Print this page
Saturday, 31 December 2016 11:24

ያልተላከ ደብዳቤ

Written by  አሰፋ ጫቦ Dallas Texas USA
Rate this item
(1 Vote)

 ግልጽ ደብዳቤ
ዛሬ ኢትዮጵያን በማስተዳደር ላይ ለሚገኙ ባለሥልጣናት በሙሉ
ኢትዮጵያ
መነሻችን
ይህ የፖለቲካ ደብዳቤ አይደለም! የዚህ ግልጽ ደብዳቤ ምክንያቱም፤ ዓላማውም አንድና አንድ ብቻ ነው። ”ኢትዮጵያን፣ የጋራ ቤታችንን”፣ ካጠለለባት የውድቀት ጽልመት እንዴትና በምን ዘዴ ልናድናት እንችላለን?” ብሎ ለመመካከር ብቻ ነው። ዛሬ የኢትዮጵያ ዋና ፖለቲካ፤ “አገር ማዳን!” ነው ብለን በጥብቅ እናምናለን። ፖለቲካው፤ በኛ አስተያየት፤ “እዬዬ ሲዳላ ነው!” እንደሚባለው ነው። ኢትዮጵያን ከደረሰችበት ቋፍ ከመለስናት በኋላ እንደርስበታለን። አጉል አባባል ሆነና ነው እንጂ ዝንጀሮ፤ “መጀመሪያ የመቀመጫዬን!” ብላለች- እንደሚባለው መሆኑ ነው። መላው ሰውነቷ እሾህ ተሰግስጎባት  ነው። ከዚህ ሌላ ግብ እንደሌለን ልናረጋግጥላችህ እንወዳለን!!
ምክንያታችን
እንደምታውቁት፤ መላው ዓለምም እንደሚያየውና እንደሚያውቀው፤ ኢትዮጵያ፤ ”የጋራ ቤታችን”፣ በተለይም ላለፈው አንድ ዓመት ምጥ ላይ ነች። የምጡ፣ የጭንቁ ሁኔታ ከቀን ወደ ቀን እየባሰ መሔድ ብቻ ሳይሆን የብዙኃን ወገኖቻችን፣ የሕጻናነት ሳይቀር መጥፊያ ሆነ። ከዛሬ ነገ ይቆማል የሚል አይነት ተስፋ እንዳናደርግም የመፍትሔ ጮራ፣ ጭላንጭሉ እንኳን አድማስ ላይ ቀርቶ፣ ከአድማስ ባሻገርም አልታይ አለን። ይህ ጨልሞ መታየት ነው፣ ይህንን ደብዳቤ እንድንጽፍላችሁ የገፋፋን። ሰው የመሆንና የዜግነት ግዴታ ነው!
ከኛ የተሻለ እንደሚያውቁት፣ ይህ ችግር እያደገ እየባሰበት የመጣ እንጅ ድንገት ከሰማይ ዱብ ያለ አይደለም። ስሙ በግልጥ እንደሚያውጀው፣ ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊት ሬፑብሊክ ነች። ይህ ማለት ዲሞክራሲ ያለባት አገር ማለት ነው። ሕገ-መንግሥቱም ይህንኑን ያረጋግጣል። ዲሞክራሲ ማለት ደግሞ የተለያየና የተለየ ሀሳብና ዕምነት ያላቸው፣” ለአገር ይህ ይበጃል” የሚሉ፤ በግልም፤ የፖለቲካ ድርጅት መስርተውም ተወዳድረው ይሸነፋሉ ወይም ያሸንፋሉ ማለት ነው። ጋዜጦችም ኖረው፣ በነጻ የሚሰማቸውን ይጽፋሉ ማለት ነው። ይህ ማለት ደግሞ በአጭሩ ለኢትዮጵያ የሚበጃትን አንድ ብቸኛ ዕውነት፣ ለብቻው በሞኖፖል የያዘ ወይም የተሰጠው ግለሰብም ሆነ ድርጅት የለም ማለት ነው።
ከዚህ መሠረታዊ የዲሞክራሲ፣ ትርጉም የማይስማማ ሁሉ፣ ዲሞክራሲ በዋለችበት አምባ ዝርም አላለም እንደማለት ይሆናል። ተቃዋሚ የሚባሉ ድርጅቶችና መሪዎቻቸው “ተሸንፋችኋል” መባል ብቻ ሳይሆን፣ መሳተፋቸው ወንጀል ሆኖባቸው ወህኒ ወረዱ። የጋዜጠኞቻችን እጣ ፋንታ ይኸው ሆነ። መተንፈሻ መላዋሻ አጣን የሚሉ፣ ጠበንጃ ወደ ማንሳት አመሩ። ይህ ለማንኛችንም አይበጅም። አለመበጀት ብቻ ሳይሆን ጉዳቱን መመጠን እንኳን አይቻልም!
