Sunday, 25 December 2016 00:00

የሰማያዊ ፓርቲ ህጋዊ አመራር ማነው!?

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

 - በሁለቱም ተወዛጋቢ ቡድኖች፤ የምርጫ ቦርድ ውሳኔ እየተጠበቀ ነው
             - ኢንጂነር ይልቃል፤ ”ጸድቋል የተባለውን የ3.1 ሚሊዮን ብር በጀት” አላውቀውም አሉ
             - “በተሰረቀ ማህተም ነው እኔን ሊቀመንበሩንም፣ አባላትንም አባረናል ያሉት”
             - “በህግ የመወሰን ስልጣን አለኝ፤በስልጣኔ እንዳልጠቀም ግን የህግ አስከባሪዎች ድጋፍ የለኝም”
             - “እውነተኛ ለውጥ ለማምጣት የሚፈልጉ ሰዎች አመራርነት አያጓጓቸውም”

    ከተመሰረተ ከ4 ዓመት በላይ ያስቆጠረው ሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች ውዝግብ አሁንም እልባት አላገኘም፡፡ ፓርቲውን እስካሁን ሲመሩት የቆዩት ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት፤ ”በህገ ወጥ መንገድ የተካሄደ ነው በሚሉት ጠቅላላ ጉባኤ” በሊቀመንበርነት ተመርጠዋል የተባሉት አቶ የሸዋስ አሰፋ፣ ሰሞኑን ፓርቲው ለሩብ አመት ያፀደቀውን የ3.1ሚ. ብር በጀት ይፋ ለማድረግ ያዘጋጁት መግለጫ በውዝግብ መቋረጡ ይታወቃል፡፡ ኢንጂነር ይልቃል የተባለውን የ3.1 ሚሊዮን ብር በጀት እንደማያውቁ ለአዲስ አድማስ ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅት የፓርቲው ህጋዊ አመራር ማን እንደሆነ አይታወቅም፤ ሁለቱም ቡድኖች ለምርጫ ቦርድ ቅሬታቸውን አቅርበው ውሳኔ እየተጠባበቁ ነው፡፡
“ህጋዊ ሊቀመንበር ነኝ” የሚሉትን ኢ/ር ይልቃል ጌትነትና “አዲስ የተመረጥኩ ነኝ” የሚሉትን አቶ የሽዋስ አሰፋን በውዝግቡ ዙሪያ ለማነጋገር ጥረት ያደረግን ሲሆን አቶ የሸዋስ “ጉዳዩ በምርጫ ቦርድ ስለተያዘና ውሳኔውን እየተጠባበቅን ስለሆነ ብዙ የምናገረው የለም” በማለት ለቃለምልልስ ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡ ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት ግን የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ከውዝግቡ መንስኤ አንስቶ እስከ ፓርቲው እጣ ፈንታ ድረስ ለቀረበላቸው ጥያቄዎች ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡


      የውዝግባችሁ መንስኤ ምንድነው?
