Sunday, 25 December 2016 00:00

ይሁነን ብለን የፈቀድነው ልመና?!

Written by  ከጉማራ ዙምራ
Rate this item
(26 votes)

 “ወገኑ ለልመና ሲሰማራ ዝም ብሎ የሚያይ ህዝብና መንግስት ሆነናል”
                         
      አንድ ለማኝ መንገድ ዳር ቁጭ ብሎ፡-
“ወንድሞቼ ሁሉ ሄዱ ወደ ስራ፣
ይኽው እኖራለሁ በልመና እንጀራ! …. ወንድሞቼ ስለ ዓይነ ብርሃን” ---- እያለ ይለምናል፡፡
አንድ ከዩኒቨርሲቲ ከተመረቀ በኋላ ለሁለት ዓመታት ስራ የፈታ ወጣት፣ ኪሱ ውስጥ የነበረች አምስት ብር አወጣና፡- “ስማ ወንድም-----ብታይም ስራ የለም፡፡ አርፈህ ለምን!” ብሎ ብሩን እጁ ላይ አስጨብጦት አለፈ፡፡
ይህ መራር ቀልድ ከማሳቅ ባለፈ አሽሙር አዘል ሸንቋጭ መልእክት ያስተላልፋል፡፡ እያንዳንዱ ስንኝ ብቻውን መጽሃፍ የሚወጣው ጠንካራ ሃሳብ ይዟል። ልመናን አለመጠየፍ፣ ደካማ የስራ ባህላችን፣ ኢትዮጵያዊ የሆነው የመረዳዳት እሴታችን፣ በትክክል መረዳት ላለበት ሰው እየረዳን ነው? በኃላፊነት የምንለግስ (responsible giver) ነን ወይ? ተቀጣሪ እንጂ ስራ ፈጣሪ ያልሆነው ለምንድን ነው? ከመለገስ ባለፈ ወንድማዊ ምክራችን ምን ይዘት ሊኖረው ይገባል? ወዘተ---በሚል ሊያነጋግሩ በሚችሉ ዳጎስ ያሉ ሃሳቦች የታጨቀ ቀልድ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። እስቲ በዚህ ቀልድ መነሻነት፤ “ሰው፣ ግብረገብና ስነምግባር፡ የዘመናችን ቁልፍ ጉዳዮች” በሚል ርዕስ የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ፕሬስ ያሳተመውን የዶ/ር ጠና ደዎ መጽሃፍ እየጠቃቀስኩ ትንሽ እንወቃቀስ፡፡   
በሃገራችን ተንሰራፍተው ከሚገኙት ግብረገባዊ ግድፈቶች መካከል አንዱ ልመና ነው፡፡ ልመና በህብረተሰባችን ውስጥ እጅግ ስር የሰደደ ባህል እስከመሆን ደርሷል፡፡ ለብዙ ሰዎች ጤናማ ይመስላል፡፡ ሃብት የሌለው ይለምናል፣ ያለውም ይለምናል፣ ጉልበት የሌለው ይለምናል፣ ጉልበት ያለውም ይለምናል፣ ግለሰብም ይለምናል፣ ድርጅትም ይለምናል፣ መንፈሳዊ ተቋማት ይለምናሉ፣ መንግስትም ይለምናል፡፡ የሚለመነው ገንዘብ፣ ዳቦ ወይም ልብስ ብቻ አይደለም፡፡ ሀብት፣ ገንዘብ፣ እድገት፣ ስልጣን ወዘተ ይለመናል፡፡ ከቀልዱ እንደተረዳነው፤ ለማኙ የእርሱ ወንድሞች ወደ ስራ የሄዱት የዓይን ብርሃን ስላላቸው ብቻ ነው የሚል ምክንያት ሊሰጠን ፈልጓል፡፡ ስለ እውነት ማየት የተሳነው ሰው የግዴታ መለመን አለበት? ስለ ሥራ ያለን ግብረገባዊ አረዳድ ምን ይመስላል? የሰው ልጅ የስልጣኔ የእድገት መሰረታዊ ምንጩ ሥራ ነው። ታሪክ ይህን ሃቅ ያረጋግጣል፡፡ ሰው ለሥራ ያለው ግብረገባዊ ግዴታ በጥልቀት መታየት አለበት፡፡ አንድ ሰው ከመለመን ይልቅ የሚሰራው የሚፈልገውን ጥቅም ለማግኘት ወይም የሚደርስበትን ጉዳት ለመከላከል ብቻ አይደለም፡፡ ስራን መስራት በራሱ ግብ ነው፡፡ ከሎተሪ ማዞር ጀምሮ የህግ ባለሙያዎች፣ ደራሲዎች፣ ሊቃውንተ ቤ/ክርስቲያን፣ የፖለቲካ ሰዎች ---- መሆን የቻሉ ዓይናቸው ሳይሆን ልባቸው የበራላቸው ለሀገር መከበሪያ፣ ተጽእኖ ፈጣሪ የሆኑና አለማየታቸው ሳይገድባቸው መሆን የሚፈልጉትን ነገር ያሳኩ ግለሰቦች በየመንገዱ፣ በየስራ ቦታውና በተለያዩ አካባቢዎች መኖራቸውን እያየን አይደለም ወይ?
