Print this page
Saturday, 31 December 2016 11:47

የኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ሕያው መዘክር

Written by  ሰሎሞን አበበ ቸኮል
Rate this item
(3 votes)

 • አስፋው ዳምጤ ከእንግሊዝ መልስ - ከንጉሱ ጋር ምን አወጉ?
                     • የግጥም መድበሎች እስከ 25 ሺ ኮፒ ይታተሙ ነበር
                     • ”ሰለሞን ደሬሳ ትምህርት አይገባኝም ይል ነበር”
                                        አስፋው ዳምጤ
 
    “አንድ ለአምስት” የተባለ ዳጎስ ያለ ረጅም ልብወለድ ደራሲው አስፋው ዳምጤ፤ራሱም ጥበበ ቃላት እያለ በሚጠራው ስነ ጽሑፍ ለኢትዮጵያ  ራሱን  የቻለ መዘክር ነው፡፡ በዘመን ቅደም ተከተል የድርሰት ሥራዎችንም ገምግሟል። በቀድሞው ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ፣ በአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከመጀመርያ ተማሪዎች  አንዱ የነበረው ጋሽ አስፋው፤የተማሪዎች መማክርት ጉባዔ ጸሐፊ በነበረበት ወቅት “በረከተ መርገም”ን የመሳሰሉ ሥራዎች የቀረቡበት “የኮሌጅ ቀን ግጥሞች” መድረክን አስጀምሯል፡፡ “ዩኒቨርሲቴ ኮልስ” የተሰኘች የተማሪዎች በራሪ መጽሔት አዘጋጅና ጸሐፊም ነበር፡፡ ከተማሪነት ዘመኑ ጀመሮ ከእነ ስብሃት ገብረ እግዚአብሔር፣ ተስፋዬ ገሠሠ፣ ሰሎሞን ዴሬሳ፣ ሣሕለሥላሴ ብርሃነ ማርያም፣ የመሳሰሉት ጋር ወዳጅ ነበር፡፡ በእንግሊዝ ኬምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ እና ፖለቲክስ የማስትሬት ዲግሪውን ይዞ ከተመለሰ በኋላ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሽልማት ድርጅትን የማቁቋም ኃላፊነት ተሰጥቶት ድርጅቱን መሥርቷል፡፡ በመጀመርያው ሽልማት ወቅት በስነ ጽሑፍ ዘርፍ ተሸላሚውን ገምግሞ በሚመርጠው ኮሚቴ ውስጥ ጉልህ ድርሻ ነበረው፡፡ የደራሲ በዓሉ ግርማ የቅርብ ወዳጅና የግል አርታዒውም ነበር፡፡ በዓሉ ከመታፈኑ በፊት አስራ አንደኛዋ ሰዓት ላይ ያገኘው ብቸኛው ሰው እርሱ ነበር፡፡ ጸሐፊ ሰለሞን አበበ ቸኮል፤ ከደራሲና ሃያሲ አስፋው ዳምጤ ጋር በአማርኛ ድርሰትና ደራሲዎች፣ ንባብና ህትመት፣ መጻሕፍትና ሒስ… ዙሪያ ያደረገውን ቃለ-ምልልስ፤ በራሳቸው አንደበት እንዲህ አጠናቅሮ አቅርቦታል፡፡

     ጥበበ ቃላት- በዘመን ቅደም ተከተል
ጥበበ ቃላት የምትለዋ ሐረጋዊ ቃል የእኔ አይደለችም። የመንግሥቱ ለማ ናት፡፡ ስነ ጽሑፍን ጥበበ ቃላት ብሎ፣ በየካቲት ወር ፲፱፻፵፰ ዓ.ም፣ ቀኑ ትዝ አይለኝም፣  “ፈረንጆች ሊትሬቸር፣ ወይም ፈረንሳውያን ሊተራቱር የሚሉትን እኛ ጥበበ ቃላት ልንለው እንችላለን፣” ብሎ በወወክማ ባደረገው ንግግር አቀረበ፡፡ እኔ ወደድኩዋት። እኔ ብቻ ሳልኾን ታደሠ ሊበንም፣ በመጽሐፉ መግቢያ ላይ፣ “በዓለም ጥበበ ቃላት አጭር ልብ ወለድ፣” ብሏል። ቀጥሎም፣ በ፲፱፻፶፰ በዚኹ ጉዳይ ሲከራከር፣ ጥበበ ቃላት እያለ ነበር የጠራው፡፡ ደበበ ሠይፉ ደግሞ “ዳይም ኖቭል” የሚሉትን ቤሳ ልብ ወለድ አለው፡፡
