Print this page
Sunday, 25 December 2016 00:00

ራስን ፍለጋ እና ትዝብት

Written by  አሰፋ ጫቦ Dallas Texas USA
Rate this item
(3 votes)

  “የአቶ አሰፋ ጫቦ  የተባ ብዕር ስለ ነገም ቢናገር!” በሚል ይገረም አለሙ የጻፈው በየድረ ገጾቹ  ወጥቶ ነበር።እኔ መወጣቱን  የሰማሁት በስልክ ከእመቤት አሰፋ ነበር። “በላይ መጀመሪያ ሥራ ቦታ አንብቦት ነገረኝና አንብቤ አሁን ልጆቹ እያነበቡት ነው…” አለች። በላይ ባለቤትዋ ነው። ”ምንድነው የሚለው?” አልኳት። “ብቻ አንብበው፤ ጥሩ ነው የጻፈው። ሥነስርዓት ያለው ሰው ነው” አለች። ሥነስርዓት የምትለው  የአያቷን የማቱኬ አጆ መለኪያ (ሰው መመዘኛ) መሆኑ ነው። ማቱኬ ነች ያሳደገቻቸው። በማቱኬ ቤት፤ ልጆቿን፤ ዘመድ አዝማድም ጨምሮ፤ ሰው ሁሉ በሁለት ይመደባል። ሥነስርዓት ያለውና ሥነስርዓት ያሌለው!
ከስልኩ መልስ እኔም አነበኩት። ከዚህ ሌላ ብዙ ወዳጆቼና  ጓደኞቼም  ደውለው  አስተያየት  ሰጡ። እዚህ ከአሜሪካ፣ ከኒውዚላንድ፤ አውስትራሊያ፤ ከአዲስ አበባ፣ ከካናዳም ደውለው ተነጋገርንበት። በመጠኑ ይለያይ እንጅ ተቀራራቢ አስተያየት ነበር የሰጡት። የተለመደው “ጠርጥር ጎንፎም ውስጥ አይጠፋም ስንጥር!” የሚለው ለስለስ ባለ መልኩ ነበረበት። “ለመሆኑ ይገረም አለሙ ማነው? ምን ፈልጎ ነው?” የሚለው አይነት መሆኑ ነው።
እኔ ይህንን አይነቱን “ማነው? ምን ፈልጎ ነው?” የሚለው አይነት ወስጥ ገፍቶ ካልመጣ በስተቀረ አልገባበትም። እዚያው ተጽፎ ወይም ተቀርጾ የተቀመጠውን ለበጎ ነው (Posetive Outlook) በሚል አይቼ፣ ተገቢ የመሰለኝን ተመን እሰጣለሁ። ”ማነው?” ለሚለው ሰው መሆኑ በቂ ነው። “ምን ፈልጎ ነው (Motive)?” የሚለውን አላጠያይቅም።
ሁላችንም አንድ አይነት ነገር ላንፈልግ እንችላላለን። የምንፈልገው አንድ አይነት ነገር ቢሆንም ግላዊ ቅላጼና ቃና ሲጨምረበት የተለየ ሊመስል ይችላል እንጅ አንድ ነው። አባይ፤ አዋሽ የብዙ ተፋሰሰ ወንዞች (Tributaries) ውጤት ናቸው። አደፍራሽ ጎርፍና ናዳ የሚፈጥር ጉዳንጉድ ይዘው የተቀላቀሉ ጀረቶችም ይኖራሉ። በትግስት ከተያዘ፤ ማለትም ረባዳው መሬት ላይ  ሲደረስ፣ ያ ላይዘልቅ የተሳፈረው ግሳንግስ  በየእዳሪው ይጣልና ይዘቅጣል። ዘላቂው አባይ፤ ሱዳንንም ግብጽንም እያለማ ወደ ባሕር ይገባል።
ለጠጥከው እንዳልባል እንጅ ዲሞክራሲ ወይም ዲሞክራሲያዊ ውይይት የሚሉት የሐሳብ መንሸራሸርና ማንሸራሸር ከዚህ ጋር የሚሔድ ይመስለኛል። የጠራው ይዘልቃል! ግብስብሱ ይሰምጣል ወይም ይዘቅጣል! ብቻ ለማለት የፈለኩት፣ ይገርም አለሙንም ሆነ ማንንም፤” እንዲህ ያሰኘው የውስጥ ምክንያቱ (Motive) ምንድነው?” ብዬ አላጠያይቅም። ግለሰቦችን  የሚገፋቸውን ምክንያት ለነሱ እተዋለሁ። አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ  ከፍተን እንድናየው የምንገደድ ይመስለኛል። ሰው ምክንያታዊነትና (Reasonable and Rational) የውስጥ ግፊት(Motive) ከሌላውማ “ጉድ ፈላ!” ወደ ማለት ሳይውስደን የሚቀር አይመስለኝም። ሰው ሊያሰኘው ከሚገባው ውስጥ መሠረታዊና ዋንኛ ቅመማት ተነፍጓል እንደ ማለት የሚሆን ይመስለኛል።
ይገረም አለሙ ስለ እኔ ጽሁፎች ብዙ ነገር አንስቷል። ሁሉንም  ባይሆን ዋናና (በኔ ግምት) መልስም፣ ማብራሪያያና ከመጋረጃው ጀርባ የነበር ምክንያት የሚመስሉኝን ለመመለስ እሞክራለሁ፡፡
