Sunday, 25 December 2016 00:00

ሴሌን ዲዮን የትራምፕን የበዓለ ሲመት ግብዣ አልቀበልም አለች

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 - ታዋቂ ድምጻውያን በበዓለ ሲመቱ ላይ አንዘፍንም ብለዋል
                        - ለመዝፈን ቃል የገባችው አንዲት ድምጻዊት ብቻ ናት

     ታዋቂዋ ድምጻዊት ሴሌን ዲዮን ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከአንድ ወር በኋላ በዋሽንግተን ዲሲ በሚከናወነው በዓለ ሲመታቸው ላይ የሙዚቃ ስራዎቿን እንድታቀርብ ያቀረቡላትን ግብዣ አልቀበልም ማለቷ ተዘግቧል፡፡
ትራምፕ በበዓለ ሲመት አዘጋጆቻቸው በኩል ለሴሌን ዲዮን በክብር ግብዣ ቢያቀርቡላትም፣ ድምጻዊቷ በፕሮግራሙ ላይ ተገኝታ ለመዝፈን ፈቃደኛ አለመሆኗን እንደገለጸች ዘራፕ ድረገጽ ከትናንት በስቲያ ዘግቧል፡፡ ከሴሌን ዲዮን በተጨማሪ የትራምፕን ግብዣ አልቀበልም ያሉ ሌሎች አለማቀፍ ዝናን ያተረፉ ድምጻውያን መኖራቸውን የጠቆመው ድረገጹ፤ ከእነዚህም መካከል ኤልተን ጆን፣ ጋርት ብሩክስና አንድሪያ ቦሴሊ እንደሚገኙበት ገልጧል፡፡
አንዳንድ ድምጻውያን ፈቃደኝነታቸውን በመግለጽ በበዓለ ሲመቱ ላይ ለመዝፈን ቀጠሮ ቢይዙም፣ የትራምፕ ተቃዋሚ የሆኑ አድናቂዎቻቸው ባደረጉባቸው ጫና ሳቢያ ከሰሞኑ ሃሳባቸውን እንደቀየሩ የጠቆመው ዘገባው፤ አብዛኞቹ ድምጻውያን ግብዣውን ያልተቀበሉት በበዓለ ሲመቱ ላይ ተገኝተው በመዝፈን ለትራምፕ ፕሬዚዳንትነት እውቅና መስጠት ባለመፈለጋቸው ነው መባሉንም ጠቅሷል፡፡
በበዓለ ሲመቱ ላይ እንዲዘፍኑ ግብዣ ከተደረገላቸው ድምጻውያን መካከል እስካሁን ድረስ በፕሮግራሙ ላይ እንደምትገኝ ለአዘጋጆቹ ማረጋገጫ የሰጠቺውና በዝግጅቱ ላይ የአሜሪካን የህዝብ መዝሙር ለመዘመር ቀጠሮ የተያዘላት የ16 አመቷ ታዳጊ ድምጻዊት ጃኪ ኢቫንቾ ብቻ ናት ተብሏል፡፡

Read 1881 times