እንደሚታወቀው ላለፈው አንድ አመት፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከአጽናፍ እስከ አጽናፍ አመፀ። ባለፈው አንድ አመት ማለታችን፣ በኦሮሞዎች ተጀምሮ መላውን የአማራ ብሔረሰብ የጨመረውን ለመጥቀስ ነው:: እንጅ በተለያየ ደረጃና መጠን አመፁ ላለፈው 25 አመት ተግና ጋብ ያለበት ጊዜ አልነበረም። መንግስትም ባለፈው 25 አመታት ያገኘው ብቸኛ መፍትሔ ቢኖር ኃይል ብቻ ነው። ይህ ደግሞ መፍትሔ አለመሆኑን መንግስትም የሚረዳው ይመስለናል። ያም ካልሆነ ደግሞ አልበርት አንስታትይን ብሏል ወደተባለው ይወስደናል። “እብደት ማለት ያንኑ አንድ ዘዴ፣  ሺ ጊዜ መደጋገምና ግን ከዚያ ለየት ያለ ውጤት አገኛለሁ ብሎ መጠበቅ ነው!” ብሏል (Insanity: Doing the same thing over and over again and expecting different results) ይህ ልናጤነው የሚገባ መሠረታዊ ነጥብ ነው። እዚያ አልደረስንም! መድረስም የለብንም ብለን በፅኑ እናምናለን!
ተፈላጊው ነጥብ
በዚህ የጭንቅ ሰዓት ከእኛ የሚፈለገው” ቀና አስተሳሰብ! ፤ መልካም ፈቃድና የአገር ፍቅር ” ብቻ ነው። እነዚህ ካሉ፤ ዛሬ ዓለማችን በደረሰበት ደረጃ ግጭትን ከግለሰብ ጀምሮ፤ በቤተሰብ፤ በመንደር፤ በመንግስትና ተቃዋሚ፤ በመንግስትና በሕዝብ፤ ብሎም በመንግስታት መካከል ለሚነሱ ችግሮች መፍትሔ ሰጭዎች (Conflict Resolution) ብዙ ግለሰቦች፣ ደርጅቶችና መንግስታት እንዲሁም ባለሙያዎች ሞልተው ተርፈዋል። አገልግሎታችውን ለመስጠትም ፈቃደኞች ናቸው። እንዳልነው ዋናው ነገር፣ የሚጠበቅብን ቀና አስተሳሰብ፤ መልካም ፈቃድና የአገር ፍቅር ብቻ ነው። የማፈላለግ ጉዳይ እንጅ እነዚህን ትምህርትም፤የስራ ልምድም ተፈጥሮም ጭምር ለግሶናል!!
የመፍትሔው ችግር ምንጭ
የመንግስትንም ችግር የምንረዳ ይመስለናል። እንደምታውቁት፣ በዛሬዉ ዘመን የመንግስት ሚስጥር የሚባል ነገር የለም። በተለይም ይህ መንግሥት ምስጢር የለውም። ሁለንተናው የተሠራው በአደባባይ ነው! በዚህ ላይ መንግስት ከምስረታው ጀምሮ ለተወሰነ ግብ በ”ይድረስ ይደርስ!” የተመሰረተ ስለነበር በውስጡ እኩልነትና አንድ አካል አንድ አምሳል የመሆን ነገር አልነበረውም። ፈታኝ  ቀን ሲመጣ የተፍረከረከ ይመስለናል:: ከዚህ የተነሳ ጭምር ይመስለናል፣ መንግስት ”በአንድ አፍ” አይናገርም። ይህም የበለጠ የሚያባብስ ከመሆኑም ሌላ መፍትሔውን ያዘገየዋል። ዘገየ አልዘገየ እንደሚታየው፣ አዝማሚያው መፍትሔ በግድም፣በውድ ወደ ማምጣት ያዘነበለ ነው!
