Saturday, 31 December 2016 11:45

“ጉጉት አምላክ ነበር”

Written by  በሰሎሞን አበበ ቸኮል
Rate this item
(3 votes)

  ባልኮኮ እና ሚስኮኮ የሚባባሉ ባልና ሚስት ሽኮኮዎች - የት ቆይተው እንደኾነ ማንም ባያውቅም - በጨለማው ውስጥ  እየወደቁ እየተነሱ ተዛዝለው፣ ወደ ማደርያቸው እያመሩ ሳሉ ነበር የኾነው ኹሉ የተጀመረው፡፡
ከጥንት ጀምሮ የኖረ ነው፣ ከሚባለው፣ ከገደሉ አፋፍ ላይ ተቆልሎ ከሚታየው ትልቅ ዋርካ ስር ከሚገኘው፣ በጭንጫው ላይ ተደራርበው ከተኮለኮሉ ዓለቶች ውስጥ ከሚገኘው መኖርያቸው  ደርሰው፤ እንደምንም ሹክክ ብለው ከመወሸቂያቸው ሊገቡ ሲሉ፣ ድንገት ጥሪ ቢሰሙ ኹለቱም ክው! ብለው ቀሩ፡፡
“ትሰማላችኹ!” ነበር ያላቸው፤ በዚያ ድድቅ ጽልመት ውስጥ ድንገት የሰሙት ጎርናና ድምፅ፡፡ በዚያ ዓይን ቢጉዋጉጥ በማይታይበት የደፈነ ጭለማ ውስጥ፣ በዱሩ ቀዬያቸው፣ ከወደ በላያቸው የወረደ ቃል!
-ማየት የሚባል ጸጋ ራሱ ከነመኖሩ በሚያስረሳ፣ ከቶ በንድያ ያለ  ጥቁረት ውሥጥ… ፡፡
 -ልክ… ብርሃን ሳይፈጠር፣ ከዚህ እስከ ላይ ጨለማው መልቶ በነበረበት ሠዓተ ሌሊት የሠራዊት አለቃው ሰማልያል እንዳሰማው ያለ ድምፅ!
የልባቸው ድውድውታ ተግ እንዳለ ደሞ፣ ያው ወፍራም ድምፅ፣ “እናንተ፣ ኹለታችሁም!!”፣ ሲል ተሰማ፡፡ ያው የሚንጓጓ ጎርናና ድምፅ ነበር፡፡
 በጨለማው ላይ የገደሉና የዋርካው ጥላ ተጨምሮ፣ ዐይን ቢጉዋጉጡ እንኩዋ በማይታይበት፣ ኹሉ ዳፍንታም በኾነበት ድድቅ የዱር ጨለማ  ውስጥ ማነው እርሱ ማየት የሚችለው?...እርሱው ራሱ አንድዬ ካልኾነ ሌላ ማን ይኾናል?...
ባልኮኮና ሚስኮኮ ቀልባቸው ምልስ ሲልላቸው እንድያ እንድያ ተባባሉ፡፡ ትንፋሻቸውን ውጠው ቆዩና ደሞ፣ የሰሙትን ድምጽ የሚያውቁት  መኾኑንና በዚያው ዱራቸው ከበላያቸው ሲኖሩ የሚያውቁዋቸው መኾናቸውንም ሹክ ሹክ ተባባሉት፡፡ ከፊቱ ተለየና የባሰ ድንጋጤ ያዛቸው፡፡
አዎን፣ ያ ድምፅ፣ እጅግ ግድንግድ በኾነው፣ ዕድሜው የትና የት ከመባል ውጭ ስንት እንደኾነ በማይታወቀው፣ በዋርካው  ግንድ ላይ ባለው ቁርቁር ዋሻ ውስጥ የሚኖሩት፤ ጉጉ!ጉጉ!…ሲሉ ሌሊት ሌሊት የሚሰሙዋቸው፣ የኝያ የጉጉቱ ነበር፡፡ ይህን ሲያስቡ ነው ድንጋጤያቸው ሌላና ጥልቅ የኾነ፡፡”-
-”እስከዛሬ ሳናውቅ፣ እኝህ የላይ ጎረቤታችን የኾኑት፣ በጨለማ ማየት ይችላሉ እንዴ?” አለች ሚስኮኪትዋ፡፡
ባልኮኮ አልሰማትም፡፡ እሱም የራሱ ነገር ነበረውና ጠጋ ብሎ ሹክ አላት፡፡
  “አወይ፣ በድንቁርና፣ በጭለማ ውሥጥ መኖር!... እስከዛሬ ድረስ ለዘመናት ሳናውቃቸው የኖርነው፣ ከላያችን የኖሩት ጉጉት ለካ አምላካችን ነበሩና !
ቁርጥ ቁርጥ በሚል ድምፅ፣በሚስኮኮ ጆሮ ውስጥ ንስሐ የሌለውን ኃጢአታቸውን ተናዘዘው፡፡
“በጨለማ ውስጥ !”