****
ይገረም አለሙ፤ “የእገሌ ጽሁፍ ኮርኮሮኝ ነው ብቅ የምለው… በቅርቡ ደግሞ  ልጽፍ ብዬ አስቤ ሳይሆን ብልጭ ሲልብኝ ወይም ሲሊልኝ ነው የምጽፈው ብለው እቅጩን ስለነገሩን…” ከሚለው ልጀምር። ይገረም  የጠቀሰው ያልኩትን ነው። እውነትም ነው! ይህ “ብልጭ ሲልብኝ!” የሚለው ነው የዚህን ጽሁፍ ርዕስ ራስን ፍለጋ ያሰኘው።
አሁን ወደ ሁለት ዓመት ሊሆነው ነው።በአንድ ወዳጄ ምክር፣ አንድ ኮሌጅ ውስጥ የሥነልቡና ሳይንስ (Psychology) ትምህርት ተከታተልኩ። የወዳጄ ምክር፤ “አስተማሪው (ፕሮፌሰሩ) የሥነልቦና ሐኪም (Psychiatrist) ሆኖ ለ25 አመት የሰራ ነውና ይጠቅምሃል!” የሚል ነው። ለጠቅላላ እውቀት (General Knowledge) እንደማለት ነው። ተመዘገብኩና ተካፈልኩ። ከሁለተኛው ሳምንት በኋላ ጥያቄ አበዛሁ መሰለኝ። ወደ ሶስተኛ ሳምንት ገደማ፤ “ሚስተር ጫቦ፤ ሁለተኛ እንዳትጠይቅ !”አለኝ። ደንግጬ “ምን አጠፋሁ?” ብለው፣ “ያጠፋኸው ነገር የለም። ጥፋቱ ያለው እምነትህ ላይ ነው። መልሱ እዚህ መመሪያው መጽሐፍ (TextBook) ውስጥ ያለ መስሎህ ነው። ወይም እኔን ያውቃል ብለህ ነው። አናውቅም! የሰው ልጅ አእምሮ፤ ጭንቅላት(Brain)፣ ብትፈልግ አንጎል (Mind) እንዴት ነው የሚሰራው? ለመሆኑ አንጎል (Mind) ጭንቅላት(Brain) የሚባለውስ ምንድነው? ለመሆኑ የምናስበውና የምናመዛዝነው በአንጎላችን ነው? በልባችን? ወይ በስሜታችን? ወይ በኩላሊታችን? ወይም በአንጀታችን? ይህንን ለመለየት ጥናቱ ቀጥሏል! ይህ መጽሐፍ ከአንድ አመት በኋላ በሌላ ይተካ (Obsolte or Revised) ይሆናል። እኔ የማውቀውም እንደዚያው! አሁን ጥናቱ ያተኮረው ድሮ በትእቢት (Supriority)፣ እኛው ብቻ እናውቃለን ተሞልተን ፤ንቀንና ኋላ ቀር ብለን በተውናቸው ሥልጣኔዎችና ሕዝቦች ታሪክ፤ ተረት፤ እምነት ላይ ነው። “ያንን ያሉትን ለምን አሉ?” ያንን ያመነቱን እንደዚያ ለምን አመኑ?” የሚል። ለጊዜው የምናውቀው፣ሰው የሚያስበው በጭንቅላቱ ወይም በአንጎሉ ሳይሆን፤ ወይም ብቻ ሳይሆን የሰራ አካላቱ ውስጥ ያሉ የተለያዩ ብልቶች በጋራ መሆኑን ነው። እንዴት ነው የተቀናጀው? ለዚህ ገና “ከማወቁ በር” (The Tip of the Iceberg) ላይ ነን!” አለ። ወይም ያለውን ሳሳጥረው ይህንን ይመስላል።
“ያንን ያሉትን ለምን አሉ፧” ”ያንን ያመነቱን እንደዚያ ለምን አመኑ፧” የሚለውን የኛ ሰው በየቀኑ የሚለው ነው። “ዛሬ ሆዴን ባር ባር አለው! ከአንጀቴ ነው የምናገረው! ልብ ያለው ልብ ያድርገው! ልቤ ጠረጠረ! ዛሬ ቀፈፈኝ! እና የመሳሰለውን ሲል ይህንኑ ማለቱ ነው። አንዳንዴ “ነገሩ ራስ ያዞራል!” ሲል ወደ አንጎል፤ ወይ ወደ ጭንቅላት ወይም ራስ (የፈለገው ስም ይኑረው)  መሔድ መሆኑ ነው ነው። ሁለንተናችን ለምንለው፣ ለምናደርገው፣ ለማናደርገው ሁሉ ተባባሪና ተሳታፊ መሆናቸውን የሚያመለክት ነው።
እንግዲህ “ብልጭ ሲልብኝ እጽፋለሁ!” ማለቴ፣ “ከአንጀቴ ነው!” ማለቴ መሆኑ ይመስለኛል። ከሆነ ደግሞ ሳይንሱም ባሕሉም ይደግፈኛል ማለት ነው። ፈረንጅ ሁሉ ማለት አለማለቱን አላውቅም እንጅ አሜሪካኖቹ፤ “ሰውነትን አዳምጠው! አይዋሽም እውነቱንም ይነግርሃል! (Listen to Your Body! It will Tell You the Truth!) የሚሉት አላቸው። እኔ ስጽፍ ሰውነቴን አዳምጭ፣ ያንን የነገረኝን “የኔን እውነት!” መጻፌ ነው ማለት ነው። “የኔ እውነት!” የኔ ቢሆንም፣ ያንን እውነት ከሌሎችም ጋር እጋራለሁ ማለት ነው። እንዳልኩት ማንም ሰው ብቸኛና አንድ ደሴት አይደለም። ከልዩነታችን ይልቅ አብረን የምንጋራው ያመዝናልና።
****
ሌላው የገረም አለሙ ጽሁፍ ላይ ያስተዋልኩት፤ “ነካ ነካ አድርጎ እመልስበታለሁ ብሎ ሳይመለስበትም ይቀራል “ የሚለው ነው። ይህም እውነት ነው! ለማስረዳት ልሞክር።
አስተማሪ ለመሆን ነበር ብቸኛ ምኞቴ። ሻሽመኔ ስምንተኛ ክፍል ስንፈተን፣ “ሰከንደሪ ማዶ!” (ያኔ ሰከንደሪ ማዶ፤ ይጥላል በረዶ የሚል ዘፈን ብጤ የነበረ ይመስለኛል) ምን ለመማር  እንደምትፈልግ ሶስት ይሁን አራት ትምህርት ቤትና አይነት ምረጥ የሚሉት ነበራቸው። እኔ ሁሉንም “መምህራን ማሰልጠኛ” ብዬ ሞላሁ። እግረመንገዴንም ሐረርንም ለማየት። በስምም ቢሆን የማውቀው መምሕራን ማሰልጠኛ የነበረው ሐረር ነበርና! ከዚህም ሌላ ስምንተኛ ክፍል እያለሁ አስተማሪ በጎደለ ጋሽ ሚካኤል፤ ዳይሬክተሩ ይልከኝ ነበር። ሐረር አይሁን እንጅ መምሕራን ማሰልጠኛ አዲስ አበባ ኮከበ ጽባሕ ደረሰኝ። የዚያን አመት መከፈቱ ነበር። ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴም   ከአስረኛ ክፍል አላለፈም። የመምህርነት ትምህርቱም የሳብኩትን አይነት አልሆነም። Education የሚል የሚያስተምር የዞረበት የሚመስል ሲድኒይ የሚባል ሕንድ ነበርና አንዱ ምክንያትም ያ ሊሆን ይችላል። ባሕር ዳር በሌላ ሙያ ሥራ ሔጄ እዚያም በትርፍ ጊዜ 7ኛና 8ኛ አስተምር ነበር። ዲሬክተሩ ሐረገወይን፤ የካርምቦላም የቢራም ጓደኛዬ ስለነበረ ሊሆን ይችላል። ዩኒቨርሲትም ስገባ የገባሁት ልክ እንደ ኮከበ ጽባሁ Faculty of Education ነበር። አልጥም አለኝና ወደ ሕግ ቀየርኩት። ይህንን  ማምጣቴ እዚያም እዚያም መረጃ ለማምጣት መሔዴና የመሳሰለው አስተማሪ ሊሆን ፈልጎ የተቀጨው ፍላጎቴ እየገባበት ሳይሆን አይቀርም እላለሁ። ከሰው ጋር ሳወራም ሆነ ብዙ በቴሌቪዥንና ራዲዮ የሰጠሁትን ቃለ መጠይቅ ያዳመጠ፣ ይህንን አንዳንዴ ሐራምባና ቆቦ የመርገጥ ነገር የሚያይ ይመስለኛል።
አንድ ሌላ ለዚህ ሃራምባና ቆቦ (እኔ ነኝ ያልኩት) የመርገጥ ነገር ምናልባትም ከአንባቢዎቹ ጋር ተሰባስበን የምናወጋ ስለሚመስለኝም ይሆነናል። የሚያነቡኝ ሳይሆን የሚያዳምጡኝ ሳይመስለኝ አይቀርም። “ብልጭ ሲልብኝ!” ወረቀት አነሳና ወይም ወደ ኮምፒውተር እሔድና የሆነውን እናገራለሁ። ወይም እላይ “ከአንጀቴ ነው!” ያልኩት መሆኑ ነው። በምጽፍበት ጊዜ እኔ እዚያ ያለሁ አይመስለኝም። ያለው አሰፋ ቃለ ተቀባይ (Trnscriber) ወይም ጸሐፊ ነው። የተነገረውን እንዳለ ያሰፍራል። ልክ ጽፌ ስጨርስ አለቀ ማለት ነው። የቃል ተቀባይነቱ ሥራ አለቀ ማለት ነው። ተመልሼ ፊደልም ሆነ ሌላ ግድፈት ካለ ማስተካከሉ ወይ ይደክመኛል፤ወይም ያስጠላኛል፤ ወይም “እኔ ቅድም ሥራዬን ጨርሻለሁ!” የማለት ነገር የሚመጣብኝ ይመስለኛል። ከዚህ የተነሳ በጻፍኳቸው ውስጥ ብዙ የፊደል ግድፈት ይገኛል።
የሐራምባና ቆቦው ሌላው ምክንያት አንድ ሰው ከሌላ ወይም ከሌሎች ጋር ሲያወራ እየተናጠቀ ወይም እየተቀባበለ  ብልጭ የሚለውን እየጨመረ እየቀነሰ፣ እንደ አመጣጡ ስለሆነ በጽሁፌ ውስጥ የሚታየው “ነካክቶ ማለፍ፣ ያንንም ያንንም መነካካት” እዚያው ቁጭ ብሎ ከማውጋት ጋር የሚገናኝ ይመስለኛል።  ይህ መልስ  መላምትነት የሚያጣው አይመስለኝም።
ይህ “እመልስበታለሁ!” ብሎ አለመመለስ ሳይንሳዊ መሠረት፤ የተፈጥሮ ህግ የሚገዛው ይመስለኛል። የምናውቀውን የምናስቀምጥበት ጊዜያዊና (Short Memory) ዘላቂ (Long Term Memory) ሳጥን አለ። ዘላቂ የምንለው ዘለዓለማዊ ባይሆንም እንደ ጉዳዩ ክብደት ከዘመናት በኋላም፣ አንዳንዴ በልጅነታችን የሆነውን እናስታውሳለን። ጊዚያዊው ሳጥን ውስጥ የሚቀመጠው ከደቂቃ ወይም አንዳንዴ ከስኮንዶች በኋላ ሊተን ይችላል። “አሁንኮ ምላሴ ላይ ነበር!” ስንል ያንን ማለታችን ነው። ይህ የተፈጥሮ ህግ፣ ዛሬ እዚህ ከገባሁበትም ለመውጣት አገለገለኝ ማለት ነው!
