Saturday, 31 December 2016 11:26

“ለምን ምሳ አብረን አንበላም…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(10 votes)

 እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ… ዘንድሮ ጠፍቶ የከረመ ሰው ድንገት ደውሎ፤ “ምሳ ልጋብዝህ…” ካለ እንደ ድሮው ለጨዋታና የሆድ የሆድን ለመነጋጋር ብቻ ላይሆን ይችላል፡፡
እናማ…የሆነ ለተወሰኑ ዓመታት ችላ ያላችሁት ሰው፣ ድንገት ደውሎ ይቀጥራችሁና ለምሳ ትገናኛላችሁ፡፡
ምሳ ከመቅረቡ በፊት…
“እሺ፣ ኑሮስ እንዴት ይዞሀል…”
“አለን፣ ምን እንሆናለን ብለህ ነው…” (የሆናችሁትንማ ሆናችኋል! አንደባበቃ፣ የሆናችሁትንማ ሆናችኋል፡፡ ሀያ አምስት ኪሎ ጤፍ ለቤተሰብ ለመንፈቅ የምታብቃቁትማ የሆነ ነገር ብትሆኑ ነው! የእድር በወር አሥር ብር መክፈል አቅቷችሁ የሰባት ወር የተጠራቀመባችሁማ የሆነ ነገር ብትሆኑ ነው! እማወራዋ… “የሹሮ እቃውም፣ የበርበሬ እቃውም፣ የዘይት ጄሪካኑም ባዷቸውን ተሰነጣጥቀው ከማለቃቸው በፊት ለምን አሁኑኑ አንሸጣቸውም…” ብላ አምስት ቀን ከአልጋ ሳትነሱ ተልባ ስትጠጡና ፌጦ ጆሯችሁ ስር ስታደርጉ የከረማችሁትማ፣ የሆነ ነገር ብትሆኑ ነው! ግን ይሄ ለማን ይነገራል…ያውም ዘንድሮ! ያውም በ‘ሶሻል ሚዲያ’ ዘመን!  ቂ…ቂ…ቂ… “ምን እንሆናለን ብለህ ነው…” የምትል ነፍስ-አድን አባባል እያለችማ መበለጥ የለም፡፡)    “ሥራስ…”
“ምንም አይል…” (እና ምን ልትሉት ኖሯል! ስብሰባ ላይ “ተነሳሽነት ይጎድለዋል…”፣ “የኪራይ ሰብሳቢነት ስሜት ያንጸባርቃል…” ምናምን የተባላችሁትን ሁሉ ልትነግሩት ኖሯል! “አንድ ቀን ለምን እራት አንበላም…ያላችኋት የሥራ አስኪያጁ ጸሀፊ፣ ገና በታህሳስ… “ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም!” ብላ ተርታ እንዴት እንደሳቀችባችሁ ልትነግሩት ኖሯል!)  
ሦስተኛው ጉርሻ ላይ…
“በጣም ተጠፋፋን አይደል፣ የሚገርም እኮ ነው፣ መረሳሳት የሚመጣው እኮ እንዲህ፣ እንዲህ አያለ ነው፡፡…”
“አንተ ነህ የጠፋኸው፣ እኔማ የት እሄዳለሁ ብለህ ነው…” (እሱ ነው እንጂ… አንዴ፣ የእነ እንትና ቡድን አባል ሲሆን፣ ሌላ ጊዜ ከሌሎቹ እነ እንትና ጋር ‘ብከዳችሁ ይክዳኝ’ እየተባባለ ያለዝውውር ገንዘብ (ቂ…ቂ…ቂ…) ቡድን ሲለዋውጥ ማን ትዝ ብሎት!)