አንዳንዶቹ የተትረፈረፈ ዳቦ መፍጠር የሚችል ፈርጣማ እጅ ይዘው የቁራሽ ዳቦ መግዣ ሳንቲም ሲለምኑ ማየት ህሊናን ያደማል፣ ልብን ይሰብራል። ይህም ነውርን የዘነጉ አንዳንድ ግለሰቦች መኖራቸውን የሚያመላክት ነው፡፡ ልመናን እንደ መደበኛ የስራ መስክ የሚቆጥሩ ወገኖች መኖራቸውን የሚያመላክት ነው፡፡ ልመና ፍቃድ የማይጠየቅበት፣ ግብር የማይከፈልበትና ምንግዜም ለማንም በሩን ክፍት ያደረገ የስራ መስክ ሆኗል፡፡ በአንዳንድ የቤተክርስትያን ዓመታዊ የንግስ ክብረ በዓላት ላይ ማለዳ ቡቱቶ ልብሳቸውን ተከናንበው ሲለምኑ ውለው፣ ማምሻውን በጠላና በአረቄ ሰክረው አላፊ አግዳሚውን እየዘለፉ ሲያልፍም እየጎነተሉ ማለፊያ መንገድ የሚከለክሉ ጋጠወጥ ደበሎ ለባሾችን ማስተዋል የተለመደ ሆኗል፡፡ ከገጠርም ቢሆን አንደኛውን የእርሻ ወቅት አጠናቀው ሌላኛው የእርሻ ወቅት ከመግባቱ በፊት ወደ ከተሞች በመፍለስ በልመና ላይ የሚሰማሩ ወቅታዊ ለማኞች አሉ፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ “መንግስት የማዳበሪያ እዳ ክፈሉ ብሎ ሲያስጨንቀን ቀዬአችንን ጥለን መጣን” ይሉናል፤ በፖለቲካ አመካኝተው ልመና በማሕበረሰቡ ዘንድ ቅቡል እንዲሆን ሲመኙ፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ እኔ በግሌ ያጋጠመኝን የአንድ ለማኝ ታሪክ ላጫውታችሁ፡፡ ካዛንቺስ አካባቢ አይጠፋም ለማኙ፡፡ እጁ ፍጹም የለማኝ እጅ አይመስልም። የገበሬ እንጂ፡፡ ተክለ ቁመናው ይማርካል፡፡ በእያንዳንዱ እጁ ሁለት ሰዎችን በቀላሉ ወደ ላይ ለመወርወር የሚችል አቅም ያለው ጎልማሳ  ነው፡፡ ሰማያዊ ጋቢውን ተከናንቦ አንገቱን ወደ ግራ ዘመም ያደርግና እጁን ይዘረጋል፡፡ ለዘረጋው እጁ እጄን ዘርግቼለት ባላውቅም በተደጋጋሚ ሻይ ቡና ወደምልበት ቤት በመመላለሱ ሰላምታ መለዋወጥ ጀምረናል፡፡ አንድ ሰሞን ጋቢውን ከአናቱ እንደማውረድ እያደረገ ሰላም ይለኝ የነበረ ቢሆንም አሁን አሁን ገና ሲያየኝ በዓይኑ ጥቅስ ያደርገኛል፡፡ “አታስፎግረኝ-----ሌሎቹን ልቀፍል” እንደማለት፡፡
አንድ ቀን ከጎኔ ቁጭ አድርጌ አዋራሁት፡- “ወንድሜ፤ ሲያዩህ ጤናማና መስራት የምትችል ትመስላለህ፡፡ ለምንድን ነው የምትለምነው?”
“ያው መቼም በእርሻ ገቢ ኑሮን መምራት አልተቻለም”
“ምን ማለት ነው?”
“ማለቴ ያው ገጠር እርሻ አለኝ፤በዚያ ገቢ ልጆቼን፣ ቤተሰቤን መቀለብ አልቻልኩም፤ ለስራ ብዬ ካገሬ ወጥቼ መጣሁ፤ ስራ እስካገኝ ብዬ ወደ ልመና መንደር ጎራ ስል ገቢው ጥሩ ነው፤ቀጠልኩበት”
“ቤተሰብህ አዲስ አበባ እንደምትለምን ያውቃሉ?”