“እሱን አይደል የምልሽ፡፡”
“ወይ መከራችን! …ምን ይሻለናል?” ሚስኮኮ ቢሰማትም ባይሰማትም መቀበጣጠር ጀመረች፡፡ “ለመኾኑ ሌሎቹስ ያውቁ ኖሯል?”
“ሌሎቹ?”
“ሌሎቹ የዱሩ አራዊቶች ናቸዋ! ሌላ ማ…”
“ቢያውቁማ ኖሮ፣ ቀዬአችን በየተሳላሚው ሲሞላ ዕለት ዕለት እናይ አልነበር!”
እንዲችው የየራሳቸው ጭንቀትና ፍርኃት መዋግድ እየተላጉ ላጭራፍታ ጭጭ ብለው ቆዩና ሚስኮኮ የጉጉቱን አምላክነት ለሌላው የመንገር ሓሳብን አነሳች፡፡
“ጥሩ አስበሻል! ግን መንገር አትበይው መስበክ ነው። እንግዲህ፣ እንዲህ ካሳዩንና ካሰሙን ለድንቅ ሥራቸው ምስክርነት ነው መታጠቅ፡፡  ማን ያውቃል፤ የእስከዛሬው በደላችንን ይምሩልንም ይኾናል፡፡”  
ወዲያው፣ ቆይ ይንጋ ሳይል፣ “በይ ተነሽ፣ ላገኘነው ኹሉ እንንገር፣” አላት፡፡ በጨለማው ውስጥ እንዴት ባለ ችግር እንደሚኼዱ አስቦ ቀኖናቸው አደረገው፡፡
እንዴት ብለው እንደሚመሰክሩላቸውም ጠየቀችው፡፡ ባልኮኮ ትንሽ አሰብ አደረገና፣ “ተነሽ፣ እየሔድን እነግርሻለኹ፣” ቢላት ተያያዙና ተነሱ፡፡ እየወደቁ እየተነሱ፣ ተመልሰው አራዊቶች ወደሚገኙበት አንድ የዱር ጫካ አመሩ፡፡
ሚስት፤ ሽኮኮ እንዴት እንደሚናገሩ እያሰላሰለች ነበር፡፡
ለዘመናት ድንቁርና ተቆጣጥሮን፣ የርሳቸውን ዓዋቂነት ሳናውቅ…፣ በጨለማ ውሥጥ እንኩዋ የሚያዩ ዐይኖች እንዳሉዋቸው …
“ ምንድነው የምትለፈልፊው?”
“ኧረ አፍክን ያዝ! አበስኩ ገበርኩ በል፤ ቶሎ በል፣ አፈር ንከስ፣”  ቀስ ብላ ተናገረችው፡፡
“እንዴት እንደምንነግር ስነግርህ፣ ልፍለፋ?”
“እኮ እሳቸውን ነው  ዓዋቂ ብቻ የምታደርጊ፣ አምላክነታቸውን ስታውቂ?”
“በል፣ ራስህ ቃል አምጣ፣” እንዳለችው ከትልቁ ዐለት ጋ ተላትማ ወደኋላዋ ወደቀች፡፡ እንደተቆላለፉ ነበሩና፣ ባልኮኮም ላይዋ ላይ!
ለስንተኛ ጊዜ ነው እንዲ ሲላተሙና ሲጋጩ!...ያኹኑ ግን ሳያቆስላትም አልቀረ፡፡  “በዚኹ በቃችሁ ይበሉን! እንጂማ፣ ሲያንሰን ነው!” ተባብለው ቀጠሉ፡፡
ባልኮኮ እንዴት እንደሚመሰክር ሲያንሰላስል ቆየና፡
ብርሓን እንደወጣልን እንኩዋ ሳናውቅ፤ ለዘመናት በጨለማ ውስጥ ስንማቅቅ፤…
እንደ ጀመረው፣ ከአፉ ነጠቀቸው፡-
እስከዛሬ ድረስ በጨለማ ስንወድቅ፣
ብርሃን እንዳለን እንኳ ሳናውቅ፤
*   *   *
ባልኮኮ፡-  በድንቁርና፣ በነገራ ደብተራ፣  
በድርሳነ ባልቴት፣ በተረታ ተረት           ስንሰለቅ፤….
ሚስኮኮ፡-  ሕይወታችንን ብሩህ ልናደርግ፣            
ሲገባን፣….
