Saturday, 31 December 2016 11:34

የመንግስት የውጭ እዳ፣ ከ 2 ቢ.ዶላር ወደ 22 ቢ.ዶላር (በአስር ዓመት)

Written by  ዮሃንስ ሰ.
Rate this item
(4 votes)

• አምና የውጭ እዳ ለመመለስ፣ 1 ቢሊዮን ዶላር ተከፍሏል።
            • የወለድ ክፍያው፣ በአመት 350 ሚሊዮን ዶላር ሆኗል።
            • አዎ፣ ብድሩ፣ ለትምህርት፣ ‘ለመሰረተ ልማት’ የሚውል ነው።
            • ግን፣ ጨርሶ አንድ ቃል ማንበብ የማይችሉ ተማሪዎች በዝተዋል።
                         
       ይሄ ነገር፣ እንዴት ቢገለፅ ይሻላል? የእዳውና የወለዱ ሸክምኮ፣ “በደብል ዲጂት” ሽቅብ እየመጠቀ ነው። ሸክሙ፣ ምንኛ ከባድ እንደሆነ፣ በውል ለመገንዘብና በደንብ ለመግባባት፣ ሁነኛ ዘዴ ያስፈልገናል። በምስል እያየን ለማገናዘብ እንሞክር? ወይስ በፅሁፍ... በቃላት ቢገለፅ ይሻላል?
“በምስል ወይስ በቃላት” እያልን የምናማርጠው፣ ለመቀናጣት እንዳልሆነ ይገባችኋል። እንዲያውም፣ ከጭንቀት የመነጨ ይመስላል። በእርግጥም፣ ጉዳዩ፣ የሚያሳስብ ወይም የሚያስጨንቅ ስለሆነ፣ አስተማማኝ የመግባቢያ ዘዴ ለመምረጥ ብንሞክር አይገርምም።
ይሄንን፣ እንደ ቀላል ነገር አትቁጠሩት። ስለ እዳውና ስለ ወለዱ አይደለም የማወራው። በምስል እና በቃላት አማካኝነት... መረጃዎችን የማገናዘብና የመግባባት ችሎታ፣ ቀላል ብቃት አይደለም። በየእለቱ ፅሁፍ እናነባለን - መልእክቱም ይገባናል። ‘ግራፍ’ አይተን፣ የትኛው እንደቀነሰና እንደጨመረ ወይም የትኛው እንደበለጠና ስንት እንደደረሰ እንገነዘባለን።
በአግባቡ እስከተገለፀ ድረስ፣ በፅሁፍና በመስል መግባባት፣ ብዙም አያስቸግረንም። ለሰላምታ የመነጋገር ያህል ነው። ወይም ደግሞ፣ በሁለት እግር የመራመድ ያህል፣... ገና ስንወለድ፣ አብሮን የተፈጠረ “ነባር ችሎታ” ይመስለናል። ግን አይደለም። ለነገሩማ፣ መራመድም፣ “ነባር ችሎታ” አይደለም። በፅሁፍና ‘በግራፍ’ መግባባትማ... በብዙ ቢሊዮን ዶላርም፣ ተፈልጎ የማይገኝ እየሆነብን ነው። እንዴት? ማንበብና ማባዛት የማይችሉ ተማሪዎች ተበራክተዋል። እና፣ እንዴት ነው፣ “ተማሪዎች” ብለን ልንጠራቸው የምንደፍረው? በየእለቱ፣ ክፍል ውስጥ የምንሰጣቸው ነገርስ፣ እንዴት “ትምህርት” ተብሎ ይጠራል? ማናናቄ አይደለም። ብዙ ገንዘብ የፈሰሰበት፣ ብዙዎች የደከሙበት ጉዳይ እንደሆነ እየካድኩ አይደለም።
