Saturday, 31 December 2016 11:50

“ኢትዮጵያዊ ኮንሰርት” በገና ዋዜማ ይካሄዳል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

 የተለያዩ የመዝናኛ ዝግጅቶችን በማዘጋጀት የሚታወቀው ጆርካ ኤቨንት ኦርጋናይዘር ከሀበሻ ቢራ ጋር በመተባበር በገና ዋዜማ ከቀኑ 11፡00 ጀምሮ ‹‹ኢትዮጵያዊ ኮንሰርት›› የተሰኘ የሙዚቃ ድግስ በላፍቶ ሞል ያቀርባል፡፡ 3 ሚ. ብር ወጥቶበታል በተባለው የዋዜማው ኮንሰርት ላይ ቤቲ ጂ.፣ ጃኪ ጎሲ፣ ሳሚ ዳን፣ ልጅ ሚካኤል፣ ታደለ ሮባ፣ ዳዊት ነጋ፣ ያሬድ ነጉ፣ ሳሚ ጎ. እና አለምዬ (ዋሸሁ እንዴ) የሙዚቃ ስራዎቻቸውን እንደሚያቀርቡ አዘጋጆቹ ገልፀዋል፡፡ በዋዜማው መሀሪ ብራዘርስ ባንድ፣ ዜማ ባንድ፣ ወዛመይ ባንድ፣ ዘውድ ባንድና ታዋቂ ዲጄዎች የሙዚቃ ድግሱን ያደምቁታል።
ከ4-5ሺ የሚደርሱ ሰዎች እንደሚታደሙበት በሚጠበቀው የገና ዋዜማ ኮንሰርት ላይ የመግቢያ ዋጋ ኖርማሉ 200 ብር፣ ለጥንዶች 300 ብር፣ ቪአይፒ 500 ብር ሲሆኑ  ቀድመው ትኬት ለሚገዙ አንድ ሺህ ሰዎች፣ ትኬቱ በ150 ብር እንደሚሸጥ አዘጋጆቹ ጠቁመዋል።  ከተዘጋጁት 5 ሺህ ትኬቶች፣ 1 ሺህ ያህሉ እጣ ያላቸው ሲሆን እድለኞችን “ሰርፕራይዝ” የሚያደርጉ ሽልማቶችም ተዘጋጅተዋል ተብሏል።
ትኬቶቹ በተለያዩ ሞሎች፣ ካፌዎችና ሬስቶራንቶች የሚሸጡ ሲሆን በቅርቡ የቦታዎቹ ስሞች ይገለጻሉ ተብሏል፡፡

Read 918 times