Saturday, 24 December 2016 12:59

አይ ካፒታል አፍሪካ ኢንስቲትዩት - የቢዝነስ ምርመራ፣ ክትትልና ህክምና

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(3 votes)

ዶ/ር ገመቹ ዋቅቶላ
                             ትምህርት
                       · የመጀመሪያ ዲግሪ - ከጅማ ዩኒቨርሲቲ በቢዝነስ ማኔጅመንት
                       · የማስተርስ ዲግሪ (ኤምቢኤ) - ከህንድ አንድራ ዩኒቨርሲቲ
                       · የዶክትሬት ዲግሪ - ከአሜሪካ ኦሃዮ ስቴት ዩኒቨርሲቲና ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኢሊኖይ ሥራ
                       · የአይ ካፒታል አፍሪካ ኢንስቲትዩት ዋና ሥራ አስፈፃሚ
                       · በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህርና የማኔጅመንት ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር

        ሰው ብቻ አይደለም የሚታከመው፤ ድርጅትም ይታከማል፡፡ ዘመናዊ አኗኗር የሚከተሉ ሰዎች ለጤናቸው ብዙ ይጨነቃሉ፡፡ ስለዚህ ቢያንስ በዓመት አንድ ጊዜ ሐኪም ቤት ሄደው ሙሉ ምርመራ በማድረግ ስለጤናቸው ያውቃሉ፡፡ ለምሳሌ ትንሽ ምቾት ካልተሰማዎት አርሾ ወይም ሌላ ላቦራቶሪ ያለበት ሄደው ሙሉ ምርመራ በማድረግ ጤናዊ ያለበትን ደረጃ ይረዳሉ፡፡
የቢዝነስ ድርጅቶችም በተመሳሳይ መንገድ የጤና ምርመራ ማድረግ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ትርፍ እያገኙና እየሰሩ ስለሆነ ብቻ ደህንነታቸውን እስካላረጋገጡ ድረስ የጤነኝነት ስሜት ሊሰማቸው አይገባም፤ ተመርምረው ጤነኛ መሆናቸውን ማረጋገጥ አለባቸው ይላሉ፤ የአይ ካፒታል አፍሪካ ኢንስቲትዩት ዋና ስራ አስፈጻሚና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህርና የማኔጅመንት ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር ገመቹ ዋቅቶላ፡፡
በአይ ካፒታል አፍሪካ የድርጅቶችን ወይም የኩባንያዎችን ጤንነትና ደህንንት የምንመረምርበት የምንፈትሽበት ላቦራቶሪ አለን ይላሉ፤ ዶ/ር ገመቹ። ማንኛውም ለመመርመር የፈለገ ድርጅት መጥቶ ጤንነቴን ፈትሹልኝ ይላል፡፡ በተቀመጠው መስፈርት መሰረት ፈትሸው (መርምረው) “እንዲህ ዓይነት ምልክቶች ታይተዋል፡፡ እነዚህ ምልክቶች ደግሞ ለድርጅታችሁ ጥሩ አይደሉም፤ መሻሻል አለባቸው” በማለት የላቦራቶሪውን ውጤት ለድርጅቱ ይሰጣሉ።
