Sunday, 25 December 2016 00:00

ተሃድሶ፣ ግምገማና የሥልጣን ሹም ሽር

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

የኢህአዴግ ጥልቅ ተሃድሶና ግምገማ እንዲሁም ሹም ሽር ቀጥሏል፡፡ በፊት አውራሪነት የኦሮሚያ፣ከዚያም የአማራ፣በቅርቡ ደግሞ የትግራይ ክልል ሹም ሽር አድርገው አዳዲስ ካቢኔዎች መስርተዋል፡፡ የህዝብ ተቃውሞና ብሶትን መነሻ አድርገው የፌደራሉን ጨምሮ በየክልሉ የተቋቋሙት ካቢኔዎች መለያቸው ምሁራንን በብዛት ማሰባሰባቸው ነው፡፡ በተለይ የትግራይ ክልል፣ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ዶክተር ምሁራንን (PHD) በካቢኔው በማካተት ቀዳሚው ሳይሆን አይቀርም፡፡
ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ባለፈው ጥር ወር አዲስ የካቢኔ ተሹዋሚዎችን ለፓርላማ አቅርበው ባጸደቁበት ወቅት፤ሹመቱ ከወትሮው በተለየ ከፓርቲ ታማኝነት ይልቅ ለትምህርት ዝግጅትና ብቃት ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት የተከናወነ መሆኑን ጠቁመው አዲሶቹ ሚኒስትሮች ለህዝብ ጥያቄዎች ምላሽ ይሰጣሉ ብለው እንደሚያምኑ ገልጸው ነበር፡፡ የአገሪቱ ተቃዋሚዎችና ፖለቲከኞች ግን በዚህ አይስማሙም፡፡ የስልጣን ሹም ሽሩ ለህዝብ ጥያቄዎች ምላሽ ከመስጠት ጋር አይገናኝም ባይ ናቸው፡፡ እንዴት? ለምን?  
የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፤በኢህአዴግ ተሃድሶ፣ግምገማና ሹም ሽር ዙሪያ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችና ፖለቲከኞችን አነጋግሮ አስተያየታቸውን አጠናቅሮታል፡፡  ለፖለቲካዊ ችግሮች መፍትሄው ፖለቲካዊ ውይይት ነው፡፡ ሃሳቦች አዕምሮን ከአዕምሮ የሚያገናኙ ድልድዮች ናቸው፡፡

                       “ሹመኞቹ የተማሩ ስለሆኑ ብቻ ለውጥ አይመጣም”
                                 ጁሃር ሳዲቅ (የመጽሄት አምደኛ)