ከጣሊያን ወረራ በፊት፣ በ፲፱፻፳ዎቹ ውስጥ እነ ዮፍታሔ ንጉሤ በትምህርት ቤት በሚሠሩዋቸው ቴአትሮች ትኩረታቸውም፣ መልእክታቸውም ኢትዮጵያን ማዘመን  ነበረ፡፡ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ በኢትዮጵያ ያሉ መጻሕፍትን ቁጥር፣ በግእዝም በሌላውም ያለውን ዝርዝር ሲያወጡ፣ ዓላማው በሌላው አገር ካታሎግ ተብሎ የሚታወቀውን በኛም ሀገር እንዲኖር ነበር፡፡ ቢቢሊዮግራፊያ ብለው ሲያወጡም፣ ፈጠራ ያልኾነ ግን ከስነ ጽሑፍ ዘርፍ አንዱ የኾነውን ሲሠሩ ነበር፡፡ ይህ ነው በዚያ ወቅት የነበረው፡፡
ከሠላሳዎቹ እስከ ዐርባዎቹ የተወሰነ ዓመት ድረስ የነበረው ደግሞ፣ ለትምህርት ገበታ የሚኾኑትን መሥራት ነው፡፡ ተክለ ጻድቅ መኵርያ፣ ‘ፈረንሳዮች ከፈረንሳይኛ አምጥተው ታሪካችንን ለልጆቻችን እንዴት ያስተምራሉ? - እንግሊዞችስ እንዴት ከእንግሊዝኛ  የታሪካችንን መጻሕፍት ጻፉ?’ ብለው ነበር የተነሱት፡፡ መርስዔ ኃዘን፣ ቀደም ብለውም እንደጀመሩት፣ ቋንቋውንና ሰዋስዉን ሥርዓት ባለው መልክ ለትምህርት ቤት አዘጋጁ፡፡ ተክለ ማርያም ፋንታዬ ኆኅተ ጥብብ ዘስነ ጽሑፍ ሲሉ፣ ቋንቋውን መሣርያ አድርጎ እንዴት መጻፍ እንደሚቻል ለማቅረብ ነበር፡፡ እነ በላምባራስ ዝክረ ነገር ብለው፣ በየዘመኑ የተደረገውን መረጃ ለመስጠት ነው፡፡ ይህ እንግዲህ፣ ዘመናዊ ዘመናዊ ሲባል፣ ጠንቀቅ እንበል እንጂ፤ ካለንም እንደባልቅ ሲሉ ነው፡፡
አርባዎቹ ውስጥ በሠላሳዎቹ  ተማሪዎች የነበሩት ደርሰው፣ ከሽማግሌዎቹ ጎን ደራሲዎች ኾኑ፡፡ እነ ብርሃኑ ዘሪኹን፣ አቤ ጒበኛ፣ ጸጋዬ ገብረ መድኅን መጡ፡፡ ሌሎች ወጣቶችም  በአርባዎቹ ነበሩ፣ እንደ መዝገቡ አባተ ያሉት። ወደ ሃምሳዎቹና ስልሳዎቹ ስትመጣ፣  ብዙ ጸሐፊዎች ማኅበራዊ ሒሶች ሊባሉ የሚችሉ፣ ብዙም የድርሰት ልምድ የሌላቸው፤ ግን ኹለት ሦስት ትላልቅ ሐሳቦችን  ይዘው ብቅ ብለው የታዩበት ጊዜ ነበር፡፡ አሳታሚም ስለሌለ፣ ገንዘብም ስለሌላቸው፣ ታላላቅ ፍልስፍናዎችንና ሐሳቦችን እየሸነከሉ ይችን በምታክል መጽሐፍ፣ ቤሳ ልብወለድ አድርገው ያወጡ ነበር፡፡ ሰሎሞን ደሬሳ  ዘ አምሓሪክ ኖቭልስ ብሎ፣ ሲሳለቅባቸው፣ ‘በኪሎ ቢሸጡ፣’ ነበር ያላቸው፡፡ ኩሸታቸውና ሥራዎቻቸው የሰማይና ምድር ያኽል ይረራቅ ነበር፡፡
በስልሳዎቹ በዓሉ ግርማም “የኅሊና ደወል”ን ጨመረ፡፡ ዳኛቸው ወርቁ መጣ፤ ወዘተ..፡፡ ከስልሳዎቹ  በኋላ፣ እስከ ዘጠናዎቹ  ያሉትን፣ ከብዛታቸው የተነሳ በደንብ ለመመልከት አልቻልኩም፡፡ የሚያስገርመው፣ ዘጠናዎቹን የግጥም ዘመን ነው ብዬ አስብ ነበር፡፡ በኋላ እየሰበሰብኩ ስመለከት ልብወለዶቹም ለካ መዓት ናቸው። ያውም ኹሉንም ሳላገኝ፡፡ እርግጥ ከጭብጣቸውና ከመሳሰሉት ብዙዎቹ ወቅታዊ ናቸው፤ አንዳንዶቹም ትንሽ ግልብ ነገር ናቸው፡፡ ለመበየን ያህል የምመለስበት ነው፡፡ ግን ስነ ግጥምም ልብወለድም ብዙ አሉን፡፡
በቴአትር በኩልም መዓት ቴአትር ይቀርባል። ግን በተውኔትነት በመጽሐፍ የታተመው ከእጅ ጣት ቁጥር የማይበልጡ ናቸው፡፡ ከነዚህም አብዛኞቹ የአያልነህ ናቸው፡፡ ደራሲዎቹን ለምን እንደማያሳትሙ ጠይቄአቸዋለኹ፡፡ ነገ በአማርኛ ተውኔት ላይ አንድ ሥራ ልሠራ ብፈልግ እኮ፣ ‘አንተ የለህበትም፣’ እያልኩ። መላኩ በጎሰውን በስሚ ስሚ ይዘን ስንጨፍር ኖርን። የሱን የተውኔት ረቂቅ አየሁ የሚል አንድ ሰው የለም።  ዮፍታሔን በመዝሙሮቹም፣  በአፋጀሽኚም፣ ዮሐንስ አድማሱ ባሰባሰባቸው ቁርጥራጮችም እናገኛለን፡፡ የራሱ የዮሐንስም የሉም፤ ማን እንደሚያሳትምልን አላውቅም፡፡ የሱማ እንደው የሚገርም ነው፤ ልክ እንደ ሀዲስ ዓለማየኹ የተውኔት ድርሰት፡፡ የእሳቸውም የለም፡፡
