Sunday, 01 January 2017 00:00

የጀግናው ሻምበል ምሩፅ ይፍጠር አሸኛኘት

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(2 votes)

ሻምበል ምሩፅ ይፍጠር በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፈር ቀዳጅ ከሆኑት ኦሎምፒያኖች ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ነው፡፡ በሩጫ ዘመኑ በዓለም ሻምፒዮና እና በኦሎምፒክ መድረክ 7 የወርቅ ሜዳልያዎች ለኢትዮጵያ አበርክቷል። በሁለት ኦሎምፒኮች በመሳተፍ 2 የወርቅ እና 1 የነሐስ የኦሎምፒክ ሜዳልያዎች ተጎናፅፏል፡፡   በ1972 እኤአ  በሙኒክ ኦሎምፒክ በ10ሺ ሜትር የነሐስ ሜዳልያ እንዲሁም በ1980 እኤአ በሞስኮ ኦሎምፒክ በ10ሺ እና በ5ሺ ሜትር ያስመዘገባቸው ሁለት የወርቅ ሜዳልያዎች  በኢትዮጵያና በአፍሪካ የረጅም ርቀት አትሌቲክስ ታሪክ ፈርቀዳጅ ስኬቶች ናቸው፡፡ በ1973 እኤአ ላይ በመላው የአፍሪካ ጨዋታዎች በ10ሺ የወርቅ ሜዳልያ እንዲሁም በ5ሺ የብር ሜዳልያ፤ በአይኤኤኤፍ ዎርልድ ካፕ በ1977 እኤአ በጀርመን ዱስልዶርፍ በ10ሺ ሜትር እና በ5ሺ ሜትር ሁለት የወርቅ ሜዳልያዎች እንዲሁም በ1979 እኤአ በካናዳ ሞንትሪያል በ10ሺ ሜትር እና በ5ሺ ሜትር ሁለት የወርቅ ሜዳልያዎች፤ በ1979 እኤአ  በመጀመርያው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በሴኔጋል ከተማ ዳካር በ10ሺ ሜትር እና በ5ሺ ሜትር ሁለት የወርቅ ሜዳልያዎችን ለመሸለምም በቅቷል፡፡ በረጅም ርቀት ሯጭነቱ ባለፈባቸው የሩጫ ዘመናት ከ410 በላይ ውድድሮች የተሳተፈ ሲሆን፤ በ271 ውድድሮች በከፍተኛ ብቃት በማሸነፍ አስደናቂነቱን በታሪክ አስመዝግቧል፡፡ በዚህ አስደናቂ ስኬትም ነው፤ አለም አቀፍ  የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር የወርቅ የክብር ሽልማት የሰጠው፡፡

---------------------

    የጀግናዉ አትሌት፤ ፈርቀዳጅ ኦሎምፒያን ሻምበል ምሩፅ ይፍጠር የቀብር ስነስርዓት በነገው እለት በቅድስት ስላሴ ቤተክርስትያን ይፈፀማል፡፡  ሻምበል ምሩፅ ይፍጠር በሳምባ ጽኑ በሽታ በ72 ዓመቱ ያረፈው ታኅሣሥ 13 ቀን 2009 ዓ.ም. መሆኑ ይታወሳል፡፡ የ‹‹ማርሽ ቀያሪው›› ምሩፅ ይፍጠር አስክሬን ነገ  ጠዋት 1፡00 ሰዓት ላይ  ቦሌ አየር ማረፊያ ይደርሳል፡፡ የቀድሞና የአሁን ዘመን አትሌቶች፤ አሰልጣኞች፤ የአትሌቲክስ ፌደሬሽን ባለስልጣናት፤ የስፖርት ቤተሰቡ፤ አድናቂዎቹ፤ ጋዜጠኞች በስፍራው ይገኛሉ፡፡ ለምሩፅበክብር ዘብ ልዩ አቀባበል ከተደረገለት በኋላ ቦሌ ዩጎ ክለብ አካባቢ ወደሚገኘው መኖሪያ ቤቱ ይሸኛል፡፡ ቀጣዩ መርሃ ግብር የሚሆነው፤ በቤተሰቡ መኖሪያ ቤት ሲሆን የክብር መዝገብ ስለተዘጋጀ የሀዘን መግለጫና ሌሎች መልዕክቶች በቅደም ተከተል እንዲሰፍሩ ይደረጋል። ከዚያም  ከመኖሪያ ቤቱ 5፡00 ሰዓት ላይ በመነሳት የምሩፅ አስክሬን በልዩ ሁኔታ በተዘጋጀ ሰረገላ ተጭኖ በመታጀብ የቀብር ስነስርዓቱ ወደሚፈፀምበት ቅድስት ሥላሴ መንበረ ጸባኦት ቤተ ክርስቲያን ጉዞ ይሆናል፡፡ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አትሌት፤ ሻለቃ ኃይሌ ገ/ሥላሴ ለስፖርት አድማስ የገለፀው  በተለይ ከቤተ መንግሥት እስከ ሥላሴ ቤተ-ክርስቲያን ድረስ የምሩፅን አስክሬን የያዘው ሰረገላ በማርሽ ባንድ እንዲታጀብ መታሰቡን ነው። በቅድስት ሥላሴ ቤተ-ክርስቲያን ቀብሩ ከመፈፀሙ በፊት የህይወት ታሪኩ የሚነበብ ሲሆን፤ ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን፣ ከኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ፤ ከወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር እንዲሁም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት በተወካዮች በኩል  ንግግሮች ቀርበው የአበባ ጉንጉንኖችም በቅደም ተከተል ተቀምጠው ስነስርዓቱ ይፈፀማል፡፡
ሰሞኑን በመላው ዓለም በተለያዩ የሚዲያ አውታሮች ምሩፅን በተመለከተ በርካታ ዘገባዎች ተሰርተዋል፡፡ ካናዳ ብሮድካስቲንግ ሰርቪስ፤ ቢሲ፤ ሲኤንኤን፤ አልጀዚራ፤ የአሜሪካዎቹ ዋሽንግተን ፖስት፤ ኒውዮርክ ታይምስና ሎሳንጀለስ ታይምስ፤ ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር፣ አትሌቲክስ ዊክሊ፣ ታዋቂዎቹ የስፔን ጋዜጦች ኤልሙንዶና ማርካ፣ የእንግሊዞቹ ጋርዲያንና ቴሌግራፍ፣ የጀርመን፣ ራሺያ፣ የጃፓንና የአፍሪካ አገራት ታላላቅ ሚዲያዎች ይጠቀሳሉ፡፡ በተለያዩ ቋንቋዎች ስለ ምሩፅ ይፍጠር ፈር ቀዳጅነት በማንሳት እና አስደናቂ ጀብዱዎቹን በማውሳት በጋዜጦቻቸው እና በድረገፆቻቸው በስፋት ዘክረውታል፡፡ በሬዲዮና በቴሌቪዥን ፕሮግራሞቻቸውም አውርተውለታል፡፡
 ‹‹ምን ትጠብቃለህ… ስለው ያፈተልካል››
ሻምበል ቶሎሳ ቆቱ
ሻምበል ቶሎሳ ቆቱ በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ብሔራዊ ቡድን የ10 ሺ እና የ5 ሺ ሜትር ዋና አሰልጣኝ ናቸው፡፡ እንደ ምሩፅ አትሌት ፤ አንጋፋ ኦሎምፒያንና የረጅም ርቀት ምርጥ ሯጭ ነበሩ፡፡ ምሩፅን በምን ያስታውሱታል በሚል ከስፖርት አድማስ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ ‹‹ትዝ የሚለኝ ምሩፅ ማንንም ተወዳዳሪ አይንቅም ነበር፡፡ ሁሌም ቁምጣ ለብሶ የገባ አትሌት እስክታሸንፈው ጠንካራ ተፎካካሪህ ነው ይል ነበር፡፡ በፍፁም መሸነፍን አይፈልግም። በሚገርም ትጋትና በከፍተኛ ጥረት በሚሰራቸው ልምምዶች ያስደንቀኝ ነበር›› ብለዋል፡፡