እንደ ማማተብ እየቃጣው፤ “እረረረ እንዲያውም አያውቁም፡፡ አዲስ አበባ ስራ እንደምሰራ እንጂ እንደምለምን በፍጹም አያውቁም፡፡”
“ታዲያ ከልመና ስራ መስራት አይሻልም ነበር?”
“ሞኝ ነህ እንዴ? የአዲስ አበባ ሰው እጄን ስዘረጋለት ይሰጠኛል፤ታዲያ ምን አገባኝ ብዬ ነው ስሸከም የምውል!” ብሎኝ አረፈው፡፡
ይሄ ጉዳይ ስንቶቻችን ነን በኃላፊነት የምንለግሰው (responsible giver የሆነው?) የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡ እጁን ለዘረጋ ብቻ ሰጥቶ ማለፍ ተገቢ አይደለም፡፡ ከኪሳችን አውጥተን የምንሰጠው ሳንቲም፣ ብዙዎችን ዳቦ እንዲገዙበት ያደረገ ቢሆንም አሁንም ሌሎች ሺዎችን ሳይሰሩ የመብላት ባህል እንዲጠናወታቸው እያበረታታ ነው፡፡  
እንደ ዶ/ር ጠና ደዎ ገለፃ፤ ዛሬ በሃገራችን ተንሰራፍቶ የሚታየው የልመና ሕይወት ሁለት ዐበይት መንስኤዎች አሉት፡- አንደኛው ግለሰባዊ፣ ቤተሰባዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና መንፈሳዊ ችግሮች ሲሆኑ ሁለተኛው ግብረገባዊ ዝቅጠት (Moral degeneration) ነው፡፡ የሁለቱም መሰረታዊ መንስኤ ግን ዞሮ ዞሮ የግብረገባዊ ህይወታችን አለመዳበር ነው፡፡ ለዚህ ማህበራዊ ችግር መግዘፍ ለማኙም ሆነ ተለማኙም፣ መንግስትም ሆነ ሕዝብ ግብረገባዊ ተጠያቂነት አለባቸው፡፡ ራስን ለልመና ማሰማራት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መከበር በሚኖርበት ማንነት (ሰብእና) ላይ እኩይ ተግባር መፈፀም ነው፤ በራስ ሰብእና ላይ ጉዳት ማድረስ ነው፡፡ ይህ ከግብረገብ ሕግጋት አኳያ የሚነቀፍ እንጂ የሚደገፍ አይደለም፡፡ ግብረገብ ራስን ማክበር እንደሚገባ ያስተምራል፣ ለራስ ዋጋ መስጠት የሁሉም ሰው ግብረገባዊ ግዴታ መሆን አለበት፡፡ በተፃራሪ የራስን ክብር የሚነካ፣ የሚያጎድፍ ወይም በራስ ሰብእና ላይ አፍራሽ ነገር መፈጸም ኢ-ግብረገባዊ መሆኑን ያስገነዝባሉ፡፡
ታሪካዊ አነሳሱ ከታየ ልመና የምርጫ ጉዳይ አይደለም፡፡ በባህሪው ማንነትን ዝቅ የሚያደርግ ስለሆነ፣ ራሱን በውል የሚያውቅ ጤናማ ሰው ፈቅዶና መርጦ የሚሰማራበት ህይወት አይደለም፡፡ ልመና ዘላቂ መፍትሄ የሚያሻው ሀገራዊ ችግር ነው። ህብረተሰቡ ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ለልመና የሚዳረግ ወገንን በዘላቂነት የመታደግ ግብረገባዊ ግዴታ አለበት፡፡ መስራት የሚያስችል አቅም ያለውን ወደ ስራ የማስገባት ኃላፊነትም እንዲሁ፡፡
በሃገራችን ውስጥ የሚታየው ልመና፤ የሰውን ደግነትና ቅንነት ትርጉም ከሚያሳጡ ነገሮች መካከል አንዱና ዋነኛው እየሆነ ነው፡፡ አንደኛ፤ ልመና ቅጥ ያጣና የማይድን በሽታ እየሆነ መምጣቱ ህዝብን አሰልችቷል፡፡ ሁለተኛ፤ በልመና ከሚኖሩ ወገኖች መካከል ብዙዎቹ የህዝብን ደግነትና ቅንነት ለክፋትና  ጥፋት አውለውታል፡፡ ለምሳሌ የራጅ ወረቀት፣ ትንሽ መድሃኒት በፌስታል ይዞ፣ ጥቁር ሻሽ አናቱ ላይ ሸብ አድርጎ፣ ከወገቡ ጎበጥ ብሎ የሚለምን ጤነኛ ሰው ሞልቷል፡፡