    መነሻ ምክንያቱ ከውጭ ሀገር ከመጣሁ ጊዜ ጀምሮ ቢሮ ቆልፈው እኔን አናስገባም ማለታቸው ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ከመስከረም 12 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምረው ደግሞ የፓርቲውን ህጋዊ ሰርተፍኬት፣ ማህተም፣ ኮምፒውተሮች፣ ካሜራዎች፣ ቴሌቪዥንና የተለያዩ የቢሮ በተለይም የፋይናንስና የአባላት ፎረም ሰነዶችን ዘርፈው ወጡ፡፡ እኛ ይሄን በቃለ ጉባኤ ይዘን ኮሚቴ አቋቁመን የንብረት ቆጠራ አካሂደን፣ ጉዳዩን ለፖሊስ አመለከትን፡፡ ማንም ሰው የፓርቲውን ማህተም እንዳይጠቀምበትም በማህበራዊ ሚዲያ ገፃችን ላይ አሳውቀናል፡፡ ይሄን ጉዳይ ፖሊስ እየተከታተለው ነው፡፡ እንግዲህ ከዚህ በኋላ ነው በተሰረቀው ማህተምና ሰነድ፣ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት ቢሮ ውስጥ ሄደው ጉባኤ አደረግን ያሉት፡፡ ለምርጫ ቦርድም ደብዳቤ ጽፈናል ብለዋል፡፡ ጉባኤ አድርገናል በማለትም ያንን ቃለ ጉባኤ ለምርጫ ቦርድ አስገቡ፡፡ ይሄ ሁሉ የፓርቲውን ደንብ ያልተከተለ፣ ህገ ወጥ አካሄድ ነበር፡፡
በሰማያዊ ፓርቲ ደንብ አንቀፅ 26 ላይ፣ የሊቀመንበሩ ተግባርና ኃላፊነት በግልፅ ተቀምጧል። አንዱ አንቀፅ፤ ሊቀመንበሩ የምክር ቤቱና የስራ አስፈፃሚው ውሳኔዎች ወጪ ደብዳቤዎች ላይ ይፈርማል ይላል፡፡ በፋይናንስ መመሪያው መሰረትም፣ ወጪዎችን ሊቀመንበሩ እንደሚያዝም በግልፅ ተቀምጧል፡፡ ይሄ ሁሉ ነገር እያለ ነው እንግዲህ፣ እኔ ሊቀመንበሩ በማላውቀው ሁኔታ ጉባኤ ተጠራ የተባለው፡፡ ፓርቲውን በህጋዊነት የሚወክለው ሊቀመንበሩ ነው፡፡ ይህ ማለት ፓርቲው ቢከሰስ፣ እንዲሁም በማንኛውም መንገድ ፓርቲውን የሚወክለው ሊቀመንበሩ ብቻ ነው ማለት ነው፡፡ ሊቀመንበሩ ደግሞ ተጠሪነቱ ለፓርቲው ጉባኤ ነው፡፡ ይህ ማለት ሊቀመንበሩን የሚሾመውም የሚሽረውም ጠቅላላ ጉባኤው ነው። ህጋዊ አሰራሩ ይሄ ሆኖ ሳለ፣ በተሰረቀው ማህተም ግለሰቦቹ፤ “ሊቀመንበሩ ታግዷል” ብለው መግለጫ ሰጡ፡፡ በዚህ ህገ ወጥ ማህተም ነው እንግዲህ አባላትንም፣ ሊቀመንበሩንም አባረናል ያሉት፡፡  
አሁን ደግሞ ይባስ ብሎ በጀት አፅድቀናል ብለዋል። በፓርቲያችን ደንብ መሰረት፤ በጀት የሚያፀድቀው የፓርቲው ምክር ቤት ነው፡፡ ይሄ በደንባችን በግልፅ ተቀምጧል፡፡ ይህ በጀት ፀደቀ የተባለው የምክር ቤት አባላት በሌሉበትና ባልተሰበሰቡበት ሁኔታ ነው፡፡ የምክር ቤቱ ፀሐፊ አወቀ ተዘራ እስር ቤት ነው ያለው፡፡ የምክር ቤቱ ሰብሳቢ አቶ ይድነቃቸውም እስር ቤት ነው ያለው። ስለዚህ የምክር ቤቱን ስብሰባ እንኳ ለመጥራት ስልጣን ያለው ሰው የለም፡፡ በዚህ ሁኔታ ነው እንግዲህ በጀት አፅድቀናል ብለው ጋዜጣዊ መግለጫ እንሰጣለን ያሉት፡፡ እርግጥ እኔ በቦታው አልነበርኩም፤ ህጋዊዎቹ የምክር ቤት አባላት ግን ጋዜጣዊ መግለጫውን እንከታተላለን ብለው ወደ አዳራሹ ገቡ፡፡ እነሱ በአዳራሹ መገኘታቸውን ሲያዩ በሊቀመንበርነት ተመርጫለሁ ያሉት አቶ የሸዋስ፤”ጋዜጣዊ መግለጫውን መስጠት አልችልም” አሉ፡፡ “እንዴ! ለህዝብ ልትናገር ያዘጋጀኸውን፣ ሁሉም ይስማልን ያላችሁትን ጋዜጣዊ መግለጫ ለመስጠት የኛ የምክር ቤት አባላት መሰብሰብ ለምን ያስፈራሃል፣ ለምን አትናገርም፣ ህጋዊ ነን ካላችሁ ምን ያስፈራችኋል? ህጋዊ መሆናችሁን ለጋዜጠኞች አሳዩ … ይህ ካልሆነ ግን በህገ ወጥ መንገድ ያደረጋችሁት ጉባኤ ነው፤ ምርጫ ቦርድ በጉዳዩ ላይ ውሳኔ ሳይሰጥ ሰማያዊን ወክላችሁ መግለጫ መስጠት አትችሉም፤ ነገር ግን የራሳችሁን ሀሳብ ለጋዜጠኞች መናገር ትችላላችሁ …” ሲሏቸው፣ እነ አቶ የሸዋስ የመግለጫ መድረኩን መበተናቸውን አውቃለሁ፡፡
ሁለታችሁም ለምርጫ ቦርድ አቤቱታ አስገብታችኋል?