    ተሃድሶ እየተባለ በስፋት ሲነገር እንሰማለን። በእኔ እይታ ምንም የታደሰ ነገር የለም ባይ ነኝ። መታደስ ወይንም ተሃድሶ ማለት ከዚህ ቀደም የነበረውን መጥፎ አስተሳሰብ፣ አመለካከት፣ ፖሊሲ፣  ባህል ወይም ልማድ ትቶ ወደ ጥሩው አሊያም ወደ መልካሙ መለወጥ መቻል ማለት ነው፡፡ ገዢው ፓርቲ ታደስኩ ሲል ምኑ እንደታደሰ ባይገባኝም፣ታደስኩ ካለበት ጊዜ አንስቶ ግን ለህዝቡ ምንም ጠብ ያለለት ወይንም የተለወጠ ነገር አላየንም። በተለይ ኢህአዴግ ከህገ መንግስቱ ጋር እርስ በእርሱ የሚጋጨውን የፓርቲ ፖሊሲ፣ በቁርጠኝነት ማደስና  መለወጥ እስካልቻለ ድረስ ሌላውን ምንም ያህል ቢለዋወጥ ተሃድሶ ሊባል አይችልም፡፡ ኢህአዴግ እስካሁን መታደሱን ያሳየበት አንድም ነገር አልሰራም፡፡ ቢያንስ ህዝቡ ያነሳቸውን  ዘርፈ ብዙ ጥያቄዎች፣ የመወያያ ርዕስ አድርጎ ሲወያይበትና ሲያወያይበት አልታየም፡፡ ይህ ገዢው ፓርቲ እንዳልታደሰ ከሚያሳዩ ነጥቦች አንዱ ነው፡፡ ሌላው ታደስኩ ካለ በኋላ እንኳን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ያለማንሳቱ ነው፡፡  የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን ሳይሆን ለማሰርና ለማስፈራራት የታወጀ ነው የሚመስለው፡፡ ኢህአዴግ ዋናው ችግር የራሱ የመልካም አስተዳደር እጥረት መሆኑን በአደባባይ ማመኑ ይታወቃል፡፡ ይሄን  ካመነ በኋላ ታዲያ ዜጎችን ማሰርና ማንገላታት ምን አመጣው? ለህዝብ ብሶት ተጠያቂ በሆኑ የራሱ ባለስልጣናት ላይ እርምጃ በመውሰድ ነበር መታደስ የነበረበት፡፡   
ኢህአዴግ ድርጅቴን ገምግሜ አዋቅሬዋለሁ ቢልም ከሥልጣን የተባረሩት የመንግስት ሃላፊዎች በምን የግምገማ መስፈርት ተገምግመው እንደተነሱ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ የተነሱበትን ምክንያት፣ ጥፋታቸውን ወይም ጉድለታቸውን በግልጽ ልናውቅ ይገባ ነበር፡፡ ኢህአዴግ ግን አለባብሶ ለማለፍ የፈለገ  ይመስላል፡፡ የአሁኖቹ ሹመኞች የተሻለ የትምህርት ደረጃ እንዳላቸው ተነግሯል። ከዚህ በፊት የነበሩትም ባለስልጣናት ቢያንስ የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው መሆኑ ይታወቃል፡፡ ለምሳሌ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ሚኒስትር የነበሩት አቶ ጌታቸው ረዳ፤ የመቀሌ ዩኒቨርስቲ መምህር የነበሩ ናቸው፡፡ እና  የግምገማው መስፈርት ግራ ያጋባል፡፡ የእውቀት ማነስ? የቁርጠኝነት ጉድለት? የፖለቲካ ውሳኔ? ----አናውቅም፡፡
የኢህአዴግ ጥልቅ ተሃድሶ ዋና ጉዳይ ሹም ሽር ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በሹም ሽሩ አዳዲስ ቴክኖክራቶች ወደ ሥልጣን መምጣታቸው ተነግሯል፡፡ ግን ኢህአዴግ እነዚህን ሰዎች ከየት ነው ያመጣቸው? እንዴትስ ሊመረጡ ቻሉ? የሚለው ዋና ጥያቄ ነው፡፡ አዳዲሶቹን የካቢኔ አባላት ከየትም አላመጣቸውም፡፡
በራሱ በኢህአዴግ የፓርቲ ፖሊሲ ስልጠና የተመለመሉ፣ ከፓርቲው ጋር አብረው የሰሩ፣ በኢህአዴግ ማህፀን ተፀንሰው የተወለዱ ናቸው። ከዚህ አንጻር  በአዲሱ ካቢኔ ለውጥ ይመጣል የሚል እምነት ጨርሶ የለኝም። ምክንያቱም ከፓርቲ ፖሊሲ ውጪ በራሳቸው ያመኑበትን፣ ህዝብን ይጠቅማል ያሉትን ለመስራት አቅሙም ሥልጣኑም አልተሰጣቸውም፡፡ ታዲያ ከበፊቶቹ ባለሥልጣናት በምን ተለይተው ነው ለውጥ እንዲያመጡ የሚጠበቀው?! የተማሩና የተመራመሩ በመሆናቸው ብቻ የሚመጣ ለውጥ የለም፡፡  

------------------

                  “ኢህአዴግ ለተሻለ ውይይት ራሱን ማዘጋጀት አለበት”
                      ዶ/ር ባንትይገኝ ታምራት (የኢዴፓ ም/ፕሬዚዳንት

     በመጀመሪያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ለምን አስፈለገ የሚለውን ነገር ማየት ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ተገቢ ነው አይደለም የሚለውን ስንመዝን፣ አንደኛ ኢትዮጵያ ውስጥ የገዥው ፓርቲና የመንግስት ሚና ባልለየበት ሁኔታ ኢህአዴግ ለ25 ዓመታት ይህቺን ሀገር በሚመራበት ወቅት የተለያዩ አይነት በደሎች ደርሰዋል፡፡ ለእስር የተዳረጉ ሰዎች አሉ፡፡ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽና ሌሎችም መብቶች በሚገባ ያልተከበሩባት ሀገር ነች። ከዚህ አኳያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከመታወጁ ቀደም ብሎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአደባባይ፤ “ህዝብን በድለናል” ብለው ተናግረውም ነበር፡፡ ህዝብን በድናል ሲባል ለኔ እስከሚገባኝ ድረስ መንግስታዊ ስልጣንን በመጠቀም ዜጎች እንዲታሰሩ ማድረግ፣ የገንዘብ ምዝበራ ማካሄድና የተለያዩ አይነት በደሎችን ይጨምራል፡፡ ይሄን ያደረገ መንግስት ወይም አድርጌያለሁ ያለ መንግስት በተቻለ አቅም “የበደልከኝን መካስ አለብህ” ሲባል ማዳመጥ አለበት እንጂ የአስቸኳይ ጊዜ ማወጅ መፍትሄ አይሆንም፡፡ እኛ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ “አግባብነት የለውም” የምንለውም ከዚህ አንፃር ነው፡፡ በትክክል የህዝቦችን ጥያቄ ለመመለስም አያስችልም ብለን ነው የምናምነው፡፡
በሌላ በኩል መንግስት በጥልቀት እየታደስኩ ነው፣ ግምገማዎችና ሹም ሽረቶችን እያደረኩ ነው ሲል ይሰማል፡፡ እኔ ግን ብዙም ወደ ዘላቂ መፍትሄ ይወስዳል ብዬ አላስብም፡፡ ምክንያቱም የሚገመገሙትም የሚታደሱትም ባለፉት 25 አመታት በሀገሪቱ ከነበረው የአብዮታዊ ዲሞክራሲ አስተሳሰብ ውጪ አይደሉም፡፡ ሹም ሽሩም ቢሆን ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ የመንፏቀቅ ነው፡፡ አሁን የመጡትም ሆነ በፊት የነበሩት የኢህአዴግን አብዮታዊ ዲሞክራሲ አስተሳሰብ ነው የሚያራምዱት፤ ከዚህ ውጪ ሊያራምዱ አይችሉም። ይሄ ደግሞ ደጋግመን እንደምንለው፣ ርዕዮተ ዓለሙ አጠቃላይ የህዝቡን ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ችግር የሚፈታ አይደለም። ከዚህ አኳያ ስር ነቀል የአስተሳሰብ ለውጦች ያስፈልጋሉ፡፡
መንግስት በሀገሪቱ ችግሮች ላይ ተቃዋሚዎችን አወያያለሁ ማለቱ በተግባር የሚገለፅ ከሆነ መልካም ነው፡፡ ኢህአዴግ ካለው ባህሪ አኳያ ግን በሩን ለውይይት ክፍት የሚያደርግ አይመስልም። ባለፉት 25 ዓመታት ይህን ሊያደርግ የሚችልበት ሰፊ እድል ነበረው፡፡ ግን ማድረግ አልቻለም። ከራሱ ሃሳብ ውጪ የተለየ ሃሳብ ይዘው የሚመጡትን ሁሉ እንደ ጠላት የሚያይ በመሆኑ ወደ ውይይት መምጣት አልሆነለትም፡፡ አሁን ተለውጦ በአዲስ መልክ ወደ ውይይት የሚመጣ ከሆነ፣ ትልቅ ነገር ነው ብዬ አስባለሁ፡፡
ይሄን ማድረግ ካልቻለ ግን አሁንም ይህቺን ሃገር ወደተወሳሰበና ያልሆነ አቅጣጫ መግፋት ነው የሚሆነው፡፡ በኮማንድ ፖስት ብቻ የዚህችን ሃገር ችግር መፍታት እንደማይቻል ማመን አለብን። በቅንነት በሚደረጉ ውይይቶች መፍትሄ እንደሚመጣ መቀበል ያስፈልጋል፡፡ በዚህች ሃገር በፓርቲ ውስጥ ያልተካተቱ ነገር ግን ጥሩ ሃሳብ፣ አመለካከትና እውቀት ያላቸው ሰዎችም አሉ፤ እነሱንም የሚያሳትፍ ውይይት መደረግ አለበት፡፡
 እኛ የሚነሱ ህዝባዊ ጥያቄዎች መሠረታቸው ሠላም እንዲሆን እንፈልጋለን፡፡ ህዝቡ ወደአልተፈለገ አቅጣጫ እንዲሄድ የገፋፉት ምክንያቶች ደግሞ መንግስት ለነፃ ውይይቶች ራሱን ዝግጁ አለማድረጉና በሩን መዝጋቱ ነው፡፡ ህዝቡ ድምፁን የሚያሠማበት እድል ባለማግኘቱ ነው ወደ ሌላ አማራጭ የሄደው፡፡
ስለዚህ የህዝብ ድምፅ የሚሠማባቸው አማራጮች መበራከት አለባቸው፡፡ ተቃዋሚዎች የፓርላማ ውይይት ላይ ይሳተፋሉ የተባለው ህገ መንግስታዊ መሠረት የለውም የሚል እምነት አለኝ። ተቃዋሚዎች ፓርላማ ገብተው እንዲከራከሩ፣ ውይይት እንዲያደምጡ የሚደረገው፣ የህዝብ ውክልና ሲኖራቸው ወይም በህዝብ ድምፅ ሲመረጡ ብቻ ነው፡፡ ሳይመረጡ ፓርላማ መግባት ከህገ መንግስቱ ውጪ ነው። ስለዚህ ዋናው መፍትሄ በቀጥታ ከህዝብ ጋር መነጋገር ነው፡፡ ሁላችንም ያለችን ብቸኛ አገር ይህቺው ናት፡፡
ስለዚህ ሁላችንም በእኔነት ስሜት በጋራ ሆነን፣ ኢህአዴግም እያንዳንዳችን ለዚህች ሃገር የምንቆረቆርና የምናስብ መሆናችንን አውቆ፣ ለተሻለ የውይይት ስርአት ራሱን ማዘጋጀት አለበት፡፡