ባል ኮኮ፡-  በስብሰን፣ በቁማችን ሞስነን፣..” .ብላ      
ተቀበለችው፡፡
ሚስኮኮ፤- አዎ፣ …
መላቅጥ እንዳጣባቸው ባያውቁትም፣ መዘባረቃቸውን አቆሙ፡፡ ወደ ጫካው እየገቡም መኾናቸውን አኹንም በሚላተሙባቸው ዛፎች ተረድተው አሰምተው ተጣሩ፤ ጉድ! ጉድ! ጉድ ነው ዘንድሮ!... እያሉ፡፡ ከዋናው የዱር ዐውድ በብዙ ጣእርና ጋእር ደረሱ፡፡ ደርሰውም፣ ስለ አምላካቸው ጉጉት ---
ለጎጋው አራዊት መሰከሩ፤…እርሳቸው በጨለማ ዐይተዋልና፡፡
ለዚህም አንድ ሌላ ምልክት ወይ ምስክርነት  የፈለገው የአራዊቱ ጉባዔ፣ “እውነት መኾኑን አጣርቶ የሚያመጣ፣የጉጉትን በጨለማ ማየት የሚያረጋግጥ አንድ አጣሪ ልዑክ ይላክ፣” አለ፡፡ በዚያው ሌሊት፣ በዚያው ድድቅ ጨለማ፣ በዚያው ዱር ችሎት  ተኩላና ቀበሮ ተመረጡና ተላኩ፡፡  
ቀበሮ፣ ተኩላ  ከትልቁ ዋርካ ሥር እንደደረሱ፣ የጉጉቱ ጓጓቴ ድምፅ ተሰማ፡፡ በዚያው ጨለማ ውስጥ፣ ያነኑ ጥሪዋቸውን አሰሙ፡፡
“እናንተ፣ ሦስታችኹም!” ብለው ተጣሩ፡፡ ተኩላ፤ “ከዚህ ወድያ ምሥክርነት!” ሲል፤ ቀበሮ ግን የታዘዘችውን ለመፈጸም፡-
“እስኪ ይህን ይወቁልን፤ በአንድ እግሬ ላይ ምን ያኽል ጣቶች እንዳሉ ይንገሩን፣” አለች፡ጉጉቱ ከዋርካው ሥር ባለ የዋርካው አንድ የወደቀ ግንድ የሜክል ሥር ላይ የቆሙትን የቀበሮይቱን እግሮች ዐይቶ በአንዱ ዐራት ጣት አንዳሉዋት ተናገረ፤ ቀበሮ ወዲያውኑ ፊቱዋን አዙራ ጡል ጡል እያለች ተመለሰችና፣ ምንም ጥያቄ የለውም ጉጉቱ፣ ሁ”ሉን ዐዋቂ አምላክ ናቸው ብላ ተናገረች፡፡ በቃ ከታመመ፣ ከአገር ከራቀ፣ ለጉዞ ካልደረሱ አራሶች በቀር አንድም ሣይቀሩ አምላክ ጉጉትን ሊያከብሩ ሊነገሡ ሊያመልኩ ሊያወድሱ፤በዚው ጭለማ በዱሩ ውስጥ ተጉዋዙ፡፡
እነጩልሌ፣ እነቁራም አልቀሩ፡፡ ተይዘው እንደደረሱ በቁርቁራው ውስጥ ያለውን ጉጉት ተንከባክበው ይዘው፣ አንደ ታቦት አክብረው አንግሠው ይዘው አወረዱት:: ራሱም ገረመው ጉጉት፤ አንዴ ወደ ግራ፣ አንዴ ወደ ቀኝ በዞረ ቁጥር አጃቢዎቹም የርሱን ይኮርጃሉ፡፡ ጉጉቱ ካለ፣ እነርሱም በአንድነት ይላሉ፡፡
ወገግ ባለ ጊዜ ጉጉቱ ግራ ተጋባ፤ግራ ቀኝ ኋላ ፊቱን አንድም መፈናፈኛ ሳይኖር ዕውር ድንብሩን በዳበሳ ይራመዳል፡፡ እግሮቹ ባዶ ቦታ እየፈለገ፣ የከበቡትን ተደግፎ ሲራመዱ ሲራመዱ፣ በነጋ ጊዜ አንድ ባቡር መንገድ ላይ ደረሱ፡፡
ከመኪናው መንገድ መኃል እንደደረሱ፣ ከላይ ከዳገቱ ሲኖትራክ የሚባለው ከላባ መኪና ያለ ሾፌር የሚነዳ መስሎ እየተንደረደረ፣ ሲወርድ ያየው ቁራ፤ጮኾ ነገራቸው፡፡ ኹሉም ወደ አምላክ ጉጉት፣ እርሳቸው ያውቃሉ ብለው ተመለከቱ፡፡ የሲኖትራኩ ጎማ ጉጉቱን ጨምሮ ያገኛቸውን ደፍጥጦ አለፈ፡፡
ከጥቂት ቀናት በኋላ ከተረፉት መካከል እነ ተኩላ፣ እነ ቀበሮ፣ እነ ሸለምጥማጥ፣… እነዚህ እነዚህ ተሰባስበው የጉጉትን አምላክነት እናስቀጥላለን ብለው ዐወጁ፡፡ በስሙም ማሉ።

Read 672 times