Sunday, 25 December 2016 00:00

ወንጀል መርማሪው!!?

Written by  ኢዮብ ካሣ
Rate this item
(9 votes)

      በሥራ አስኪያጅነት የምመራው ድርጅት ነው፡፡ ከእኔ በፊት አባቴም ታናሽ ወንድሜም መርተውታል፡፡  ማናቸውም  ግን እንዲህ ዳጎስ ያለ ገንዘብ  ጠፍቶባቸው አያውቅም፡፡ ጠዋት ወደ ቢሮዬ ገብቼ፣ ገንዘቡን ራሴ ካስቀመጥኩበት ሥፍራ  ሳጣው፣ በአስማት ወይም በሌላ ሃይል የበነነ ወይም የተነነ ነበር የመሰለኝ፡፡ የቢሮውን በር ራሴ ነኝ  በቁልፍ ከፍቼ  የገባሁት፡፡ የተሰበረ መስኮት አልገጠመኝም፡፡ ኮርኒስ አልተነቀለም፡፡ ገንዘቡን ያስቀመጥኩበት ኮሞዲኖም እንደተከረቸመ ነበር፡፡ ስከፍተው ግን ገንዘቡ የለም!! ዕምጥ ይግባ ስምጥ አልታወቀም፡፡  ታዲያ የበነነ ወይም የተነነ ቢመስለኝ  ይፈረድብኛል?!  
የቢሮው ሶፋ ላይ ቁጭ ብዬ ለግማሽ ሰዓት ያህል አደፈጥኩ፡፡  ከተቀመጥኩበት  ስነሳ ግን ሁለመናዬ ተነቃቃ፡፡ የቢሮዬን ዙሪያ ገባ በንቃት መፈተሽ  ጀመርኩ፡፡  ዓይኖቼን  ወደ ኮመዲኖው ያነጣጣርኩት ሥራዬ  ብዬ አልነበረም፡፡ ያለ ቀልቤ ነው፡፡ ድንገት ግን እስካሁን የተሰወረብኝን ነገር አየሁ፡፡ ዓይኔን ማመን አቃተኝ፡፡ ገንዘቡን ያስቀመጥኩበት ኮሞዲኖ፣ በጎን በኩል በትልቁ ተቦርድሷል፡፡  ፈርሷል ማለት ይቀላል፡፡ ክው ብዬ ደነገጥኩ፡፡ ትልቅ የዝርፊያ ወንጀል የተፈጸመ የመሰለኝ አሁን ነው፡፡ ግን ሌባው ማነው?በየት በኩል ገባ ? ምንም ፍንጭ የለም፡፡ ፊልም ላይ ግድግዳ ጥሰው የሚገቡ ሰዎች አይቻለሁ፡፡ ግድግዳው ንክች ሳይል፡፡
በቢሮዬ ታሪክ ተከስቶ የማያውቅ ከባድ ወንጀል ነው የተፈጸመው፡፡ ትልቅ ዝርፊያ! ለሽማግሌው  የአስተዳደር ሃላፊ  ቢሮአቸው  ሄጄ ነገርኳቸው። ክው ብለው ደነገጡ፡፡ ወዲያው ለፖሊስ እንዳመለክት አነቁኝ፡፡ ከመቅጽበት ወደ ቢሮዬ ተመለስኩ - ፖሊስ ጣቢያ ለመሄድ፡፡   
ከቢሮዬ ስወጣ አስተዳደሩን በር ላይ አገኘኋቸው፡፡ ድምጻቸውን ዝቅ አድርገው፤
“ግን--- ለምን መጀመሪያ  ሠራተኞቹን  አናወጣጣቸውም?” አሉኝ፡፡ እኔ ግን ልቤ ፖሊስ ጋ ነው፡፡
“ከፖሊስ ጣቢያ ስመለስ ይሻላል” አልኩና፤ መልሳቸውን ሳልጠብቅ ወደ መኪናዬ አመራሁ፡፡  
ፖሊስ ጣቢያው  የደራ ገበያ መስሏል፡፡ ሲቪሎችና  ፖሊሶች  ይርመሰመሳሉ፡፡ ሁሉም እንደኔ ከቢሮው ገንዘብ የተዘረፈ መስሎኝ ነበር፡፡ መኪናዬን ውጭ አቁሜ ወደ ግቢው  ስዘልቅ ፣ አንድ አንድ እጃቸውን በብረት ካቴና የታሰሩ ሁለት  ወጠምሻ ጎረምሶች አየሁ፡፡   “ትኩስ” ሌቦች ይመስላሉ፡፡  
