Print this page
Saturday, 31 December 2016 11:43

“ከኒያ ልጆች ጋር”

Written by  በግርማ ይ. ጌታኹን
Rate this item
(0 votes)

 (ደራሲ - ፋሲካ መለሰ፣ ኅትመት 2008 ዓ.ም፣
                አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ) ቋንቋ-ነክ ሒሳዊ ዳሳሳ
                                  
       መግቢያ
“ከኒያ ልጆች ጋር” በጣም የወደድኩት ሥራ ነው። መጽሐፉን በቅርቡ አግኝቼ አነበብኩት፡፡ ይዘቱ የኔ ብጤውን አእምሮ በቀላሉ ይቆጣጠራል። ቁም ነገርን በቀልድ እያዋዛ ይተርካል፡፡ ቋንቋው ቀላል ነው፤ የአንባቢን ትዕግስትና የመረዳት ችሎታ እማይወግጥ። ደራሲው ባለውለታችን ናቸው፤ አስደማሚ ታሪካቸውን እያቅማሙም ቢኾን (reluctantly) - እንድናውቅ ዕድል ሰጥተውናልና። ታሪካቸውን ሲያወጉን ደግሞ እንደ ማለፊያ ፈላስፋ ከስሜታዊነት ርቀው፣ ሐቅ-ተኮር ሆነው፣ በጥልቅ አስተውሎና በሚዛናዊነት ዐጅበው፣ በቀልድና ተረብ አዋዝተው ነውና ለነዚህ ፍሬ ነገሮች እና የወግ ቅመሞች የምሰጠው እኳቴ (appreciation) ከፍተኛ ነው።
“ከኒያ ልጆች ጋር”  ተወዳጅና ትልቅ ርባና ያለው ሥራ ኾኖ ባገኘውም፣በሥነ-ጽሑፍ ረገድ ደረጃውን ዝቅ የሚያደርጉ ሕጸጾች ሞልተውበታል። እጅግ ብዙ የከተባ ስሕተቶች (typos)፣ ሰዋሰዋዊ ግድፈቶች፣ የአገባብና አገላለጽ ችግሮች የጽሑፉን ጥበባዊ ውበት  ጐድተውታል።
መጠነኛ ሐተታ
በቃል ምልልሱ ላይ ትንሣኤ በኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ወጣቶች ሊግ (ኢሕአወሊ) ታሪክ ላይ መጽሐፍ እንዳልተጻፈ ይጠቁማሉ (ገ. 392)። የክፍሉ ታደሰና የሕይወት ተፈራ መጻሕፍት ስለ ወጣት ክንፉተጋድሎ ብዙ የሚሉት ቢኖርም የሊጉ ታሪክ - እንደ ኢሕአፓ እና ኢሕአሰ ታሪክ - ወጥ ኾኖ በዝርዝር አለመጻፉን መጥቀሳቸው ትክክለኛ አስተውሎ ነው። ለዚህ ያቀረቡት ዋነኛ ምክንያት ደርግ ለወሬ ነጋሪ ያህል እንኳ ሳያስተርፍ ከማእከላዊ ኮሚቴ እስከ ዞን ያሉ የሊጉን መሪዎች መጨፍጨፉ ነው። የሊጉ ግዙፍ መዋቅርና መጠነ-ሰፊ እንቅስቃሴ፣ ሰነዶችና ሌሎች መረጃዎችን ለታሪክ ያልተወ መኾኑ ሌላው መሠረታዊ ችግር ነው፡፡ (ከገ. 392-93) በዚህ የተነሣ እንደ ትንሣኤና ሕይወት ያሉ ጥቂት ሐያውያን (survivors) የሚተዉልን የግል ማስታወሻ ትልቅ እርባና አለው። እልፍ አእላፍ ወጣቶችን በትግል አሳትፎ ስለወደቀው ኢሕአወሊ፣የተሟላ ታሪክ መጻፍ ባይቻል እንኳ ስለ ጀግና አባላቱ ጽኑ እምነት፣ ስለሚንበለበል ሕዝባዊ ፍቅራቸው፣ በወኔና ባለመታከት ስላደረጉት ተጋድሎና ስለከፈሉት ከፍተኛ መሥዋዕትነት በቍንጽልም ቢኾን የሚያሳዩ