ለምሳሌ የድርጅቱ የሰው ኃይል ልማት አስተዳደር፣ ስትራቴጂ፣ የፈጠራ ችሎታ፣ … ተፈተሸ እንበል፡፡ አንድ ኩባንያ ጤነኛ ነው ማለት የሚቻለው የፈጠራ ችሎታውን ተጠቅሞ የገበያውንና የደንበኞችን ፍላጎት ማርካት ሲችል እንዲሁም በቢዝነሱ ውስጥ ካሉ ሌሎች ድርጅቶች ጋር መወዳደር ሲችል ነው፡፡ ኮርፖሬት ማኔጅመንቱ ምን ይመስላል? የድርጅቱ የቦርድና የከፍተኛ የሥራ አመራር ጥምረት ምን ይመስላል? ጤነኛ ነው? የፋይናንስ አስተዳደር አቅማቸው ምን ያህል ነው? የሰው ኃይላቸው ማኔጅመንት ለዛሬ 10 ወይም 20 ዓመት ተወዳዳሪ አድርጎ ማቆየት ይችላል ከፋይናንስ፣ ከመልካም አስተዳደር፣ ከሰው ኃይል አያያዝ፣ ከፈጠራ ችሎታ፣ … ጋር የተያያዙ ነጥቦች በዝርዝር ይታያሉ፡፡ እነዚህ ነጥቦች የአጭር ጊዜ፣ የመካከለኛና የረዥም ጊዜ መፍትሄ የሚሹ ናቸው በማለት የላቦራቶሪ ምርመራ ውጤቱን ይሰጣል፡፡
የመመርመሪያ ነጥቦቹ አይ ካፒታል አፍሪካ ያዘጋጃቸው ናቸው፡፡ ሌሎች ነጥቦችንም እያዘጋጀን ነው፡፡ በመመዘኛ ነጥቦች አዘገጃጀት የካበተ ልምድ ያላቸው ዓለም አቀፍ ሸሪኮቻችን የቀመሯቸውን ነጥቦችም እንጠቀማለን ያሉት ዶ/ር ገመቹ፣ በቅርቡ በኮርፖሬት ጋቨርናንስ ላይ ከሚሰራውና የዓለም ባንክ ግሩፕ ከሆነው አይ ኤፍ ሲ (ኢንተርናሽናል ፋይናንሻል ኮርፖሬሽን) ጋር መፈራረማቸውን፣ የኩባንያዎችን የፈጠራ ችሎታ ለማጥናት ከጀርመኑ ላፕዚግ ዩኒቨርሲቲ ጋር፣ በሰው ኃይል አስተዳደር ላይ ደግሞ ከዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኤሊኖይ ጋር ስምምነት እንዳላቸውና የእነሱን ተሞክሮ ከአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር አዛምደው እንደ አንድ ፓኬጅ እንደሚጠቀሙ፤ ድርጅቱ ሙሉ ምርመራ አድርጉልኝ ካለ፣ ሁሉንም ወይም እነዚህን ብቻ አድርጉልኝ ካለም በተናጠል መርመረው ውጤቱን እንደሚሰጡ ገልፀዋል፡፡
በመጀመሪያው የድርጅቱ ጤና ምርመራ (ኦርጋኒዜሽናል ሄልዝ አሰስመንት ላብ) እነዚህ እነዚህ ችግሮች ታይተዋልና አሻሽላቸው ተብሎ ምክር ይሰጠዋል፡፡ መታከም ወይም ማሻሻል ከፈለገ፣ ከችግሮቼ መላቀቅና አሰራሬን ማዘመን እፈልጋለሁ ካለ፣ ለህክምና ወደ ኢምፓክት ክሊኒክ ይገባል፡፡ በዚህ ክሊኒክ፣ የችግሩ መፍቻ የሆነ ስልጠና፣ የአቅም ግንባታ፣ ሲስተሙን እንደገና ማዋቀር፣ አዲስ ሲስተም መዘርጋት ወይም አዲስ ስትራቴጂ ማዘጋጀት፣ … ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ እንደየችግራቸው መፍትሄ ይዘጋጅላቸዋል በማለት ዋና ስራ አስፈጻሚው አስረድተዋል፡፡