****
ይገረም አለሙ ስምንት ጥያቄዎች ሰንዝሮልኛል። ከአንድ እስከ አራት ያለው ጥያቄ ተቀራራቢነት ያለው ስለመሰለኝ፣ አንድ መልስ ልሰጥ ፈለግሁ። ተቀራራቢነቱ  “በጽሁፎችህ ውስጥ “ያም ሆነ፤ይህም ሆነ እያልክ ነካክተህ ተውካቸው እንጅ እንዲህ ቢሆን፤እንዲያ ቢሆን የሚል ቁልጭና ጥርት ያለ ምስል ጠልቀህ አልሳልክም “ የሚል ነው። ቃል በቃል ባይሆንም መንፈሱ ይኸውይመስለኛል። አባባሉ በከፊል ልክ ነው። በከፊል ልክ አይደለም። ለማስረዳት ልሞክር።
አሁን ወደ ሁለት አመት ይጠጋዋል።ዋሺንግቶን ዲሲ ሔጀ ነበርና ያሬድ ጥበቡ፤ “መወያየት መልካም” በሚለው ፕሮግራሙ፤ ለረዥም ሰአታት ጠይቆኝ ነበር። ከውልደቴ፣ እድገቴ ጀምሮ እስከ አሁን ዝቅጠት ድረስ። እኔ ተከታትዬ አላዳመጥኩትም። የራሴው ስለሆነ የምማርበት አዲስ ነገር የለውም በሚል ይመስለኛል። በዚህ ሰሞን በሆነ ምክንያት Utube ስገባ፣ ያ ከያሬድ ጥበቡ ጋር ያደርግነው “መወያየት መልካም“ እዚያ ተለጥፎ አብዛኛውን ቦታ ይዞ አገኘሁት። ከዚህም በላይ ከ35,000 በላይ ሰው እስካሁን አዳምጦታል የሚልም አነበብኩና እስቲ እኔም ላድምጠው ብዬ አንድ ሶስቱን ያክል አዳመጥኩ። በስድስት ክፍል ተከፋፍሎ ነበር የቀረበው።
እኔ ሳዳምጠው ወደድኩት። እንደዚያ በዝርዝርና በጥልቀት መሔዳችን ትዝ አይለኝም ነበር። የነበረውን የኦሮሞ እንቅስቃሴ ይዳስሳል። ይህ የሆነው የአሁኑ ሕዝባዊ አመጽ ከመጀመሩ ከአመት በፊት ነበር።
ይሕ ሕዝባዊ አመጽ እንደሚነሳ በግልጽና በማያሻማ ቋንቋ ተናግሬአለሁ። በሁለት ምሳሌ ነበር ያስረዳሁት። በደርግ ዘመን፣ “ውስጥ ውስጡን ሲብላላ ቆይቶ የካቲት ኢ 1966 ፈነዳ” የሚለውንና  “መከራ ሲመጣ አይነግርም አዋጅ፤ ሲገሰግስ አድሮ  ከተፍ ይላላል እንጅ!” የሚለውን።  በነዚህ  ምሳሌዎች ወያኔን፤ “የፈተናህ ቀን ተቃርቧልና፤ መጀመሪያ ራስህን አድን። ለራስህ መዳን የምታደርገው፣ ከተነጋገርንበት ዘልቆም ለጋራ ቤታችን መዳንም ይረዳል” የሚል ነው። ለማጋነን ብፈልግ፣ “ትንቢት ተናገረ” ተብሎ ሊወሰድ የሚችል ይመስለኛል:: ተቃዋሚ ፓርቲዎች ላይም ያተኮረ ረዥምና ሰፋ ያለ ትንተና እና ምክርም ሰጥቻለሁ።
ይህ “የመወያየት መልካም” ፕሮግራም የተላለፈው በድረገጾች ላይ ነው።ከዚህም የተነሳ ምንም እስከ ዛሬ ከ35,000 በላይ ሕዝብ ያዳምጠው እንጅ ይገረም አለሙን ጨምሮ ብዙዎች ያዳመጡት አልመሰለኝም። በዚህ ጉዳይ ላይ የምሰጠው ምክር ወይም ማሳሰቢያ ቢኖር እባካችህ፤ “መወያየት መልካም” የሚለውን ቃለ መጠይቅ አዳምጡት የሚል ነው። እኔ በዚህ ድረ ገጾችን በመኮርኮር ይህንንም ያክል የላቀ እውቀት የሌለኝ Utube ላይ ያለ ችግር ማግኘት ከቻልኩ ለአብዛኛው ሰው ቀሎ የሚታይ ይመስለኛል።
*****
የይገረም አለሙ ጥያቄ፤ “አሁን ባለው ሕዝባዊ አመጽ ጉዳይ በቀጥታ ለምን አትጽፍም?” የሚል አንድምታም አለው። በነሐሴ ወር 2008 ፣አንድ “ግልጽ ደብዳቤ” “ለኢትዮጵያ መንግስት መሪዎች” የተዘጋጀ ረቂቅ፣ ለመነጋገሪያ ርእስ ይሆናል በሚል፤ ከዚያም ተነስቶ የአማራጭ መንገድ አዘጋጆች ማደራጀት የሚችል የሽምግልናና የሁከት አስወጋጅ አካል  Conflict/Dispute Resolution) ለማቋቋም በማሰብ ለዚህ ይመጥናሉ ለምላቸው ወደ አስራ አምስት ለሚሆኑ በቅርብም፤ በሩቁም፤ በስምም ለማውቃቸው በEmail ላኩኝ። ከአንድ ሰው በስተቀር ደርሶኛል የሚል ተራ መልስ የሰጠኝም አልነበረም። የዚህ የአንዱ ሰዉዬ መልስም የለበጣ ነበር። ይህንን “ግልጽ ደብዳቤ” አደባባይ ላይ እንዲነበብ ሰሞኑን ከትንሽ ማብራሪያ ጋር ድረገጻት ላይ እለጥፋለሁ። ለአዲስ አድማስም እልካለሁ።
