Sunday, 25 December 2016 00:00

ከ‹ጭን› እስከ ‹ንቅል›

Written by  ጣሪቅ እዮብ
Rate this item
(3 votes)

 ‹‹አዲስ አበባ በሕገ ወጥ ልማዶችና የወሲብ ድርጊቶች እየተናጠች ነው›› በሚል ርዕስ ከአራት ዓመት በፊት በዚሁ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ የወጣ ዜና ነበር፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በወቅቱ አካሂዶት የነበረው ጥናት ውጤት ይፋ የተደረገበትን መረጃ ዋቢ አድርጎ የተሰናዳው ዜና፤ ‹መጤ› በተባሉ የባህል ‹ግድፈቶች› መነሻነት በርካታ ሁነቶችን እያስተናገደች ያለችው አዲስ አበባ፤ ከዚሁ ከወሲብ ጋር በተያያዘ ማጥ ውስጥ መሆኗን ያትታል። ወሲብ የዚያን ሰሞን ጉዳይ ከመሆን አልፎም አሁን አሁን በተለይ የአደባባይ ምስጢራችን የሆነ ይመስላል፡፡ እንዲህም ሆኖ ታዲያ ምስጢር እንወዳለን፡፡ እንደብቃለንም፡፡ በተለይም አሁን እንዳነሳነው አይነት፡፡
ምስጢራውያን ነን፡፡ በርካታ ነገሮቻችን ምስጢር ናቸው፡፡ እኒህ ምስጢራት ደግሞ እንዲሁ በዘፈቀደ የተፈጠሩ አይደሉም፡፡ ያደግንበት፣ የመጣንበት መንገድ ያበጀልን ነው፡፡ እንዲህ ከተበጁልን ነገሮች መካከል ደግሞ ወሲብ ዋናውና በጣም አይነኬ ከሚባለው የማህበረሰብ ጉያችን መካከል ነው፡፡ ገመናችን ልንለው እንችላለን፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመጽሐፍት መልክ ብቅ ብቅ ማለት ከጀመሩት መጽሐፍት በፊት የማስታውሰው፤ “መኀልየ መኀልየ ዘ ካዛንቺስ”ን ነው፡፡ ይህንን መጽሐፍ በዩኒቨርሲቲ ተማሪነት ዘመናችን ዶርም ውስጥ ድምጻችንን ከፍ አድርገን እያነበብን ተሳልቀናል፡፡ ስቀንበታልም። ቶሎ እንዳያልቅብን ገጾች እየቆጠርን ብሎም እየቆጠብን አንብበናል። የዩኒቨርሲቲ ተማሪነትን ዘመን ካነሳን፣ እንዲህ ነውር/ምስጢር ተብለው የተያዙ በርካታ ነገሮቻችን በተለይ ሰዓት ካለፈ ወዲያ (በደንብ ሲመሽ ማለቴ ነው) ይወራል፤ ይሳቃል፤ ይቀለዳል፡፡ (በዘመኑ ክዋኔ መሰረት ሙድ ይያዛልም፡፡)
በመሠረቱ ምስጢር መሆን ያለባቸው ጉዳዮች የሉንም ማለቴ አይደለም፡፡ ምስጢር ብለን አፍነናቸው ግን የማህበረሰቡን ጓዳ ዕርቃኑን እንዲያስቀሩትም መፍቀድ መልካም አይደለምና። እውነት ለመናገር ዘመናዊነት ተብሎ ከዚሁ ጋር በተያያዘ የመጡ በርካታ ነገሮችን ስንመለከት፤ በተለይም ለወላጆችና ዕድሜያቸው ለገፉ ሰዎች የሚሰጠው ስሜት ትንሽ ከበድ እንደሚል ማሰብ ባይከብድም፤ እውነቱን መጋፈጥ ግን ምንም ልናደርገው የምንችለው ጉዳይ ስላልሆነ፣ ወደድንም ጠላንም እርሱን ተቀብለን ልንኖረው/ህይወታችንን ልናሰምረው ግድ ይላል፡፡
