Saturday, 31 December 2016 11:43

ክብሪት አዟሪዋ ሕፃን!

Written by  በሐንስ ክርስቲያን አንደርሰን ትርጉም - ተፈራ ተክሉ
Rate this item
(0 votes)

    ቅዝቃዜው አጥንት ሰብሮ ይገባል፤ በረዶ እየጣለ፣ እንዲሁም እየመሸ ነበር፡ የዓመቱ የመጨረሻ ምሽት፡፡ በዚህ ቅዝቃዜና ምሽት ጎዳናው ላይ አንዲት ጭንቅላቷን ያልተከናነበችና በባዶ እግሯ የምትዘዋወር ምስኪን ትንሽ ልጅ ነበረች፡፡ እውነት ነው፡ ከቤት ነጠላ ጫማ አድርጋ ነበር የወጣችው፤ ነገር ግን ያ ምን ጥቅም አለው? እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ እናቷ ትለብሳቸው የነበሩና ለሷ እግሮች የማይሆኑ ሰፋፊ ጫማዎች ነበሩ፡፡ ምስኪኗ እነሱንም በጣም እየፈጠኑ ከነበሩ ሁለት ሰረገላዎች ለማምለጥ መንገድ ላይ ስትንደፋደፍ አጠፋቻቸው፡፡
አንዱ የገባበት ጠፋ፤ ሌላኛውን አንድ ዱርየ ልጅ ይዞት በረረ፤ እጅግ ጠቃሚ ነገር ያገኘ ያህል ነበር የተሰማው፡፡ ትንሿ ልጅም ከቅዝቃዜው ብዛት በተዥጎረጎሩት ትንንሽ ባዶ እግሮቿ መንገዷን ቀጠለች። ብዙውን ክብሪቷን ባረጀው ሽርጧ ውስጥ አድርጋ ቀሪውን በጭብጧ ይዛለች፡፡ ቀኑን ሙሉ ግን ማንም ከሷ ላይ ምንም አልገዛም፤ ሽርፍራፊ ሳንቲም እንኳን የሰጣት የለም፡፡
በብርድ እየተንቀጠቀጠችና በረኀብ ዛል ብላ ማዝገሟን ተያይዛዋለች… የሐዘን ምስሏ፣ ምስኪን ሕፃን!
እንደጥጥ የሳሱ በረዶዎች አየተጥመዘመዘ በአንገቷ የሚወርደውን ረዥም የሚያምር ጸጉሯን አልብሰውታል፡፡ ነገር ግን እሷ ይህንን በእርግጠኝነት አንዴም አላሰበችውም፡፡ ከእያንዳንዱ መስኮቶች ሻማዎች ያንጸባርቃሉ፣ የዝይ ሥጋ ጥብስ ሽታም አካባቢውን እያወደው ነበር፣ የአዲስ ዓመት ዋዜማ ነዋ፤ አዎ፡ ስለዚህ ግን እያሰበች ነበር፡፡ በሁለት ቤቶች ጥግ መካከል እጥፍጥፍ ብላ ቁጭ አለች፡፡ እግሮቿን እቅፍቅፍ አደረገቻቸው፡ ነገር ግን የበለጠ እየበረዳት ሄደ፡፡ ምንም ክብሪት ባለመሸጧና ሽርፍራፊ ሳንቲም ባለማምጣቷ አባቷ በጥፊ ስለሚያላጋትና የቤታቸውም ጣራና ግድግዳው የተሸነቆረና ትልልቆቹ ቀዳዳዎች በገለባና በእራፊ ጨርቅ ቢሸፈኑም፣ በዚያ የሚገባው የሚያፏጭ ንፋስ፣ የበለጠ ቀዝቃዛ ስለሚያደርገው ወደ ቤት ለመሄድም ድፍረት አጣች፡፡
ትንንሽ እጆቿ  በቅዝቃዜ ደንዝዘዋል፡፡ ኦ! ድፍረቱን አግኝታ በጭብጧ ከያዘቻቸው አንዷን ክብሪት ብትጭርና ጣቶቿን ብታሞቃቸው የአለምን ምቾት ይሰጣት ይሆናል፡፡ አንዷን መዘዝ አደረገቻት፡፡ “ሪሽ!” እንዴት እንደተንቀለቀለ፡ እንዴት እንደነደደ! የሚሞቅ፣ እንደ ሻማ ብሩህ የሆነ ነበልባል፡ በእጆቿ ሽፍንፍን አድርጋ የያዘችው ድንቅ ብርሀን፡፡ ለሕፃኗ ልጅ አንድ ትልቅ የሚያምር የብረት እሳት ማንደጃ (ስቶቭ) አጠገብ የተቀመጠች ያህል ሆኖ ነበር የተሰማት፡፡ ክብሪቷ እየነደደች ደስ የሚል ሙቀት ፈጠረችላት፡፡ ትንሿ ልጅ፤እግሮቿንም ለማሞቅ ዘረጋቻቸው፡፡ ነገር ግን ትንሿ ነበልባል ከሰመች፤ ስቶቩ ጠፋ፤ በእጇ ላይ የተቃጠለችው ክብሪት ቅሪት አካል ብቻ ቀረ፡፡