ከዚያ በኋላ ይህ “የሕዝብ አመጽ”፤ የ”አማራ” እና “የኦሮሞ” “ምሁራንና ብሔርተኞች ነን” የሚሉ ፈለፈለ። ሁሉም የዚህ “የሕዝቡ አመጽ ጠንሳሽ አነቃናቂ፤ መሪ --- እኔ ነኝ! የሚል ሆነ። ከዚህም ሌላ ግልጽ ደብዳቤውን ከላኩላቸው ወዳጆቼ ሌላ፣ በግል የማውቃቸው፤ ቢያንስ በሳምንት አንዴ ስልክ የሚደውሉልኝና የምደውልላቸውም ሰዎች ሸሹኝ። እንኳንስ ስልክ ሊደውሉ ስደውልም አላነሳም አሉ። አንዳንድ የሕዝብ መገናኛዎች (MassMedia) እኔንም ስልኬንም አናውቅም ያሉ መሰለኝ። በዚህ ላይ የሚጽፉትንና የሚናገሩትን ሳነበው ሳዳምጠው “ይህ የመጨረሻው እውነት ነውና ወይ ተከተለኝ ወይም አርፈህ ተቀመጥ!  ያለበለዚያ…!” የሚል አንድምታም ያለው ሁኖ አገኘሁት። በዚህ ላይ “የሚያልፍ ቀን የማያልፍ ስም ይሰጣል!” አይነት ዘለፋ መዘላለፍ በአደባባይ ላይ አየሁ። “የውሻን ጥርስ ማየት  አጥንት ሲግጥ ነው!” የሚባለውንም አስታወስኩት። የሾለ ጥርሱንም አየሁት! ይህ ጅምላ ጩኸት ደርግ “የታሪክ ሽሚያ” ያለው አይነቱ ጋብ እስኪል፣ እስቲ ጋብ ልብል ብዬ  መለስተኛ ሱባዔ (Introspection) ውስጥ ያለሁ ይመስለኛል። ወዳጄ የነበረው ጸጋዬ ገብረመድኅን፤ “የከርሞ ሰው” ውስጥ አብዬ  ዘርፉን ያናገራቸውንም ያስታውሰኛል።”ምኞቴ እንደጉም ፈንጥቆ፤ ተስፋዬ እንደጉድፍ ወድቆ…” ይላሉ አብዬ ዘርፉ። እነኝህም፤ “ቅዠቴ እንደጉም መንጥቆ፤ እውነቱ ግን አዚሁ ፊታችን ተደብቆ…” የሚሉ ወይም ማለት ያለባቸው ይመስለኛል።
ያም ሆኖ መሀል ለመሀል ሰንጥቄ አልሂድ እንጅ ዙሪያውን ማንዣበቤ አልቀረም። ይገረም አለሙ የሚጠቅሳቸው ጽሁፎቼ የዚህ ተአቅቦ (Introspection) ውጤቶችም ሳይሆኑ አይቀሩም ብዬ አስባለሁ።
አሁን እኒህ የኢትዮጵያን ሰፊ ሕዝብ አመጽ ባለቤትና መቀራመት የፈለገው መጯጯህ ጋብ ወደማለት የመጣ ይመስለኛል። “ሽል ከሆነ ይገፋል፤ ቦርጭ ከሆነ ይጠፋል!” የሚባለው አይነት መሆኑ መሰለኝ። ቦርጭ ነውና የሚግበሰበስ ሲጠፋ ወይም ሲያልቅ መሟሸሹ ያለ ነው። ለመጠባባቂያ ብለው መጋዘን ውስጥ ያስቀመጡት፤ ይህም ማለትታሪክ፣ ትምህርት፤ ተመክሮ፤ የፖለቲካ ንድፈሐሳብ (Theory)፤ እምነት፣ የኢትዮጵያ  ፍቅር በአብዛኛው የሚጎድለው ስለነበረ መሟሽሹ ባይገርመኝም “እስኪያልፍ ያለፋል!” ማለቴም አልቀረም።
 የ”አማራ” ንቅናቄ፤ እንቅስቃሴ፣ “የኦሮሞ” ያ ይህ” እያሉ መድረኩን አጣበው በነበሩት ላይ የጻፍኩት፤ ”የጋራ ቤታችን፤ ሳይደፈርስ አይጠራም!” የሚል ሰሞኑን አወጣለሁ። በመጠኑ “ከፈት አድርጎ ለማየት!” ነው። በአውራ ጎዳናው መጓዝ ለምንፈልገው መነጋገሪያ ይሆናል ብዬ አስባለሁ፡፡
****
አሁን ደግሞ ወደ ይገረም አለሙ ስድስተኛ ጥያቄ ልሂድ፡፡ ”ወያኔ አዲስ አበባ እንደገባ፤ ለፖለቲካው ጫወታ “በየጎሳችህ ተደራጁና ኑ” ሲል በአንድ ጀንበር ሊባል በሚችል መልኩ፣ ከደቡብ ወደ አስራ አምስት ድርጅቶች ተመሠረቱ። ከነዚህ አንዱ የእርሶ ነበር” ይላል።
ይህ ጥያቄ ከፊል እውነት፣ ከፊል እውነትም ያልሆነ አለው።