ሌላው፣ የመንግስትን መሰረታዊ ፍርሐትም የምንረዳ ይመስለናል። ፍርሐቱ “ነገን መፍራት!” ይመስለናል። ”ነገ” ደግሞ ፈሩም አልፈሩም መምጣቱ አይቀርም!። “ከአዳኙ ለመሰወር አንገቷን አሸዋ ውስጥ ቀበረች!” እንደሚባለው፣ የሰጎን ተረት አይነት መሆኑይመስለናል። አንገቷን ትቅበር እንጅ ይህ የአዳኙን ፍጥነት ሆነ ፍላጎት የሚገታው አይደለም። “እንቅልፍ ተፈርቶ ሳይተኛ አይታደርም!” ይባላል፡፡  
የበለጠ መዘባበቻ እንዳንሆን
በድርቅና በድህነት ተመጽዋችነታችን የ መላው ዓለም መዘባበቻ ሆነን ኖርን። በፖለቲካ አለመረጋጋት መናወጥ ከጀመርን ይሔው ወደ 50 አመት እየተጠጋን ነው።
ኢትዮጵያ ታሪካዊ አገር ነች። ዛሬ በዓለም ላይ በዲፕሎማቲክ መልእክተኞች ብዛት፣ ከኒዮርክና ከዥነብ ለጥቆ ሶስተኛው አገር ኢትዮጵያ ነች። የ አፍሪቃ አንድነትና የተባበሩት መንግስታት የአፍሪቃ ኤኮኖሚ ዋና መስሪያ ቤት የሚገኘው አዲስ አበባ ነው። ያለምክንያት አልነበረም። ኢትዮጵያ ስለሆነች ነው። ይህ ሁሉ መንግስታት እያዩን እየታዘቡን ነው።
የውስጥ ችግራቸውን በጨዋ ደንብ ተነጋግረው መፍታት ያልቻሉ የት እንደደረሱ የምናውቀው ነው። ዩጎዝላቢያ ይባል የነበረው አገር ብጥቅጥቁ ወቷል። ሶማሌን እዚህ ጓሯችን የምናየው ነው። ሶሪያ በፍጥነት ወደዚያ እያመራች ነው። ይህ ሁሉ የሚሆነው፣ ቁጭ ብሎ ለመነጋገር ባለመቻል ነው። “አንተም ተው! አንቺም ተይ!” የሚል መጥፋትና ማጣት ነው። ሰሚም ማጣት ነው! የጋራ ቤታችን ይህ ዕጣ ፋንታው እንዲሆን አንፈልግም። የዚህ ደብዳቤ ዋና አላማ፤ “አንተም ተው! አንችም ተይ!” ብሎ መነጋገር/ማነጋገር ለመፍጠር ነው።
መፍትሔው
መፍትሔው ክብ ጠረጴዛ ብቻ ነው ! እንዳልነው ለተለያየ አይነት ወዝግብ መፍትሔ መፈለግ (Conflict Resolution) አዲስና ዛሬ እኛ ሀ ብለን የምንፈጥረው አይደለም። የታውቁ፤ የተመሰከረላቸው የተረጋጋጡ መንገዶችና ዘዴዎች አሉ። ክቡ ጠረጴዛ የት ነው የሚዘረጋው? ልን ነጋገርበት እንችላለን! ክቡ ጠረጴዛ ዙሪያ ማንና እነማን ይቀመጣሉ? ያንንም ልንወያይበት እንችላለን! መቼ? የሚለው ግን አጣዳፊ ነው። ከላይ እንደገለጽነው ዋናው ነገር በጎ ፈቃድ ማሳየት ብቻ ነው። ያ ካልሆነ “ሳይሞከር የቀረው አማራጭ!” ጸጸት ሆኖ፣ እስከወዲያኛው፣ ከኛም ከታሪካችንም ጋር ተመዝግቦ አብሮን ይኖራል!!
ይህንን ማመቻቸት እንድንችል፣ በሩን እንድትከፍቱ፤ “በጋራ ቤታችን!” በኢትዮጵያ ስም በብርቱ እንጠይቃለን!
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር !!!

Read 2291 times