የግድግዳ ቀለሙ የተላላጠውን፣ የመርማሪ ፖሊሱን ቢሮ በር አንኳኩቼ ገፋ ሳደርገው፣ ባለ ጉዳዮች ጠባቧን ክፍል አጨናንቀዋታል።  ወዲያው በሩን መልሼ ዘጋሁና ደጃፉ ላይ ቆሜ መጠበቅ ጀመርኩኝ -  ተራዬ እስኪደርስ፡፡  የመቶ አለቃ ማዕረግ ያለው  መርማሪው ቢሮ ውስጥ ያየኋቸው ባለጉዳዮች፣ የጋራ ጉዳይ እንዳላቸው ነበር የገመትኩት፡፡ ግምት ደግሞ ለስህተት የመጋለጥ ዕድሉ የላቀ ነው፡፡  እንደተሳሳትኩ የገባኝ  በ15 እና 20 ደቂቃዎች ልዩነት ባለጉዳዮች  በየተራ ከቢሮው ሲወጡ ስመለከት ነው፡፡ ግን እንዴት ይሆናል? የአንዱን ባለጉዳይ ምስጢር ሌላው ቁጭ ብሎ እየሰማ? ከፖሊስ የሙያ ስነምግባር አንጻርስ? ወይስ አንዴ የተፈጸመ ወንጀል ምስጢር የለውም? ምንም ይሁን ምንም ግን እኔ መርማሪውን ማነጋገር የምፈልገው ለብችዬ ነው፤ሌሎች ሰዎች የሚኖሩ ከሆነ ምቾት እንዳይሰማኝ እነግረዋለሁ------እያልኩ ከራሴ ጋር ስሟገት፣ የመጨረሻው ባለጉዳይ ወጣና እኔን ወደ ውስጥ እንድገባ ጋበዘኝ፡፡
 ወደ ቢሮው ስገባ  መርማሪ ፖሊሱን እያወራ ነው ያገኘሁት፡፡ ከእኔ ጋር መሆኑን ያወቅሁት ዘግይቼ ነው፡፡    
“--- ግርም እኮ ነው የሚለው---- ሰዉ ንብረቱን ቁጭ ብሎ እያዘረፈ እኛን ውለዱ ይለናል!” አለ - ፖሊሱ ጠረጴዛው ላይ በስፋት የተዘረጋው ሰፌድ የሚያህል መዝገብ ላይ በፍጥነት እየጻፈ፡፡
“ዓይኑ እያየ ላፕቶፑን ከቤቱ አሰርቆ ----- ፖሊስ ሌባውን ይዞ፣ ንብረቱን እንዲያስመልስለት ይፈልጋል!
ይሄ ታዲያ የጤና ነው?! -----”
መርማሪው ፖሊስ  ከእኔ ቀድመው ከነበሩት ባለጉዳዮች አንዳቸውን እያማልኝ እንደሆነ  አልጠፋኝም፡፡
መቶ አለቃው የተናገረውን  እያብሰለሰልኩ  ሳለሁ፤
 “እሺ  የእኔ ወንድም--- ምን ልታዘዝ ---?” አለና ከሃሳቤ አናጠበኝ፡፡
“አንድ ጉዳይ ሪፖርት ለማድረግ ፈልጌ ነው---“
“ጉዳዩ ምንድን ነው?---- አይዞህ ንገረኝ ----” አለና፤የፈራሁ አስመሰለኝ፡፡
“ወንጀል ነው------ ስርቆት------” አልኩት፤ ባልተረጋጋ ስሜት፡፡
ለምን ስሜቴ  እንደተረበሸ አልገባኝም፡፡  
“ያንተ መቼም ላፕቶፕ አይደለም ------ ነው እንዴ!?” አለ መቶ አለቃው፤ የለበጣ ፈገግታ እያሳየኝ።
“አይደለም!----- 50 ሺ ብር ነው!” አልኩት፤ ፍርጥም ብዬ፡፡
“ያንተ ይሻላል! እስካሁን የሰማሁት ሌብነት ትርኪምርኪ  ነው--- የኩሽና ሌባ ዓይነት!”