በሌላ አጋጣሚ ደግሞ በአንድ ድረ-ገጽ ላይ ያነበብኩትን ላካፍላች፡- ‹‹እኔ ባለትዳርና የልጆች አባት ነኝ፡፡ የምወዳትና የምትወደኝ ባለቤትም አለኝ። ከባለቤቴ ጋር ከጅምሩ አንስቶ የሞቀ ፍቅር ውስጥ ሆነን ቆይተን፣ ልጆችም ወልደን በደስታ ኖረናል። በቅርርባችን ውስጥ ችግር አልነበረም፡፡ የወሲብ ህይወታችንም ግሩም ነበር፡፡ ይሁንና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይህ ተለውጦ፣ የወሲብ ህይወታችን በጣም ተቀዛቅዟል፡፡ እኔ ወሲብ ለመፈፀም ከፍተኛ ፍላጎት ቢኖረኝም፣ በእርሷ በኩል ግን ከፍተኛ መቀዛቀዝ ይታያል፡፡ ስለ ሁኔታው ለመወያየትም ፍቃደኝነት አይታይባትም፡፡ እኔ በዚህ የጉልምስና ዕድሜዬ ሌላ ሴት ጋር ለወሲብ ብዬ መሄድን ጭንቅላቴም አይፈቅደውም፡፡ እንደ አንድ የትዳር ቅመም ወሲብ አስፈላጊ እንደመሆኑ የዚህ መጉደል ትዳራችንን አደጋ ላይ እንዳይጥለው እየፈራሁ ነው፡፡ ምን ትመክሩኛላችሁ? መልሳችሁን በጉጉት እጠብቃለሁ።›› ከዚህ ጠያቂ በመነሳት ‹ሙያዊ› ምላሽና ትንታኔ ተሰጥቶበታል፡፡ እኔ ወደ እርሱ አልገባም፡፡ አስገራሚ ሌሎች ታሪኮችም አንብቤያለሁ፡፡ ሰምቻለሁም፡፡ አዝኛለሁ፡፡ ስቄያለሁ፡፡ ተገርሜያለሁ፡፡ ደንግጫለሁ፡፡ ሌላም ሌላም፡፡
ስለ ወሲብ ሲነሳም፤ ከዓመታት ወዲህ የተለያዩ መጻሕፍትን ማንበብ ጀምረናል፡፡ በተለይም ‹እንደወረደ› - ቃሉም ግብሩም ክዋኔውም ያለ ያህል፣ እየተጻፉ መሆናቸውን መጻሕፍቱን በማንበብ መረዳት ይቻላል፡፡ በርካቶቹ ታዲያ ትዕይንቱን ብቻ የሚያሳዩ ናቸው፡፡ ‹እንዲህ ሆኖ፤ እንዲህ ተደርጎ› እያሉ የሚዘክሩ፤ የግብር ዝክር አይነቶች፡፡ በእነዚህ ሁነቶች መካከል ከሰሞኑ ያገኘኋት መጽሐፍ ደግሞ ‹ጭን-ንቅል› ትሰኛለች፡፡ አስገራሚው ነገር ርዕሱ ነው፡፡ ጭን- ብሎ ሳይጨርስ ንቅልን ያስከትላል፡፡ ደራሲው ቴዲ ፀጋዬ (ነጋድራስ) እነሆ ብሎ፣ በ150 ገፆች የቀነበበውን አድርሶናል፡፡ እውነተኛ ታሪክ፤ ድርሳን ነው፡፡ ሁነት፡፡ ክዋኔ፡፡ “ነገር በዓይን ይገባል ይባል እንደነበረ ሁሉ፤ እንዲህ በመጽሐፍም በንባብ ይገባል፡፡
ጭን-ንቅል በተለይም ከርዕሱ ጀምሮ ሁለት በበርካቶች ‹ሊወደዱ› የሚችሉ ነገሮችን በአንድ ሰድሮ ጭን ብለን ሳናበቃ፤ ወሳኙን የሥጋ አካል የተመረጠውን ንቅል ያስከትላል፡፡ ደራሲው በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ ሊያሳየን የፈለገው አንዳች ነገር እንዳለ፤ በእኛ ውስጥ ትልቅ ግምት ያገኙ/የሚያገኙትን አንድም የሰው፤ ሌላም ሰው በሚወደው የበሬ ሥጋ መካከል፣ ለዚያውም ንቅልን አስከትሎልናል፡፡ ርዕሱን በአጽንኦት ለተመለከተ ሰው፤ አንዳች ሰፍ እንድንል የሚያደርግ ነገር እንዳለው ለመረዳት ይቻላል፡፡
በምዕራፍ አንዱ ደራሲው፣ ጥያቄና መልስን አስታኮ ይሞግታል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ከራሱ ጋር የሚሟገትባቸውን የተወሰኑ ጥያቄዎችን አንስቷል። እንዲህ ያለው ጥያቄ በራሱ የሚፈጥረው ስሜት አለ፡፡ ‹እንዴትና ስለምን እንዲህ ያለ ጥያቄ ይነሳል?› ብሎ የሚያስብ አካል እንደሚኖር መገመት ይቻላል። ከዚህ ወዲያ ‹ሊያነጋግር የሚችል ጉዳይ አለ ወይ?› ብሎ የሚያስብ አካል ደግሞ እንዳለ ሆኖ ማለት ነው። በምዕራፍ ሁለቱ ደግሞ ስለ ቤታችን ጉድ ያወሳል። ‹ሰልፍ ዘ ሥጋዌ ወ ነፍሳዌ› ያጫውተናል። በተለይም በበዓልና በአንዳንድ ዘወትሮች ያለውን ሰለፍ፡፡