አይ ካፒታል አፍሪካ ኢንስቲትዩት አማካሪ ድርጅት ቢሆንም ከሌሎች ለየት ይላል፡፡ የድርጅቱ መስራቾች አማክረውም፣ አሰልጥነውም ያውቃሉ፣ የውጭ አገር ልምድም አላቸው፡፡ ነገር ግን በስራቸው አይረኩም፡፡ “አማካሪ ነኝ፤ አማክራለሁ፤ አሰለጥናለሁ፤ ነገር ግን ውጤት እንደማያመጣ አውቃለሁ፡፡ ስምምነቴ ማሰልጠን ብቻ ስለሆነ ውጤት እንደማያወጣ እያወቅሁ ግዴታዬን ተወጥቼ እሄዳለሁ፡፡ መስራቾቹ “ውጤት እንደማያመጣ እያወቅን ለምንድንነው የምናሰለጥነው?” በማለት እንጠይቅ ነበር፡፡ ሌላው ደግሞ አንዳንድ ቦታ ለስልጠና የሚመጡ ሰዎች መሰልጠን የሚገባቸው ሳይሆን ማሰልጠን የሚገባቸው ሰዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ ትክክለኛ ሰው እየሰለጠነ አይደለም ማለት ነው፡፡ ስልጠና መሰጠት ያለበት የእውቀት ወይም የክህሎት ክፍተት ላለበት ሰው ነው፡፡ ድርጅቱ ስልጠናው ለምን እንደተፈለገ፣ ማን መሰልጠን እንዳለበት ቀድሞውኑ አልተረዳም ማለት ነው፡፡
ሌላው ደግሞ ከድርጅቱ መሪዎች ጋር ስንነጋገር፣ የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ የተዘጋ ስለሆነ መሰረት የሌለው፣ የማይዘልቅ፣ ያልተፈተነ በራስ መተማመን ታይባቸዋለህ፡፡ በእውቀት ላይ ከተመሰረተ ከሌላ አገር ድርጅት ጋር ተወዳድረህ መስራት ካልቻልክ፣ በተለምዶ አሰራር በራስ መተማመን ሊኖርህ አይገባም፡፡ ቢዝነሱን ለማዘመንና በቢዝነስ ዓለም ተወዳዳሪ ሆኖ ለመዝለቅ እውቀት እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ስለዚህ ይህን እውቀት የሚያስጨብጥ ተቋም ለመመስረት ወስነን ነው የጀመርነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡
በዚች አገር አማካሪነት ዋጋ ያጣ ዓይነት ስራ ሆኖ ነው የምታገኘው፡፡ ለአንዱ ድርጅት የተደረገውን ጥናት ስምና አንዳንድ ነገሮ ቀይሮ ሲሰጥ ነው የሚታየው፡፡ ማማከር ማለት ግን ይህ አይደለም፤ ትክክለኛውን ዓለም አቀፍ ባህርይ ይዞ ነው መሄድ ያለበት፡፡ በዚህ መንገድ ለመስራት ነው የተቋቋምነው፡፡ እኛ ከሌሎች አማካሪ ድርጅቶች እንለያለን፡፡ እኛም ሆንን ተባባሪዎቻችን የምናምነው “ይኼውና የጥናቱን ውጤት ምርቱን ተጠቀሙበት” ብሎ ሰጥቶ መሄድ አይደለም፡፡ እኛ የስራ ላይ ስልጠና እንሰጣለን፡፡ ስልጠናው የሚሰጥበት መንገድ ግን ደርዝ ያለው (ስትራክቸርድ) መሆን አለበት ብለን እናምናለን፡፡ በዚህ መሰረት ዲዛይን እናደርጋለን። እናማክራለን፣ ስልጠና እንሰጣለን፡፡ ስትራክቸር መሆን አለበት ስንል፣ ምን መምሰል አለበት? ክፍተቱ ምንድነው? የስራው ይዘት ምንድነው? ማለት ነው፡፡
ኩባንያዎች እንዲህ ዓይነት ስትራክቸርድ የሆነ አሰራር አያውቁም፡፡ ስለዚህ መጀመሪያ ማሰልጠን፣ ቀጥሎ ዲዛይን የማድረግ አቅም መገንባት ከዚያም፣ ዲዛይን የተደረገውን ቀጣይነት እንዲኖረው ማድረግ አለባቸው፡፡ ስለዚህ አይ ካፒታል የሚያደረገው ምንድነው? መጀመሪያ እውቀቱ እንዲኖቸው እናሰለጥናለን፤ ከዚያም ዲዛይን ያደርጋሉ፡፡ እኛ የተወሰነውን እንበል 25 በመቶ ያህል እነሱ እያዩ ዲዛይን እናደርጋለን፡፡ 25 በመቶውን እኛ እያየናቸው እነሱ ዲዛይን እንዲያደረጉ እናደርጋለን፡፡ የተቀረውን 50 በመቶ አቅም ስለፈጠርንላቸው ራሳቸው ዲዛይን ያደርጋሉ በማለት ገልጸዋል፡፡     