ሻምበል ቶሎሳ ቆቱ ምሩፅን የሚያውቁት ከ1963 ዓ.ም ጀምሮ ነው፡፡ ሩጫ ስፖርት የጀመረው ከሳቸው ቀደም ብሎ ነው፡፡ በአስመራ ከነአበበ እና ማሞ ወልዴ ጋር ልምምድ ይሰራ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ከአስመራም በኋላ ደብረዘይት በሚገኘው አየር ኃይል ከገባ በኋላ የተሻለ ልምድ እንደነበረው ጠቅሰውም፤ ያኔ  በ1500 እና በ 800 ሜትሮች ይሮጡ እንደነበር እነምሩፅም  ከደብረዘይት አየር ኃይል፣ እነ ውሂብ ማስረሻ ከምድር ጦር የወጡ ታላላቆቻቸው የነበሩ የረጅም ርቀት ሯጮች መሆናቸውን ይገልፃሉ፡፡ ሻምበል ቶሎሳ ቆቱ ከእነምሩፅ ጋር ያሳለፉትን ታሪክ ለስፖርት አድማስ ሲያጫወቱ ከተናገሯቸው ሁኔታዎች  በአዲስ አበባ ስታዲየም በኳስ ጨዋታዎች ጣልቃ ማለትም በእረፍት ሰዓት ይደረጉ ስለነበሩት የአትሌቲክስ ውድድሮች ያነሱት ይገኝበታል፡፡ በመካከለኛ ርቀት እነ ምሩፅና ሌሎቹም የረጅም ርቀት ሯጮች የሚሳተፉባቸው ውድድሮች በከፍተኛ የተመልካች ድጋፍ እና ትኩረት የሚካሄዱበትን ሁኔታ ሲያስታውሱም፡፡ “አንዳንዴ አሸንፈነዋል ፡፡ ብዙውን ጊዜ ግን በፍፁም የበላይነት ደጋግሞ ያሸንፈን ነበር” ብለው  ‹‹እንደውም በጓደኞቻችን መካከል ስናወራ ከደብረዘይት የምትመጣው አጭር ተወዳዳሪን አልቻልናትም እያልን እንነጋገር ነበር›› ሲሉ ትዝታቸውን አውግተዋል፡፡
በ1980 እ.ኤ.አ ሞስኮ ላይ ሲካሄድ ለኢትዮጵያና ለአፍሪካ የረጅም ርቀት ሩጫ ፈር ቀዳጅ ገድል እና ታሪክ የተሰራበት ነበር፡፡ ሻምበል ቶሎሳ ቆቱም ይህን ታሪካዊ የኦሎምፒክ ተሳትፎ ለስፖርት አድማስ በማስታወስ ሲያወጉ፡፡ ‹‹በዚያም ኦሎምፒክ በረጅም ርቀት ውጤታማ ይሆናሉ በሚል ብዙ የሚወራው ስለፊላንዶቹ አትሌቶች ላርስ ቪረንና ካርል ማኒንካ ነበረ፡፡ ትዝ የሚለኝለአምስትሺ ሜትር የፍፃሜ ውድድር ወደ ሞስኮው  ሉዝንስኪ ውስጥ ስንገባ ተመልካቹ ስታዲየሙን በፊላንድ ባንዲራ አጥለቅልቆታል፡፡ በተሰጠን አነስተኛ ግምት ተናድደናል፡፡ ግን ሁላችንም ሜዳሊያዎቹን ጠቅልለን ለመውሰድ እቅድ ነበረን፡፡ በዛ ሁሉ የፊላንድ ባንዲራዎች መካከል አንዲት የኢትዮጵያ ባንዲራ ከሩቅ ተመለከትንና ውድድሩ ከመጀመሩ በፊት  ትራኩ ላይ ተሰበሰብን እኔ፤ ምሩፅና መሀመድ ከድር። ለዛች ባንዲራ እንሙትላት ብለን ተነጋገርን፡፡ ውድድሩ ተጀመረ፤ እያንዳንዱን ዙር ስንሮጥ የነበረው እየተመካከርን ነበር፡፡ የመጨረሻው ዙር እስኪደርስ እኔና መሀመድ ከድር አብዛኛውን ዙር እየተፈራረቅን ስንመራ ነበር፡፡ ምሩፅ እንዳደፈጠ ነው፡፡ 400 ሜትሮች ሲቀሩ ጠጋ አልኩትና ምን ትጠብቃለህ ስል ጮህኩበት፤ በቃ ድንገት ነው ያፈተለከው። እኔም በድንጋጤ እሱን