“የኩሽና  እና የሳሎን ሌባ አለ እንዴ ?” አልኩት፤ በአባባሉ ተገርሜ፡፡
“በትክክል! ለምሳሌ  የባንክ ዘራፊዎችና ኪስ አውላቂዎች አንድ አይደሉም!?”
ማቆሚያ የሌለው  ሙግት እንዳይሆን በመስጋት ዝምታን መረጥኩኝ፡፡
“እውነቱን ልንገርህ አይደል፤ እኔ ሶፍስቲኬትድ የሆነ ሌብነት ነው ደስ የሚለኝ----በውጭ ፊልሞች ላይ እንደሚታየው---ዘ ባንክ ጆብ ---- የሚለውን ፊልም አይተኸዋል? ዘ ዩዥዋል ሰስፔክትንስ? ዘ ዳርክ ናይትንስ? ---- እነዚህ ፊልሞች የዓለም ሶፍስቲኬትድ  ሌብነት የደረሰበትን የሚያዩ ናቸው -----  ችግሩ ግን የእኛ አገር ሌባ የረቀቀ አይደለም------- የወንጀል ምርመራ አቅምህን የሚፈታተን ስርቆት አታገኝም!”
“የረቀቀ ሌባ የጠፋው ለምን ይመስልሃል?” ስል ጠየቅሁት፤ ጉዱን ልስማ ብዬ፡፡
“የውጭ ፊልም አያዩማ! ባንክ ሮበሪ ሳታይ እንዴ ት ፕሮፌሽናል ሌባ ልትሆን ትችላለህ?!”
ፖሊሱ እየኮመከ  ነበር የመሰለኝ፡፡ በመሃል የእኔ ጉዳይ ተረስቶ ቁጭ አለ፡፡
 “ለመሆኑ-----ስርቆቱ የተፈጸመው የት ነው-----ቤትህ ነው መኪና ውስጥ?”
መርማሪው በራሱ ጊዜ ወደ እኔ ጉዳይ በመመለሱ ደስ አለኝ፡፡
“-- ከቢሮዬ ነው የተሰረቀው-----ትላንት ሌሊት!”
“ጎበዝ ሰው ነህ!------ ወንጀል ፖሊስ ጋ መድረስ ያለበት እንዲህ በትኩሱ ነው------ አበሻ እኮ ይገርምሃል ----- ለፖሊስ የሚያመለክተው ሌባው ዱባይ ከገባ በኋላ ነው! “
መቶ አለቃው በሰጠኝ ውዳሴ  ውስጤን እንደሞቀው አልሸሽግም፡፡
“ስርቆቱ  የተፈጸመው ሌሊት ነው አልከኝ?”
“ሌሊት መሆን አለበት ፤ ጠዋት ቢሮ ስገባ ነው መሰረቁን ያወቅሁት”
 “እንዴት ነው የምትጠረጥራቸው ሰዎች አሉ?----- ከሰራተኞችህ ማለቴ ነው ?” ጠየቀኝ መርማሪው ፖሊስ፡፡
“በፍጹም! ሰራተኞቼን በታማኝነታቸው ነው የማውቃቸው----ማንም  የምጠረጥረው  የለም”
“የምትጠረጥረውማ መኖር አለበት፤ያንተን 50 ሺ ብር ለመስረቅ ባህር አቋርጦ የሚመጣ ሌባ  የለም!
የዋህ አትሁን --- እንኳን ሌላው የእናት ልጅም  አይታመንም! በፖሊስ  ሙያ ደግሞ መጠርጠር ሳይንሳዊ ነው! “አለና በእርካታ ስሜት ጥያቄውን ቀጠለ፡-
“ከዚህ ቀደም ከቢሮህ ገንዘብ ወይም ሌላ ንብረት ተሰርቆብህ  ያውቃል?”