በ”አንድ ጀንበር” ላለው አንድ የማውቀውን ብናገር ጥሩ ይመስለኛል። ምክር ቤት እንደተገባ ሕዝብ ደሕንነት ወስጥ የሚሰሩ ይመስሉኛል፤ ሁለት ወላይታዎች፣ የወላይታን ህዝብ እንወክላለን ብለው መቀመጫ ያዙ። በኋላ በወያኔ መለኪያ መሠረት፤ “ንክኪ” ናችሁ ተባለ። ንክኪ ማለት የደርግ ጠረን፣ ኢሰፓ የሚሉት መሆኑ ነበር። በደርግ የተነዛዛ ክርክር ፈጥረው አንወጣም አሉ። በነጋታው ይሁን እንዲያ ኢትዮጵያ ሆቴል ፊት ለፊት አቶ ሙሉ ማጃን አገኘሁት። የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ ሆኖ አርባምንጭ በመጠኑ አውቀዋለሁ። ወላይታ ነው። ይህንኑ ችግር ነገርኩት። በነጋታው ሶስት ሰዓት አራት ኪሎ ምክር ቤት በራፍ ላይ አገኘሁትና፤ “ምን ታደርጋለህ?” ስለው፣ “የወላይታን ሕዝብ ወክለን መጣን!” አለ ።አብሮት በኋላ ስሙን ያወኩት አቶ ሉለሥላሴ ቴማሞ ነበር። ሉለሥላሴ ባለቤቱ የትግራይ ሰው ነች ያሉኝ መሰለኝ። በኋላ የባህል ሚኒስቴር ሆነ። ከስንት አመት በኋላ፣ ሙሉ ማጃ ከዶክተር በየነ ጴጥሮስ ጋር ስለ ደቡብ ሊያስረዳ አሜሪካን መጥቶ ነበር። አላገኘሁትም። ሙሉ በዚያ ሽፋን ዘመድ ለመጠየቅ ነው የመጣውና፣ ካናዳ ሔደ ብሎ በየነ ነገረኝ። ፊታውራሪ መኮንን ዶሪም አብሮ መጥቶ ነበር። ለደቡብ ጉዳይ! ፊታዉራሪ መኮንን ከኦሞቲክ “ውሐ ቀጠነ!” ብሎ ለቆ፣ ኢሕአዴግ ሆኖ፣ የማስታወቂያ ምክትል ሚኒስትር ሆኖ ተሹሞ ነበር። ነገርን ነገር ያነሳዋል። እግረ መንገዱን በየነ ጴጥሮስ፣ የደቡብ ሕብረትን እንዴት እንደቀበረው የሚጠቁምም ይመስለኛል።
እኔ  ምክር ቤት የገባሁት በጎሳ አይደለም። “ጎሳ”ቃሉንም ሲባል ከመስማቴ በስተቀር ተጠቅሜበት አላውቅም። በተፈጥሮ ሕግ መሠረት፤ “ቆሞ- ቀር” ነገር የለም። ይወለዳል፤ ያድጋል፤ ይተካል፤ ይሞታልም። ይህ ለሰውም ለሕብረተሰብም ለፍጡራን ሁሉ የሚያገለግል ነው። እኔም፤ ወደድኩም ጠላሁም፣ በዚሁ ሕግ መሠረት እጓዛለሁ። ይህንን ሕግ አንቀበልም የሚሉ ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ በግልጽ በአደባባይ ላይ ይታያሉ። ወደ ”ዘመነ መሣፍንት” ለመጓዝ መፈለጋቸውን በተለያየ መንገድና ቃላትም ይገልጹታል። ”የጎበዝ አለቃ” የሚለው ከነዚህ ውስጥ አንዱ ይመስለኛል።ጉድ የሚያክል መጽሐፍም የጻፉም አሉ። ለክፉም ለደጉም የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ አካል ነበርኩ። አምሳልም ባልሆን። ግራ ዘመም የፖለቲካ እምነት አለኝ። ገና ለገና ሶቭየት ሕብረት ወደቀ ብለው፣ “ቅሌን ጨርቄን!” ሳይሉ ፈርጥጠው ዕምነት አልባ የሆኑት ውስጥ አይደለሁም። የምኖረውም በ21ኛው ምዕተአመት ውስጥ ነው። “ብሔረሰብ” ነው የምለው። “ጎሳ” ማለት ዘመናይ አባባል አይመስለኝም:: የሕብረተሰብን እድገት አያንጸባርቅማና! ይህንን ጥያቄ፤እላይ ባነሳሁት “መወያየት መልካም” ውይይት ውስጥ ያሬድ ጥበቡም አንስቶብኝ ስመልስ፣ በሳቅ የፈነዳ ይመስለኛል። ያንን መመልከቱ ጥሩ ነው። ከጅምላ መደመር (Generalization,) የመጣ ጥያቄ ይመስለኛል። ”ከነእንትና ጋር ነበርና …ስለዚህም…” (by Association) እንደማለት፡፡
****
እኔ፤ አፍሪቃ አዳራሽ ስብሰባውም ሆነ በኋላም የሽግግር ምክር ቤቱ አባል የሆንኩት “ኦሞቲክ” የሚል ድርጅት ሊቀመንበርና አባል ሆኜ ነበር።
ለመሆኑ ኦሞቲክ ምንድነው? የኦሞን ወንዝ ሥም ተከትሎ የወጣ ስም ይመስለኛል። የኦማቴ ሕዝቦች ዝርያ ማለት ነው። ከሲዳማ ይጀምርና ዛሬ አሶሳ አካባቢ ያለው ባምባሲ ድረስ የሚደርስ ህዝብ ነበር። ማእከሉ የከፋ ንጉሥ ነበር። የከፋው ንጉስ ጋኪ ሸረቾ፣ በራስ ወልደጊዮርጊስ፤ ደጃዝማች ደምሰው ነሲቡና ደጃዝማች ተሰማ ናደው በሚመራ የምንሊክ ጦር ተሸንፈው በግዞት፣በ1911 አመት ሞቱ። የጅማው አባ ጅፋር የራሱን 30,0000 ጦር ይዞ ይዚህ ዘመች አካል ነበረ። ለአባ ጅፋር ሁለተኛ ዙር መሆኑ ነው!
