Monday, 26 December 2016 09:43

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(9 votes)

-በቁጥጥር ስር የዋሉ - 24 ሺ
-ሰሞኑን የተፈቱ - 9800
-ክስ የሚመሰረትባቸው - 2400
- ጉዳያቸው እየተጣራ የሚገኝ - 12 ሺ

            ተቃዋሚዎች የቀሩት አመራሮችና አባላትም እንዲለቀቁ ጠየቁ
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ታውጆ በቆየባቸው ያለፉት ሁለት ወራት ውስጥ ከ24 ሺ በላይ ግለሰቦች በኮማንድ ፖስቱ ቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን 9800 ያህሉ የተለያዩ ስልጠናዎች ወስደው ሰሞኑን ከእስር ተለቀዋል፡፡ 2 ሺ 400 የሚሆኑት ክስ እንደሚመሰረትባቸው የተገለፀ ሲሆን 12 ሺህ በሚሆኑት ላይ ደግሞ ማጣራት እየተደረገ ነው ተብሏል፡፡
ሰሞኑን የተለቀቁት 9800 ግለሰቦች፤ “የህገ መንግስትና ፊደራሊዝም፣ ዲሞክራሲ፣ የሠብአዊ መብት ጉዳይ፣ የወጣቶች ሚና በሃገሪቱ ህዳሴ፣ ተቃውሞን በሠላማዊ መንገድ መግለፅ፣  የወንጀል ጉዳትና የሃገሪቱ ታሪክ” እና በመሳሰሉ በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ለ1 ወር ሰልጥነው የተመረቁ መሆናቸውን የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ሚኒስትር ዴኤታ፣ አቶ ዛዲግ አብርሃም ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
ስልጠና የተሠጣቸው ወጣቶች፤ የወንጀል ድርጊት ላይ የተሣተፉ ቢሆንም የተሣትፎአቸው መጠን አነስተኛ መሆኑና የተሳተፉበት ምክንያት ታይቶ መለቀቃቸው ተገልጿል፡፡
“አብዛኞቹ ወጣቶች በአቻ ግፊት፣ በማህበራዊ ሚዲያ መልዕክቶችና በተለያዩ የሃሠት ፕሮፓጋንዳ ተነሳስተው የተሣተፉ እንጂ ሃገርን ለማፍረስ የወጠኑ አለመሆናቸው ታይቶ በስልጠና ታልፈዋል” ብለዋል - ሚኒስትር ዴኤታው፡፡
ከእስር የተለቀቁት ሁሉም ወጣቶች ወደየስራ መስካቸው እንደሚመለሱም፤ አቶ ዛዲግ ጨምረው ገልፀዋል፡፡ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በርካታ አመራሮችና አባላት እንደታሠሩባቸው ተደጋጋሚ አቤቱታ ሲያቀርቡ የቆዩት ተቃዋሚ ፓርቲዎች በበኩላቸው፤ ታስረው የነበሩ ግለሠቦች መለቀቃቸውን በበጎ እንደሚመለከቱት ጠቁመው፤ የቀሩ የፓርቲ አመራሮችና አባላትም በአስቸኳይ እንዲፈቱ ጠይቀዋል፡፡
የታሰሩ አመራሮችና አባላቱ እንዲፈቱ መንግስትን በተደጋጋሚ ሲጠይቅ እንደነበር የጠቆመው መኢአድ፤ ጥቂት አባላቱ መፈታታቸውንና በርካቶች አሁንም በእስር ላይ እንደሚገኙ አስታውቋል፡፡ የፓርቲው ዋና ፀሐፊ አቶ አዳነ ጥላሁን፤ እንደገለፁት ምስራቅ ጎጃም ላይ ታስረው የነበሩ አባሎቻቸው በሙሉ የተለቀቁ ሲሆን ደቡብ ጎንደር የታሰሩ 8 የፓርቲው አባላት፣ እብናት ወረዳ 10 እና ስማዳ ወረዳ 3 አባሎቻቸው አልተለቀቁም ብለዋል፡፡ በእስር ላይ የሚገኙ ቀሪ አመራሮቹና አባላቱ በአስቸኳይ እንዲለቀቁለትም መኢአድ ጠይቋል፡፡
“በመጀመሪያም ቢሆን ከ10 ሺህ ሰው በላይ ማሰር ተገቢ አልነበረም” ያሉት አቶ አዳነ፤ “ያለ ምንም የፍርድ ሂደት ሰዎችን አስሮ “አይደገምም” የሚል ቲ - ሸርት በማልበስ፣ አሰልጥኜ ለቅቄያለሁ ማለት የዲሞክራሲያዊ አሰራር መገለጫ አይደለም” ብለዋል፡፡
ሊቀመንበሩን ጨምሮ በርካታ አባላቱና አመራሮቹ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁና ከዚያም በፊት መታሰራቸውን ሲገልፅ የቆየው የኦሮሞ ፊደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ም/ሊቀመንበር አቶ ሙላቱ ገመቹ በበኩላቸው፤ ፓርቲያቸው ታስረው የነበሩ ከፊል ደጋፊዎቹና አባላቱ መለቀቃቸውን በበጎ እንደሚመለከተው ጠቁመው፤ የቀሩት ከፍተኛ የፓርቲ አመራሮቹም በአስቸኳይ እንዲለቀቁለት አሁንም ጥሪውን ለመንግስት እንደሚያቀርብ አስታውቀዋል፡፡
ከታሰሩት የፓርቲው አመራሮች አንድም የተፈታ አለመኖሩን ያስታወቁት አቶ ሙላቱ፤ መንግስት አመራሮቻቸውን ከእስር ለቆ፣ ለሰላማዊ የፖለቲካ ውይይት መድረኮችን እንዲያዘጋጅ ጠይቀዋል፡፡
እስረኞች መለቀቃቸውን ፓርቲያቸው በመልካም እንደሚቀብለው የገለፁት የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ወንደወሠን ተሾመ፤ አስቀድሞም ቢሆን እስሩ አስፈላጊ ያልነበረና የታሠሩበት ሁኔታም ግልፅነት የጎደለው፤ የብዙዎችንም መንፈስ የሚገድል አይነት በመሆኑ፣ ፓርቲያቸው ድርጊቱን ፈፅሞ እንደማይቀበለው ገልፀዋል፡፡ ‹‹ግለሠቦቹ ፖለቲካን እንዲፀየፉና መብትን መጠየቅ አደገኛ መሆኑን ተረድተው እንዲወጡ መደረጉንም አጥብቀን እንቃወማለን›› ያሉት አቶ ወንድወሠን፤ ፓርቲያቸው በታሰሩ ሰዎች ቁጥር ላይ ጥያቄ እንዳለውና ቀሪ ታሣሪዎችም በአስቸኳይ እንዲፈቱ አሁንም እንደሚጠይቅ ጠቁመዋል፡፡
የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ፤ የዜጎች ጅምላ እስር በእጅጉ እንደሚያሳስባቸው ሲገልፁ መቆየታቸው የሚታወቅ ሲሆን ባለፈው ማክሰኞ  በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአሜሪካ አምባሣደር ሣማንታ ፓወር፤  የኢትዮጵያ መንግስት የታሠሩ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ አመራሮችን እንዲለቅ ጠይቀዋል፡፡ -

Read 5392 times