“በፍጹም! ድንቡሎ  ከቢሮዬ ጠፍቶ አያውቅም፤ያሁኑ የመጀመሪያው ነው”
“ለመሆኑ ምን ያህል ሰራተኞች በቢሮህ ይሰራሉ?”
“ሻይ የምታፈላውንና ጥበቃውን ጨምሮ 13 ----ማለቴ 14 ---15 ---ይሆናሉ”
“ሰራተኞችህን  በቅጡ ያላወቅህ ----- እንዴት ነው ገንዘብህን ልታውቅ የምትችለው?!”
አለ ፖሊሱ፤ በሽሙጥ ሊዘልፈኝ እየሞከረ፡፡  
“ኸረ አውቃቸዋለሁ ------- ሁለቱንም አሳምሬ አውቃቸዋለሁ! “ አልኩኝ በደመ ነፍስ፡፡
“በደንብ የምታውቃቸው ከሆነ ጥሩ ነው ----- እኔ ላንተው ብዬ ነው” አለና ቀጠለ፡-
“እንደነገርከኝ ወደ 15 ሰራተኞች አሉህ ---- የረሳሃቸው ሲጨመሩበት 20 መድረሳቸው አይቀርም፤ የእነዚህን  ሁሉ  አሻራ መውሰድ ደግሞ---- በጣም ከባድና ረዥም ጊዜ የሚወስድ  ነው፤ በዚህ መሃል ሌባው ሊሰወር ይችላል ----- ስለዚህ ለምን እንደዚህ አናደርግም----?” የመቶ አለቃው ምን የተሻለ ሃሳብ ሊነግረኝ ነው ብዬ መጓጓቴ አልቀረም፡፡
“ለምን ቢሮ ውስጥ ተደብቃችሁ እያደራችሁ ---- ሌባውን እጅ ከፍንጅ አትይዙትም ?!” ሲል ትዕዛዝና ጥያቄ የተደባለቀበት ሃሳብ አቀረበልኝ፤ትክ ብሎ ዓይን ዓይኔን እየተመለከተኝ፡፡ እውነት ለመናገር መርማሪው እየቀለደ እንጂ የምሩን አልመሰለኝም ነበር፡፡ ከልቡ መሆኑን ለመረዳት ግን ብዙ አልፈጀብኝም፡፡ እኔም ከልቤ የተሰማኝን መለስኩለት፡፡
“መቶ አለቃ ------ ከምርህ ነው? እኔ እኮ እየቀለድክ  መስሎኝ ነበር?!”
“ለምንድን ነው የምቀልደው? ሥራ አይደለም እንዴ የያዝኩት? ከተገቢው በላይ ረዥም ሰዓት ሰጥቼ ስለሰማሁህ ቀልድ አደረግኸው አይደል?! ባንተ አይፈረድም ---- እኔ ነኝ ጥፋተኛው “ ሲል በቁጣ አምባረቀብኝ፤መርማሪው ፖሊስ፡፡
በወረደብኝ የቁጣ ዱብ ዕዳ ስሙኒ አክዬ መለማመጥ ያዝኩኝ፡-” እንደሱ አይደለም መቶ አለቃ ------” ሆኖም የመቀጠል ዕድል አልሰጠኝም፡፡ “ነው እንጂ! እንደውም አሁኑኑ ከቢሮዬ ውጣልኝ ------ ያንተን ጉዳይ ጨርሻለሁ ---- ብዙ ባለጉዳዮች ውጭ እየጠበቁኝ ነው” አለና ከመቀመጫው ተነስቶ ቆመ፡፡
“መቶ አለቃ፤ የእኔስ ጉዳይ?-----20 ሺ ብሬስ? ----- ሌባው ይብላው -----?!”  
