Saturday, 31 December 2016 11:48

የሴት ልጅ ግርዛት ከ2000 አመት በላይ....

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶ
Rate this item
(0 votes)

 • በየአስር ሴኮንዱ በአለማችን አንዲት ልጃገረድ ግርዛት ይፈጸም ባታል።
     ታህሳስ 6/2009 ዓ/ም በአዲስ አበባ አንድ የምክክር አውደ ጥናት ተካሂዶ ነበር። የምክክር አውደጥናቱ ትኩረትም በአለም አቀፍ ደረጃ እ.ኤ.አ እስከ 2025 ድረስ በሴት ልጆች ላይ የሚፈ ጸመውን ግርዛት የብልት ትልተላ ጭርሱንም ለማስቆም የተለያዩ እርምጃዎችን መውሰድ የሚቻልበትን መንገድ መምከር ነበር።
የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ጤና ጥበቃ ሚኒስር እና የኢትዮያ ጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን ባዘጋጁት የምክክር አውደ ጥናት ከተወካዮች ምክር ቤት እንዲሁም ከተለያዩ መስተዳድሮች የጤና ተቋማት እና ጤና ቢሮዎች የተወከሉ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል። ከዚህም በተጨማሪ ሕብረተሰቡን ይወክላሉ ተብሎ የሚታመንባቸው ከሀይማኖት ተቋማት እና ሌሎች መስሪያቤቶች ተወካዮችም ተገኝተው ነበር።
የምክክር አውደጥናቱን ለማስጀመር ንግግር ያደረጉት ወ/ሮ ያምሮት አንዱአለም በጤና ጥበቃ ሚኒስር የሴቶችና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሚከተለውን ብለዋል።
“...ሀገራችን በ2025 ያለእድሜ ጋብቻንና የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስወገድ የገባችውን ቃል ተግባራዊ ለማድረግ የጤናው ዘርፍ የሴት ልጅ ግርዛትን ለመከላከልና ተገቢውን የህክምና አገልግሎት ለመስጠት ኃላፊነትና ድርሻው ምን መሆን እንዳለበት ለመለየት የተሸለ ስራ እንዲከናወን ይህ የጋራ ስብሰባ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ሙሉ እምነ ነው። ምክንያቱም ጉዳዩ በአህጉራችን ሲታይ እጅግ አሳሳቢ በመሆኑ ነው። ለአብነትም በአፍሪካ 125 ሚሊዮን ሴቶችና ልጆች በየቀኑ ግርዛት ይፈጸመባቸዋል።እንዲሁም ከ30 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ልጃገረዶች በቀጣዮቹ አስር አመታት በዚህ ችግር ምክንያት ተጽእኖ ይደርስ ባቸዋል ተብሎ ይታመናል። በየአስር ሴኮንዱም በአለማችን አንዲት ልጃገረድ ግርዛት ይፈጸም ባታል። የሴት ልጅ ግርዛት በኢትዮጵያ አስከፊ ሁኔታ ላይ እንደሆነ ይታያል። 