 ስለ አገራችን ኅትመት- ድሮና ዘንድሮ
በፊት ብዙ ትኩረት የምንሰጣቸውና መበረታት አለባቸው ብለን በቀጥታም ይኹን በተዘዋዋሪ የምንደግፋቸው ለትምህርት  የሚዘጋጁትንና ቀድሞ በሌሎች ሲጻፉ የነበሩትን የሚተኩ፣ በኢትዮጵያውን የሚጻፉ ኢትዮጵያን የሚመለከቱ ጉዳዮችንና እንደነዚህ ዓይነቶችን ነበር፡፡ ሌሎቹ ደግሞ የፈጠራ ሥራዎች ናቸው። ጥበበ ቃላት ብለን ስንነሳ ዋናው ሐሳባችንም ይኼው ነበር፤ በሌላው ሀገር ስነ ጽሑፉ እዚህ ደርሷል እያልን፡፡ አኹን ግን ግለ-ታሪኮች፣ ግለሰቦች በየተሠማሩበት መስክ ያከናወኑትን የሚመለከቱት ናቸው በብዛት የሚወጡት፡፡
ከሥርጭት አንጻር፣ ኢትዮጵያ መጻሕፍት ድርጅትና ኩራዝ ለአጭር ጊዜ መደበኛ የማሳተም ሥራ ሲያከናውኑ ከነበረው ውጭ ተቋማዊ የኾነም ነበረ፡፡ ለምሳሌ፣ ትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት መሣሪያዎችን ያሳትም ነበር፡፡ አለዚያም፣ የሃይማኖት ድርጅት፣ ወይ ሚሲዮናውያን ነበሩ፡፡ ከነዚያ ውጭ፣ ለማንኛውም ዓይነት ደራሲ የሚኾን ሙያዊ እገዛ አድርጎ፣ ሥርጭቱንም ራሱ ይዞ፣ ለደራሲው የሚገባውን አድርጎ የመሥራቱ ዓይነት አካሔድ ተቀጭቷል፡፡ አኹን የተከሠተው ፣ልክ በጃንሆይ ጊዜ እንደነበረው፣ መደበኛ አሳታሚ ሳይኖር ተቋማዊ ወይም በግለሰቡ አሳታሚነት የሚሠራው ነው፡፡
ደራሲ ነኝ የሚለው በጣም የሚተማመንበት፣ወይ ውጭ የሚኖር ዘመድም ኾነ ወዳጅ ካለው ማሳተሚያ ገንዘብ ይልክለታል፡፡ ያ የሚታተመው ነገር  በሚገባው ደረጃ፣ የአርትዖት ሥራ ሣይካሔድበት ይታተማል። ሌላው ራሱ ደራሲው ተሟሙቶ፣ ተበድሮም ይኹን ተለቅቶ፣ አምስት መቶ  ቅጂም ብትኾን ያሳትማል፡፡ ፭፻ ቅጂ! ይህን ታምናለህ ወይ ሰምተህ ታውቃለህ? በአንድ ሰው እጅ ካልኾነ በቀር ወይም በቤተ መጻሕፍት እንዴት ይኾናል?...
በፊት በኩራዝ ይታተም የነበረው ዝቅተኛው (በተለይ ወደ መጨረሻ ላይ) ኻያ አምስት ሺህ ነበር። ዝቅተኛው ስልህ፣ ለምሳሌ፣ የደበበ ሰይፉ የ”ብርሃን ፍቅር” እና የሰይፉ መታፈርያ “ውስጠት”ን ፳ ፳ሺ ነበር ያሳተምነው - ግጥሞችን!
አንዴ ከቡልጋርያ የከፍተኛ ባለሥልጣን እንግዶች መጥተው ሲጎበኙ፣ “ግጥም ያን ያኽል ቅጂ ይታተማል፣” ሲባሉ በጣም ነበር የገረማቸው፡፡ “ግጥም!? የኢትዮጵያ ሕዝብ ግጥም ይሄን ያኽል ያነብባል ማለት ነው? … ተሸጦስ ያልቃል? እኛ ጋ እኮ ከ፭፻ እስከ ፲፭፻ ነው፤ ሺ አምስት መቶው ቅጂም በጣም፣ በጣም ታዋቂ ከኾነ ነው!” ብለውናል፡፡ ግርም! ነበር ያላቸው፡፡
ረጃጅም ልብ ወለድ፣ ለምሳሌ፣ የልምዣት ሃምሳ ሺ፣ የታንጉት ምሥጢር ሃምሳ ሺ! በሦስት ጊዜ ኾነ እንጂ፣ የሲሳይ ንጉሡ ሰመመን 60ሺ! መጀመርያ፣ አስራ አምስት ሺ፤ ኹለተኛ፣ ኡኡ እያለ ሌላ አስራ አምስት ሺ ታተመ። ‘ሦስተኛ ስንት ይታተም?’ ሲባል፣ እኔ፣ “ሠላሳ ሺ፣” አልኩ። የበዓሉ ኦሮማይ፣ ኢሕአዴግ ሲገባ እንዲታተም ሲጠየቅ፣ “መቶ ሺህ አሳትሙ፣” አልኩአቸው፡፡ ያኔ ከኩራዝ ወጥቻለኹ፡፡ “በፍጹም!” ብለው ሠላሳ ሺ አሳተሙ፡፡ ያ በአንድ ቀን አለቀ!  በአንድ ቀን ውስጥ ተመልሰህ ወደ ማተሚያ ቤት ትሔዳለህ? ተመልሰው ሠላሳ ሺ አዘዙ:: ከስድሳ ሺ በኋላ ባለቤቱ ፐርሰንቴጅ ጨምሩልኝ አለች። በዚያ ሲደራደሩ ዋለ፣ አደረና ሌላ ሠላሳ ሺ! እንግዲህ ከአንድ አመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ዘጠና ሺ!