ከመንግስት በጀት ውስጥኮ፣ ሩቡ ያህል፣ ለትምህርት ነው የሚመደበው። ‘የትምህርት ጥራትን እናሻሽላለን’ ብለው፣ በብድርና በእርዳታ፣ ላይ-ታች የተሯሯጡ የውጭ መንግስታትና አለማቀፍ ተቋማትም ብዙ ናቸው (አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ጃፓን... የአለም ባንክ፣ ዩኔስኮ፣ ዩኒሴፍ፣ ሴቭ ዘ ቺልድረን... በጣም ብዙ ናቸው)። ለዚያውም፣ ለብዙ ዓመታት ነው የተሯሯጡት - ለአስርና ከዚያ በላይ ዓመታት።
ግን፣... ዛሬም ድረስ፣ የትምህርት ጥራት፣... ገና ‘ጠብ’ አላለም። ይሄ፣ “በይመስለኛል” የተነገረ መርዶ አይደለም። የቆዩና ያረጁ መረጃዎችን ብቻ በመያዝ የተነገረ ድምዳሜም አይደለም።    
ከአዳዲስና ሰፋፊ ጥናቶች የተገኘ መረጃ ነው።
በትምህርት ሚኒስቴር ፈቃድና በዩኒሴፍ መሪነት፣ በአለማቀፍ የምርምር ተቋማት አማካኝት፣ በ297 ትምህርት ቤቶች የተካሄደውን ጥናት መጥቀስ ይቻላል። ቀለል ተደርጎ የተሰራ ‘ግራፍ’፣ ለአብዛኞቹ ተማሪዎች፣ ትልቅ ‘እንቆቅልሽ’ እንደሚሆንባቸው ሪፖርቱ ይገልፃል።
ለምሳሌ፣ “የወለድ ክፍያን ለማሳየት የተዘጋጀውን ግራፍ ተመልከቱ። በ2007 ዓም፣ የኢትዮጵያ መንግስት፣ ስንት ሚሊዮን ዶላር የብድር ወለድ እንደከፈለ ግለፁ” የሚል ጥያቄ፣ በእጅጉ ይከብዳቸዋል - ለአራተኛ ክፍል ተማሪዎች።
“255 ነዋ። ማለትም 255 ሚሊዮን ዶላር” ብለው በቀላሉ መመለስ አይችሉም። ከዚህ የቀለለ ጥያቄ ቀርቦላቸው፣ በትክክል መመለስ የቻሉ የአራተኛ ክፍል ተማሪዎች፣ 23% ብቻ ናቸው። ከመቶ ተማሪዎች መካከል፣ 23ቱ ብቻ።
“ይሄማ መራቀቅ ነው” ልትሉ ትችላላችሁ። ፈፅሞ አይደለም። ግን ይሁን። የማንበብ ችሎታም እንደሰማይ ሩቅ እየሆነ ነው።
በእንግሊዝ መንግስት እርዳታ ተጀምሮ፣ የኔዘርላንድና የአየርላንድ መንግስታትም ድጋፍ ተጨምሮበት፣ ለአስር ዓመታት በስፋት የተካሄው ‘ያንግ ላይቭዝ’ ጥናት፣ አዳዲስ መረጃዎችን ይዞ መጥቷል። አዲሱ መረጃ፣ የ12 ዓመት ልጆች ላይ ያተኮረ ነው። ልጆቹ... ግማሽ ያህሉ፣ 6ኛ ክፍል ደርሰዋል። ሌሎቹ ደግሞ፣ በአብዛኛው ከ3ኛ እስከ 5ኛ ክፍል ላይ ናቸው።
ጥሩ። ግን፣ የማንበብ ችሎታቸው እንዴት ነው?
ከመቶ ልጆች መካከል 35ቱ፣ አንዲት ዓረፍተነገር እንኳ ማንበብ አይችሉም (በየትኛውም ቋንቋ)።
የሂሳብ ችሎታቸውስ? ለምሳሌ የማባዛት ችሎታቸው እንዴት ነው? ለልጆቹ የቀረበላቸው የማባዛት ጥያቄ ቀላል ነው። 2 x 4 ስንት ይሆናል?
