Sunday, 25 December 2016 00:00

“መቼ ነው መሸዋወድ የምንጀምረው…?”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(13 votes)

  “--- ሴቶች በራሳቸው ተነሳሽነት እሱዬውን ለትዳር ለመጠየቅ ወደ ቤተሰብ ሽማግሌ የማይልኩትሳ!!”
                                    
        እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ሰውየው አንድ ቀን ጠዋት ጓደኛውን ሲያገኘው ዓይኑ አካባቢ በልዟል፡፡ ጓደኝየውም….
“ምን ሆነህ ነው! የሆነ ሰው መቶህ መሆን አለበት…” ይለዋል፡፡
“የዛች የውሽማዬ ባል ቻይና ሄዷል ብዬህ አልነበረም…”
“አዎ እንደውም ወር ነው ምናምን ይቆያል ብለኸኝ ነበር…”
“ሰውየው ቻይና አልሄደም…”
ለካስ ባል እጅ ከፍንጅ ይዞት ነው፣ የዓይኑን ዙሪያ ያረረ ቦምቦሊኖ ያስመሰለለት! ቂ…ቂ…ቂ…
ስሙኝማ…የዘንድሮ አየር እንዴት ነው! ሙቀቱ ቀቅሎን፣ ብርዱ ‘ቀቅሎን፣’ ኑሮው ቀቅሎን፣ የሰው ነገር ቀቅሎን!... አንድ ዘመን ሲያቀብጠን “ተፈጥሮን በቁጥጥር ስር እናውላለን!” እያልን ፎከርንና ይኸው ተፈጥሮ ‘ጉዳችሁን አያለሁ…’ አይነት መከራችንን እያሳየችን ነው፡፡ እናማ… የማያደርጉትን፣ የማይሆነውን ነገር… አለ አይደል… መፈክር ማብዛት አሪፍ አይደለም፡፡
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…በዛ ሰሞን የሆኑ ወዳጃሞች ሰብሰብ ብለው እየተጫወቱ ነበር፡፡ እናማ ከመሀላቸው አንዷ ምን ታደርጋለች … እንትናዋን በጓደኞቹ ፊት…
“ታገባኛለህ!” ብላ ትጠይቀዋለች፡፡ እናም ሰለጠንኩ የሚለውም፣ እውቀት በዛብኝ የሚለው ሁሉ ክው አለላችሁ አሉ፡፡ እና ዘላለም ወንድ ብቻ  ይንበርከክ እንዴ…
የምር ግን…ሀሳብ አለን… ሴቶች በራሳቸው ተነሳሽነት እሱዬውን ለትዳር ለመጠየቅ ወደ ቤተሰብ ሽማግሌ የማይልኩትሳ!!
“እሁድ ቤታችን እንግዶች ይመጣሉ…”
“የምን እንግዶች፣ የአገር ቤት ሰዎች መጡ እንዴ?…”
“እኔ ምን አውቄ፣ በጠዋት ሰዎች ስለሚመጡ ከቤት እንዳትወጡ ነው ያሉኝ…ደግሞ ጥቂት ዘመድ አብሯችሁ ይሁን ብለዋል…”
እናማ እሁድ ይደርስና ቀደም ብለው ታይተው የማያውቁ እንግዶች ይመጣሉ…
የተለመደው “ደህና ናችሁ… ጤናችሁስ…” ምናምን ከተባለ በኋላ አንደኛው ሽማግሌ ብድግ ይሉና ወደ ጉዳዩ ይገባሉ፡፡
“ዛሬ አመጣጣችን ልጃችሁን ለልጃችን በጋብቻ እንድትሰጡን ለመጠየቅ ነው…”
ባል ድንግጥ፣  ሚስት ድንግጥ፤ ባልም ሚስታቸው ላይ አፍጥጠው…
“አንቺ ሴትዮ፣ እኔ ሳላውቅ ሴት ልጅ ወልደናል እንዴ!” ማለት!