ስለ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የሽልማት ድርጅት፡-
ከኬምብሪጅ ወደ አዲስ አበባ ስመለስ፣ በጥበቡ ዓለም ያሉት “እኔ-ነኝ--ንጉሥ-እኔ” እየተባባሉ ነበር፡፡ ስለዚህ፣ አንድ ነገር ለማድረግ አሰብኹ፡፡ እኔ አገናኝ ወይም ተላላኪ መኮንን ሆኜ፣ ደራሲውን ከደራሲ፣ ሠዓሊውን ከሠዓሊ፣… እንደዚህ ዓይነት ሥራ በመሥራት፣ ጥበቡን በየዘርፉ ማሳደግ የሚቻልበትን ነገር ለማድረግ ፈለግኹ። እነሱ ተስማምተው ሲቀጥሉ እኔ እወጣለሁ፡፡ ለምን? - ሠዓሊ አይደለሁማ! ለምን? - ደራሲ አይደለሁማ? ወይንም ሙዚቀኛ አይደለሁም፡፡    
መጀመሪያ ጸጋዬን አማከርኹ፡፡ “በጣም ጥሩ ሐሳብ ነው፣” አለኝ፡፡ መንግሥቱ ለማን (ያን ጊዜ ለእኛ ሌጀንድ ነበር) ቤቱ ድረስ ሄጄ አነጋገርኹት፡፡ “ማለፊያ ሐሳብ ነው! ማለፊያ ሐሳብ!” አለኝ፡፡ “እንደውም፣ የመጀመሪያዎቹ ስብሰባዎች እኔ ቤት ይኹኑ፣” ብሎ ቃል ገባ፡፡ ከቴአትር ጌታቸው ደባልቄን አገኘኹ፡፡ (ከሱ ጋር የኮከበ ጽባሕ ተማሪ በነበረበት ጊዜ እንቀራረባለን። ከውጭ ከተመለስኩ በኋላ ደሞ አንዳችን ለአንዳችን ሚዜ ኾነናል)። ገብረ ክርስቶስን ደሞ  ከሠዓሊያን ያዝን፡፡ እንደዚያ አድርገን ልናቋቁም ነበር፡፡
በዚህ መኻል የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የሽልማት ድርጅትን የማቋቋም እንቅስቃሴ ተጀምሮ ነበረ፡፡ በእንግሊዝ ስማር የማውቀው የኢትዮጵያ ኤምባሲ፣ ባህል አታሼ የነበረውን፣ ጋሽ አበበ ከበደን እዚህ የበጎ አድራጎት ድርጅት  አስተዳዳሪ ኾኖ አገኘሁት፡፡ “የምታግዘኝ ነገር አለ፣” ሲለኝ፤ “በደስታ ነዋ!”  አልኩት፡፡ ከዛ፣ አንድ ቀን፣ “ና እፈልግሀለሁ፣” አለኝ፡፡ ቢሮው ስሄድ አንድ ፋይል ሰጠኝ፡፡ ፋይሉ ውስጥ አንድ ማስታወሻ አለ - “ግርማዊ ጃንሆይ” የሚል፡፡ “ከጎን በእርሳስ የተጻፈውን አይተኻል?” ይለኛል፣ ጋሸ አበበ፡፡ በስሜ አኳያ በእርሳስ “ይሁን፣” የሚል ተጽፏል፡፡ “የጌቶቹ እጅ ጽሑፍ እኮ ነው፣” ይለኛል፤ እንዲገባኝ ነው፡፡ ስለዚህ፣ “ጃንሆይ፣ ነገ ጠዋት በአምስት ሰዓት ይዘኸው ና፣ ብለውኛል፣” አለኝ፡፡
‹‹ምነው ሳታማክረኝ እንዲህ ታረገኛለህ?›› አልኩት፡፡ እሱ ማማከር እንደማያስፈልገው ተናግሮ፣ “አምስት ሰዓት ብለዋል፤ አደራህን፣›› አለኝ፡፡
በቀጣዩ ዕለት ሔድኩ፡፡ ጠየቁኝ - የት የት እንደተማርኩ፣ የት እስፔሻሊዜ እንዳደረግሁ፣ የመሳሰለውን፡፡ ትምህርቴን ስነግራቸው፣ “ኣሃ፣ ኢኮኖሚ ፖሊቲክ?” አሉ፡፡
 “አይ፣ አይደለም፣ ኢ-ኮ-ኖ-ሚ-ክስ እና ፖለቲክስ። ፖለቲካል ኢኮኖሚ ማለት ከዚህ ሌላ ይመስለኛል፣” አልኳቸው፡፡
ከዚያም፣ፖለቲክስ ማለት ምን እንደኾነ ጠየቁኝና በቀላሉ መለስኩላቸው፡፡ “አይደለም!” አሉኝ፡፡ ”ፖለቲካ ማለት እውነትን በሐሰት ቀይረው ለማሳመን የሚሞክሩ ሰዎች ተግባር ነው፣” አሉኝ፡፡ አፌ ውስጥ እንደመጣልኝ አልመለስኩም፡፡ ልክ እሳቸው እንደማያውቁ፣ በዩኒቨርሲቲ ትምህርት የሚሰጠው.. እንዲህ ነው፣ እንዲያ ነው አላልኩም፡፡ ተረፍኩ፣ እንደዚያ ባለማለቴ፡፡
