Sunday, 25 December 2016 00:00

ቆብ ደፊው (ወግ)

Written by  ደረጀ ይመር
Rate this item
(2 votes)

    አንደርድሮ ከመሀል ሀገር የዶለኝ ያ መልቲ ሎንችን ነበር፡፡ ዘመኑ እንዴት ይበራል ጎበዝ፡፡ ቆብ ከደፋሁ ይኸው ሰኔ ግም ሲል አምስት ዓመት ከመንፈቅ ሊሆነኝም  አይደል፡፡ ድሮ በቀያችን ከአስኳላ የሚሰደድ ኮበሌ የኑሮን ማዕበል በመላ ለማለፍ ከኖህ መርከብ ላይ እንደተሳፈረ ይቆጠር ነበር፡፡ እኔም የቀዬው ወግ አድጦኝ ከእዚህ ማጥ ውስጥ  ስዳክር ዘመናት ነጎዱ፡፡
ጦቢያ ከምትመካበት ትልቁ አስኳላ በስነ-ባሕሪ የጥናት መስክ ቆብ ብደፋም ከኑሮ ሱናሜ  ነጣ መውጣት ግን ተስኖኛል፡፡ ኑሮ ግራ ቀኝ እያላጋ መቀመቅ ከሆነው እልፍኙ ሊዶለኝ  በብርቱ ይጣደፋል፡፡ ይታደገኛል ያልኩት የጥናት መስክ ዋግ እንደበላው አዝመራ ከጥቅም ውጪ ከሆነ ሰነበተ፡፡ የሥራ ማስታወቂያ ላይ ያንጋጠጥኩትን ያህል ለፈጣሪዬ ማንጋጠጤን አላስታውስም፡፡ ከጎተራዬ አልፌ ጥሪት ለመቋጠር እግደረደራለሁ። ግና፣ ምን ያደርጋል፤ እጅ ያጥረኛል። አስኳላው ያስታቀፈኝ መመኪያ እንደሆነ፣ ከባለቆቡ ጉርድ ፎቶ በቀር ሌላው እንደ ጠዋት ጤዛ ከስሟል። እግዜር የሰጠኝን ጉልበት ተመክቼ  ሲቀናኝ በኮብል ድንጋይ አንጣፊነት ባስ ሲል በሸክም ሥራ ሥላጋ ውዬ አድራለሁ፡፡ ከከፋም ጥሬ ቆርጥሜ፣ ከፊሉን በውሃ አደላድዬ ከመውደቂያዬ ጋር እወዳጃለሁ። በይህ ቅጥበት ምንአልባት ከመዳፌ ላይ  ያለው ጥሪት  አፍላነቴ ብቻ ነው፡፡ ያ ድንቅ ጠሀፊ በአፍላነትህ ቢከፋህ፣ ምን ትሆናለህ ነበር ያለው፡፡ ግድየላችሁም ጎብዝ አሁን አሁን እጅ ለመስጠት እያዘመምኩ ነው። ቆብ ደፍቶ ከኮብል ድንጋይ ላይ ተደፍቶ መዋሉ አእምሮዬን እየጠገነነኝ ነው፡፡ ክው ክው ብለው አንድ ቀን ለመነጠፍ ስንት ዘመን ማንጠፍ!
