Print this page
Saturday, 24 December 2016 12:30

በኢትዮጵያ በየዕለቱ ከ530 በላይ ህፃናት ይሞታሉ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(4 votes)

“አንድም ልጅ እንዳይቀር” በሶማሌ ክልል ተጀመረ

       በኢትዮጵያ በቀላሉ ሊከላከሏቸው በሚችሉ በሽታዎች ሣቢያ 537 ህፃናት በየዕለቱ እንደሚሞቱ የተገለጸ ሲሆን ከእነዚህ የህፃናት ሞቶች 44 በመቶ የሚሆኑት የሚከሰቱት ዕድሜያቸው ከ28 ቀናት ባልበለጠ ጨቅላ ህፃናት ላይ ነው ተባለ፡፡
“ሴቭ ዘ ቺልድረን” በአርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች የሚኖሩ ማህበረሰቦች የጨቅላ ህፃናት ህክምና፤ እንዲሁም ቅድመ መደበኛ ትምህርት እንዲያገኙ ለማድረግና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ለማስቀረት የጀመረውን ‹‹አንድም ልጅ እንዳይቀር›› የተሰኘ ዘመቻ ሰሞኑን በይፋ ከፍቷል። በሱማሌ ክልል ጅጅጋ ከተማ ውስጥ በተካሄደው የመክፈቻ ፕሮግራም ላይ እንደተገለፀው፤ በአገሪቱ የህፃናት ሞት እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ የደረሰ ሲሆን በየአመቱም 196 ሺህ ህፃናት በቀላሉ መከላከል በሚቻልባቸው በሽታዎች ሳቢያ ሕይወታቸውን ያጣሉ፡፡ ከእነዚህ የህፃናት ሞቶች መካከል 44 በመቶ የሚሆነው የሚከሰተው እድሜያቸው ከ28 ቀናት በማይበልጥ ጨቅላ ህፃናት ላይ ነው ተብሏል፡፡
ለቀጣዮቹ 3 ዓመታት በአርብቶ አደርና በከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች ውስጥ በሚኖሩ ማህበረሰቦች ላይ ተግባራዊ ይደረጋል በተባለው በዚህ ፕሮጀክት፣ በአካባቢዎቹ በስፋት የሚታዩትን የጨቅላ ህፃናት ሞት፣ ያለ ዕድሜ ጋብቻና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች እንዲሁም የመደበኛ ትምህርት አለመኖር ላይ በትኩረት እንደሚሰራ ተገልጿል፡፡ በ”ሴቭ ዘ ቺልድረን” የምርምር ስርፀትና የዘመቻ ዳይሬክተር፣ ዶ/ር እሸቱ በቀለ  የዘመቻው መክፈቺያ ፕሮግራም ላይ እንደተናገሩት፤ በቀጣዮች 3 ዓመታት በአርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች፣ ሁሉም ህፃናት ተገቢውን የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ፣ ዕድሜያቸው ከ4-6 ዓመት የሚሆናቸው ህፃናት ጥራቱን የጠበቀ የቅድመ መደበኛ ትምህርት እንዲከታተሉ ለማድረግና ያለ ዕድሜ ጋብቻንና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስቀረት የሚሰራ ይሆናል - ፕሮጀክቱ፡፡  
ዘመቻው በሱማሌ ክልል እንዲጀመር የተደረገበትን ምክንያት ዶ/ር እሸቱ ሲያስረዱ፤ ሁሉም ችግሮች፡- የህፃናት ሞት፣ የቅድመ መደበኛ ትምህርት አለመኖር፣ ያለ ዕድሜ ጋብቻና ጎጂ ባህላዊ ድርጊቶች በስፋት የሚታዩበት አካባቢ በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡
ዘመቻው ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት ችግሩን ለማስቀረት የሚችሉበትን መንገድ እንዲፈልጉ ለማድረግ የታለመ ሲሆን ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ ለማግኘት የሁሉም ዜጋ ርብርብ እጅግ ወሳኝ መሆኑን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
የሱማሌ ክልል ፕሬዚዳንት፣ የሰብአዊ መብት ጉዳዮች አማካሪ አቶ አብዱልፈታ አህመድ በበኩላቸው፤“ክልሉ ካሉበት በርካታ ችግሮች መካከል ዋንኛው የሆነውን ጎጂ ባህላዊ ድርጊቶችን ለማስቀረት፣ የህፃናት ሞትን ለመቀነስና ቅድመ መደበኛ ትምህርቶችን ለማስፋፋት የሚደረገው ዘመቻ ውጤታማ እንዲሆን የበኩላችንን ጥረት እናደርጋለን” ብለዋል፡፡ ለዚህ ዘመቻ ስኬታማነት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ሊወጡ ይገባል ሲሉም አሳስበዋል፡፡
ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች በስፋት ከሚታዩባቸው አካባቢዎች አንዱ በሆነው የሱማሌ ክልል 60 በመቶ ሴት ህፃናት ግርዛት የሚካሄድባቸው ሲሆን በአማራ ክልል 47 በመቶ፣ በአፋር 31 በመቶ ሴት ህፃናት የግርዛት ሰለባ እንደሚሆኑ “ሴቭ ዘ ቺልድረን” ይፋ ያደረገው መረጃ ያመለክታል፡፡

Read 4550 times