ከመቶ ተማሪዎች መካከል፣ 30ዎቹ ጥያቄውን በትክክል መመለስ አልቻሉም። አትርሱ። የ12 ዓመት ልጆች ናቸው። አብዛኞቹም፣ ከሦስተኛ እስከ ስድስተኛ ክፍል የደረሱ። ግን፣ ሲሶዎቹ፣ ገና... ማባዛት አይችሉም።
ሌላ አዲስ ጥናትም አለ - በአሜሪካ መንግስት እርዳታ አምና የተካሄደ ጥናት። የሦስተኛ ክፍል ተማሪዎችን ተመልከቱ።
ከመቶ ተማሪዎች መካከል 20ዎቹ፣ ፈፅሞ አንዲትንም ቃል ማንበብ አይችሉም።
ከመቶ ተማሪዎች መካከል፣ ዓረፍተነገር አንብበው መረዳት የሚችሉት ከሃያ ያንሳሉ። 80 ከመቶ ተማሪዎች፣ አንብበው መረዳት አይችሉም።
ይሄ ትልቅ ችግር ነው - ከእዳና ከወለድ ሸክም በእጅጉ የሚበልጥ፣ የሚያሳስብና የሚያስጨንቅ ችግር!
ግን፣ ከዚህም የባሰ ችግር አለ።
የፖለቲካ ቁማር ይበልጥብናል
አብዛኞቹ የሦስተኛ ክፍል ተማሪዎች፣ አንዲት ዓረፍተነገር አንብበው መረዳት እንደማይችሉ አየን። 2 ሲባዛ በ4 ስንት እንደሚሆን ማስላት የማይችሉ ተማሪዎችን ተመለከትንም። እንዲህ አይነት አሳሳቢ ችግር የተጋረጠበት ሰው፣ ምን ማድረግ አለበት?
ለጤናማ አስተሳሰብ፣ ክብር ያለው ሰው፣... ከምር ጉዳዩ አሳስቦት፣ “የዚህ ችግር መንስኤ ምንድነው? ከምን ጋር የተያያዘ ነው? ጊዜያዊና ዘላቂ መፍትሄዎቹስ ምንድናቸው?” ብሎ ይመረምራል።
አብዛኞቻችን ግን፣ ያን ያህልም፣ ከምር አያሳስበንም። “የችግሩ መንስኤና መፍትሄ”... ምናምን... ብሎ ማሰብ፣ ሞኝነት የመስለናል። ያው፣ እንደተለመደው፣ ከሁሉም በፊት፣ “የፖለቲካ ጨዋታ” ይቀድምብናል - ጎራ ለይተን ‘ቲፎዞ’ ለመሆን። በቃ፣ ‘ጌም’ ነው።
አንዳንዶቹ፣ የገዢው ፓርቲ ጭፍን ደጋፊ በመሆን፣ ትምህርት ምንኛ እጥፍ ድርብ እንደተስፋፋ፣ ትምህርት ቤቶች እንደተበራከቱ፣ ‘የሚሊዬኔም ግቦች’ እንደተሳኩ... እለት በእለት በመዘርዘር፣ ነገሩን ዋና የፖለቲካ መቆራቆሻ ያደርጉታል።
ገሚሶቹም፣ በጭፍን ተቃዋሚነት፣ መንግስትን ለማብጠልጠል፣ ትልቅ አዳፍኔ መሳሪያ አገኘን ብለው፣ የውግዘት ውርጅብኝ ለማዝነብ ይሽቀዳደማሉ። እንዲያውም፣ ሁሉም ተማሪ፣ ማንበብና መደመር የማይችልበት ጨለማ እንዲፈጠር እስከመመኘትም ይደርሳሉ - መንግስትን ይበልጥ ለማውገዝ።
ታዲያ ከሁሉም የከፋው ችግር፣ እንዲህ አይነት የጭፍንነት ችግር አይደለም ትላላችሁ?