አዎ! ግን እስካሁን ውሳኔ አልሰጠንም፡፡ ይህ ባልሆነበት ደግሞ ህጋዊ የፓርቲው ሊቀመንበር አሁንም እኔ ነኝ፡፡ ግን ይሄ አመራር ስራውን በአግባቡ እንዳይሰራ ማህተም ሰርቀው በጎን መንቀሳቀሳቸው ፈተና ሆኖበታል፡፡ እኛ በተደጋጋሚ ምርጫ ቦርድ ለጉዳዩ አፋጣኝ እልባት እንዲሰጥ ብንጠይቅም ሊሰጠን ባለመቻሉና በመዘግየቱ በፓርቲያችን ስራ ላይ ችግር ፈጥሮብናል፡፡ ዞሮ ዞሮ ይሄ አደረግነው ያሉት ጉባኤ፤ ሊፀድቅ እንደማይችል ምንም ጥርጥር የለኝም፡፡ ማህተም ሰርቆ፣ በሰው ቢሮ ኮረም ሳይሞላ፣ ሊቀመንበሩ ሳያውቀው፣ አባላት ሳይገኙ-----የተደረገ ስብሰባ፤ በምንም መንገድ ህጋዊ አይሆንም፡፡
በመካከላችሁ የተፈጠረውን ውዝግብ እንዴት በውስጠ- ፓርቲ ዲሲፕሊን መፍታት ተሳናችሁ? ከአሁን በፊት በተመሳሳይ መንገድ ከፈራረሱ ፓርቲዎች ትምህርት አልወሰዳችሁም ማለት ነው?
እንግዲህ የሰማያዊ ፓርቲ ችግር በሌሎች ፓርቲዎች ላይ ከተፈጠረው በመሰረቱ ለየት ያለ ነው። “የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ይሄንን አባል አባረረ፣ ይሄንን አገደ፣ ይሄን ውሳኔ አልቀበልም አለ” የሚል ነገር የለም፡፡ በብዛት ሌሎች ሰዎች ከታች ሆነው ፓርቲውን የማፍረስ እንቅስቃሴ ነው የነበረው፡፡ በተለያየ ጊዜ የፓርቲውን ገፅታ ለማጥፋት በመገናኛ ብዙኀን መግለጫ ሲሰጡ ነበር። የሊቀመንበሩን ስም፣ ፓርቲውን ለዚህ ያደረሱትን ሁሉ ስም ሲያጠፉ ነበር፡፡ አንዱን አባረናል፣ ሌላውን አግደናል ሲሉ ነው የከረሙት፡፡ የሚገርመው ነገር ተባረዋል የተባሉት፡- እኔን ሊቀመንበሩን ጨምሮ፣ ምክትል ሊቀመንበሩ ስለሺ ፈይሳ፣ የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዮናታን ተስፋዬ፣ የፓርቲው የወጣቶች ጉዳይ ኃላፊ እያስፔድ ተስፋዬ፣ የምክር ቤቱ አባል ዮናስ ከድር፣ የምክር ቤቱ አባልና አደራጅ የሆነችው ወይንሸት ሞላ፣ የምክር ቤቱ አባል ጋሻነህ ላቀ፣ የብሄራዊ ም/ቤት አባሏ ምዕራፍ ይመር እንዲሁም የፓርቲው አመራር አቶ ወረታው ዋሴ ናቸው፡፡ ይሄ ጤነኛ አዕምሮ ላለው ሰው፣ እንዴት የሚል ጥያቄ እንዲያነሳ ያደርገዋል፡፡ እነዚህ ተባረዋል የተባሉት ሁሉ በፓርቲው ውስጥ ከፍተኛ ትግል የሚያደርጉ ጠንካራ አመራሮች ናቸው፡፡ ብዙዎቹ ደግሞ አሁን እስር ቤት ናቸው፡፡ ታዲያ እነዚህን ሁሉ አመራሮች የሚያባርር አካል፣ዓላማው ምንድን ነው? ይሄ ሆን ብሎ ፓርቲውን ለማፍረስ የሚደረግ እንቅስቃሴ ነው፡፡
