Print this page
Saturday, 24 December 2016 13:02

ህብረት ባንክ በወጪ ንግድ ውጤታማ የሆኑ ደንበኞቹን ሸለመ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

 ህብረት ባንክ በወጪ ንግድ ተሰማርተው ውጤታማ በመሆን ለባንኩ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ያስገኙ ደንበኞቹን የዋንጫና የምስክር ወረቀት ሸለመ፡፡
ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ በሂልተን ሆቴል በተደረገው የሽልማት ስነ-ስርዓት፤ ባንኩ በቡና፣ በቅባት እህሎች፣ በጥራጥሬ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በጫት፣ በቅመማ ቅመም በእጣን ምርት፣ በአበባና በሻይ ቅጠል እንዲሁም በመሰል የወጪ ንግድ ተሰማርተው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ላስገኙ ደንበኞቹ ዕውቅናና ሽልማት ሰጥቷል፡፡
በሽልማት ስነስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የህብረት ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ታዬ ዲበኩሉ፤ ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶቻችንን በጥራት፣ በተወዳዳሪ ዋጋና በሚፈለገው መጠን ለዓለም ገበያ ለማቅረብ ዘርፈ ብዙ ተግዳሮቶች እንዳሉ ጠቅሰው፤ ከነዚህም መካከል የዓለም አቀፍ ገበያ ፍላጎት መቀዛቀዝ፣ የምርት ግብአት ጥራት መጓደል፣ የቴክኖሎጂ አቅም ውስንነት፣ ብቁና የሰለጠነ የሰው ሃይል እጥረትና በዘርፉ የሚታየው ህገ-ወጥ ንግድ አለመገታት በዋናነት ፈታኝ እንደነበሩ ተናግረዋል፡፡
እነዚህን ፈታኝ ሁኔታዎች ተቋቁመው በተሰማሩበት ዘርፍ ምርቶችን ለዓለም ገበያ በማቅረብ፣ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ለባንኩ ያስገኙትን ደንበኞች ያመሰገኑት አቶ ታዬ፤ ባንኩና ደንበኞች በትብብር አብረው ለማደግ በሚያደርጉት ጥረት ሁሌም ባንኩ ከጎናቸው በመቆም አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ለጋራ እድገት ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ቃል ገብተዋል፡፡ በዕለቱ ካለፉት 15 ወራት የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ 15 አስመጪና ላኪዎች የዋንጫና የእውቅና የምስክር ወረቀት፣ ለ36 ደንበኞች ደግሞ የሰርተፍኬት ሽልማት ተበርክቷል። ህብረት ባንክ ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ ላለፉት 18 ዓመታት በግል ባንክ ደረጃ ከፍተኛ የካፒታል አቅም በማካበት ግንባር ቀደም ከሆኑ የግል ባንኮች አንዱ እንደሆነ የተነገረለት ህብረት ባንክ፤ የኢንተርኔት የባንክ አገልግሎት፣ የኤስ ኤም ኤስ የባንክ አገልግሎትና የስልክ የባንክ አገልግሎትን በመስጠት ዘመናዊ አሰራርን ከሚጠቀሙ ባንኮች አንዱና ግንባር ቀደም እንደሆነ በዕለቱ ተገልጿል፡፡
ባንኩ በሁሉም የአገሪቱ ክልሎች ቅርንጫፎች ያሉት ሲሆን የባንኩ ጠቅላላ ሀብት 17.3 ቢሊዮን ብር፣ ሆኖ ሲመዘገብ የባንኩ ጠቅላላ ካፒታል ደግሞ 2.07 ቢሊዮን ብር መድረሱ ታውቋል፡፡ እ.ኤ.አ በ2015/16 በጀት ዓመት መጨረሻ ከ3200 በላይ ዜጎች በባንኩ የስራ ዕድል አግኝተው እየሰሩ መሆናቸውን የተገለፀ ሲሆን ከአጠቃላይ ብድር መጠን ወጪ ንግድ ዘርፍ 20.74 በመቶ ድርሻ መያዙም ተጠቁሟል፡፡

Read 2488 times