23.8 ሚ ሊዮን ሴቶች እና ልጃገረዶች ላይ ተጽእኖ በማሳደርም ሀገሪቱ በችግሩ ብዛት ከተመዘገቡ አገሮች ውስጥ አንዱዋ እንድትሆን አድርጎአታል። በአፋር 91.6ኀ በሱማሌ ክልል ደቡባዊ ምስራቅ 97.3 ኀ በድሬደዋ 92.3 ኀ ተመዝግቦአል። በኢትዮያ የሴት ልጅ ግርዛት ዝቅተኛ የእውቀት ደረጃ ባለባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ፣ እኩልነት በማይስተዋልባቸው ፣ ላቅመ ሔዋን ባልደረሱ ሴቶች ጋብቻና አነስተኛ የምጣኔ ኃብት ባላቸው ሴቶች ላይ በብዛት ይስተዋላል። የሴት ልጅ ግርዛት ከ2000 አመት በላይ እድሜ ያስቆጠረ ሲሆን እንደባህል፣ ደንብና የማህበረሰብ ልማድ ይቆጠራል። አልፎ አልፎም እንደማህበረሰብ ሕገደንብ ይታያል። ይሁን እንጂ የሴት ልጅ ግርዛት ምንም የጤና ጥቅም የሌለውና ከባድ የሆነ አካላዊና ስነልቡናዊ ቀውስን የሚያስከትል ነው። ኢትዮጵያ የሴት ልጅ ግርዛትን ለመታገል አስፈላጊውን እርምጃ ስትወስድ ቆይታለች። በሕገመንግስቱም ጎጂ ልማዶች በሚል ተደንግጎአል። የሴቶችን አካላዊና ስነልቡናዊ ጉዳት የሚ ያደርሱና ለጉዳት መንስኤ የሚሆኑ ማናቸውም ባህልና ልማዶች የተከለከሉ ናቸው። ሴቶች ይህንን የታሪክ ውርስ ለማስቀረት አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ ይገባቸዋል። የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስቀረት ውጤታማ የሆኑ ሕጎች ሊጠናከሩ ይገባል። በዚህም ኢትዮጵያ በስትራ ጂና በጋራ ዘርፉ ጥረት የሴት ልጅ ግርዛት በ2025 እንደኤሮፓውያን አቆጣጠር በአጠቃላይ ለማ ስወገድ ቆርጣ ተነስ ታለች። ቁርጠኛነታችንን እንድናድስና እንድንገነባ የሴት ልጅ ግርዛትን በ2025 እ.ኤ.አ ለማስወገድ የተጠናከረ ጥረት ይሻል። እንዲሁም ጥረቶቹ ለተሻለ ውጤት የተቀናጁ መሆን ይጠበቅባቸዋል። ...” ብለዋል።
ከወ/ሮ ያምሮት አንዱአለም በመቀጠል ንግግር ያደረጉት ዶ/ር ደረጀ ንጉሴ የኢትዮጵያ ጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ፕሬዝዳንት ናቸው ።
“...በሴት ልጅ ግርዛት የሴት ልጅን የተዋልዶ ጤንነት የሚጥስ ጎጂ ባህላዊና ልማዳዊ ድርጊት ችግሩ በአለም ማህበረሰብ ዘንድ ዘርፈ ብዙ ልማድ ከሆኑት አንጻር በተለያዩ ድንጋጌዎች ስምምነቶችና ቃልኪዳኖች ላይ ተገልጾአል። እንደየአለም ጤና ድርጅት ዘገባ ከሆነ የሴት ልጅ ግርዛት በልማድ፣ በስነልቡና ፣በባህል ፣በተዋልዶ ጤና ሂደትና በስነወሲብ ልማዳዊ ድርጊት ጋር ተጠቃሎ ተካትቶአል። የአለም የጤና ድርጅት የሴት ልጅ ግርዛትን እንደሂደቱ በአራት አበይት ክፍሎች ከፍሎታል። ድርጊቱ የሴት ልጅን የውጭ ብልት ከመብሳት አንስቶ በአጠቃላይ የውጫዊ የብልትን ክፍል እስከማንሳት ደረጃ ይደርሳል።የዚህ አጉል ልማዳዊ ሂደት አይነት ምንም አይነት ይሁን የሴት ልጅ ግርዛት ጠንቅ ትግበራ ሂደቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስከ ሕይወታቸው መጨረሻ ድረስ የሚዘልቅ ጠንቅ ያስከትልባቸዋል። ምንም እንኩዋን አንዳንድ ከችግሩ ጠንቆች ጋር የተያያዙ ሕክምናዎችን ለመስጠት በከፍተኛ ደረጃ የሰለጠኑ የህክምና ባለሙያዎችን የሚፈልግ ቢሆንም በአብዣኛው ግን በመካከለኛ ደረጃ በሚገኙ የህክምና ባለሙ ያዎች አገልግሎቱ እንደሚሰጥ ይጠበቃል። ከዚህ በተጨማሪም የጤና አገልግሎቱ ሰጪዎች ችግሩን በመከላከል ረገድም በተጉዋዳኝ የሚጠበቅባቸውን ነገር እንዲፈጽሙና ተገቢውን ሚና እንዲጫወቱ ይጠበቃል። ሰውነትን ከማንኛውም ጥቃት መጠበቅ ሕገመንግስታዊ መብት ነው። እንዲሁም በተሻሻለው አዲሱ የወንጀለኛ መቅጫ የሴት ልጅ ግርዛት የወንጀል ቅጣት እንደሆነ ተደንግጎአል። ይህ በእንዲህ እንዳለ የሴት ልጅ ግርዛት በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በተለያዩ ክልሎች እየተፈጸመ ይገኛል። ምንም እንኩዋን ኢትዮጵያ እ.ኤ.አበ2025 የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስቆም የአለምአቀፍ ግብን ለማሳካት ቆርጣ ብትነሳም የሴት ልጅ ግርዛት ተጠቂዎች የህክምና አገልግሎት ለመስጠትና የተለያዩ የማህበረሰብ ግንዛቤዎችን የመፍጠርና የማዳረስ እንዲሁም የመከላከል ስራዎችን ለማሳካት ብዙ ተግዳሮቶች ከፊትዋ እንደሚጠብቁዋት ይጠበቃል። ስለሆነም የህክምና እርዳታን ማሻሻል የማህበረሰብ ግንዛቤን የተሸለ ማድረግና በተሻለ ሁኔታ መምራት የላቀ ጠቀሜታ እንደሚኖራቸው ይገመታል።” ብለዋል።
እ.ኤ.አ በ2025 የሴት ልጅ ግርዛትን በአጠቃላይ ለማስወገድ አለም አቀፉ ሕብረተሰቡ ቃል የገባ ሲሆን ኢትዮጵያም አንዱዋ ነች። ስለዚህም ይህንን በሴቶች ልጆች ላይ ድርጊቱ ከሚፈጸም ባቸው ወቅት አንስቶ እስከዘለቄታው ድረስ የአካል እና የስነልቡና ጉዳት ብሎም ሕይወትን እስከመ ቅጠፍ ለሚያበቁ ሕመሞች የሚያጋልጥ ድርጊት ለማስቆም የተለያዩ እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚገባ ለመምከር ከተሰበሰቡት መካከል የተወሰኑትን ለዚህ አምድ አነጋግረናቸዋል።
“...ፋጡማ እባላለሁ። የመጣሁት ከኢትዮጵያ ሱማሌ ከጅግጅጋ ነው። በክልላችን በእርግጥ መረጃው አለ። ግን ድርጊቱ ላይ ለውጥ አለ ቢባልም አሁንም ሴት ልጆች ብልታቸውን ከመተልተል አልዳኑም። ግርዛቱ በሴቶች ላይ የሚያስከትለውን ችግር በተመለከተ ገና አሁንም እየተጎዱ ያሉ ብዙ ናቸው። ከአስርና አስራአምስት አመት በፊት የተገረዙ ሆነው ነገር ግን በዚያ ምክንያት የሚሰቃዩ ብዙ ሴቶች መኖራቸውን ጥናቶችም ያሳያሉ። ግርዛቱን በሚመለከት ግን አሁን በተለይም ከሶስት አመት ወዲህ በተለይም በከተሞች አካባቢ ግርዛት የለም ማለት ይቻላል። ነገር ግን በገጠራማው ክፍል አሁንም ገና ነው። በከተሞችም ቢሆን ሊቀንስ የቻለው ህብረተሰቡን በተለያዩ መድረኮች ለማስተማር ጥረት ስለተደረገ ነው። ሰዎችን ማስተማር ቀላል አይደለም። መጀመሪያ ሲነገራቸው ሁሉም ይቃወማሉ። ነገር ግን ችግሩን በእርጋታ ሲሰሙ ይቀበሉታል። በዚህም የሀይማኖት አባቶች፣ የሴቶች ቢሮዎች ፣የጤና ቢሮ እና ሌሎችም የሚመለከታቸው ተቀናጅተው እየሰሩ በመሆኑ ለውጥ ታይቶአል። ግን ይህ ልማድ በቀላሉ የሚወገድ አይደለም። አላህ ካለ በ2025 ሊጠፋ ይችላል።...”