የውስጥ ችግራችሁ አደባባይ ሳይወጣ እዚያው ተነጋግራችሁ ለመፍታት ያደረጋችሁት ጥረት ምን ያህል ነው? ወይስ ጨርሶ አልሞከራችሁትም?
እውነት ስለሌላቸው እነዚህ ሰዎች ወደ ውይይት አይመጡም፡፡ ዋና ስራቸው በየጋዜጦች ላይ ስም ማጥፋት ነው፡፡ አንድ ችግር ነቅሰው አውጥተው ለውይይት ሲያቀርቡ አላየንም፡፡ ችግሩ በዋናነት ተራ ጥላቻና አሉባልተኝነት ነው፡፡ ፓርቲውን የሚመሩ ሰዎችን መጥላት፡፡ ለምሳሌ አሁን ተባረዋል የተባሉት አመራሮች፣”ምን አድርገው ነው የተባረሩት?” ቢባሉ፣ምንም ምክንያት የላቸውም፡፡ ተራ ጥላቻ ብቻ ነው፡፡
እርስዎ እንደ ሊቀመንበርነትዎ----ሌሎች አመራሮችና አባላት ራሳቸውን ለዲሲፕሊን አስገዝተው እንዲንቀሳቀሱ ውጤታማ የፓርቲ አመራር አልሰጡም ማለት ነው፤የሚል ትችት ቢሰነዘርብዎ ምላሽዎ ምንድን ነው?
በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ አንዱ አስቸጋሪው ነገር፣ የህግ አስከባሪ አካላት ይሄን አያግዙም። ለምሳሌ በፓርቲው ህጋዊ ሊቀ መንበር እኔ ነኝ፤ አንድ ሰው ማህተም ይዞ አልሰጥም አለ፤ ያ ሰው ከጓደኞቹ ጋር እየተመካከረ፣ የፓርቲውን አመራሮች ማባረር ጀመረ፤ ይሄን ለፀጥታ አካል ብናመለክት ድጋፍ የለንም፡፡ ታዲያ እኔ እዚህ ላይ ምን ማድረግ እችላለሁ፡፡ በህግ የመወሰን ስልጣን አለኝ፤ ግን ያንን ስልጣኔን እንዳልጠቀም የህግ አስከባሪዎች አይተባበሩኝም፡፡ እውነቱን ለመናገር፣ ኢህአዴግ ውስጥ ቢሆን ይሄ አይፈጠርም፡፡ ምክንያቱም ህግ አስከባሪ አለ፤ ፖሊስ ይዞ ያስወጣዋል፡፡ ለኔ ማን ያስወጣልኛል? እንደውም ፓርቲ የሚያፈርስ ሰው፣ በገዥው ፓርቲ ይከበራል፤ በመንግስት መገናኛ ብዙኃን ይነገርለታል፡፡
በተቃዋሚ ፓርቲዎች ውስጥ ሰው የሚያከብራቸውንና ምልክት የሆኑ ሰዎችን ማዋረድ በሌላው ወገን ድጋፍ የሚያስቸር ነው፡፡ ይኸው እኛ ለፖሊስ “ንብረታችን ተዘርፏል” ብለን ካመለከትን 3 ወር ቢሆነንም፣ ምንም ምላሽ አላገኘንም፡፡ ምርጫ ቦርድም ውሳኔ አልሰጠንም፡፡ ስለዚህ ምን ማድረግ እንችላለን? እንዲሁ ጥርስ የሌለው አንበሳ መሆን ብቻ ነው፡፡
የእናንተ ውዝግብ የአባሎቻችሁንና የደጋፊዎቻችሁን ስሜት አይጎዳም? ድጋፍስ አያሳጣችሁም? በሌላ በኩል ገዥው ፓርቲ፤ “እርስ በእርሳቸው እንኳ የማይስማሙ፣ እንዴት ሀገር ሊመሩ ይችላሉ?” የሚለውን መከራከሪያ አያጠናክርለትም? እርስዎ በዚህ ጉዳይ ላይ ያለዎት አስተያየት ምንድን ነው?