---------------------

                         “ጊዜው የእርቅ መሆን አለበት”
                            ዶ/ር ኃይሉ አርአያ (አንጋፋ ፖለቲከኛ)

      እንደኔ በዚህች ሀገር አሁን የሚፈለገው እርቅ ነው፡፡ ሁሉም ወገኖች ወደ እርቅ መምጣት አለባቸው፡፡ በደርግ ጊዜም የነበሩ እነ መኢሶን፣ ኢህአፓ፣ ኢሰፓ አሉ፡፡
እነዚህ ሁሉ የእርቁ አካል መሆን አለባቸው፡፡ ምንም እንኳ እድሜያቸው እየገፋ ቢሆንም እነዚህ ሰዎች ወደ እርቅ መድረክ መምጣት አለባቸው። ዋነኛው መፍትሄ ይሄ ነው። እርቁ ደግሞ ከልብ መሆን አለበት፡፡ ይቅር ለእግዚአብሔር የሚባልበት ጊዜ ነው መምጣት ያለበት፡፡ የይቅርታ መንፈስ ከሁሉም ወገኖች በኩል መምጣት አለበት፡፡ ይህ ካልተፈጠረ በስተቀር ሌላ ምንም መፍትሄ አይታየኝም፡፡
ከይቅርታው በኋላ ሁሉም ወገኖች በእኩልነት ተወያይተው፣ የየራሳቸውን መፍትሄ ማቅረብ እንጂ የኔ ሀሳብ ብቻ ነው መፍትሄው በሚለው አካሄድ የትም ልንደርስ አንችልም፡፡ ይሄ አጋጣሚ ታሪካዊ ስህተቶች የሚታረሙበትና የይቅርታ ጊዜ ቢሆን መልካም ነበር፡፡ ጥገናዊ ለውጥ ብቻውን የትም አያደርሰንም የሚል እምነት አለኝ፡፡ የኔ ምኞት እርቅ ነው፡፡

----------------

                        “ግምገማውን ማካሄድ ያለበት ህዝብ ነው”
                             አቶ በለጠ ገብሬ (የመኢአድ አመራር)