ከአፋር ክልል የመጡ ተሳታፊዎችም ለዚህ አምድ እንግዶች ነበሩ።
“...አይሻ አብደላ እባላለሁ። የመጣሁት ከአፋር ክልል ጤና ቢሮ ነው። በአፋር የሴት ልጅ ግርዛት ከፍተኛ ነው። ነገር ግን በተወሰነ መልኩ አሁን አሁን በተለይም በከተሞች እየቀነሰ ነው። ትንሽ እያስቸገረ ያለው በገጠሩ አካባቢ ነው። በአብዛኛው የአኑዋኑዋር ባህርይው ከቦታ ቦታ የሚያንቀሳቅሳቸው ስለሆነ ለማስተማርም አስቸጋሪ ስለሆነ ነው። ...”
“...እኔ ስሜ ኡስማን አብዱ ይባላል። የመጣሁት ከአፋር ክልል ነው። በሙስሊም እምነት የሴት ልጅ ግርዛት ምንም መሰረት የሌለው ነው። እስልምና ስለሴት ልጅ ግርዛት ምንም የሚገልጸው የለም። የሴት ልጅ ግርዛት በጤናና ስነልቡና ላይ ከፍተኛ ጉዳት ስለሚያደርስ ያንን ለማስወገድ የተቻለውን ጥረት ለማድረግ አንዳንድ ስራዎች ተጀምረዋል። ለጤና ባለሙያዎችና የጤና ኤክስንሽን ሰራተኞች በሴት ልጅ ግርዛት አስከፊነት ላይ በጽንስና ማህጸን ሕክምና ባለሙያዎች አማካኝነት ስልጠናዎች ተሰጥተዋል። የሀይማኖት አባቶችና ሌሎች የሚመለከታ ቸው የህብረተ ሰቡ አባላት ባሉበትም የተለያዩ ንቃተ ህሊናን የሚያዳብሩ ስራዎች እየተሰሩ ስለሆነ ለውጥ ለማምጣት ያስችላል የሚል እምነት አለኝ።...”
ጥሪ ከተደረገላቸው የእምነት ተቋማት ከኦርቶዶክስ የመጡት አባትም የሚከተለውን ብለዋል።
“...መላከ ሕይወት ቆሞስ አባ ወልደጊዮርጊስ እባላለሁ። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተሰክርስቲያን ጠቅላይ ጽህፈት ቤት የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ምክትል መምሪያ ኃላፊ ነኝ። መምሪያው ለሕዝብ ተደራሽ የሆነ አገልግሎት የሚሰጥ በመሆኑ በዚህ መድረክ የሚቀርበውን ቁምነገር በቀጣይ ለባለድርሻ አካላት ለማድረስ ይቻላል በሚል ነው የተሳተፍኩት። ለሴት ልጅ ግርዛት እንደማይገባ ለይቶ የወንድ ልጆች ግርዛት መፈጸም እንዳለባ ቸው እግዚአብሔር ለወዳጁ ለአብረሐም ነግሮታል። በዚህም መሰረት ሰዎች በአስተሳሰብ ወይ ንም በአመለካከት ጉድለት ምክንያት የአብረሀም ዘር መሆናቸውን የሚለይ በመሆኑ ወንዶችም ሴቶችም መገረዝ አለባቸው በሚል ነገሩ ከ2000 አመት በላይ ሲከናወን መጥቶአል። ነገር ግን ከአስራ አምስት አመታት በላይ በስፋት በስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ በየ ክልሉና ዞኑ ላሉ የወንጌል መምህራን ከኤችአይቪ ፕሮጀክት ጋር በማያያዝ ስልጠና ስለተሰጠ በአሁኑ ሰአት መቶ በመቶ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ተደራሽ ሁኖ የሴት ልጅ ግርዛት እንዲቆም የሚያስችል ስራ ተሰርቶአል ማለት እችላለሁ። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተሰክርስቲያን የሴት ልጅ ግርዛትን ፈጽማ ትቃወማለች።...” ሲሉ ለአምዱ አዘጋጅ ገልጸዋል።

Read 3827 times