“ምን ላድርግ ብለህ ነው፣ ኑሮ ሩጫ ሆኗል…አንዱን ስትለው አንዱ…መባከን ሆኗል…ሰው ያለ መሰለህ…” (አጅሬው ፊልሙ ‘ተቃጠለበት’ እንዴ! የምር ግን…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ፊልሙ አንዳንዴ ‘ጠቁሮ ታጠበልኝ’ ሲሉ፣ አንዳንዴ ደግሞ ገና ሳይጠቆር ‘የሚቃጠልባቸው’ ሰዎች…አለ አይደል.. ቁጥር አንድ “ምን ሰው አለ ብለህ ነው…” ባይ ሲሆኑ አይገርማችሁም! ችግሩ ምን መሰላችሁ…ዘንድሮ ብዙዎቻችን… “ይሉሽን አልሰማሽ…” የሚለው ተረት ጠፍቶብን… ‘ልዕልቲቱና ልዑሉ እንቁራሪት…’ ምናምን አይነት የህልም ዓለም ውስጥ ገብተን የሚያወጣን መጥፋቱ ነው፡፡ ኸረ የ‘ላይፍጋርድ’ ያለህ! ቂ...ቂ…ቂ…)
አምስተኛ ጉርሻ ላይ…
“የሚገርምህ ነገር በቀደም መጽሐፍ እያነበበኩ እያለሁ እኮ ነው ድንገት ትዝ ያልከኝ፡፡ ይሄ ነገር ተገናኙ ሲለን ነው፣ ለምን ምሳ አልጋብዘውም ብዬ ደወልኩልህ…” (“እሪ በል እሪ በከንቱ…” ምናምን ብሎ መዝፈን ይሄኔ ነው፡፡ ልክ ነዋ…ኮሚኩ ነገር ድንገት ትዝ ማለቱ አይደለም፡፡ ኮሚኩ ነገር ‘ትዝ ያለው’ መጽሐፍ እያነበበ እያለ መሆኑ ነው፡፡ ምን አለ… “ሦስተኛውን ብርሌ ጨርሼ አራተኛውን ሳስቀዳ…”፣ “ሰባተኛውን ጃምቦ ሳጋምስ…” ምናንም የማይለውሳ! የምር… እንዴት ነው ሮሚዮ ወደ ጁሊየት ’መኝታ ቤት‘ በዛፍ ተንጠላጥሎ እየወጣ ሌላ ሰው ትዝ የሚለው! ስሙኝማ…እግረ መንገዴን… “አንድ ቡቲክ በራፍ ላይ አሪፍ ያለበሷት አሻንጉሊት አይቼ ድንገት ትዝ አልሽኝ…” የተባለች እንትናዬ፣ ምን ልትመስል እንደምትችል አስቡትማ!”
“ጥሩ አድርገሀል…የድሮ ወዳጅ ማግኘት እኮ ጥሩ ነው…”
“እኔም እሱን ብዬ አይደል የደወልኩልህ…” (ሳቁ ትክክል አይደለም፡፡ አለ አይደል… ከመድረክ ተውኔት ላይ… አለ አይደል… ያለ ኮፒራይት ስምምነት የተመነተፈ በመሆኑ ‘ዜማው’ ራሱ ልክ አይደለም፡፡)
ሰባተኛ ጉርሻ ላይ…
“ለመሆኑ እጮኛህ እንዴት ነች?” (“እጮኛ! ከእሷ በኋላ ሁለቱ የእናንተን መስፈርት ስላላሟሉ፣ የሦስቱን መስፈርት ደግሞ እናንተ ስላላሟላችሁ ሲፈራረቁ ከርመው እጮኛ ይላችኋል! “ፌስቡክህ ፔጅህ ላይ ፕሮፋይል ፒክቸር ያደረግኸውን ፎቶዬን አንሳልኝ” ብላ…ሦስተኛ ዓለም ጦርነት ሊቀሰቀስ ዳር ደርሶ በቋፍ ተርፋችሁ “እጮኛህ…”ይላል! ግን ለምን ደስ ይበለው!…)
“ደህና ነች፣ ምንም አትል…”
“ስማ ተጋቡና ሰርግ አብሉን እንጂ! ምን ትጠብቃላችሁ…” (ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… ይቺ “ሰርግ አብሉን እንጂ!” ኮሚክ ነች። ልክ ነዋ… “ተጋቡና ቤተሰብ መስርቱ…” ወይ “ተጋቡና ልጀ ውለዱ እንጂ...” ምናምን ሳይሆን --- “ሰርግ አብሉን እንጂ!” የምትለዋ ሆድ--ተኮር ምኞት ትሻሻልልንማ!)