‹‹የማንትስን መጽሐፍ አንብበሀል ወይ?›› አሉኝ። እሳቸው ትርጉሙ ነው ያላቸው፡፡ እንደ አጋጣሚ እኔ ዋናው ነበረኝ፡፡ የሀሮልድ ኒከልሰን ዲፕሎማሲ የምትል መጽሐፍ ነች፡፡ በኋላ እንግሊዝኛውን መጣ አየኹት፡፡ እሱን ነው የተረጎሙት፡፡
ከዚያ፣ ሽልማት ድርጅት የማቋቋም ሐሳቡ እንዳላቸው፣ ራሳቸው (ጃንሆይ) የሰላም ኖቤል ሽልማት ለማግኘት በአንድ ድምፅ እንደተሸነፉ ጨምረው ተናገሩ፡፡ በፈረንጅ በሃምሳዎቹ መጀመሪያ፣ እንደዚህ ገደማ ፣ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ይኹን ጠቅላይ ሚኒስትር  አላውቅም፣ ግን ካናዳዊ ነው አሉ፣ በአንድ ነጥብ የበለጣቸው፡፡
“በአንድ ድምፅ አሸነፈና ቆጨን፣” አሉኝ፡፡ በኋላ ደግሞ፣ “እንዴ፣ ምን ይቀርብንና ነው? እንዴት ይቆጨናል?” አሉ፡፡
“በኋላ  ስናስበው፣ ሽልማት ለካ ያተጋል፡፡… እኛን እንዲህ ከተሰማን፣  ታዲያ ለሕዝባችን፣ ለምን …? ብለናል።”  
“ይሄንን ወስነን፣ ግን ጊዜው ስላልደረሰ ውሎ አደረ። አኹን ግን ጊዜው ስለደረሰ፣…” አሉኝ፡፡ እግዚአብሔርም አለበት፣ እንግዲህ እዚህ ውስጥ፡፡
“እንደ አልፍሬድ ኖቤል ሃብታምም ባንኾን፣ በዚያ ደረጃ እና በዚያ መንገድ ነዋሪነት ያለው፣ መሠረት ያለው ነገር ማቋቋም፣” ብለው አሳወቁኝ፡፡ በዚሁ ተመደብኩ፡፡ ከመዝገብ ቤት ወረቀት ወሰድኩ፡፡ አብሮት ስለ አልፍሬድ ኖቤል፣ ስለ ሕይወት ታሪኩ፣ እንዴት እንዳቋቋመው አለ። ለጊዜው በጎ አድራጎት ውስጥ ቢሮ ተሰጠኝ፡፡ ፒያሳ ዳርማር የሚባለው ሱቅ አለ አይደል? እዚያ ፎቅ አናቱ ላይ፣ “የፊደል ሰራዊት” የሚባል ነበረ፡፡  እዚያ ላይ ነው። መጀመሪያ ከበጎ አድራጎት ድርጅት ሥር መስሎኝ፣ ለጋሽ አበበ ከበደ፣ “ይሄ ራሱን ችሎ በኹለት እግሩ መቆም ያለበት ነው፡፡ በምንም ዓይነት ከአንተ ድርጅት ሥራ እና መንፈስ ጋር የሚገናኝ አይደለም፣” አልኩት፡፡ እሱም  ደሞዝ እንኳን ሲቆርጥ ከእሱ ደሞዝ በላይ ሀምሳ ብር ጨምሮ ነው ያስፈቀደው - ስድስት መቶ ሀምሳ ብር፡፡ እሱ ስድስት ነበር የሚያገኘው፡፡ የዋና ‹ዲሬክተር› ደሞዝ ነው። ከዋና ሚኒስትር ፣ ከረዳት ሚኒስትር አይደርስም፡፡ የነሱ ሰባት መቶ ነበረ፡፡
“ቻርተር” መኖር ነበረበት፡፡ ለዚሕ የሕግ ባለሞያ ያስፈልጋል፡፡ ለሕግ ባለሞያው ይዘቶቹ ምን ይኾናሉ?  በምን በምን ነው ሽልማቱ?  ለአንዱ ሽልማት በግርድፍ ስንት ይኹን?…  የሚሉት መቀመጥ አለባቸው፡፡ ሽልማቱን “እንዴ፣ እነሱ ፍራንክ የላቸውም፣”  እያለ ጋሽ አበበ ነው የወሰነው፡፡ በእሱ  መመሪያ መሠረት አዘጋጅቼ ለንጉሡ ስሰጣቸው ፣ “ይኼማ የደሀ በጀት ነው፣” አሉኝ፡፡ “ምን እንኳን የአልፍሬድ ኖቤልን ያኽል ባይኖረንም፣ ….” አሉ፡፡
ትምህርትን  ማስቀደም ነበረብኝ፤ ረሳሁት እኔ፡፡ ያንን አረሙኝ፡፡  በኢንዱስትሪ፣ ከዛ በጥበባት፡፡ ከጥበባት ዘርፍም በጥበበ ቃላት፣ በቋንቋ  ላይ…፡፡ ከጥበበ ቃላት ራሱ በዚያን ጊዜ ትያትሩ ኹሉ  ገብቷል፡፡ በኋላ  ነው የተቀየረው፡፡ እንደዚያ ኾኖ ተረቀቀ፡፡