አሁን ችግር የፈጠሩ ሰዎች አላማም ይኸው ነው። ተቃዋሚ ፓርቲዎች አይረቡም ማስባል ነው፤ ዓላማቸው፡፡ ፓርቲውን አቅመ ቢስ አድርጎ ማቅረብና በህዝብ የነበረውን አመኔታ ማሳጣት፣በአለማቀፍ ማህበሰረብ ያገኘውን ተቀባይነት ማስነፈግ፣----ይሄ ነው የዚህ እንቅስቃሴ አላማ፡፡ እኛ እንግዲህ ምን ልናደርግ እንችላለን? የብዙኃን ፓርቲ አሰራር እዚህ ሀገር እንደማይሆን አንዱ ማሳያ ይሄ ነው። የህግ አካላት እንዲህ አይነት ህገ ወጥ ስራ ሲሰራ ጣልቃ ገብተው፣ ህግ አለማስከበራቸው ችግሩ ፈጦ እንዲወጣና እንዲራገብ፣ህዝቡም በተቃዋሚዎች ላይ ተስፋ እንዲቆርጥ ያደርጋል፡፡ ገዥው ፓርቲም በደካማ ፓርቲዎች እንዲታጀብ ይሆናል። እስከዛሬም የተደረገው ህዝቡ “የፓርቲ ፖለቲካ በኢትዮጵያ አይሰራም” ብሎ ተስፋ እንዲቆርጥ ነው፡፡ አሁንም እየተደረገ ያለው ይኸው ነው፡፡ የኛም ፓርቲ መዳከሙና ገፅታው መጥፋቱ የሚደበቅ አይደለም፤ ግልፅ ነው፡፡ ከፍተኛ ተፅዕኖ እንዳለውም ይታወቃል። ነገር ግን ይሄ ሁሉ የመጣው፣እኔ አባላትን በማባረሬ፣ የፓርቲውን ሀሳብ ባለማሳወቄ ወይም ተገቢ አሰራር ባለመተግበሩ አይደለም፡፡
በነገራችን ላይ ሰማያዊ ፓርቲ ከሌሎቹ ፓርቲዎች በተለየ ለምርጫ ማካሄጃ የተሰጠውን 900ሺህ ብር በውጭ ኦዲተር አስመርምሮ ሪፖርት ያደረገ ፓርቲ ነው፡፡ ንፅህናችንን አሳይተን፣ ቦርዱም ያመሰገነን ፓርቲ ነን፡፡ አሁን ይሄ ሁሉ ችግር የመጣው፣ከውስጥና ከውጭ፣ ፓርቲውን ለማዳከም ተልዕኮ ባላቸው ግለሰቦች ነው፡፡
ብዙ ጊዜ የፓርቲዎች ውዝግብ መነሻ የአመራርነት ይገባኛል ጥያቄ ነው… የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ መሆን ምንድን ነው ትርጉሙ? አንዳንድ ወገኖች የውዝግቡን መካረርና ተደጋግሞ መከሰት በመታዘብ የፓርቲ ሊቀመንበር ወይም ፕሬዚዳንት መሆን ከፍተኛ የገንዘብ ጥቅም ሳያስገኝ አይቀርም ወደ ሚል ጥርጣሬ እየገቡ ነው -----