“የት ይቀራል ብለህ ነው…”
ዘጠነኛ ጉርሻ ላይ…
ጎርነን ባለ ድምጽ…“ስማኝማ አንድ ነገር ላማክርህ ፈልጌ…” (አሁን እውነተኛዋ ጨዋታ መጣች…‘ሮማንቲክ ኮሜዲው’ አለቀ ማለት ነው፡ ቂ…ቂ…ቂ…)
“ምነው፣ ደህና አይደለህም እንዴ! ቤተሰብ ደህና አይደለም እንዴ…” (ከአንገት በሉት፣ ከአንጀት በሉት፣ ‘ሳይታሰብ አምልጦ የወጣ’ በሉት…ማህበረሰብ እንደዛ እንድትሉ ስለሚጠብቅ… “ቤተሰብ ደህና አይደለም እንዴ…” ምናምን ትላላችሁ፡፡
“ሁላችንም ደህና ነን፣ ምን መሰለህ…”  ያመነታል፡፡ (እንግዲህ ጨዋታም አይደል… “ምን መሰለህ…” ብሎ እያመነታ ዳር፣ ዳር የሚል ሰው… አለ አይደል… “እንኳን ደስ አለህ፣ ደሞዝህ በሦስት እጥፍ እንዳደገልህ ቢሮ አካባቢ ሰማሁ…” ምናምን አይነት የምስራች ወሬ ይዞ እንዳልመጣ እርግጠኛ ሁኑ፡፡ በተለይም…በጣት ራስን ቆፈር፣ ቆፈር ማድረግ ካለ ወይ… “ገንዘብ ስጠኝ…” ነው፣ ወይ የሆነ ውለታ ዋልልኝ ነው፡፡ እናም… መጽሐፍ ሲያነብ ድንገት ትዝ ያላችሁት ሰው…ጨዋታው ሌላ እንደሆነ ትጠረጥራላችሁ፡፡)
“አይ ደህና አትመስለኝም፣ የገጠመህ ነገር አለ እንዴ?” (ምን ይደረግ…ዘንድሮ ሁሉ ነገር ‘ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ’ ስለሆነ… አለ አይደል…ባልጨነቀን ነገር የተጨነቅን መምሰል የ‘አብሮ መኖር በዓለም ዙሪያ’ ምናምን ህግ ስለሆነ… እናንተም የሚጠበቅባችሁን ገጸ ባህሪይ ትጫወታላችሁ፡፡)
“ምን መሰለህ…አንድ ጉዳይ ገጠመኝና...” (ሌላ ደግሞ ምን አለ መሰላችሁ… “ምን መሰለህ...” ብለን ነገር የምንጀምር ሰዎች… አለ አይደል… ‘ሰስፔንስ’ ምናምን ለመፍጠር የምናደርገው ሙከራ…በራሱ ለ‘ስታንድአፕ ኮሜዲ’ አንድ አርባና ሀምሳ ርዕስ ባይወጣው ነው! ከእንግዲህ የሚመጣ ‘ሰስፔንስ’ ከ‘ጥቁር ፍቅር’ ካልበለጠ ፉርሽ ነዋ!...ቂ…ቂ…ቂ…)
“ምን መሰለህ አንድ እቁብ ነበረኝ፡፡ እጣ ገና አልደረሰኝም…አሁን ደግሞ ገንዘብ በጣም የሚያስፈልገኝ ጉዳይ ገጠመኝ…”
ዝም ብላችሁ ትጠብቁታላችሁ፡፡
“ምን መሰለህ…እንደው እኮ ምናልባት ግፋ ቢል በሳምንት የምመልሰው አንድ ሠላሳ ሺህ ብር ልትሰጠኝ ብትችል ብዬ ነው…” (ከት ብላችሁ ከሳቃችሁ ትን ሊላችሁ ይችላል፡፡ ትን ካላችሁ ደግሞ በዛው ‘እልም’ ማለት ሊመጣ ይችላል። ሠላሳ ሺህ! በሆዳችሁ “ሠላሳ ቦታ ይቁረጥህ” ማለት ስትችሉ ትተዉታላችሁ፡፡ ለዚህ አይነት ‘የዓመቱ ምርጥ ፌዝ’ ሠላሳ ትንሽ ነቻ! ቂ…ቂ…ቂ…)
እናማ…ድንገት ‘መጽሐፍ ሲያነብ ትዝ ላላችሁት’ ረጅም ጊዜ የጠፋ ወዳጃችሁ… ‘ሳይጠበቅ ደውሎ’… አለ አይደል… “ለምን ምሳ አብረን አንበላም…” ሲላችሁ… “ብድር የማትጠይቀኝ ከሆነ እሺ…” ካላችሁት በምድሩም፣ በሰማዩም አያስጠይቅም፡፡ ልክ ነዋ…‘ተረዳዱ’ ተባለ እንጂ፣ በምሳ ተሳቦ… ‘ተሸወዱ’ አልተባለም!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 6923 times