በቀደም ነው፣ የሰንበት ጀንበር ከጽልመት ዋሻ ብቅ ለማለት በምትግደረደርበት ቅጽበት በሰመመን የተያዝኩት፡፡ ለቁም እልም ብሰንፍም ወድቆ ለማለም ማን ቀድሞኝ፡-
ብረት ባነገቱ መለዮ ለባሾች የሚዘወር ባለ ፍርጎ አውቶቢስ ውስጥ ይመስለኛል፡፡ ኮሪደር ላይ መለመላዬን ቆሜ፣ ዙሪያ ገባዬን እሰልላለሁ። አፋቸውን የተለጎሙ ተሳፋሪዎች በምድብ በምድብ ተከፋፍለዋል፡፡ የምድባቸው ስያሜ ከግምባራቸው ላይ ተነቅሷል፡፡ “ኪስ አውላቂዎች”   የሚለው የምድብ መጠሪያ ከአቻዎቹ መሀል ገኖ ያንጠባርቃል፡፡
“ጎሽ እንዲህ አንድ ፊቱን ገሃድ ያውጡት እንጂ። ከእዚህ ቅጥበት አንስቶ በኪስ አውላቂ መዳፍ የሚደባበስ መንገደኛ ብርቅ መሆን ይጀምራል።” ድምጼን ዘለግ አድርጌ ለተሳፋሪው በሙሉ አስተጋባሁ፡፡ ቁብ የሰጠኝ ተሳፋሪ ግን አልነበረም።
ግምባራቸው ላይ ኪስ አውላቂ የሚል ታፔላ የተለጠፈባቸው ተሳፋሪዎች፣ አንድ እጃቸውን ደረታቸው ላይ ሌላኛውን ደግሞ  ኪሳቸው ላይ አሳርፈዋል፡፡ “ወግ ነው አሉ….. አሁን..ሌባን ሌባ ቢሰርቀው..” በውስጤ አጉተመተምኩና  ፈገግ አልኩ፡፡
አውቶቢሱ ከሆነ ገደላገደል አካባቢ ከተጠነፈ ፌርማታ ላይ ሲደርስ ተንገጫግጮ ቆመ፡፡ ፌርማታው ላይ ጠጠር መጣያ የለም፡፡ ከሁሉም የራስ ቅል ላይ ጥቁር ቆብ ተደፍቷል፡፡ ቆብ ደፊው እየተንኳተተ ወደ አውቶቢሱ እልፍኝ መከተት እንደጀመረ አፍታም ሳይቆይ የአውቶቢሱ መዝጊያ ተጠረቀመ፡፡ የኋላ ማርሽ አስገብቶ ወደ መጣበት አቅጣጫ የኋሊት ይንደረደር ጀመር፡፡ ከደጃፍ የቀረው ስፍር ቁጥር የሌለው ቆብ ደፊ፣ ወደ አውቶቢሱ እልህ እየተናነቀው እንደግሪሳ ይተም ያዘ፡፡ ፍላጻ፣ ቆመጥ፣ ኮብል ድንጋይ የአውቶቢሱን ገላ ለመንደል ከግሪሳው ባለቆብ ያለፋታ ይወነጨፋል። መለዮ ለባሾቹ ወደሚተመው ቆብ ደፊ ያለርህራሄ መሣሪያቸውን አንደ ፈንዲሻ ያርከፈክፉታል፡፡ ቆብ ደፊው ከገላው ላይ የሚርከፈከፈውን የጥይት ቀለሃ እንደ አቧራ እያራገፈ፣ በሚያስደንቅ ፍጥነት አውቶቢሱን የበለጠ እየቀረበው መጣ፡፡ ቀስ በቀስ አውቶቢሱ  የሚወረወርበትን ጥቃት መመከት ተስኖት፣ ተንተፋተፈና አቅጣጫውን ስቶ ከገደል አፋፋ ላይ ተንጠላጠለ፡፡ ድንገት ከየት መጣ ያላልኩት ጅብራ የሚያህል ፍጡር ከጭብጦው ከቶ በአውቶቢሱ መስኮት አሻግሮ ከባሕር ዶለኝ፡፡ ባሕሩ እንዳይውጠኝ ነፍስ ውጪ፣ ነፍስ ግቢ በምልበት ቅጽበት፣ የመላእክ ቀጠሮ ያለው የሚመስል የወፍ ጫጫታ ከአስፈሪው ሕልም ነጣ አወጣኝ፡፡
ሕልም እንደፈቺው ነው ጎበዝ፡፡ ይህንን ከገሀድ የማይተናነስ ቅዠት አይሉት ሰመመን ችላ ማለት ዕጣ-ፈንታዬን መበደል መስሎ ስለተሰማኝ ከአዋቂ ዘንድ ላስፈታ በዕለት ሐሙስ ተመምኩ፡፡
***
እኩለ ለሊት ግድም ነው፡፡ ዝይራው ቀልጧል። ሐድራው ተጫጭሷል፡፡ የባለዛር አበዛዙ አጃኢብ ነው፡፡ አዋቂው ከጋረደው መጋረጃ ባሻገር ሆኖ፣ በአስገምጋሚ ድምጹ መሬት ላይ የተደፉትን አስጠንቋይ ምእመኑን ምልጃ እየሰማ ብይን ይሰጣል፡-
“እህ …….ጠቋር አዳል ሞቴ…በልብሽ ያለውን መሻት ያውቅበታል”
“ልክ ነው የእኔ አባት”
“ከበላይሽ ያለችው ጠይም ቀጭን ሴት”
“ሀቅ ነው የእኔ አባት’
“ከባድ ሴራ በላይሽ ላይ እየጎነጎነች ነው’’
“ከአንተ የሚሰወር ምን አለ’’
“ሳይውል ሳያድር የእርሷን ነገር አናሳይሻለን”
  ደግሞ ሌላው በአናቱ ተደፋ፡፡
“ምንድን ነው ደግሞ….ሽብር ሽብር ማለት…ስማ.. እኛ እኮ ከፋንድያ ላይ ማንሳት እናውቅበታለን”
“ሀቅ ነው የእኔ አባት”
“ሐሙስ ማለዳ ….ወፍ  ጭጭ  ሳይል…ወሰራ ዶሮ አርደህ ደሙን ከደጃፍህ ላይ በአራቱም አቅጣጫ እርጨው…...ያን ጊዜ የእኛን ተአምር በዓይንህ በብረቱ ትመለከታለህ፡፡ ታዲያ … ከአናቱ ላይ አስራቱን እንዳትዘነጋ……..”
