Print this page
Saturday, 31 December 2016 11:22

በርካታ የዓለም ዝነኞችን በሞት ያጣንበት ዓመት!!

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 ባለፉት 9 ወራት ብቻ 71 ያህል ዝነኞች ሞተዋል

      የመጨረሻዋ ቀን ላይ በሚገኘው የፈረንጆች አመት 2016፣ ባልተለመደ ሁኔታ ከፖለቲካ እስከ ስፖርት፣ ከፊልም እስከ ሙዚቃ በየሙያ መስኩ እውቅናን ያተረፉ በርካታ ዝነኞችና ታዋቂ ሰዎች ከዚህ አለም በሞት የተሰናበቱበት መሆኑ ተነግሯል፡፡
ሲኤንኤን በአለማቀፍ ደረጃ የተሰራ የጥናት ውጤት ጠቅሶ ሰሞኑን እንደዘገበው፣ እስካለፈው ጥቅምት ወር ድረስ በነበሩት የአመቱ 9 ወራት ብቻ፣ በተለያዩ የሙያ መስኮች ስማቸውን በአለም መድረክ ላይ ማስጠራት የቻሉ ከ71 በላይ የዓለማችን ታዋቂ ሰዎችና ዝነኞች ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል፡፡ ከስፖርቱ አለም ብንጀምር፣ እድሜ የማያዝላቸው፣ ህመም የማይረታቸው ከሚመስሉ ጠንካራ እጆቹ በሚወነጨፉ ቡጢዎቹ ብዙዎችን ያደባየው የአለም የከባድ ሚዛን ሻምፒዮናው መሃመድ አሊ፣ ባለፈው ሀምሌ ወር መጀመሪያ ላይ ነበር በተወለደ በ74 አመቱ ይህቺን ዓለም በሞት የተሰናበተው፡፡
ወደ ፖለቲካው ጎራ ስንል ደግሞ፣ አለማችን በአመቱ ካጣቻቸው ታላላቅ ሰዎች መካከል አንዱ የሆኑትን የቀድሞውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ ግብጻዊውን ቡትሮስ ቡትሮስ ጋሊን እናገኛለን። ቡትሮስ ጋሊ በወርሃ የካቲት ነበር በ93 ዓመታቸው በሞት የተለዩት፡፡ አለማችን በዓመቱ ካጣቻቸው ሌሎች ፖለቲከኞች መካከልም የኖቤል የሰላም ተሸላሚውን ሺሞን ፔሬዝን እናገኛለን፡፡ እስራኤልን በፕሬዚዳንትነትና በጠቅላይ ሚኒስትርነት ያስተዳደሩት ፔሬዝ፣ ባለፈው መስከረም ወር መጨረሻ ላይ ነበር በ93 ዓመታቸው ይህቺን አለም በሞት የተሰናበቱት፡፡
መስከረም ላይ ፔሬዝን የወሰደ ጨካኝ ሞት፣ በህዳር ዞሮ መጣና ሌላ የፖለቲካው መስክ ገናና ይዞ ሄደ፡፡ ኮሙኒስት ኩባን ለግማሽ ምዕተ አመት ያህል ያስተዳደሩት ፊደል ካስትሮ ሩዝ፤ በ90 አመታቸው ወደማይቀርበት መሄዳቸው ተሰማ፡፡ ከሙዚቃው መስክ ከተሰሙት አስደንጋጭ መርዶዎች መካከል ከሰሞኑ የተደመጠው የጆርጅ ማይክል ሞት አንዱ ነበር፡፡ ታዋቂው ድምጻዊ ጆርጅ ማይክል፣ በፈረንጆች የገና እለት ከዚህ አለም በሞት የመለየቱ መርዶ ተሰምቷል፡፡ በካንሰር ሲሰቃይ የቆየው እንግሊዛዊው የሮክ አቀንቃኝ ዴቪድ ቦዌም በዚሁ ጦሰኛ አመት ነበር በ69 ዓመቱ ይህቺን አለም በሞት የተሰናበተው፡፡
አመቱ ሊጠናቀቅ ጥቂት ቀናት በቀረበት ሁኔታ አለምን በድንጋጤ ክው ያደረገ ሌላ የመዝናኛው መስክ መርዶ ከሰሞኑ ተሰምቷል፡፡ በ”ስታር ዎርስ” ፊልም ላይ በመተወን የዓለምን ቀልብ ገዝታ የዘለቀቺው የፊልም ተዋናይትና ደራሲ ኬሪ ፊሸር፣ ባለፈው ሰኞ በልብ ድካም ህመም በ60 አመቷ አለምን ተሰናብታለች፡፡

Read 4041 times
Administrator

Latest from Administrator