ትውስቶችን በጽሑፍ እና በዝግብ-ድምፅ መተው ታላቅ ዐደራን መወጣት ነው። ትንሣኤ ይህን ዐደራ በሚገባ ተወጥተዋል እላለኹ።
ከዚህ ጋር በተያያዘ መነሣት ያለባቸው ቁምነገሮች አሉ። አንደኛው የትንሣኤ ትርክት ከምሬትና ከጸያፍ
ቋንቋ የጸዳ መኾኑ ነው። ምንም ሰብአዊነት ለሌላቸው፣ በጥላቻና ጭካኔ ለተሞሉ የደርግ ሹማምንትና መርማሪዎች እንኳ የተጠቀሟቸው ቃላት ቁጥብ ናቸው (ገ. 229፣ 231፣ 314)። ስለ ሰዎቹ ሲናገሩ ጥላቻና በቀለኛነት አይንጸባረቅባቸውም፡፡ (ገ. 381)። ይልቁንም ለብዙዎቹ ንቀት-ዐዘል ሐዘኔታ (pity) እንደተሰማቸው መገመት ይቻላል፤ የአእምሮ እውከት (mental disorder) እና ጸላኤ-ማኅበረሰብ (sociopathy) የተጠናወታቸው ሊኾኑ እንደሚችሉ በመገመት ሊኾ ን ይችላል፤ ወይም ለፍቅርና ርኅራኄ ያልታደሉ መኾናቸውን በመታዘብ ይመስለኛል።
ሁለተኛው ቁም ነገር ትርክታቸው በጥልቅ አስተውሎዎች የጎለበተ መኾኑ ነው። የጠቢባንን ምክር ለግሰው በትሑት አንደበት የታሪካቸውን ውሱንነት ያስገነዝባሉ። አንባቢያን ይህን ዐቢይ ነጥብ እንዳይዘነጉ ያሳስባሉ።
የርሳቸው ታሪክ የ-ኢሕአፓ ወጣት ክንፍ ታሪክ እንዳልኾነ፣ እንኳንስ የሀገር-ዐቀፉ ድርጅት እርሳቸው የተሳተፉበት በመዲናዋ የነበረው የሊጉ ቅርንጫፍ ታሪክ እንኳ ሊባል እንደማይገባው በማያወላዳ ቋንቋ ይገልጻሉ።
“እናም፣ እስከ ዛሬ የነገርኩህ ታሪክ የአዲስ አበባ የወጣት ክንፉ ታሪክ ነው ብለህ ለጓደኞቻችን አውርተህ መሳቂያ እንዳታረገኝ።” ይላሉ ለቃል ተቀባይ ምናባዊ ጓደኛቸው። ታሪካቸው ከሞቱትና በሕይወት ካሉት ጓዶቻቸው ታሪክ ጋር ቢመሳሰልም የእንቅስቃሴያቸው አድማስ ከራሳቸው የአዲሳባ ዞን እምብዛ ያልዘለለ መኾኑን አለመሳታቸው ያስመሰግናቸዋል፤ በተለይም በልቦለድ ሽፋን፣ ውስጥ-ዐወቅ/ኹሉን-ዐወቅ ኾኖ፣ ኢሕአፓን ግልብ፣ ጐጠኛና ተራ የነፍሰ-ገዳዮች ጥርቅም አድርጎ ለማሳየት የሚሞክር መጽሐፍ ታትሞ በሚቸበቸብበት በዛሬው ጊዜ። አንድ የተማረ ወጣት ትውልድ በመምተር የፖለቲካ ወንጀል ፈጽመው ዛሬም “አበጀን” ለሚሉት የደርግ መሪዎችማ፣ የትንሣኤ ትሑትና ሐቀኛ ትርክት የሚሰጠው ትምህርት ብዙ ነው፤ ኮለኔሎቹ ለመማር ያልታደሉ ናቸው እንጂ።
