Print this page
Sunday, 25 December 2016 00:00

ፑቲን በአመቱ የአለማችን ሃያላን ዝርዝር ቀዳሚነቱን ይዘዋል

Written by 
Rate this item
(5 votes)

 - አምና 72ኛ የነበሩት ትራምፕ፣ ዘንድሮ 2ኛ ሆነዋል - ከ74 የአለማችን ሃያላን፣ አፍሪካውያን 2 ብቻ ናቸው

    ታዋቂው ፎርብስ መጽሄት 74 ሰዎች የተካተቱበትን የ2016 የአለማችን ሃያላን ዝርዝር ከሰሞኑ ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ የሩስያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን፣ ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና የጀርመን መራሂተ መንግስት አንጌላ መርኬል በቅደም ተከተል ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል፡፡
የቻይናው ፕሬዚዳንት ዢ ጂፒንግ፣ የሮማው ሊቀጳጳስ ፍራንሴስ እና የአሜሪካ የፌደራል ሪዘርቭ ሃላፊ ጃኔት የለን እስከ ስድስተኛ ያለውን ደረጃ ሲይዙ፣ የማይክሮሶፍቱ መስራች ቢል ጌትስ፣ የአልፋቤት ኩባንያ ዋና ስራ አስፈጻሚ ላሪ ፔጅ፣ የህንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ እና የፌስቡኩ መስራች ማርክ ዙክበርግ በቅደም ተከተል እስከ አስረኛ ደረጃን ይዘዋል፡፡ አምና 72ኛ ደረጃ ላይ የነበሩት ትራምፕ፣ በሚገርም መሻሻል ዘንድሮ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡ ሲሆን፣ አምና በ2ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠው የነበሩት ተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በአንጻሩ ዘንድሮ ወደ 48ኛ ደረጃ አሽቆልቁለዋል፡፡ በዘንድሮው የፎርብስ የአለማችን ሃያላን ዝርዝር ውስጥ ሁለት አፍሪካውያን ብቻ የተካተቱ ሲሆን፣ 44ኛ ደረጃን የያዙት የግብጹ ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ፣ ከአፍሪካውያን መካከል ቀዳሚው ሃያል ሰው ሲባሉ፣ የአፍሪካ ቁጥር አንድ ቢሊየነር አሊኮ ዳንጎቴ 68ኛ ደረጃን በመያዝ ሁለተኛው ሃያል ሰው ሆነዋል፡፡
በፎርብስ የአመቱ ሃያላን ዝርዝር ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ስማቸው የተካተተ ግለሰቦች ቁጥር 11 እንደሆነ የጠቆመው መጽሄቱ፣ ከእነዚህም መካከል የእንግሊዟ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬሳ ሜይ እና የፊሊፒንሱ ፕሬዚዳንት ሮዲሪጎ ዱሬቴ እንደሚገኙበት ገልጧል፡፡ ፎርብስ መጽሄት የአመቱን የአለማችን ሃያላን የመረጠባቸው መስፈርቶች በብዙ ሰዎች ላይ ተጽዕኖ የማሳደር ብቃት፣ የፋይናንስ አቅም፣ የተጽዕኖ ወሰን ስፋትና አቅምን የመጠቀም ብቃት የሚሉ እንደሆኑ አስታውቋል፡፡

Read 4795 times
Administrator

Latest from Administrator