አይ ካፒታል አፍሪካ አማካሪ ድርጅት ቢሆንም የተለመደው ዓይነት የማማከር ሥራ ግን አይደለም። ሁለት መሠረታዊ ቋሚ ምስሶዎች ኖሮት ነው የተቋቋመው፡፡ እነሱም የእውቀት ልውውጥ (ኖሌጅ ሼሪንግ ፕላትፎርም) እና ኢንቴሌክቿል ካፒታል ፓኬጅ ናቸው፡፡ አይ ካፒታል ሲባል አይ የምትወክለው ኢንቴሌክቿል ካፒታልን ነው፡፡ አፍሪካ የሚለውን የሚጠቀሙት ብዙ ጊዜ እውቀት ላይ መሰረት ያደረጉ ትላልቅ ሥራዎችን የሚሠሩት ከውጭ በመጡ ወይም ከአፍሪካ ውጭ በሆኑ ኩባንያዎች ነው ተብሎ ይታስባል፡፡ አይ ካፒታል አፍሪካ ግን አፍሪካዊ ሆኖ ጀማሪና እየሰፋ የሚሄድ ድርጅት እንደሆነ ለማመላከት ነው፡፡
የድርጅቱ መሪ ቃል ‹‹ዩር አፍሪካን ኢንሌሌክቿል ካፒታል ፓርትነርስ›› የሚል ነው፡፡ እውቀት ማስተላለፍ ሳይሆን እውቀት ማካፈል (ሼሪንግ) ነው፡፡ በዚህ ረገድ ባለፈው ሳምንት ‹‹የምሥራቅ አፍሪካ ዓመታዊ የፋይናስ ሰሚት›› አዘጋጅቶ፣ በፋይናስ ዘርፍ የእውቀት ልውውጥ እንዲደረግ አመቻችቷል፡፡ ባለፈው ዓመት በጣም አርኪ ውጤት የታየበትን ‹‹የመጀመሪያውን የምሥራቅ አፍሪካ የሲሚንቶ፣ የኮንክሪትና ኤነርጂ ሰሚት›› አዘጋጅተዋል፡፡ በሚቀጥለው ሰኔ ደግሞ በምስራቅ አፍሪካ ብቻ ሳይወሰኑ መሠረቱን ሰፋ በማድረግ፣ በመላው አፍሪካ ያለውን ልምድ ለመለዋወጥ ‹‹ሂዩማን ሪሶርስ ዴቨሎፕመንት ኮንፈረንስ ኢን አፍሪካ›› እንደሚያዘጋጁ ዶ/ር ገመቹ ተናግረዋል፡፡
ተቋሙ የተገነባበት ሁለተኛው ቋሚ መሰረት ኢንቴሌክቿል ካፒታል ፓኬጅ ነው፡፡ ዴቬሎፕመንት ፓኬጅ የሚባሉ አሉ፡፡ እነዚህ እውቀት ልውውጥ (ሼሪንግ) የሚደረጉ ሳይሆን አዲስ እውቀት መፍጠር ወይም ዴቬሎፕ መደረግን የሚጠይቅ ነው፡፡ የንግድ ድርጅት፡- ፋብሪካዎች እንደ ባንኮችና ኢንሹራንስ፣ ያሉ አገልግሎቶች የሚሰጡ የፋይናንስ፣ የመንግስት ተቋማት፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣… ማንኛውም ኩባንያ የኢንቴሌክቿል ካፒታል ደቬሎፕ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ እነዚያ ውስጥ አይ ካፒታል የድርሻውን እውቀት ማበርከት ይችላል ብለን ነው የተነሳነው በማለት አስረድተዋል፡፡
አይ ካፒታል ከሁለት ዓመት በፊት በዩኒቨርሲቲ ምሁራን በ15 ሺህ ብር ተመዝግቦ የተቋቋመ ድርጅት ቢሆንም ስራው እየሰፋ ስለሄደ፣ አሁን ላይ ካፒታሉ 300 ሺህ ብር ደርሷል፡፡ አሁንም ካፒታሉን የማሳደግ እቅድ አለው፡፡

Read 2139 times