ሚስትም፤ “አሽሙር መሆኑ ነው! ዲቃላ አለሽ ለማለት ነው!” ብለው ‘ህብረቱ’ የመፍረስ አደጋ ሊገጥመው ዳር፣ ዳር ይላል፡፡
“ስህተቱ የእኔ አነጋገር ነው መሰለኝ፣ ለማለት የፈለግሁት ትልቁ ልጃችሁን ወሰንየለህን ለልጃችን ለቤዛ በጋብቻ እንድትሰጡን ለመጠየቅ ነው…”
እዛ ከተሰበሰቡት የወሰንየለህ ዘመዶች ሁለቱ “ኧረ ድንገተኛ ቀጥቀጥ አድርጋችሁ ስጡኝ…” ሲሉ ሦስቱ ደግሞ ቤት ውስጥ አንድ ፍሬ የራስ ምታት ኪኒን አይኖራችሁም… እንደሚሉ ቀልባችሁ አይነግራችሁም!
አሀ…ታዲያ ዘላለም…ወንዶች ሽማግሌ ሲልኩ፡- “ልጃችሁን በጋብቻ ስጡኝ፣” ለማለት…ሴቶች ሽማግሌ ሲልኩ፡- “ከዚህ ሰውዬ አፋቱኝ” ለማለት መሆን አለበት እንዴ! ቂ…ቂ…ቂ…
ስሙኝማ…ይቺን ነገር የሆነ ጊዜ ሳናወራት አልቀረንም፡፡ ምን መሰላችሁ…እሷና እሱ ይጋባሉ። ቸበር ቻቻው አልቆ አንድ ቀን ማታ መኝታ ቤታቸው ጋደም ብለው ሳለ አዲሲቷ ሚስት አዲሱ ባሏን ምን ብትለው ጥሩ ነው…
“የእኔ ማር አሁን ተጋብተናል አይደል…መቼ ነው መሸዋወድ የምንጀምረው?” ብላው አረፈች። ይሄኔ ባልየው ወይ በሳቅ፣ ወይ በድንጋጤ ተንፈራፍሯታል!
የምር ግን… አንዳንዴ እንዲህ አይነት ግልጽነት ሳይሻል አይቀርም፡፡ የምንሰማው ሁሉ አስቸጋሪ ነዋ! የፍቺው መብዛት ምን አይነት ጉድ መጥቶብን ነው እያሰኘ ነዋ!
እናላችሁ… አሁን እንግዲህ የሰርግ ሰሞን እየተቃረበ አይደል፡፡ የሰርግ ሰሞን በደረሰ ቁጥር “ይዟት፣ ይዟት በረረ…” ከመብዛቱ የተነሳ የከተማው ሰው ሁሉ ካለመጋባት ሌላ ሥራ ያለው አይመስልም። የምር እኮ የሆነ… “በዚህ ሳምንት ያልተጋባችሁ ሰዎች ሌላ የመፈራረም ዕድል የሚመጣው ኢትዮጵያ የዓለም ዋንጫን ስታዘጋጅ ነው…” ምናምን የሚል መመሪያ ነገር የወጣ ነው የሚመስለው፡፡
ታዲያላችሁ… ተጋቢው ከመብዛቱ የተነሳ የምናውቃቸው ሰዎች ማግባታቸውን የምናውቀው በጥሪ ወረቀት ሳይሆን በየመንገዱ እንዳይሆን ያሰኛል፡፡ የሙሽሮችን መኪና እያዩ…
“ያቺ እንትና አይደለችም እንዴ! ወይ ጊዜ ለእሷም ባል መጣና ሙሽራ ሆነች!”
