞክሯል ያሉት የፕሮዳክሽኑ ኃላፊዎች፤የቴሌቪዥን ጣቢያው ምቹ ሁኔታዎችን ባለመፍጠሩ፣ድራማው ከስፖንሰር ሊያገኝ የሚገባውን ጥቅም አጥቷል ብለዋል፡፡ “በተከታታይ በደብዳቤ፣ በቃልና በስልክ ምላሽ ለማግኘት ወደ አቶ ዮሴፍ ገብሬ ብንደውልም ብንፅፍም ምላሽ ባለማግኘታችን ውላችንን ለማቋረጥ ተገደናል”ያለው ካሌብ ፊልም ፕሮዳክሽን፤ “ውላችንን ከክፍል 16 በኋላ ብናቋርጥም፣ ጣቢያው ከድርጅታችን እውቅና ውጭ ድራማውን ማስተላለፉ ህገ-ወጥነት ነው” ሲል
ወቅሷል፡፡የፊልም ፕሮዳክሽኑ አያይዞም፤ ከፍተኛ የቴክኖሎጂ ጥራት ባላቸው ካሜራዎች፣ በሰለጠኑ ባለሙያዎችና
በጥሩ ፕሮዳክሽን ሰርተን የምንሰጣቸውን ድራማ፤ ‹‹ወደማሰራጫ ጣቢያው ስንልከው የምስልና የድምፅ መለያየት
ያመጣል›› በሚል ለተመልካቹ በወረደ ምስል ድራማው እንዲታይ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ተናግረዋል። ‹‹ችግሩን
ለማስተካከል ብቃት ያለው የቴሌቪዥን ባለሙያ ባለመኖሩ፣ ይህን ከፍተታቸውን በእኛ ድካም ሊሸፍኑ ይሞክራሉ” በማለት ጄቲቪን ነቅፏል፡፡‹‹ጣቢያው፤ ‹‹በዝነኞች የሙዚቃ ምርጫ›› እና በ“ጆሲ ኢንዘሃውስ ሾው›› እንግዳ ሆነው የቀረቡት እንደነ አርቲስት ገለታ ገ/ፃዲቅ፣ ኤልሳቤት መላኩና መሳይ ተፈራ ያሉ የሻሞ ድራማ ተዋንያን፤ በእንግድነታቸው ወቅት ስለ ድራማው እንዳይናገሩ፣ የጣቢያው ባለቤት ጆሲ ገብሬ ከልክሏቸዋል የተናገሩትንም በኤዲቲንግ በመቆራረጥ፣ ድራማው እንደ ሌለ ለማስመሰል ሞክሯል›› ያለው የፊልም ፕሮዳክሽኑ፤ ‹‹ይህ ሁሉ ጣቢያው ለኪነ ጥበቡ ያለውን ዝቅተኛ ግምት የሚያሳይ ነው›› ብሏል፡፡ ችግሮቹ በንግግር እንዲፈቱና መፍትሄ እ ንዲመጣ በ ቃልም በ ደብዳቤም በ ተደጋጋሚ አሳውቀናል ያለው ፊልም ፕሮዳክሽኑ፤ ‹‹የጄቲቪ ስራ ኢትዮጵያዊነት መልካምነት” ከሚለው መርሁ ጋር በእጅጉ የሚጋጭ ነው ሲልም ተችሏል፡፡ አዲስ አድማስ በጉዳዩ ዙሪያ ማብራሪያ የጠየቃቸው የጆሲ መልቲ ሚዲያ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ አብረሀም አለማየሁ ‹‹ውንጀላው ተራ አሉባልታና በጥረትና በቁርጠኝነት ተሰርቶ፣ ተወዳጅ የሆነውን የጄቲቪን ስም ለማበላሸት የተወጠነ ሴራ ነው›› ብለዋል።
የድራማው ሶስት ክፍል ያለ እውቅናዬ ተላልፏል የተባለው ሀሰት መሆኑን ጠቁመው ለ3 ወር የሚሆን ስራ አንዴ እንደተሰጣቸው ገልፀዋል፡፡ የምስል ጥራትን በተመለከተ፣ ጄቲቪ የአየር ሰዓት ከመስጠት ውጭ በድራማው ቀረፃም ሆነ ኤዲቲንግ ላይ እንደማይሳተፍ ገልፀው፣ ‹‹የድራማው ፕሮዲዩሰር ካሌብ ፊልም ፕሮዳክሽን፣ ሰርቶ ያመጣውን ድራማ ከመልቀቅ
ውጭ በፊልሙ ጥራት ልንጠየቅ የምንችልበት አንድም ምክንያት የለም›› ብለዋል፡፡‹‹በየትኛውም አጋጣሚ ለድራማው ስፖንሰር
ለማምጣት ጄቲቪ ውል አልገባም›› ያሉት የህዝብ ግንኙነት ሀላፊው ‹‹ይሄ በየትኛውም አሰራር የተለመደ አይደለም፤
እኛ ግን ከውል ውጭ ደራሲውንና ዳይሬክተሩን እንዲሁም ተዋንያኑን ለማበረታታት፣ ራሳችን ለድራማው የ400 ሺህ ብር ስፖንሰር በማምጣት የሚገባውን ከፍለናል›› ብለዋል፡፡ “የድራማውን ደራሲና ዳይሬክተር የጄቲቪ አመራሮች በአካል አግኝተው፣ የድራማውን የይዘትና የምስል ጥራት እንዲያስተካክል ጠይቀውት፣አሻሽላለሁ ብሎ ቢስማማም አለማሻሻሉን፤ በዚህ
የተነሳም ስፖንሰር አድራጊዎቹ ውል ማቋረጣቸውን፣ይሄን ተከትሎም ደራሲና ዳይሬክተሩ ተስፋ ቆርጦ፣ ወደ
ስም ማጥፋት መሄዱን አቶ አብርሃም ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡ ‹‹በቴሌቪዥን ጣቢያው በእንግድነት ቀርበው ስለ ድራማው እንዳያወሩ ሆን ተብለው ተከልክለዋል የተባለው ከእውነት የራቀ ነው›› በማለት ያስተባበሉት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው፤ “ይህ ከአንድ ባለሙያና የጥበብ ሰው ነኝ ከሚል የሚመነጭ አይደለም፤ የፕሮግራሙ ቅጂ በጄቲቪ የሚገኝ በመሆኑ ማየት ይቻላል፤ እነ ኤልሳቤት መላኩ ስለድራማው በደንብ ተናግረዋል›› ብለዋል ኃላፊው፡፡ ደራሲና ዳይሬክተሩ ያለበትን የአቅም ውስንነትና
ተስፋ መቁረጥ ለመሸፈን፣ በ8 ወራት አጭር ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ ተቀባይነት ያገኘውን የቴሌቪዥን ጣቢያ ስም
ለማጠልሸት የሚያደርገውን ሩጫ፤ በህግ ለመፋረድ በዝግጅት ላይ ነን” ብለዋል የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው፡፡

Read 5695 times