በልመና ውስጥ ውሸት፣ ብልጠትና ክፋት መብዛቱ ባልተለመደ ሁኔታ መጨካከንን አስከትሏል፡፡ በእርግጥም እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች እንዳይረዱ እንቅፋት እየሆነ ነው፡፡ ለመርዳት ፍቃድም አቅምም እያለን መርዳት አለመፈለግ ተፈጥሮአል፡፡ ከልመናው ጀርባ ያሉ እኩይ ነገሮችን በማሰብ፣ ብዙ ሰዎች ከመርዳት መታቀብን እየመረጡ  ነው። ይህ ኢትዮጵያዊ የመረዳዳት በጎ ባህላችንን እያደበዘዘው ነው፡፡  
ልመና በተለይ በከተሞች ውስጥ የውጭ ሀገር ዜጎችንና ሀገር ጎብኚዎችን በነጻነት የመንቀሳቀስ መብት ይጥሳል፡፡ ቱሪስቶች በተለይ በከተሞችና በሚጎበኙ ቦታዎች የተወሰነ ርቀት በእግር መጓዝ ይመርጣሉ፡፡ ነገር ግን እጅግ በሚያሳፍር ሁኔታ ህጻናት፣ ወጣቶች፣ አዛውንት፣ ሴቶች ተራ በተራ ይረባረቡባቸዋል፡፡ አንዱን ሰጥተው ቢገላገሉትም ሌላኛው ባለተራ ይተካል፡፡ አሁን አሁን በትራፊክ መብራቶች ላይ ህጻናትን ተሸክመው መለመን ፋሽን ሆኗል፡፡ አንዳንዴ እንደውም ልጅ ይዞ መለመን ጠቀም ያለ ገቢ ስለሚያስገኝ ተገደው ተደፍረው ሳይሆን ሆነ ብለው የሚወልዱ እንዳሉ ይነገራል፡፡
እነዚህና ሌሎች ያልተጠቀሱ ችግሮች የተፈጠሩትና የሚፈጠሩት መኖር የማይገባውን  ልመና እንዲኖር በመፍቀዳችን ነው፡፡ ልመና ጥገኝነት ነው፣ የህብረተሰብ በሽታም ነው፡፡ የተሟላ አካል ያለው ዜጋ ከቤት ወጥቶ ለልመና ሲሰማራ፣ ህዝብና መንግስት ዝም ብለው ሊያዩት አይገባም፡፡ ይህ ዝምታ ከፍተኛ የግብረገብ ጉድለት ለመኖሩ ማረጋገጫ ነው። ሰው ለራሱ ብቻ አይደለም የሚኖረው፡፡ በዋናነት ወገኑ ለሆነው ሌላ ሰውም ነው፡፡ ልመና በሀገራችን ውስጥ እንዲኖር በመፍቀዳችን ልናፍርበት ይገባል፡፡ ወገኑ ለልመና ሲሰማራ ዝም ብሎ የሚያይ ህዝብና መንግስት ሆነናል፡፡ “እኛ ምን ሆነን ነው ወገኖቻችን ለልመና የሚሰማሩት” ብለን መነሳሳት ሲኖርብን፣ “ሌላ ምርጫ የላችሁምና መለመን መብታችሁ ነው” በሚል የፈቀድንላቸው ይመስላል፡፡ ወገን መሆን የማይገባውን ሲሆን እያየን፣በቸልታ አልፈነዋል። ይህን ማድረግ አልነበረብንም፡፡ በዚህ የተጎዳው በልመና የተሰማራው የህብረተሰብ ክፍል (ግለሰቦች) ብቻ አይደሉም፡፡ መሰረታዊው ጉዳት የግለሰብ ሳይሆን የሀገርና የህዝብ ነው፡፡ ከሚያደርሰው ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ባህላዊ ችግሮች ሌላ የሀገርንና የህዝብን ክብርና ቁመና ያበላሻል፡፡ ሃገርና ህዝብም ተዋርደውበታል፡፡ ይህ ካልተለወጠ የተሻለ ሕይወት መመኘት ከቅዠት ያለፈ ሊሆን አይችልም።
ከመሰነባበታችን በፊት ሌላ በልመና ዙሪያ የተባለ ቀልድ ልንገራችሁ፡፡
ሰውየው ይለምናል፡- “ወንድሞቼ፣ ወገኖቼ አግኝቼ ያጣሁ ነኝ፤ አግኝታችሁ አትጡ ---- ስለ እመብርሃን አግኝታችሁ አትጡ ---”
ወጣቱ ከአፉ ነጠቅ አድርጎት፡- “ወንድሜ፤ አንተ አግኝቼ ያጣሁ ነኝ ትለኛለህ፤ እኔ አለሁ አይደል እንዴ ማግኘትን ያጣሁ፤ ገና ማግኘትን ፍለጋ ላይ ነኝ፡፡” ብሎት አለፈ፡፡

Read 11437 times