Sunday, 25 December 2016 00:00

የኮንጎው መሪ ስልጣን አለመልቀቃቸው የከፋ ተቃውሞና ግጭት ፈጥሯል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

   - ከ26 በላይ ሰዎች ሲገደሉ፣ 45 ያህል ቆስለዋል - የ92 አመቱ ሙጋቤ በቀጣዩ ምርጫም ይወዳደራሉ

      የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ካቢላ የስልጣን ዘመን ገደባቸው መጠናቀቁን ተከትሎ ስልጣን ለመልቀቅ ፍላጎት አለማሳየታቸው የቀሰቀሰው ከፍተኛ ተቃውሞ፣ በአገሪቱ ከፍተኛ ውጥረት የፈጠረ ሲሆን  የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች እስካለፈው ረቡዕ ድረስ ከ26 በላይ ሰዎችን መግደላቸው ተዘግቧል፡፡
የፕሬዚዳንቱ የስልጣን ዘመን ቆይታ ባለፈው ማክሰኞ ቢያበቃም እስከ 2018 በስልጣናቸው ላይ እንደሚቆዩ በፓርቲያቸው ከተገለጸ በኋላ  የአገሪቱ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች የጠሩት ሰላማዊ ተቃውሞ ወደ ግጭት ማምራቱን የጠቆመው ዘገባው፤ በርካታ ተቃዋሚዎች ባለፈው ማክሰኞ የገዢውን ፓርቲ ቢሮ ማቃጠላቸውን ተከትሎ፣ በፖሊስና በተቃዋሚዎች መካከል ግጭት መከሰቱንና የጸጥታ ሃይሎች ቤት ለቤት አሰሳ በማድረግ በርካታ ዜጎችን ማሰራቸውን ገልጧል፡፡
በመዲናዋ ኪንሻሳ የተጀመረው ተቃውሞው ወደተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች እየተስፋፋና ውጥረቱ እየተባባሰ መምጣቱን ያመለከተው ዘገባው፤ ተመድ 45 ያህል ተቃዋሚዎች በተተኮሰባቸው ጥይት መቁሰላቸውን ባለፈው ረቡዕ ማስታወቁንና በአገሪቱ የተሰማራው የተመድ የሰላም አስከባሪ ሃይልም ግጭቱ ወደ እርስ በእርስ ግጭት እንዳያመራ መስጋቱንና ውጥረቱን ለማርገብ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ አብራርቷል፡፡
አሜሪካ ፕሬዚዳንት ካቢላ ምርጫ እንዲካሄድ በማድረግ ስልጣናቸውን ለማስረከብ ተነሳሽነት አለማሳየታቸው አሳዝኖኛል ማለቷን የጠቆመው ዘገባው፤ በአገሪቱ ባለፈው ወር ላይ ምርጫ መደረግ ቢገባውም የምርጫ ኮሚሽኑ ሰበብ አስባብ በማብዛት ምርጫውን ማራዘሙ ካቢላን በስልጣን ላይ ለማቆየት የታሰበ ሴራ ነው የሚል ቁጣ መፍጠሩንም ገልጧል፡፡
ከ2001 አንስተው አገሪቱን በመምራት ላይ የሚገኙት የ45 አመቱ ጆሴፍ ካቢላ፣ በህገመንግስቱ በተደነገገው መሰረት ለሶስተኛ የስልጣን ዘመን መወዳደር የማይችሉ ቢሆንም፣ ፕሬዚዳንቱ ግን 74 አባላት ያሉት የሽግግር መንግስት በማቋቋም እስከ 2018 ድረስ አገሪቱን በመምራት ለመቀጠል አቋም መያዛቸውን ዘገባው አስረድቷል፡፡
በተያያዘ ዜናም፣ ከ36 አመታት በላይ ዚምባብዌን የመሩትና አገሪቱን ወደከፋ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ስላስገቧት ስልጣን ይበቃቸዋል የሚል ጫና ከውስጥም ከውጭም የበረታባቸው የ92 አመቱ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ፤ ከአንድ አመት በኋላ በሚካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እንደሚወዳደሩ ፓርቲያቸው አስታውቋል፡፡ ሙጋቤ በ2018 ምርጫ ለፕሬዚዳንትነት እንደሚወዳደሩ ይፋ መደረጉን ተከትሎ፣ የአገሪቱ ተቃዋሚ ሃይሎች የፓርቲውን ውሳኔ በማውገዝ አገሪቱን ወደ ከፋ ስራ አጥነት፣ የገንዘብ ቀውስና የኢኮኖሚ ድቀት ያስገቧት ሙጋቤ ስልጣን የሚይዙ ከሆነ የከፋ ቀውስ ይከተላል ሲሉ ማስጠንቀቃቸውን ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡
ፓርቲያቸው ዛኑ-ፒኤፍ ከሰሞኑ ባደረገው ጉባኤ ላይ በፓርቲው የወጣቶች ክንፍ፣ ሙጋቤ እስከ ህልፈተ ህይወታቸው የአገሪቱ መሪ ሆነው ይቀጥሉ የሚል ሃሳብ መነሳቱን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ በርካታ የአገሪቱ ዜጎች ባለፉት አመታት የሙጋቤን አምባገነናዊ ስርዓት በማውገዝ ተቃውሟቸውን አደባባይ ወጥተው ሲያሰሙ እንደነበርም ዘገባው አስታውሷል፡፡
በሌላ ዜና ደግሞ በቅርቡ በተካሄደው ምርጫ የተሸነፉትና ስልጣናቸውን እንዲለቁ በምዕራብ አፍሪካ አገራት ጫና ሲደረግባቸው የሰነበቱት የጋምቢያው ፕሬዚዳንት ያያ ጃሜህ፤ የማንም ጫና ከስልጣኔ አያስለቅቀኝም ሲሉ በድጋሚ በአቋማቸው መጽናታቸውን ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ባለፈው ማክሰኞ በሰጡት መግለጫ፣ ከፈጣሪ በቀር ስልጣኔን ሊያስለቅቀኝ የሚችል አንዳች እንኳን ምድራዊ ሃይል የለም በማለት እቅጩን ተናግረዋል፡፡

Read 1387 times