ጂማ ጅማ የሆነው፤ ማለትም የተፈጠረው፤ የኦሮሞን የ16 ምእተ አመት ወረራ ተከትሎ ነው። በዚያ ወረራ የአካባቢውን ሕዝብ ደምሰሰዋል ማለት ነው። አሁን የምንሊክ አካልና አምሳል ሆነው ከፋን ሲወር ሁለተኛ ዙር መሆኑ ነው። አባ ጅፋር ምናልባትም በመላው አለም ተዋዳዳሪ የማይገኝለት የባሪያ ፈንጋይና ነጋዴ ሆነ። የተለያዩ ጸሐፊዎች በዚህ የባሪያ ንግድ ላይ ጽፈዋል። ከታወቁት ውስጥ ታዋቂው ሪቻርድ ፓንክረስት ይገኙበታል። የበለጠ በጥልቀት ለመረዳት፡ Ethiopian Slave Export at Matama,Massawaand Tajura  c1850-1885 by Abdussamad H.Ahmed  የሚል ጥናት ማንበብ  ሙሉ ምስሉን ይሰጣል ብዬ አምናለሁ።
በዚያን ዘመን ከኢትዮጵያ ወደ 500,000 ባርያ ወደ መካከለኛው ምስራቅ እንደተሸጠ ተመዝግቧል። ባሪያዎቹ የተፈነገሉት በአብዛኛው ከዚህ የከፋ ግዛት ወይም ተባባሪ ግዛት ከነበሩት ሁሉ ነው። ይህም ማለት ከጋሞም የተፈነገሉ እንዳሉ፣ የተፈነገሉበት አገርና ስም ጭምር ተመዝግቧል። የጋሞ ባሪያዎቹ፣ ብርቱ ሠራተኛ ስለሆኑ ጥሩ ዋጋ ያወጣሉ ይላል። ከሁሉም የሚደንቀው አባ ጆብር ለጥርስ ሃኪማቸው የከፈሉት አምስት ባሪያ ነው። አንድ ውሻ በሁለት ባሪያ ለውጧል። የሰውን ልጅ በውሻ ሲለውጥ ነበር። ከዚህም ሌላ አባ ጆብር፤ ምንሊክ ወላሞ (በወቅቱ አጠራር) ሲሞቱ 10,00 ወታደር አሰልፎ የዘመተና ዎላሞ ለመሸጥ መለወጡ አባልና አካል ነበረ።
ጅማ የአባጆብር ቤተመንግስት ያለበት፤ ሔርማታ፣ ምንልባትም በዓለምም ደረጃ ትልቁ የባሪያ መሸጫ ገበያ ነበር። ከዚህ ገበያ የተገዙ ባሪያዎች በመተማ፤ በታጁራ፤ በምጽዋ በኩል ለመካከለኛው ምስራቅ ገበያ ይቀርባሉ። የጉዞው መንገድ ከሔርማታ ወደ ጂረን- ወደ ሰቃ፤ ወለጋ ሌቃ- ነቀምቴ ውስጥ ቢሎ፣ በሆሮ ጉድሩ ውስጥ አሳንዳቦ፤ ጎጃም ውስጥ ባሶ፣ ትግራይ ውስጥ አድዋ ነበር። ጥቂቶችን ለመጥቀስ!
ከነዚህ አጥኒዎችና ጸሐፊዎች መረዳት የሚቻለው፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ለተፈጸመው ባሪያ ፍንገላ፤ ማጓጓዝ፤ መሸጥና መለዋወጥ ትልቁ ድርሻ የሚወድቀው ዛሬ ከፋ፤ ኢሊባቦርና ወለጋ በሚለው አካባቢ በሚገኙ ኦሮሞዎች ላይ መሆኑ ነው። ምንሊክም፤ ጎጃም፤ ጎንደርና ትግሬም የዚያው ንግድ ሰንሰለት አካልና አባል ነበሩ። የሚገርመው ለክርስቲያኖቹ እምነታቸውም፤ ሕጋቸውም ባሪያ መሸጥ መለወጥን ይፈቅድላቸዋል። ፍትሐነገሥቱ የሚለው ይህንኑ ነው። ፍትሐነገሥቱ የተቀዳው ደግሞ ከኦሪት(Old Testament) ነው።
****
እናም እነዚህ ኦሞቲክ ወይም ኦማቴ ተብለው ይጠሩ የነበሩ ሕዝብ፤ ከሲዳማ አስከ አሶሳ ባምባሲ ይደርሱ የነበረው ሕዝብ ዛሬ የት ደረሰ?
