Saturday, 24 December 2016 12:58

“ፒዩርውድ” በ1 ቢሊዮን ብር ግዙፍ የወረቀት ፋብሪካ ሊገነባ ነው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ለጋዜጦች፣ መጽሃፍት፣ መጽሄቶች፣ ደረሰኞች--- ህትመት የሚሆኑ ወረቀቶችን ያመርታል

     “ፒዩርውድ ፐልፕ ፔፐር ኤንድ ፓኬጂንግ” ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ፣ በአንድ ቢሊዮን ብር አጠቃላይ የኢንቨስትመንት ካፒታል ግዙፍ የወረቀትና የማሸጊያ ካርቶን ማምረቻ ፋብሪካ በዱከም አካባቢ ሊገነባ መሆኑን በተለይ ለአዲስ አድማስ በላከው መግለጫ አስታወቀ፡፡
በኢትዮጵያውያን፣ በውጭ አገራት በሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና በቻይናውያን ባለሃብቶች የጋራ ጥምረት የተቋቋመው ኩባንያው፤ ፕሮጀክቱን በተመለከተ ከኢንቨስትመንት ኮሚሽን ጋር የመግባቢያ ሰነድ መፈራረሙንና በኦሮምያ ክልል በዱከም ከተማ አካባቢ በሚገኘው የኢንዱስትሪ ዞን፣ ለፋብሪካው ግንባታ የሚውል 68 ሄክታር ቦታ መረከቡን በመጠቆም፣ የፋብሪካው ግንባታ በቅርቡ እንደሚጀመርም ገልጧል፡፡
ግንባታው በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ተጠናቅቆ ማምረት ይጀምራል ተብሎ የሚጠበቀው ፋብሪካው፤ ዘመኑ የደረሰበትን የማምረቻ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ጥራት ያላቸው የተለያዩ አይነት ምርቶችን በማምረት በስፋት ለገበያ እንደሚያቀርብ ኩባንያው በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡ ኩባንያው ቀዳሚ ትኩረቱን የሚያደርገው ከውጭ አገራት ጥቅል የመጸዳጃ ቤትና የህትመት ወረቀቶችን እያስመጡ በጥሬ እቃነት ለሚጠቀሙ የአገር ውስጥ ፋብሪካዎች የተለያዩ አይነት ጥቅል ወረቀቶችን በማቅረብ ላይ እንደሆነ የጠቆሙት የኩባንያው ስራ አስኪያጅ አቶ ማሂር ኢስማኤል፤ ፋብሪካው በአመት 32 ሺህ 500 ቶን ያህል የተለያዩ አይነት የንጽህና መጠበቂያና የህትመት ወረቀቶችን እንዲሁም የማሸጊያ ካርቶኖችን የማምረት አቅም እንደሚኖረውም ገልጸዋል፡፡
ፕሮጀክቱ ለ700 ያህል ዜጎች ቋሚ የስራ እድል እንደሚፈጥር የጠቆሙት ስራ አስኪያጁ፤ ፋብሪካው የሸንኮራ አገዳ ተረፈ ምርትንና ጥቅም ላይ የዋሉ ወረቀቶችን መልሶ በጥሬ እቃነት የሚጠቀም በመሆኑ ለአካባቢ ጥበቃ የራሱን ሚና እንደሚጫወትም ገልጸዋል፡፡ ለንጽህና መጠበቂያና ለመጸዳጃ ቤት አገልግሎት ከሚውሉ ለስላሳ ወረቀቶች በተጨማሪ ለጋዜጦች፣ ለመጽሃፍት፣ ለመጽሄቶች፣ ለደረሰኞች፣ ለቀን መቁጠሪያዎችና ለሌሎች የህትመት ስራዎች የሚውሉ የተለያዩ አይነት ወረቀቶችን እንዲሁም የማሸጊያ ካርቶኖችን እያመረተ ለገበያ የሚያቀርበው ፋብሪካው፤ ለአገር ውስጥ የወረቀት አምራቾች ጥቅል ወረቀቶችን የማቅረብ እቅድ እንዳለውም ተነግሯል፡፡
በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ የመጣውን የወረቀት ፍላጎት በአገር ውስጥ ምርት መሸፈን ባለመቻሉ፣ አገሪቱ የወረቀት ምርቶችን በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ከውጭ አገራት እየገዛች ለመጠቀም ተገድዳ መቆየቷን የጠቆሙት አቶ ማሂር፤ የዚህ ግዙፍ ፋብሪካ መገንባት ለወረቀት ግዢ የሚወጣውን በመቶ ሚሊዮኖች ዶላር የሚቆጠር የውጭ ምንዛሬ በማዳን ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ገልጸዋል፡፡

Read 2882 times