ሌላው ጥልቅ አስተውሎ የዚያን ዘመን እውነት አፍረጥርጦ፣ ማኅበራዊ ዕርቅ የማድረግን አስፈላጊነት ያመለከቱበት ነው፡፡ (ገ. 380-83) ይህ አሁን ላለው የፖለቲካ ቀውስ እንደ መፍትሔ ከሚሰነዘረው “ብሔራዊ ዕርቅ” ጋር የተያያዘ አይደለም፤ ለርሱም ትልቅ እርባና ያለው አስተውሎ ቢኾንም። ደራሲው፤ በ“ቀይ ሽብር” የሆነው ሁሉ ሐቁ አደባባይ ወጥቶ፣ ዕርቅ አልተካሄደም ይሉናል። የዚያ የሽብር ዘመን ተዋንያን ሁሉ አደባባይ ወጥተው፣ የሠሩትን በሙሉ ያለ ፍርሀት በዜና ማሰራጫዎች አማካይነት ቢናገሩና ሕዝቡን ይቅርታ ቢጠይቁ፣ ለራሳቸውና ለተተኪው ትውልድ በጎ ይኾን እንደነበር ያምናሉ። እንዲህ ያለው ሂደት እውነቱን አደባባይ ከማውጣቱ ሌላ የዕርቅ መንፈስ በማኅበረሰቡ ያሠርጻል ይላሉ። ዳግመኛም አኩሪና አሳፋሪ ታሪኮቻችንን በሐቅ መጻፍ እንድንችል ልምድ ያስገኛል ባይ ናቸው፤ በሐቅ የተጻፈ ታሪክ ብቻ ለመጪው ትውልድ ጥሩ መማሪያ ስለሚኾን።
አቀራረብ ነክ ነጥቦች
ፋሲካ መለሰ፤ የሕይወት ትውስቶቻቸውን ለማቅረብ ጮሌ ሥነ-ጽሑፋዊ ብጅት (clever literary device) ተጠቅመዋል። በአማርኛ የግል ሕይወት ታሪክ አጻጻፍ ለተለመደው የአንደኛ ሰው ትረካ አማራጭ (alternative) የሚኾን ሌላ የአቀራረብ ዘዴን ይወክፋል (it offers) ። ባለ ገድሉ እና አዘጋጁ - ትንሣኤ እና ፋሲካ - ኹለት ግለሰቦች አይደሉም፤ ደራሲው እና ምናባዊ ጠያቂያቸው እንጂ። ለዚህ ደግሞ የስማቸው ፍቺያዊ አንድነት ፍንጭ ይሰጣል፤ ፋሲካ እና ትንሣኤ ተተካኪ የአንድ በዓል ስሞች (synonyms) ናቸውና።
ደራሲው በዋና ስማቸው እንደ ጠያቂ እና አዘጋጅ ቀርበው፣ በትንሣኤ መወክላቸው (alternate persona) ደግሞ ገድላቸውን ይተርካሉ። ግን ትንሣኤ የደራሲው ሌላውኔ (alter ego) አይደሉም፤ የፋሲካ ወቃሽ/ወጋጭ ኅሊና (conscience) እንዲሆኑ የታሰቡም አይመስለኝም።
የባለ ገድሉ ታሪክ በጥያቄ እና መልስ መልክ በመቅረቡ የደረሰ ጉዳት አይታየኝም። ቃል-ምልልሱ የታሪኩን ወጥነት አላበላሸውም። ለምሳሌ የታሪኩ ፍሰት አልተቆራረጠም፤ አንጓዎቹ አልተለያዩም። እንዲያውም ታሪኩ የጥያቄ ጭብጥ ላይ አትኳሪ በኾኑ ዕጥር-ምጥን የትርክት ጠገጎች (chain links) ተከፍሎና ተሰናስሎ እንዲቀርብ አስችሎታል። የቃል ምልልሱ ሌላ ጠቀሜታ “ጠያቂ” እና “መላሽ” ንግግራቸውን በቀልድና ተረብ እንዲያዋዙ ማመቸቱ ይመስለኛል። ምልልሱ ደረቅና ወግ-ጠበቅ (formal) አይደለም። ደራሲው ከጓደኞቻቸው ጋር “ሰዲ ሰዲ” በሚሉ ጊዜ የሚለዋወጧቸውን ተረብ፣ ቧልትና ፌዝ እዚህም በጨዋ አንደበት ስለሚጠቀሙባቸው ምልልሱ ወግ-ለቀቅ (informal) እና ማራኪ ነው።
