Sunday, 25 December 2016 00:00

ከ1 ቢ. በላይ የያሁ አካውንቶች የዝርፊያ ሰለባ ሆነዋል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ታዋቂው የድረገጽ ኩባንያ ያሁ፣ ከ1 ቢሊዮን በላይ የያሁ አካውንቶች የኢንተርኔት መረጃ ዘራፊዎች ከሶስት አመታት በፊት የፈጸሟቸው የሚስጥራዊ መረጃ ዝርፊያ ጥቃቶች ሰለባ መሆናቸውን አስታውቋል፡፡
ያሁ ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫ እንዳለው፣ እ.ኤ.አ በ2013 በተፈጸሙ ጥቃቶች ከአንድ ቢሊዮን በላይ የድረገጹ ተጠቃሚዎች ስም፣ የስልክ ቁጥር፣ ሚስጥራዊ የይለፍ ቃል፣ የኢሜይል አድራሻ እና ሌሎች ሚስጥራዊ መረጃዎች በዘራፊዎች ተሰርቀዋል፡፡ የኢንተርኔት ዘራፊዎች የተጠቀሱትን ሚስጥራዊ መረጃዎች ቢዘርፉም፣ የባንክና የክፍያ መረጃዎችን አለመዝረፋቸውን ኩባንያው አክሎ ገልጧል፡፡ ያሁ ባለፈው መስከረም ባወጣው መረጃ፣ በ2014 ላይም 500 ሚሊዮን ያህል አካውንቶች የመሰል ጥቃቶች ሰለባ መሆናቸውን እንዳስታወቀ ያስታወሰው ዘገባው፤ ኩባንያው ሰሞኑን ባወጣው መግለጫም የያሁ ተጠቃሚዎች ከመሰል አደገኛ የመረጃ ዘረፋዎችና ጥቃቶች ራሳቸውን ለመጠበቅ፣ የአካውንቶቻቸውን ሚስጥራዊ የይለፍ ቃሎችና የደህንነት ማረጋገጫ ጥያቄዎች እንዲቀይሩ ኩባንያው አሳስቧል፡፡
ተቀማጭነቱን በካሊፎርኒያ ያደረገው ያሁ፣ ከአንድ ቢሊዮን በላይ ወርሃዊ ተጠቃሚዎች እንዳሉት የጠቆመው ዘገባው፣ ዘራፊዎች የፈጸሙበት ጥቃት ቨሪዞን የተባለው ተቋም ያሁን ለመግዛት በጀመረው ድርድር ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ይፈጥራል የሚል ስጋት መፈጠሩንም አክሎ ገልጧል፡፡

Read 1277 times