በዶክተር ምናሴ ኃይሌ ሊቀመንበርነት፣ አቶ አበበ ከበደ፣ የጃንሆይ ወኪል ተብሎ ፣አቶ ከበደ ሚካኤል፣ ሥዩም ሐረጎት- ከጠቅላይ ሚኒስትር፣ ፓራዲዝ የሚባል የሕግ አማካሪ፣  ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ እንዲህ እንዲህ ሆነው ---- በደንብ ተወያዩበትና እንደገና ተብራራ፡፡ ያም እንደገና እንግሊዝ ሀገር ያለ ሲባ ፋውንዴሽን የሚባል ድርጅት ዲሬክተር ነበረ፡፡ ከኖቤል ሽልማቱ፣ በተለይ ከሜዲካል ኮሚቴው ጋር ቅርብ ግንኙነት የነበረው  ባለሙያም  ታይቶ ተዘጋጀ፡፡ እንደገና መልክ እንዲይዝ፣  እኔው ራሴ ስዊድን ሄጄ የኖቤል የሽልማት ድርጅትን እንድጎበኝና ልምዱን እንዳመጣ ተደረግኹ፡፡
ንጉሡ ራሳቸው ናቸው ያዘዙት፡፡ ልሔድ ስል፣ ቀረብኩኝና እጅ ነስቼ ሳበቃ፣ “ለመሆኑ የምትሔድበትን ጉዳይ አውቀኸዋል?” አሉኝ፡፡
“አዎን፤ እንዲህ ነው፣ እንዲህ ነው፣ እንዲህ ነው፤ ይዘቱ እንደዚህ ነው፡፡ ሕጋዊ መልኩማ ያው የባለሞያው ነው፣” አልኩዋቸው፡፡
 “ገብቶሀል! ገብቶሀል!” ተባልኩ፡፡
እዛ እያለሁ ነው እንግዲህ ከሽልማት ድርጅቱ ወደ ገንዘብ ሚኒስቴር እንድዛወር የተደረገው፡፡ ግን ከሽልማት ድርጅቱ ወደ ገንዘብ ሚኒስቴር በተዛወርኩ በመጀመሪያው ዓመት የመጀመሪያው የሽልማት ዕድል ላይ፣ “የስነጽሑፍ ኮሚቴ አባል ኾነው እንዲያገለግሉ ተመርጠዋል፣›› ተብሎ፣ በዶ/ር አምባቸው የተፈረመ ደብዳቤ ደረሰኝ። ተገረምኩ፤ ተደሰትኩም! ምክንያቱም፣ ሥነ ጽሁፍ የተባለውን ኹሉ፣ የአማርኛ የፈጠራ ሥራዎችን በሙሉ ነበር የምንገመግመው፡፡ የትንሹን፣ የትልቁን፣ የምኑን የምኑን በሙሉ ነበር የገመገምነው፡፡ ከዛ፣ ወደ ስንት ነበር  መጀመሪያ  የሰበሰብነው?  ወደ ሰባ ምናምን የሚሆኑ ርዕሶችን ነበር፡፡ ቢያንስ፣ ያወቅናቸውንና ከየቦታው የተገኙ፡፡ በወቅቱ የወጡት ነበሩ ለሽልማት የታሰቡት፡፡ ያየነው ግን ከአስራ ዘጠኝ መቶ ወዲህ ነው፣ እና ከዚያ በኋላ፤ 54ቱ ተዘረዘሩ፣ ከሰባው፡፡ ከዛ ሠላሳ፡፡ መጨረሻ ላይ አራት ሰዎች ላይ ደረስን፡፡ ከበደ ሚካኤል እና ባላምባራስ ማኅተመ ሥላሴ፣ መንግስቱ ለማ እና ጸጋዬ ገብረ መድኅን፤ ከድሮዎቹ ኹለት፣ ከአዲሶቹ ኹለት። ከዛ፣ በሚቀጥለው ዙር ላይ ጸጋዬ ወደቀና መንግሥቱ ከሽማግሌዎቹ ጋር ቀጠለ፡፡ በኋላ መንግሥቱ ወደቀ፡፡ ኹለቱ ቀሩ፡፡ እዚህ ላይ ጦርነት መጣ፡፡
ፕሮፌሰር  ጌታቸው ኃይሌ የጁሪው አባል ነው። እሱ ባላምባራስ ናቸው ተሸላሚ፣ እኛ የለም ከበደ ሚካኤል። ጦርነት! እሱ፣ እኔ፣ ተስፋዬ ገሠሠ፣ አሰፋ ሊበን ነበርን። አሰፋ ሊበን፣ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛው፡፡ ድንቅ የጽሑፍ ሰው ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ሆነን “መጻሕፍት ቀምሰዋል?” የምትል አውጥቶ ነበር፡፡ እንዴት ያለች ለዛ ያላት ነገር ናት መሰለህ! በጣም የሚያሳዝንህ፣ እነዚህን ነገሮች በኋላ በዚህ ዘርፍ ትኩረት የማደርግ መኾኔን ባውቅ ኖሮ ያኔውኑ እንዳይጠፋ አደርግ ነበር፡፡ እሱም ራሱ ግን ቁም ነገሬ ብሎ ቢያሳትመው ጥሩ ነበር፡፡ ባያሳትማቸው እንኳን ተተይበው፣ ተባዝተው፣ ተጠርዘው ሊያስቀምጣቸው ይችል ነበር፡፡ ነገር ግን፣ እዚያ እስካልደረስክ ድረስ ወደፊት የሚኾነውን አታውቅም፡፡ ግን፣ መቼም፣ በጣም በሳልና ረቀቅ ያሉ አገላለፆች ናቸው።