“የተባልኩትን አደርጋለሁ ---ጌታዬ”
በአናታቸው ተደፍተው ቃልቻውን የሚማጸኑት አማኞች በሙሉ በባላንጣ፣በጠላት የተከበቡ ተጠቂዎች ናቸው፡፡ ጠይም ቀጠን ያለ፣ቀጠን ያለች በአዋቂው ዘንድ ለግምት ተመራጭ የሆነ ተክለ-ሰውነት ነው፡፡ እስቲ አሁን ማን ይሙት፣ የሀገሬን ጎበዛዝት በጠይም ቀጭንነት መገመት፣ ሰማይን በጥይት እንደመሳት አይቆጠርም…
ባለተራው እኔ ሆንኩኝ፡፡ ለቃልቻው ስለ ሕልሜ ልተነፍስ በአናቴ ተደፋሁ፡፡
“አረግ …አረግ..አረግ ውስጥህ ማቅ ለብሷል”
“…ሰነበትኮ ማቅ ከለበስኩ…..ያኔ…የዛሬ አምስት  ዓመት ቆብ የደፋሁ ዕለት…” ወጉን ላለመጣስ ድምጼን ዘለግ አድርጌ፤ “ልክ ነው የእኔ አባት” አልኩኝ
“ከበላይህ ያለችው፣ ነጠላ ተረከዝ….”
“አረ ከበላዬ ያሉት እመት አዛሉ ናቸው። ለመሬት የከበዱ፡፡ ምን ይዘባርቃል” አልኩኝ በልቤ፡፡ በአንደበቴ ግን፡- “ልክ ነው የእኔ አባት፤ ካንተ ምን ይሰወራል” በማለት  የወጉን አደረስኩ፡፡
“ዕጣ ክፍልህ እርሷ ነች”
“የጉድ ቀን ቶሎ አይመሽም….”አንደበቴን ለጉሜ፣ ግርምታዬን በውስጤ አደረኩት፡፡      
“ምልክት ይሆን ዘንድ …ገሀድ የሆነ ሕልም በቅርቡ ታያለህ”
“የእኔ አባት…..እረ አመጣጤስ ሕልም ለማስፈታት ነበር”አልኩና የቃልቻውን መቀባጠር ፈር ለማስያዝ ሞከርኩ፡፡
“የሕልሙን ፍሬ ነገር በዝርዝር ተናዘዝ”
 በተሰጠኝ ቀጭን ትዕዛዝ መሠረት፣ ከጅምሩ እስከ መቋጫው ሕልሜን ተወጣሁት፡፡
“ይኼ ሕልም በደረቁ አይፈታም፡፡ ለፍቺው ሌላ ሕልም ለማለም ደጋግሞ ማሸለብን ይጠይቃል፡፡ የመፍቺያው ሕልም እስኪከሰትልህ ድረስ አስራትህን እንዳታጓድል”
***
 ይኸው ከቃልቻው ቃልኪዳን ለጥቀው በመጡ ቀናት፣ ወራት  አስራት ለመገበር በሚል ሰበብ የአዋቂውን እልፍኝ የውሃ መንገድ አድርጌው አረፍኩት፡፡ ለሕልም ፍቺ ለማለም  ተቀምጬ በተነሳሁ ቁጥር የዓይኔን ቆብ ከመክደን ሰልሼ አላውቅም፡፡ እኔ ሕልመኛው ቆብ ደፊ፣ በቁም ቅዥት፣ በጥልቅ ሕልም የምባጅ ተስፈኛ፣ምተሃተኛ………

Read 5253 times