“እምቢ አልካ---- ሌባው በቁጥጥር ስር የሚውልበትን ዘዴ ብነግርህ ፌዝ አደረከው----እንደውም በደንብ ሳይህ ----- እንኳን 20 ሺ ብር 1ሺ ብር የተሰረቅህ አትመስልም---- መደበሪያ ነው ያደረግኸኝ -----ጊዜ ማሳለፊያ-----ይሄ ደግሞ በህግ ያስጠይቅሃል----ስንት ወንጀል የምከላከልበትን ሰዓት በዋዛ ፈዛዛ አባክነህብኛል---”
በድንጋጤና በመገረም ስሜት ውስጥ ሆኜ ራሴን ከመርማሪው የፈጠራ ክስ ለመከላከል ያለ የሌለ አቅሜን  አሰባስቤ  መናገር ጀመርኩ፡- “መቶ አለቃ ሳንግባባ ቀርተን ነው እንጂ እኔ አንተ የሳልከው ዓይነት  ሰው አይደለሁም----- 20 ሺ ብር ለመሰረቄም በቂ ምስክር ማቅረብ እችላለሁ፤ ግራ የገባኝ እኮ ሌባው የሚያዝበት መንገድ ነው ------”
የመጨረሻውም  አስቤበት የተናገርኩት ሳይሆን ድንገት ከአፌ አፈትልኮ  የወጣ በመሆኑ መደንገጤ አልቀረም፡፡
“አሁን እኔ ግራ የሚያጋባ ነገር ተናገርኩ ---- የኒውክሌር ሳይንስ ያወራሁ አስመሰልከው እኮ!” አለ መርማሪው፤ ከሚግለበለብ ስሜቱ አደብ ገዝቶ፡፡
“ይቅርታ መቶ አለቃ ----” ቃሉ ከአንደበቴ ከወጣ በኋላ ተጸጸትኩ፡፡ ይቅርታዬን እንደከሸፈ ጥይት ቆጠርኩት፡፡  መርማሪው ግን ይቅርታ በመጠየቄ የድል እርካታ እንደተሰማው ከምላሹ ተገነዘብኩ፡፡  
“ሌላው መንገድ ምን መሰለህ ----” አለ በጥልቀት ትክ ብሎ እያሰበ፤ “የሰራተኞችህን ሁኔታ በቅርበት ተከታተል---”
“መከታተል ስትል------እንዴት?” ስል ጠየቅሁት፡፡
“አየህ ገንዘብ የሰረቀ ሰው የኑሮ ስታይሉን ይቀይራል-------ሽሮ ይበላ የነበረው ክትፎ መብላት-----ድራፍት ቤት ያዘወትር የነበረው ውስኪ ቤት መግባት ይጀምራል --------- ልብሶችም ለወጥ ለወጥ ያደርጋል ------በዚህ መንገድ ሌባውን መያዝ ትችላለህ-----ከዚያ እኛ ዘንድ ታመጣውና ---- በሳይንሳዊ የምርመራ ዘዴ እውነቱን እናስወጣዋለን --- አሁንስ ተግባባን?!” ረገጥ አድርጎ ጠየቀኝ፡፡
“አዎ መቶ አለቃ፤ግን  ከዚህ ውጭ  ልትረዳኝ  አትችልም? ማለቴ በራሳችሁ የምርመራ ዘዴ?----”
“እስካሁን የነገርኩህ የማንን  የምርመራ ዘዴ ነው ታዲያ!?”
“ማለቴ በአሻራ በምናምን -----?”
“በአሻራ ተለክፈሃል እንዴ ? ከፈለግህ የአንተን አሻራ ልንወስድ እንችላለን !”
“መቶ አለቃ፤ ይሄ ሙያ ላንተ አይሆንም-------አንተ መሆን ያለብህ-------” አልኩት በንዴት በግኜ።
በረዥሙ ከትከትከት ብሎ ሳቀና፤”የኛ ሙያ መዳቢ ---- ምን መሆን ነበረብኝ?”
“የቴሌቪዥን ድራማ ወንጀል መርማሪ!” አልኩትና፤ ከቢሮው ወጥቼ ሄድኩ፡፡
*****
(የጸሃፊው ማስታወሻ፡- ይሄን አጭር ልብወለድ ለመጻፍ ያነሳሳኝን እውነተኛ ታሪክ ላጋራኝ ልባዊ ወዳጄ እስክንድር ሃይሉ፣ ምስጋናዬ የላቀ ነው!)

Read 3684 times