ለዚህ የዚህ  Afroasiatic Languages  ብለው የሚያጠኑትን የቋንቋ ሊቃውንት የጥናት ወጤት ማንበብ የሚጠቅም ይመስለኛል። ከነዚህ አንዱ M.Lionel Bender ብዙ መጽሐፍ ጽፏልና Comparative Merphology of the Omotic Languages  የሚለውን ማንበቡ ያግዛል። ከነዚህ ሕዝብ ዛሬ በላው ኢሉባቦርና ወለጋ የተረፈፉትን በቁጥር ይመዘግባል። አንፊሎ፤ ወለጋ፤ ደምቢዶሎ፣ ውስኪ በመለኪያ ሳይሆን በጠርሙስ በሚቀርብበት ከተማ (1967 ክረምት አይቻለሁና) የኦሞቲክ ተናጋሪ 50 ያህል ቀርተዋል። ዶክተር ግርማ ደመቀ፤ የቋንቋ ምሁር፤ አንዴ ለጥናት ሔዶ አንድ ቋንቋውን በመጠኑ የሚናገሩ ሽማግሌ እንደ አገኘ ነግሮኛል። ባምባሲወደ 500 ተርፈዋል ይላል በንደር። አንዴ፤ በ1967 ወዳጄ ከነበረው የደርግ አባል፤ በኋላም ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነ ከነበረው ሻለቃ ደበላ ዲንሳ ጋር ወለጋ፣ ነጆ ከተማ በተደረገ፤ ወደ100,000 ሕዝብ በተካፈለበት ስብሰባ ላይ፣ አንድ የዚህ የኦማቴ ሕዝብ ተራፊ ሽማግሌ ተነስተው፤ “ዛሬ ለማመን የሚያዳግት ነገር ሰማሁ! ኦሮሞ ተጨቆንኩ ሲል ሰማሁ! እኛ በአለም ላይ የምናውቀው አንድ ጨቋኝ ቢኖር ኦሮሞ ብቻ ነው!” ብለው ነበር።
 ሁሉም የሚያየው ከራሱ አንጻር መሆኑ ነው። ግና ለእኩልነት እንታገላለን የምንል፤በተለይም ተማርን ተመራመርን የምንል በአንጻራዊ መልኩ (In Context) ሙሉውን ስዕል ብናይና ብናሳይ፣ ቢያሳዩን ለሁላችንም የሚበጅ ይመስለኛል። በነገራችን ላይ  ዛሬ ይህ የኦሞቲክ ሕዝብ አናኗር፤ ልክ በኦፓርታይድ ዘመን ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ Homeland እንደሚሉት ወይም እዚህ አሜሪካ ቀይ ሕንዶች ብለው የሰየሟቸውን የጥንት ባለርስቶችን Reservetion ብለው በሰየሙት ውስጥ እንደሚያኖሩት ነው! የሞትና እልቂት ፈፋ ላይ ማለት ነው!
አጥኝዎቹ፤ ይህንን የኦሞቲክ ሕዝብ የአፍሪቃ ቀንድ (Horn of Africa) የመጀመሪያው ሕዝብ ይሉታል። ዝርያዎቻቸው ጥቂትም ቢሆን ታንዛኒያ ውስጥ እንደሚገኙ ጽፈዋል።
 ይህ አርሲ ውስጥ ምንሊክ ስለቆረጣቸው ጡቶች የቆመውን ሐውልት አስታወሰኝ። ጅማ፤ሔርማታ ሰነጋል ወስጥ የሚገኝ  ደሴት ላይ  ያለ አንድ በባርነት እየተፈነገሉ ለተሸጡ አፍሪቃውያን የቆመ ሐውልት አስታውሰኝ። Gore Island! Home of “The Door Of Never Return!” ይላል። ጅማ ከተማ በሙሉ ባይሆንም ሔርማታ ላይ “ተፈንግለው ወጥተው ለቀሩ!” መታሰቢያ ሐውልት ማቆም ተገቢ ይመስለኛል። ቢያንስ ከአንድ ታሪካዊ እድፋችን የሚያነጻን ይሆናል ብዬ አስባለሁ። እገረመንገዱን ለጅማም የቱሪስት ትኩረት የሚፈጥር ይመስለኛል። የዚህ የሴነጋሉን የማይመለሱበት በርን፡- The Door Of No Return  ሐውልት የአለም ቱሪስት ይጎበኘዋል። ፕሬዚዳንት ባራክ ኦቦማም ገብኝቶታል።
ይህ ሁሉ እኔ ተካፋይነቴ “በጎሳ” ሳይሆን ኦሞቲክ በሚል ነበር ለማለት ነው። ወዳጄ የነበረው ጸጋዬ ገብረመድኅን፤ “ማነው ምንትስ?” በሚለው ግጥሙ ውስጥ “ዝም ብንል፤ብናደባ ዘመን ስንቱን አሸክሞን፤ ተረስቶንኮ አይደለም እንድንቻቻል ብለን ነው…”  የሚለው አለው። እውነቱ ታውቆ ለዚህ አይናችን ስር ቁጭ ብሎ በመውደም ላይ ላለ ሕዝብ፤ “ለመሆኑ ማድረግና መደረግ የሚቻል ምን አለ” ብሎ ለማጠያየቅ አስቤ ነበር፤ ኦሞቲክ ያልኩት፡፡
            (ይቀጥላል)

Read 3419 times