በምዕራፍ ሶስት ነው ከዋናው የመጽሐፉ ክፍል ጋር የሚያገናኘን፡፡ ይህ ክፍል በተለይም ከወሲብ መፈጸሚያ ጉያዎቻችንና መዳሪያ ስፍራዎች ጋር ያስተዋውቀናል፡፡ ከበርካታ ሰዎች ጋርም ያገናኛል። እውነቱን ያጋፍጠናል። ስሜቶችን በእርግጥም እያስተናገድን እንድናልፍ ያስገድደናል። አንዳንዴም እጃችንን በአፋችን እንድንጭን በአግራሞት ያስቆዝመናል፡፡ በድንጋጤ እንድንፈዝ ያደርገናል። ገራሚ አውነቶችን እንድንጋፈጥ ግድ ይለናል። ይህንን ግዴታ ማለፍ አይቻለንምና እርሱን ሁሉ እንድንካፈል ግድ ይሆናል፡፡ በዚህ የስሜት መዘባረቆች ውስጥ ራሳችንን፣ ከተማችንን፣ ጓዳችንን እንድናይ፤ መለስ ብለን እንድንቆዝም ያደርገናል። በተለይ አንዳንዶቹ ሁነቶች ከቦታ ቦታ፣ ከቤት ቤት፣ ከሰው ሰው እየተቀያየሩ፣ አንዳንዴም በምናብ የምናውቃቸው የሚመስሉንን ሰዎች እየሳልን እንድናነበው ከማድረጉም በላይ በመሃል የሚነሱት ቁምነገሮች ልዩ ናቸው፡፡
በሌሎች መሰል ወሲብ-ነክ መጽሐፎች ከምናገኘው በጣም በተለየ መልኩ በምዕራፍ አራት ከባለሙያ ጋር የተደረገ ውይይት ያስኮመኩመናል። እኒህ ባለሙያ የሚነግሩንም ነገር አስገራሚ ነው፡፡ በመጨረሻም ከወሲብ ጋር የተያያዙ የማኅበረሰቡ ቀልዶችን አስታቅፎን በእነርሱ ፈገግ እያስባለን መጽሐፉን ከፍጻሜ ያኖረዋል፡፡
ሥነ ምግባር ብዙ ጊዜ በተለይም በእኛ አገር ነባራዊ ሁኔታ ትልቅ ግምት የሚሰጠው፣ በበርካቶችም እንደ አንድ የሰው ግብርና ሰብዕና መለኪያ ተደርጎ የሚቆጠር ነው፡፡ እንዲህ እንደኛ ባለው ወግ አጥባቂና በተለይም በቀደመው ወግ ለጸና ማህበረሰብ፤ እንዲያ እንደ ወሲብ ያለውን ነገር በገሀድ/በግልጽ መናገር እንደ ነውር ቢቆጠርም። በምስጢር ከሚከወነው ነገር አንጻር ሲታይ በተለይም ማኅበረሰባችን በጣም ጥንቃቄ በተሞላበት አኳኃን በግልጽ ሊወያይበት የሚገባ ጉዳይ መሆኑን መገንዘብ ያሻል፡፡ ከሀፍረታችን ባሻገር ያሉ በርካታ እውነቶቻችን፤ አውቀነውም ይሁን ሳናውቀው ዋጋ እያስከፈሉን ነውና እንዲህ ያሉት መጽሐፍት በተለይም እንዲህ እንደ‹ጭን-ንቅል› ያለው፤ የባለሙያም ምክርን አንስቶ ለማኅበረሰቡ ማቅረቡ በጣም ወሳኝና አስተማሪ ነውና ልንማርባቸው እንደምንችል አስባለሁ፡፡ ደራሲው ቴዲ ፀጋዬ ብርሃኔ (ነጋድራስ)፤ በዚህ ረገድ እውነቱን ለማሳየት የሄደበት መንገድ መልካም ነበር ለማለት ይቻላል፡፡
ከመጽሐፉ በተወሰደ አንቀጽ እንለያይ፡- ‹‹ክብደቷ ከቁመቷ ጋር ተጣጥሟል፡፡ መካከለኛ የሴት ቁመና ተጎናጽፋለች፡፡ ጠይም ፊቷ፤ ብዙም ያልሰፋና ያልጠበበው አፏ፤ በሊፒስቲክና በቻፒስቲክ የደመቀው ከንፈሯ፣ ተተኩሳውና ተቀጥሎ የተዘናፈለው ጸጉሯ ስሜትን ያነሳሳሉ፡፡ ይህቺን ልጅ ለመግባባት ለዓመታት አራዳ ተመላልሻለሁ። እንዳማረችኝ ስላወቀች እንደ ጥሩ ኖቭል ልቤን ለመስቀል የተለያዩ ብልኃቶችን ትጠቀማለች። ……. ለማግባባት ብዬ ብጋብዛትም… ጥላኝ ከመሄድ ውጭ አልጠጋ አለችኝ፡፡››…… ሙሉውን ከመጽሐፉ ታገኙታላችሁና እኔ እዚሁ ላብቃ፡፡ ሰላም!

Read 950 times