“ስማ ሙሽራውን ታየዋለህ…”  
“አንተ! እንትና አይደለም እንዴ…”
“እሱን አይደል የምልህ…”
“የሚገርም ነው…እውነት አግብቶ ነው ወይስ ለዘፈን ክሊፕ እየተቀረጸ ነው…” ምናምን ይባላል፡፡
ነገርየው ግን “እንትናና እንትና ተጋቡ...” የሚለውና “እነ እንትና እኮ ተፋቱ…” የሚለው አነጋገሮች እኩል ለእኩል ሊሆኑ ምንም አልቀራቸው።
ምን መሰላችሁ…ልክ እንደ ሰርግ ሁሉ ባልና ሚስት ሲፋቱ በሊሞ እየዞሩ የሚያሳውቁ ቢሆን… አለ አይደል… ከሰርግ ሊሞዎችና ከፍቺ ሊሞዎች የትኞቹ እንደሚበዙ እሱ ብቻ ነው የሚያውቀው፡፡
ታዲያላችሁ…አሁን፣ አሁን “እከሌና እከሊት እኮ ተፋቱ…” ሲባል አዝነን “ምን ሰይጣን ገባባቸው… ማለት ትተናል፡፡ ይልቁንም…
“እኔም እኮ ድሮም አውቄው ነበር፣ አይሆናትም ብያለሁ…”
“መጀመሪያ ነገር እነሱ ተጋቡ ማለት ውሃና ዘይት ተዋሀዱ ማለት ነው…” ምናምን እንባባላለን፡፡
በ‘ትኩሱ ፍቅር’ ጊዜ… “ካላገባሽኝ በእግሬ በደማስቆና በሞሱል አድርጌ ቡርኪና ፋሶ ነው የምገባው…” ይላል፡፡ (ኧረ መንገዱ በየት በየት በኩል ነው! ለነገሩ መንገዱ ራቅ ስለሚል፣ ማን ያውቃል፣ መንገድ ላይ ሃሳቡን ለውጦ “ደግሞ ላልጠፋ ሴት…” ብሎ ሊመለስ ይችላል፡፡) ምናልባት በ‘ችቦ ወገቧ’ ተማርኮ ሊሆን ይችላል፡፡ ትንሽ ቆይቶ መቼም፣ በተለይ እዚህ አገር፣ ‘እንዳማሩ መክረም’ የለምና…‘ችቦ ወገቧ’ የእትዬ እንትናን ጠጅ መጣያ ሲመስል…አይደለም በሞሱል ማቆራረጥ፣ የሞጆ መንገድም ትዝ አይልም፡፡
“ይቺ ሴትዮ በእጄ ሰበብ እንዳትሆን ካሁኑ ለያዩኝ…” ምናምን ማለት ይጀምራል፡፡ እግረ መንገዴን… ‘ችቦ ወገብ’ እና ‘ዳሌ’ በአርማታ የተሠሩ ለሚመስለን…አለ አይደል…ንቃተ ህሊና ምናምን ይሰጠንማ!
ይኸው ነዋ… ችቦ ወገብ ነው የማረከኝ ብሎ ያገባው ሰውዬ፣ ጉድ ሲሆን ምን ይደረጋል፡፡
ይቺን ስሙኝማ…ሴትየዋ ጠበቃ ዘንድ ሄዳ “ፍቺ እፈልጋለሁ…” ትለዋለች፡፡ እሱም…
“ባለቤትሽ ምን አድርጎሽ ነው፣ ፍቺ የፈለግሽው?” ይላታል፡፡
“እሱን መናገር አስፈላጊ ነው?”
“የግድ እንጂ… ባልሽ ላይ ክስ ለመመስረት እኮ የፍቺውን ምክንያት ማወቅ ያስፈልጋል፡፡”
“እሱስ ምንም አላደረገኝም፡፡ እንደ እውነቱ ባል የለኝም፡፡ እጮኛ ግን አለኝ…”
“ታዲያ ባል ከሌለሽ ስለ ፍቺ ምን አሳሰበሽ?”
“አይ… ከተጋባን በኋላ መፋታቱ ምን ያህል ይቀል እንደሆነ ለማወቅ ነው…” ብላ አረፈችው፡፡ ለነገሩ… ቅድመ ዝግጅት ክፋት የለውም፡፡
ሳስበው… ይቺ ሴትዮ… “መቼ ነው መሸዋወድ የምንጀምረው?” ያለችው ሳትሆን አትቀርም፡፡
“መቼ ነው መሸዋወድ የምንጀምረው?” ከሚል ‘ከጊዜያችን የቀደመ’ (ቂ…ቂ…ቂ…) ጥያቄ ይሰውራችሁማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 5094 times Last modified on Monday, 26 December 2016 10:05