ሌላ ጫረች፡ ብሩህ ሆኖ ነደደ፡፡ ግድግዳው ላይ ሲያርፍም ግድግዳው እንደ ሥሥ ጨርቅ ወደ ውስጥ ክፍሎቹ ምን እየተደረገ እንደሆነ እስከሚያሳይ ድረስ ያንጸባርቅ ጀመረ፡፡ ጠረጴዛው ላይ እንደ በረዶ የነጣ የጠረጴዛ ልብስ ታያት፤ ከሸክላ የተሰራ ድንቅ ሰርቪስም ተቀምጦበታል፡ እሱ ላይም በአፕልና በፕሪም ቅመም ተለውሶ የተጠበሰው ዝይ ሽታ የአካባቢውን አየር አውዶታል፡፡ እነሆ ከዝዩ ደረት በቢላዋና በሹካ አማካኝነት የተገኘ ቁራጭ ሥጋ ወደ ሕፃኗ ሲመጣ፣ ለመዋጥ አፏን ከፈት ስታደርግ አብርታው የነበረው ክብሪት ብርሃን ጠፍቶ ከባዶ፣ ወፍራምና እርጥበት ያዘለ ግድግዳ ጋር ተፋጠጠች፡፡ ሌላ ክብሪት ለኮሰች፡፡ አሁን ደግሞ በአንድ እጅግ የተዋበ የገና ዛፍ ሥር ተቀምጣለች፡ በጣም ትልቅና በሀብታሙ ነጋዴ ሰው የመስታወት በር ውስጥ ካየችው ዛፍ በበለጠ ተጊጧል፡፡
በሺ የሚቆጠሩ መብራቶች በአረንጓዴው ቅርንጫፍ ላይ ይንቦገቦጋሉ፣ በሱቆቹ መስኮት ውስጥ የተመለከተቻቸው ዓይነት በደማቅ ቀለም ያሸበረቁ ሥዕሎችም ቁልቁል ይመለከቷታል፡፡ ትንሿ ልጅ፤ እጆቿን ወደ ሥዕሎቹ ዘረጋች፡ በዚያው ቅጽበትም… የክብሪቱ ብርሃን ጠፋ፡፡ የገናው ዛፍ ላይ መብራቶች ወደ ላይ ከፍ፡ ከፍ አሉ፣ እሷም አሁን ሰማይ ላይ እንዳሉት ኮከቦች ታያቸው ጀመር፤ አንዱ ወደቀና ረዥም የእሳት መስመር ሰራ፡፡
“የሆነ ሰው ሞተ!” አለች ትንሿ ልጅ፤ አሁን በሕይወት የሌሉትና ይወዷት የነበሩት ብቸኛ ሴት፣ ሽማግሌዋ አያቷ እንደነገሯት፤ ኮከቦች ሲወድቁ አንዲት ነፍስ ወደ ፈጣሪ ትሄዳለች፡፡  ሌላ ክብሪት ለኮሰች፡ እንደገና ብርሃን ሆነ። በነጸብራቁም ውስጥ ሽማግሌዋ አያቷ ፊት ለፊቷ ቆመዋል፡ ብሩህ፣ ፍልቅልቅ፣ ፍጹም እርጋታና ፍቅርን ያዘለ ገጽታ ተላብሰው፡፡
“አያቴ!” ትንሿ ልጅ ተጣራች፡፡ “ኦ፡ አንቺ ጋ ውሰጂኝ! ክብሪቱ ነዶ ሲያልቅ ትሄጃለሽ፤ ልክ እንደሚሞቀው ስቶቭ፣ ልክ እንደ ጣፋጩ የዝይ ጥብስ፣ ልክ እንደ አስገራሚው የገና ዛፍ በድንገት ትሰወሪያለሽ!” አያቷን በአቅራቢያዋ የማቆየቷን ነገር እርግጠኛ መሆን ስለፈለገች ወዲያው ሁሉንም በእጇ የያዘቻቸውን ክብሪቶች አንድ ላይ በፍጥነት ጫረቻቸው፡፡ ክብሪቶቹም ከቀትር የሚልቅ ድንቅ ብርሃን ሰጡ፡ አያቷ ከዚህ በፊት በፍጹም እንዲህ አምረውና ረዝመው አያውቁም፡፡ አያቷ ትንሿን ልጅ በእቅፋቸው ይዘው ሁለቱም በደማቅ ብርሃን ውስጥ በከፍተኛ ደስታ ተውጠው ከፍ፡ በጣም ከፍ ብለው በረሩ፡ ከዚያም ከላይ ብርድም፣ ረኀብም፣ ጭንቀትም አልነበረም… ሁለቱም ከፈጣሪ ጋር ነበሩ፡፡
ነገር ግን ጥግ ጋ፡ በቀዝቃዛው የንጋት ሰዓት፡ ምስኪኗ ልጅ ተቀምጣለች፣ ጉንጮቿ ወደ ሮዛማ ቀለም ተለውጠውና ፊቷ ፈገግታ ተላብሶ፣ ወደ ግድግዳው ዘመም እንዳለች፣… የአሮጌው ዓመት የመጨረሻ ምሽት በቅዝቃዜ ሕይወቷን ነጠቃት፡፡ በተቀመጠችበት ከነክሪቶቿ ድርቅ፡ ግግር ብላለች፤ የተቃጠሉ አንድ ጭብጥ ክብሪቶችም ነበሩ፡፡ “ራሷን ልታሞቅ ፈልጋ ነበር፡” አሉ የከበቧት ሰዎች፡፡ ስላየቻቸው ድንቃድንቅ ነገሮች ማንኛቸውም ቅንጣት ታክል ጥርጣሬ የላቸውም፤ ከአያቷ ጋር እንዴት ድምቅ ባለ መልኩ ወደ አዲሱ ዓመት ደስታ እንደተሻገረች፣ ማንኛቸውም ሊያልሙት እንኳን አይችሉም፡፡

Read 559 times