እናልህ፣ እኔ፤ ከበደ ሚካኤል ብዬ መከራከርያዬን ደረደርኩ፡፡ መጀመርያ ላይ እኮ አንዱ ተቃዋሚ እኔ ነበርኩ፡ እንደው በወሬ ደረጃ፡፡ እዛ ዝግጅቱ ውስጥ ከገባን በኋላም ተቃውሜ ነበር፡፡ “አይ እሳቸው የጃንሆይ እንትን ናቸው፣” እል ነበር፡፡ ግን በኋላ ሥራውን ስንጀምር፣ እንማማር ዓይነት ሐሳብ ነበረውና ያኔ ተመለስኩ፡፡ እስካሁንም አናውቃቸውም፣ መፅሐፎቻችንን፡፡ እንደገና ሀ ብለን ነው የምናነበው፡፡ ክፍት አዕምሮ ይዘን ነው መክፈት ያለብን፤ ሥራዎቹ ይምሩን፡፡ በኋላ የከበደ ሚካኤልን ሥራዎች ዋጋና ጠቃሚነት  ሳይ በቃ ሐሳቤን ቀየርኩ፡፡ ከበደ ሚካኤልን ትልቅ ዋጋ የሚያሰጣቸው አንደኛው ነገር፣ የተማረውም ክፍል አማርኛን እንዳይሸሽ፣ በአማርኛ ሐሳቡን መግለጽ እንዲችል ማድረጋቸው ነው። ኹለተኛ፤ ከግእዝ ተጋፍተው አማርኛን በኹለት እግሩ እንዲቆም አድርገዋል፡፡ ፕሮፌሰር ጌታቸው ግን፣ “እንዴ፣ አንድ የአማርኛ ቅኔ ከነመፍቻው ብቻ ከከበደ ሚካኤል  ጋር በሚዛን ላይ ብታደርጓቸው …” አሉን፡፡
 ‹‹እሱ ልክ ነው! ግን ማኅተመ ሥላሴ አልጻፉትም፤ ሰብሰቡት እንጂ! እሳቸው የኢትዮጵያ ጥናት የሚል ዘርፍ ቢኖረን በዛ ነው ማግኘት ያለባቸው፣” አልኩ፡፡ በዛ ቢሆን ትክክል፣ አንደኛ ይሆናሉ፡፡ የአባቶች ቅርስ አለ፤ እንቅልፍ ለምኔ አለ፡፡ ስንት  አለ!
እንደዚያ  ስለው እሱ አቅማማ፡፡ በኋላ ጉዳዩ ወደ ንዑስ ኮሚቴ ወጣ፡፡ ብሔራዊ ኮሚቴ ላይ አቀረብን፡፡ ሊቀመንበሩን “ወሳኝ ድምፅ አለህ፣” ብንለውም ዶክተር አምባቸው አልፈለገም፡፡ ብሔራዊ ኮሚቴው “ሽልማቱን ይካፈሉ” አለ፡፡ ከዛ ወደ ባለ አደራዎች ቦርድ ሊቀመንበር ፀሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ኃ/ወልድ፣ አቶ ይልማ ዴሬሳ፣ እስክንደር ደስታ፣ ጋሽ አበበ (የጃንሆይ ተወካይ ሆነው)። በኋላ፣ “እስቲ፣ ቃለ ጉባኤያቸውን እንይ፣” አሉ፡፡ አዩትና  ከበደ ሚካኤል ነው ተሸላሚ ተባለ፡፡
“ከበደ ተርጓሚ እንጂ ደራሲ አይደለም፣” የሚል አስተያየት ስለነበረ፣ ከበደ ያን ሰምቶ፣ ተበሳጭቶ ለሽልማት ሲጠራም፣ “ዞር በሉ!” አለ፡፡ “አልቀበልም!  በመጀመሪያ፣ ማነው እሱ ይህን  የሚወስነው? በማን ዳኝነት ነው የሚወሰነው? በኋላ  ሽልማቱ ቤታቸው ተላከላቸው እንጂ ከበደ ሚካኤል የዕለቱ - ለት መጥተው አልተቀበሉም፡፡
በኹለተኛው ዙርም ዳኝነቱ ላይ ተመድቤ ነበር። ግን ገንዘብ ሚኒስቴር ስለገባሁ ያን ዓመት በደንብ አልተሳተፍኩም፡፡ ባላምባራስ አገኘሁ፣---- ጸጋዬም በጣም እየሠራ ነበር፡፡ ያኔ የኹለቱ ፉክክር የተጋጋለ  ነበረ።
ስለ ሰሎሞን ዴሬሳ፡-