 እውነተኛ ለውጥ ለማምጣት የሚፈልጉ ሰዎች አመራርነት አያጓጓቸውም፡፡ እኔ በግሌ ወጣት መሃንዲስ ነኝ፤ በራሴ መኖር እችላለሁ፡፡ የሶስትና አራት ሀገራት ቪዛ ያለኝ፣ እንደፈለግሁ መውጣትና መግባት የምችል ሰው ነኝ፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ ባለፉት 4 ዓመታት ያጠፋውን በጀት ያህል በግሌ  መስራት እችላለሁ፡፡ እኔ ከፈጠርኩት ፓርቲ ውስጥ የተለየ ጥቅም አልፈልግም፡፡ እውነት ለመናገር፣ ቅናትና ምቀኝነት ነው፤ የሁሉም ችግር መነሻ፡፡ የፖለቲካችን ኋላ ቀርነት፤ በድርጅት ውስጥ የሚሰባሰቡ ሰዎች ከስሜት በላይ የፖለቲካ እውቀትና ብስለት አለማዳበራቸው ተደማምሮ ነው፣ ገና ፓርቲዎች በቅጡ ሳያድጉ፣አመራርነት የውዝግብ መነሻ እየሆነ በአጭሩ የሚቀጩት፡፡
በአሁኑ አካሄድ የፓርቲው ዕጣ ፈንታ ምን ይሆናል ብለው ያስባሉ ?
እኔ እስከሚገባኝ ድረስ ተደርጓል የተባለው ጉባኤ፣ ህጋዊ የሚሆንበት ምንም ምክንያት የለውም። አባላቱም በብዛት ከኛ ጋር ነው ያሉት፡፡ ህዝቡን አሁን ባለው ሁኔታ “እገሌ ነው መሪ፣ አይ እገሌ ነው” የሚለውን ጨዋታ አይፈልገውም፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ በሆደ ሰፊነት ነገሮች እንዲያልቁ የተቻለንን ሁሉ እንጥራለን፡፡ ነገር ግን ይሄን ለማድረግ ህግ የማይደግፈን ከሆነ፣ ከአባሎቻችን ጋር ተመካክረን የራሳችንን ውሳኔ እናሳልፋለን፡፡
በቅርቡ ፓርቲያችሁ ለቢሮ ኪራይ የሚከፍለው እንኳ አጥሮት ተቸግሮ እንደነበር ተሰምቷል። ከሰሞኑ ደግሞ ለሩብ ዓመት የ3.1 ሚሊዮን ብር በጀት እንደፀደቀ ተነግሯል … ይሄ ሁሉ ገንዘብ በአጭር ውስጥ እንዴት ተገኘ? እርስዎ የሚያውቁት ነገር አለ?
አላውቅም፡፡ በፓርቲው ህጋዊ ድጋፍ የመጣም ገንዘብ የለም፤ እኛም የምናውቀው ገንዘብ የለም፡፡ እኔ የተባለው ገንዘብ አለ ብዬም አላምንም፡፡ ዝም ብለው ራሳቸውን ህጋዊና ስራ ላይ ያሉ አመራሮች አድርገው ለማቅረብ እንጂ እውነትነት ያለው አይደለም፡፡ በጀቱም ቢኖር ይሄን የማድረግ ስልጣን የላቸውም፡፡ ለሚዲያዎች የተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫም፣ በህገ ወጥ ማህተም መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡ ፓርቲው እነዚህን ሰዎች  በአመራርነት አያውቃቸውም፡፡ ምርጫ ቦርድም አያውቃቸውም። ከዚህ አንጻር ሚዲያዎች መረጃውን መጠቀማቸው በህግ ሊያስጠይቃቸው ይችላል፡፡  

Read 2385 times