እና ምን ተሻለ?
ከጭፍን የድጋፍና የተቃውሞ ስካር ተገላግለን፣ የችግሮቻችንን መንስኤዎች ለማጥናትና መፍትሄ ለመፈለግ፣ በጊዜ ብንጣጣር ይሻላል።
አለበለዚያኮ፣ ጉዟችን ወደ ጨለማ ነው የሚሆነው። አንብቦ መረዳትና የሂሳብ ስሌት የማይችሉ የሦስተኛና የአራተኛ ክፍል ተማሪዎች እየተበራከቱ እያየን፣ ለፖለቲካ ጨዋታ መሽቀዳደም ሞኝነት ነው።
በበኩሌ፣ ስለመንስኤውና ስለመፍትሄው፣ ለመወያያ የሚሆኑ መረጃዎችንና የቁምነገር ሃሳቦችን ይዤ እመጣለሁ።
ለዛሬ ግን፣
በአንድ በኩል፣ በፅሁፍና በምስል፣ በቃላትና በ’ግራፍ’፣ መረጃዎችን የመግለፅና የማገናዘብ ችሎታን ቀለል አድርገን እንዳናይ ለማስታወስ በመመኘት፣...
በሌላ በኩል ደግሞ፣ የውጭ እዳና ወለድ፣ ራሱን የቻለ ትልቅ ችግር እንደሆነ እንድንገነዘብና መፍትሄ እንድናበጅለት አስቤ፣ በምስል ያዘጋጀኋቸውን መረጃዎች ተመልከቱልኝ።
መረጃዎቹ፣ ባለፈው ሳምንት በገንዘብ ሚኒስቴር ከተሰራጨው የብድር መረጃዎች ሪፖርት በመነሳት ያሰባሰብኳቸው ናቸው - የበርካታ አመታት ሪፖርቶችን በማሰስ።
መቼም፣ በምስል አጠናቅሬ ያቀረብኳቸውን መረጃዎች፣ በፅሁፍ አልደግምባችሁም። ግን... አንድ ሁለቱን ብቻ ልድገማቸው።   
እዳ ለመክፈል የሚውለው የውጭ ምንዛሬ፣ በሦስት ዓመት ልዩነት በእጥፍ ጨምሮ፣ 1 ቢሊዮን ዶላር መድረሱና ከዚያም ማለፉ፣ ለአገሪቱ ትልቅ ፈተና ነው። በተለይ ደግሞ፣ የኤክስፖርት ንግድ እያደገ አለመሆኑ፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ያባብሳል።
በእርግጥ፣ እስካሁን፣ ከፍተኛ ቀውስ አልተፈጠረም - በሁለት ምክንያቶች።
አንደኛ፣ በዓለም ገበያ የነዳጅ ዋጋ ባለፉት ሁለት ዓመታት ቀንሷል። በዚህም ምክንያት፣ ለነዳጅ ግዢ የሚውለው የውጭ ምንዛሬ በግማሽ ቀንሷል። 1.2 ቢሊዮን ዶላር ዳነ ማለት ነው። ለዚያምኮ፣ ተገዝቶ የሚመጣው ነዳጅ አልቀነሰም። እንዲያውም ጨምሯል። ከ2005 ዓ.ም ጋር ሲነፃፀር፣ አምና ተገዝቶ የመጣው የነዳጅ መጠን በእጥፍ ይበልጣል። በዋጋ ግን ያንሳል። ይህም፣ በውጭ ምንዛሬ እጥረት ሳቢያ፣ ክፉኛ ከመቃወስ እንድንተርፍ አግዞናል - እስካሁን።
ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ቀውስ እንዳይፈጠር የረዳን ሁለተኛ ነገር፣ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ለቤተሰብ የሚልኩት ዶላር መጨመሩ ነው። ከ2003 ወዲህ በእጥፍ ስለጨመረ፣ አምና ወደ አራት ቢሊዮን ዶላር ተጠግቷል።

Read 3869 times