Saturday, 31 December 2016 11:31

አስገራሚ እውነታዎች!!!

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 (ከዝነኞች ህይወት)
ዝነኛው የፊልም ተዋናይ ጃኪ ቻን፤ በ1954 (እ.ኤ.አ) ከድሃ ጥንዶች ነው የተወለደው፡፡ ወላጆቹ ያጡ የነጡ ድሃ ስለነበሩ ለሆስፒታል የሚከፍሉት ገንዘብ አጥተው ልጃቸውን (ጃኪ ቻንን) ለመሸጥ ሁሉ ዳድተው ነበር፡፡ በመጨረሻ ግን ተግተው ሰሩና ለሆስፒታሉ ክፍያ በቂ  ገንዘብ አገኙ፡፡ ዛሬ ጃኪ ቻን የሆሊውድ ተከፋይ ነው፡፡  
ታዋቂው አሜሪካዊ ኮሜዲያን ጂም ኬሪ፤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን አቋርጦ የወጣው በ16 ዓመቱ ነበር፡፡ ለምን? ትኩረቱን ኮሜዲ ላይ አድርጎ ለመሥራት፡፡  
“Rocky” የተሰኘውን የፊልም ስክሪፕት የጻፈው ዝነኛው ተዋናይ ሲልቪስተር ስታሎን ነበር- ራሱ። ነገር ግን ስክሪፕቱን ሲጽፍ የሚኖርበት ቤት እንኳን አልነበረውም፡፡ ስክሪፕቱን ከመሸጡ ከአንድ ሳምንት በፊት በጣም ተቸግሮ ውሻውን በ50 ዶላር ሸጧት ነበር፡፡ በኋላ ግን መልሶ ገዛት - በ3ሺ ዶላር!! ገንዘብ ከየት ፈሰሰለት? ከስክሪፕት ሽያጩ ነዋ!!
የፊልም ተዋናዩ ሳን ዊሊያም ስኮት፤ ሴቶች ሲያፍርና ሲሽኮረመም አይጣል ነበር፡፡ እንስቶች በአካባቢው ካሉ በጭንቀት ላብ በላብ ይሆናል። በዚህም የተነሳ 30 ዓመት እስኪሞላው ድረስ የሴት ጓደኛ ወይም ፍቅረኛ አልነበረውም፡፡
የፊልም ተዋናዩ ጃክ ኒኮልሰን፤ ዓይናፋርነት አይነካካውም፡፡ ከልጅነቱ ጀምሮ ያሳደጉት  አያቶቹ ነበሩ፡፡ እሱ ግን እውነተኛ ወላጆቹ እንደሆኑ ነበር የሚያውቀው፡፡ እ.ኤ.አ በ1973 ዓ.ም ከ”ታይም” መፅሄት ጋዜጠኛ የሰማው መረጃ ዱብዕዳ ነው የሆነበት፡፡  “እህቱ” እንደነበረች የሚያውቃት ጁን፤ እውነተኛ እናቱ ሆና ተገኘች። በ37 ዓመት ዕድሜው!! ክፋቱ ደግሞ ይሄን እውነት ከመስማቱ በፊት እናቱም ሴት አያቱም ሞተዋል፡፡  
ጄምስ ቦንድን ሆኖ የሚተውነው የፊልም ባለሙያው ዳንኤል ክሬይግ፤ በትወናው ከፍተኛ ዝናና ተወዳጅነት፣ እንዲሁም በሽበሽ ገንዘብ አግኝቷል፡፡ ይሄ ብቻ ግን አይደለም፡፡ በፊልሙ ላይ ሲተውን የሚያሽከረክራትን Aston Martin የተሰኘች አውቶሞቢል የሚያመርተው ፋብሪካ፤ የህይወት ዘመን ስጦታ (መብት) አሽሮታል፡፡ በማንኛውም ጊዜ ደስ ያለውን መኪና (አስቶን ማርቲን ጨምሮ) አስነስቶ መፈትለክ ነው - በቀሪው ህይወቱ ሁሉ፡፡
“ሚስተር ቢን”ን ሆኖ የሚተውነው እንግሊዛዊው ኮሜዲያን ሮዋን አትኪንሰን፤ እንደ አሜሪካዊው ኮሜዲያን ጂም ኬሪ በ16 ዓመቱ ትምህርት አላቋረጠም፡፡ እንደውም ወደ ትወና የገባው በኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ የማስተርስ ዲግሪውን ከተቀበለ በኋላ ነው-  ከእንግሊዙ ኒውካስትል ዩኒቨርሲቲ፡፡  

Read 2503 times