ደራሲው ታሪካቸውን ከመጻፋቸው በፊት ያደረጉትን አእምሯዊ ሙግት - ለመጻፍ-ላለመጻፍ ያኼዱትን ውስጣዊ የሐሳብ ፍጭት - ለመግለጽም ይህ የትንሣኤ እና የፋሲካ ቃል-ምልልሳዊ የአተራረክ ዘዴ አመችቷል እላለኹ። ኾኖም የቃል ምልልሱ ጽሑፋዊ አቀማመጥ አመርቂ አይደለም። ብዙ ቦታዎች ላይ የባለ ገድሉ ትርክት እና የአዘጋጁ ጥያቄ/አስተያየት የጐላ ልዩነት አይታይባቸውም። (ለምሳሌ በሚከተሉት ገጾች ላይ ያሉትን ይመለከቷል - ገገ. 133-134፣ 158ቀ፣ 174፣ 278፣ 310፣ 319፣ 330፣ 344-45፣ 373።) የጠያቂን ጽሑፍ ከመላሽ ጽሑፍ ለመለየት አዘጋጁ ዝንብሌ ፊደል (italics) እና ገባ ያለ የአንቀጽ መጀመሪያን ተጠቅመዋል። ግን ዝንብሌው ፊደል ከመደበኛው እምብዛም አይለይም። የተለየ ፎንትና የፎንት መጠን ቢጠቀሙ ኖሮ ልዩነቶቹን ማጉላት ይቻል ነበር። የአንቀጽን መጀመሪያ ብቻ ገባ ከማድረግ ሙሉውን አንቀጽ ገባ ያለ ማድረግ ተጨማሪ መለያ በመኾን ያገለግል ነበር። ይህም የጠያቂና መላሽ ጽሑፎችን ከመለያያት በተጨማሪ አጠቃላይ የጽሑፉን አቀማመጥ ለዐይን ቀለል ያደርገው ነበር።
ከገጽ 394 ጀምሮ ያለው ታሪክ፣ የትንሣኤ ታሪክ አይደለም፤ በርሳቸው ጥያቄና በጎ ፍቃድ የተጨመረ ማከያ እንጂ፡፡  ታዲያ ይህን እንደ “ማከያ” ወይም “ድኅረ-ታሪክ” በተለየ ምዕራፍ ማቅረብ ይበጅ ነበር። እንዲህ ማድረግ ከአቀራረብ የላቀ ፋይዳ አለው። ቀጣዩ የኢሕአፓ ልጆች የእስር ቤት ታሪክ፣ ከደራሲው ሳይለይ መቅረቡ ቀደም ሲል ያቀረቡትን ማሳሰቢያ - ታሪኩ የግል እንጂ የ”ኢሕአወሊ” ስላለመኾኑ ያሉትን ያዳክመዋልና።
ሥነ-ጽሑፋዊ ሕጸጾች
ከላይ እንደተጠቆመው መጽሐፉ  ብዙ ሕጸጾች አሉበት። ይህ ዳሰሳ በመጽሐፉ ውስጥ ያሉ ሕጸጾችን ጠቁሞ ማረሚያና ማሻሻያ ከሚያቀርብ አንድ ተማግቦ (feedback) የተቀዳ ነው። የተማግቦው ባለ ብዙ-ገጽ ዝርዝር ለዚህ ዳሰሳ አላስፈላጊ ቢኾንም የመጽሐፉ ረቂቅ በባለሙያ አርታዒና የናሙና ዕትም አራሚ (proof reader) ሳይታይ ለኅትመት እንደበቃ መገመት ያስችላል። ከሕጸጾቹ ውስጥ የከተባ ስሕተቶች በጣም የጐላ ድርሻ አላቸው። በተለይም “ኋ” በ “ኌ” እየተተካ መጻፉ የሚገርም ነው። የፊተኛውን እንዴት መክተብ እንደሚቻል ካለማወቅ ነው እንዳይባል፣ የኋለኛውን መክተብ አንጻራዊ ክብደት አለው።