ሰሎሞን ከኛ ቀድሞ የገባ  ነበር፡፡ ከኛ ጋር ባንድ ላይ የተማረው ስለ ደገመ ነው፡፡ እሱም እኛ ስንማር የነበረውን ኹሉንም ዓይነት ትምህርት ተምሯል፡፡ እነዚያኑ እኛ የተማርናቸውን የትምህርት ዓይነቶች፡፡ (ልክ እንደ ኋላ ጊዜው እኮ በየትምህርት መስኩ አልነበረም የምንማረው፡፡ እኔ አስታውሳለኹ፤ አንደኛ ዓመት ላይ ፲፫ የትምህርት ዓይነቶች ነበር የተማርነው፡፡ አሥራ ሦስት! ያልተማርነው ዐቢይ የሚባል የትምህርት ዓይነት የለም፡፡ ለምሳሌ፣ ሶሲዮሎጂ፣ ፖለቲክስ፣ ኢንትሮዳክሽን ቱ ኢኮኖሚክስ፣ ሊትሬቸር፣ ፌሎሶፊ፣ ኢንትሮዳክሽን ቱ ጁሩስፕሩስደንስ (የሕግ ሳይንሥ)፣ … እንግሊዝኛ ሁለት ዓመት! እንግሊሽ ሊትሬቸር አራት ዓመት! ፊሎሶፊ - አራት ዓመት! ግን ቶሚስቲክ (የቶማስ አኩዊናስ) ፊሎሶፊ ነበር፤ የጄስዊትሶች ነው፡፡ በመምህሩ በክሎድ ሳምነር ቆስቋሽነት፣… ግን እነ ሰሎሞን ዴሬሳ፣ እነ ስብሃት፣ እነዚህ እነዚህ የሚያወግዟቸውን ጭምር ነው እየፈለግህ የምታነብበው፡፡ እና አስበህና ፈልገህ ስለሚኾን፣ ያኛውን ለመሞገት ወደ ኋላ አትልም፡፡ እኔ ደግሞ የኦርቶዶክስ ተዋኅዶ አጥባቂነት ነበረብኝ፡፡)
 በርግጥ፣ ከሰሎሞን ዴሬሳ ጋ የጠበቀ ግንኙነትም አልነበረንም፡፡ አንድ ጊዜ ክርክር ገጥመናል፡፡ እንዲያውም ኹለታችንም ለክርክር ክበብ ለመመረጥም ተወዳድረናል። ያኔ እሱ አስቀድሞ የቤት ሥራውን ሠርቷል፣ በውድድሩ ላይ፡፡ “ማይ ኔም ኢዝ ሶሎሞን!” - ኖ፣ “ሶሎሞን ዲ! ‘ዲ’ ዳዝ ኖት ስታንድ ፎር ዘ ዴቪል፣ በት ፎር ደሬሳ!”
ያኔ፣ የርሱ ደጋፊዎች፣ ‘ዋህ!...’ ብለው ጮኹ፡፡ በበኩሌ ለክርክር ቢሮው ተገቢ መስሎ አልታየኝም፡፡ ከዚያ፣ በቃ፤ እሱ አሸነፈ፡፡ፕሬዚዳንት ኾነ፡፡ እንዳልኩህ ተዘጋጅቶበት ነበር፡፡ ደሞ እሱ የዊንጌት ተማሪ ነበር፤ እኔ ከኮከበ ጽባሕ የመጣኹ፡፡ ሰሎሞን አንባቢም ነበረ፤ በጣም! በጣም! በጣም አንባቢ - ቮሬሽየስ ሪደር! ነበረ። ለትምህርቱ ግን ግድ አልነበረውም፡፡ በኋላ ላይ የሱን ነገር ስገመግመው፣ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁን ማደሪያውና መኖርያው እንጂ መማርያው አላደረገውም ነበር፡፡ ቁርስና ምሳ እየበላ ማደር እንጂ ትምህርቱን አይፈልገውም ነበር። እርሱ ራሱን ነው የሚያስተምረው፡፡ ላይብረሪ እየሔደ የሚያነብበው ሌላ ነገር፣ በሌላ ርእሰ ጉዳይ ላይ እንጂ ለክፍል ፈተናው አልነበረም፡፡ ለዚያም ነበር የደጋገመው። ከኛ ጋርም ኾኖ እኮ ዲግሪውን ኣላገኘም፤ ለኹለተኛ ጊዜ ማለት ነው፡፡ አንዴ፣ ከአሜሪካ መጥቶ፣ ይህን ጉዳይ አንስተን ስናወራ፣ “እኔ ትምህርት አይገባኝም፡፡ ትምህርት አልገባ ሲለኝ፣ ጭራሹኑ ዊንጌት ጨመሩኝ፣”  እያለ ቀላልዷል፡፡… እስኪ ይታይህ. አንድ ሰው እንዲህ ኾኖ ነው ጄኔራል ዊንጌት የሚገባው? - በቃ! እሱ ራሱን በራሱ ማስተማር  ነው የፈለገው፡፡… ቤቱ ገብቶ፣ “አልማርም፣” ቢላቸው ያስቀምጡታል እንዴ? - ስለዚህ፣ እዚያው ግቢ ውስጥ ኾኖ የፈለገውን ይማራል፡፡ ሌክቸር ይገባል፡፡ የሚጥመው ከኾነ ያዳምጣል፤ ካልኾነ፣ ይሄን ስላልመረመርኩ እርግጠኛ ባልኾንም፣ ዝም ብሎ የራሱን ማስታወሻ ይጽፍ እንደኾነ እንጂ----

Read 3575 times