     የስልጣን ሹም ሽረቱ መንግስት ብልሹ ናቸው ያላቸውን አመራሮች በማንሳት የራሱን የውስጠ ፓርቲ ችግር የፈታበት እንጂ መሰረታዊ የሆነ የህዝቡን ጥያቄ የመለሰ አይደለም፡፡ የህዝብ ጥያቄ እንደውም በቂ ትኩረት ያገኘ አይመስልም። ጥልቅ ተሃድሶ የሚባለውም ቢሆን እነሱ  ራሳቸውን በራሳቸው ተገማግመው አልነበረም መታደስ የነበረባቸው፤ ህዝብ ነው ሊገመግማቸው የሚገባው። ግምገማውን በየትኛውም መመዘኛ ማካሄድ የነበረበት ህዝብ ነው፡፡ ፓርቲው ግምገማ አድርጎ የራሱን ውሳኔ አሳልፎ የመረጣቸውን ሰዎች ነው ተቀበሉ እያለ ያለው፡፡ ከዚህ ይልቅ ህዝብ ራሱ የገመገማቸውና ይሁንታ የሰጣቸው ሰዎች በቦታው ሊቀመጡ ይገባ ነበር፡፡
ለእኔ ተሃድሶው እርስ በእርስ ተደጋግፈው፣ ተሿሹመው በስልጣን የሚቀጥሉበትን ሁኔታ ያመቻቹበት እንጂ በግልፅ የሚታይ የተሃድሶ ውጤት የተገኘበት አይመስለኝም፡፡ ጥፋተኛው በግልፅ ተለይቶ ተጠያቂ የተደረገበት ሁኔታ የለም፡፡ በሙስና የተዘፈቁ አመራሮች አሁንም ሌላ ቦታ ተፈልጎላቸው እንዲቀመጡ ነው የተደረገው፡፡
የህዝብ ጥያቄ፤ የዲሞክራሲና የሰብአዊ መብት እንዲሁም የፍትሃዊ ሀብት ክፍፍል ነው፣ የህዝብ ጥያቄ፤ ሙስናና ዘረፋ አስመርሮናል፣ የመልካም አስተዳደር እጦቱ አንገፍግፎናል የሚል ነው፡፡ በዚህ ልክ ጥልቅ ተሃድሶው እየተደረገ ነው ወይ? ችግሮችንስ ሊፈታ በሚችልበት አግባብ ነው ወይ? የሚለው አጠያያቂ ነው፡፡
ዋናው መፍትሄ ሁሉን አቀፍ ውይይት ነው፡፡ ነገር ግን የኢህአዴግን ባህሪ ስንመለከት ብዙም ተስፋ ሰጪ አይመስልም፡፡ ከአሁን በፊት በተደጋጋሚ በተቃዋሚዎች የውይይት መድረክ ተጠይቋል። እርቅ፣ ድርድር እንዲካሄድ ብዙ ጊዜ ጥያቄ ቀርቧል። ሆኖም ኢህአዴግ ፈጽሞ ፍላጎት አላሳየም። እስካሁንም በተለያዩ አካሎች ኢህአዴግ ወደ ውይይት እንዲመጣ ጥረቶች ሲደረጉ አያለሁ፤ ግን ጥያቄውን ተቀብሎ ወደ ጠረጴዛ ውይይት ይመጣል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ኢህአዴግን በአሸናፊነት ሊያወጡት በሚችል መንገድ ካልሆነ በቀር ውይይት ተደርጎ ሀገሪቱ ካለችበት ችግር ልትወጣ የምትችልበትን መንገድ ያመቻቻል ብዬ አላምንም፡፡ ነገር ግን ለችግሮች ሁሉ መፍትሄው ውይይትና ንግግር ነው፡፡
የፖለቲካ ቁርጠኝነቱ ኖሮ በኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባናል ከሚሉ ኃይሎች ጋር በሰፊው መወያየት በእጅጉ ያስፈልጋል፡፡ ሀገሪቱን ከገባችበት አጣብቂኝ ውስጥ በዚህ መልኩ ብናወጣት ምኞቴ ነው፡፡ ሀገራችን ወደተሻለ አቅጣጫ እንድታመራ የተቻለው ሁሉ መደረግ አለበት፡፡  

Read 1737 times