አገባብ-ነክ ችግሮችም በጣም ጐልተው ይታያሉ፤ የነዚህ መሠረታዊ መነሻ አፋዊ ቋንቋ (colloquial language) በመኾኑ። ደራሲው ትውስቶቻቸውን በአፍ ትረካ ቢያቀርቡ ያ ትርክት ለአድልካች (audience) እንደሚደመጠው አድርገው በክትብ ጽሑፍ (typed script) ያስቀመጡት ይመስላል። ግን በክትቡ ትርክት ላይ ባለሙያ አርታዒዎች እርማትና ማሻሻያዎች ቢያደርጉበት መልካም ይኾን ነበር፤ በጽሑፋዊ ቋንቋ ረገድ ደረጃው ከፍ ያለ ሥራ (of high literary standard) ለማሳተም። ከዐባሪው የተቀነጨቡ ጥቂት ምሳሌዎችን ልስጥ።
ሀ. ሽፌ ከብሩኬ ጋራ ያክስት ልጆች ናቸው።    (ገ. 336)
ለ.1 ሽፌ እና ብሩኬ የእትማማች ልጆች ናቸው።
ለ.2 ሽፌ እና ብሩኬ ዝሞት (cousins) ናቸው።
ለ.3 ሽፌ እና ብሩኬ፣ አንዱ ለሌላው የአክስት ልጅ ነው።
በ(ሀ) የተሰጠው ዐረፍተ-ነገር በመጽሐፉ ውስጥ የሚገኝ ነው። በአፋዊ ዐማርኛ አዘወትረን የምንሰማው ዐይነት ነው። ዐረፍተ-ነገሩ ቃል-በ-ቃል ያዘለው ፍቺ ግን እቅጭ ሐሳብን አይገልጽም። “ያክስት ልጆች” በዐውደ- አገባቡ “የእትማማች ልጆች” ማለት አይደለም፤ ለማለት የተፈለገው እርሱ ቢኾንም። በርግጥ አድማጭ ይህን ይረዳል። የሚረዳው ግን ደምሳሳ ስሜቱን ከአጠቃላይ ጭውውቱ በመውሰድ ነው። እንዲህ ያለው አፋዊ አገላለጽ በጽሑፍ ሲቀርብ እቅጭ ሐሳብን እንዲገልጽ ማድረግ ይቻላል። በ(ለ.1)፣ በ(ለ.2) እና በ(ለ.3) የተሰጡት አማራጮች (alternatives) በጽሑፋዊ ቋንቋ ረገድ የተሳኩ ናቸው። የሰዋሰው እና የአገባብ ደንቦችን ስለሚጠብቁ፣ (ሀ) ማስተላለፍ ያልቻለውን ሐሳብ በእቅጩ ይገልጻሉ።
ሐ. የነበረኝ ሁለት ቀጠሮ ብቻ  ነበር። (ገ. 213)
መ. ኹለት ቀጠሮዎች ብቻ ነበሩኝ።
በ(ሐ) የተሰጠው ዐረፍተ-ነገር ያዘለው ሐሳብ ግልጽ ቢኾንም የቃል ድግግሞሽ ይታይበታል። “የነበረኝ” እና “ነበር” በርባታ ረገድ ካልኾነ ተመሳሳይ ናቸው። በተጨማሪ በዐረፍተ-ነገሩ ውስጥ የቁጥር አለመጣጣም አለ። ቀጠሮው ብዙ ሆኖ ሳለ ማሰሪያው ግስ ግን ነጠላ ነው። በአማርኛ አፋዊ ቋንቋ ይህ የቁጥር ደንብ ጥሰት የተለመደ/የተፈቀደ ቢኾንም ጽሑፋዊ አማርኛ ግን ደንቡን  መጠበቅ ያለበት ይመስለኛል። በ(መ) የተሰጠው አማራጭ በ (ሐ) ከተሰጠው ቀና እና ግልጽ ነው። ድግግሞሽን ከማስወገዱም በላይ በግስና በመሙያው ሐረግ መካከል ያለው ቁጥር ስምም ነው።
