Saturday, 24 December 2016 13:10

ጀርመን ፌስቡክን በ1 ሃሰተኛ ዜና፣ 500 ሺ ዩሮ ለመቅጣት አስባለች

Written by 
Rate this item
(0 votes)

- ቱርክ ፌስቡክ፣ ትዊተርና ዋትዛፕን ዘግታለች

      የጀርመን ሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ ሊቀመንበር ቶማስ ኦፐርማን ፌስቡክ ሃሰተኛ ዜናዎችን በአፋጣኝ ከድረገጹ ላይ የማያስወግድ ከሆነ በአንድ ሃሰተኛ ዜና 500 ሺህ ዩሮ ቅጣት እንዲጣልበት የሚያስገድድ ህግ እንዲወጣ ሃሳብ ማቅረባቸውን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘግቧል። ፌስቡክ ግለሰቦችንና ተቋማትን ተጠቂ የሚደርጉ ሃሰተኛ ዜናዎችንና መረጃዎችን በተመለከተ የሚቀርቡለትን አቤቱታዎች በአግባቡ ተቀብሎ አፋጣኝ እርምጃ እየወሰደ አይደለም ያሉት ኦፐርማን፤ ይህን እንዲያደርግ የሚያስገድድ ህግ መውጣት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ ፌስቡክ መሰል ሃሰተኛ ዜናዎችንና መረጃዎችን በተመለከተ የሚቀርቡለትን አቤቱታዎች ተቀብሎ፣ በ24 ሰዓታት ጊዜ ውስጥ ከማህበራዊ ድረገጹ ላይ የማይሰርዝ ከሆነ፣ እስከ 500 ሺህ ዩሮ የሚደርስ ቅጣት ሊጣልበት ይገባል ብለዋል፡፡ በመሰል ዜናዎችና መረጃዎች ተጠቂ የሆኑ ግለሰቦችና ተቋማትም ከፌስቡክ ካሳ ሊሰጣቸው ይገባል ሲሉም አክለዋል፡፡
ፖለቲከኛው ያቀረቡት የቅጣት ሃሳብ፣ አገሪቱ በመጪው የፈረንጆች አመት 2017 ልታካሂደው ያሰበቺው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በማህበራዊ ድረገጾች አማካይነት ሊረበሽ ይችላል በሚል የጀርመን መንግስት በድረገጾቹ ላይ ጥብቅ ክትትል ሊደረግ እንደሚገባ የያዘው አቋም አካል ነው ተብሏል፡፡
በተያያዘ ዜናም፣ ባለፈው ሰኞ በቱርክ የሩስያ አምባሳደር አንድሪ ካርሎቭ በጥይት መገደላቸውን ተከትሎ፣ የአገሪቱ መንግስት ፌስቡክ፣ ትዊተርና ዋትዛፕን መዝጋቱን ዘ ቴሌግራፍ ዘግቧል፡፡

Read 1498 times