ተጨማሪ ምሳሌዎች ለመስጠት ያኽል ከአጉል የቁጥር ርባታዎች “ወራቶች” (ገገ. 3፣ 77፣ 245) እና “አባላቶቻችን” (ገገ. 184፣ 189፣ 196፣ 200) ይጠቀሳሉ። ግን ወራት ወይም ወሮች እንጂ “ወራቶች”፣ አባላታችን/አባሎቻችን እንጂ “አባላቶቻችን” አይሉም፤ በዘልማድ ካልኾነ በቀር። ቁጥረ-ብዙ ስምን እንደገና ማብዛት አላስፈላጊ ከመኾኑም በላይ የግእዝና የአማርኛ ስም ማርቢያ ሥርዓትን አላግባብ የሚያዳቅል ልማዳዊ ስሕተት ነው። በቃላት ምርጫም ረገድ ችግሮች ይታያሉ። ለምሳሌ ጥይት በማለት ፈንታ “ቀለህ” (143)፣ “ጥቂት ጭራሮ እና ኩበት” ለማለት ደግሞ “ጭራሮ ቢጤና እበት” (292) ጥቅም ላይ ውለው ይታያሉ።
በጣም በርካታ ዐረፍተ-ነገሮች የአገባብ ችግር ባይታይባቸውም፣ ሐሳብን አጥርቶ  የመግለጽ ድክመት (poor articulation of thought) ይታይባቸዋል። ለምሳሌ “በርካታ የድርጅቱ ጋዜጦች” የሚለው ሐረግ (57) ቃል-በ-ቃል የሚገልጸው ድርጅቱ ብዙ ጋዜጦች እንዳለው ነው። ትንሣኤ ግን ፓርቲው ሁለት ጋዜጦች ብቻ - “ዴሞክራሲያ” እና “አብዮት” - እንዳሉት ስለሚያውቁ፣ ለማለት የፈለጉት ከነዚህ ሁለት ጋዜጦች የአንዱን ዕትም በርካታ ቅጂዎች ይመስላል። እንዲያ ከኾነ “የድርጅቱን ጋዜጣ(ጦች) በርካታ ቅጂዎች” ማለቱ ጥርት ያለ ሐሳብን ያቀርባል። (ድርጅቱ ሲሉ በአእምሮ የያዙት የወጣት ክንፉን ከነበር ደግሞ የሊጉ ይፋዊ ጋዜጣ አንድ
ነበር፤ “አብዮታዊ ወጣት”። በርግጥ አንዳንድ የሊጉ ዞኖች/ሪጅኖች የየራሳቸው የአካባቢ ጋዜጣ ነበራቸው፤ ለምሳሌ “ወደፊት” ይባል የነበረው ጋዜጣ)።
መደምደሚያ
ይህ አጭር ቅኝት እንጂ በጥልቀትና በስፋት የተዘጋጀ ምሁራዊ ዳሰሳ አይደለም። በመጽሐፉ ይዘት ላይ (በታሪኩ ሐቆች፣ በባለገድሉ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ አመለካከቶች፣ ወዘተ. ላይ) አያተኩርም። አብዮቱንና ድኅረ-አብዮቱን በሚመለከት ከተታሙ መጻሕፍት ጋር እየተነጻጸረ አልተመዘነም/አልተገመገመም። የደራሲውን ታሪክ እኔና እጅግ ብዙ ጓደኞቼ - የወደቁም በቁም ያሉም - ኖረነዋል። በእርሳቸው ታሪክ ውስጥ የየራሳችንን እንድናይ ስላደረጉን ባለውለታችን ናቸው። በመጨረሻም የፋሲካ መለሰ ማራኪ ታሪክ ግድፈቶቹና ህጸጾቹ ታርመው፣ እንደገና ታትሞ  ለማየት እጓጓለሁ። ታሪኩን ብቻ ሳይኾን ሥነ-ጽሑፋዊ ብቃቱን የወደፊት ትውልድ እንዲደመምበት ማድረግ አስፈላጊ ነው እላለሁ።
(ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢሜይል አድራሻቸው: This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. __ማግኘት ይቻላል፡፡)

Read 1146 times