ስመለከት ጉልበት እየራቀኝ መጣ። ሁለቱንም የፊላንድ አትሌቶች በምናከረው የዙር አሯሯጥ አዳክመናቸዋል፡፡ ምሩፅ ባፈተለከበት ፍጥነት ገባና አሸነፈ። መሀመድ ከድር ተከተለው፡፡ በሜዳልያ ሰንጠረዡ የፊላንዱ አትሌት ጣልቃ ገባ፡፡ እኔ አራተኛ ሆኜ ጨረስኩ። የሚገርመው የዚያን ጊዜ የፊላንዱ አትሌት በዶፒንግ የሚጠረጠር ነበር፡፡ በፌዴሬሽናችን በኩል አቅም ስላልነበር የሚከራከር ጠፍቶ እንጅ ከአንድ እስከ ሦስት ሜዳሊያውን የምንጠቀልልበት እድል ቢኖርም ተበላሽቷል” ብለዋል፡፡
ሻምበል ቶሎሳ ቆቱ የዚህ ዘመን አትሌቶች ከምሩፅ ጀግንነት፣ የልምምድ ትጋት ብዙ እንዲማሩ ይፈልጋሉ። ይህንንም በቀጣይ በሚያከናውኗቸው ስራዎቻቸው በትኩረት ሊሰሩበት ፍላጎት አላቸው፡፡ በመጨረሻ ግን  “ምሩፅ በጣም ጀግና አትሌት ነው፡፡ የትም ይሁን ለጀግና የሚሰራ ሀውልት ያስፈልገዋል፡፡ መንግስትም ትኩረት ሰጥቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር ኮሚቴ አዋቅሮ እየተንቀሳቀሰበት እንደሆነ አውቃለሁ፡፡ ከነ ኃይሌም ጋር ስንመካከር ለምሩፅ ብቻ ሳይሆን ለዶ/ር ወልደመስቀል ኮስትሬም ይገባል እያልን ነበር፡፡” በማለት አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
‹‹ ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ጀግኖችና ባለታሪኮች የተለያዩ መታሰቢያዎች ያስፈልጋሉ፡፡›› አሰልጣኝ ካሱ አለማየሁ
አሰልጣኝ ካሱ አለማየሁ በአሁኑ ወቅት በብሔራዊ ቡድን የ10 ሺና የ5ሺ ሜትር ምክትል አሰልጣኝ ናቸው፡፡ ምሩፅን ከ1968 ጀምሮ እንደሚያውቁት ለስፖርት አድማስ ሲናገሩ፤ በተለይ የማይረሱት  በተለያዩ አገር አቀፍ ከዚያም ዓለም አቀፍ ውድድሮች በ5 ሺ እና በ10 ሺ ሜትር ብዙ ፈር ቀዳጅ ታሪኮችን መስራቱን በማስታወስ እና በርካታ ውድድሮችን በማሸነፍ የሚስተካከለው እንዳልነበርም በመጥቀስ ነው፡፡ ‹‹ከነ ምሩፅ በፊት በአበበ በቂላና በማሞ ወልዴ ምክንያት ከረጅም ርቀት ይዘወተር የነበረው ማራቶን ብቻ ነበር፡፡ ሁሉም ክለቦች በተለይ አየር ኃይል፣ ባህር ኃይል፣ ምድር ጦር እና ሌሎችም ትኩረታቸው የአጭር ርቀት ውድድሮች ናቸው፡፡ በ5 ሺ እና በ10 ሺ ትኩረት መደረግ የጀመረው በተለይ በምሩፅ ይፍጠር ስኬቶች አነሳሽነት ነው። ምሩፅ አበበን እየሰማ አበበ አበበ እያለ ነው ወደ ሩጫ የገባው፡፡ ኃይሌ ደግሞ ምሩፅን እየሰማ ምሩፅ ምሩፅ እያለ  የሩጫ ዘመኑን አሳለፈ›› ብለዋል አሰልጣኝ ካሱ አለማየሁ
‹‹ለምሩፅ ብቻ አይደለም ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ጀግኖችና ባለታሪኮች የተለያዩ መታሰቢያዎች ያስፈልጋሉ። ሀውልቶች፣ የስፖርቱን ታሪክ እንደቅርስ የሚያኖርና የሚያስተዋውቅ ልዩ ሙዚየም ይገባሉ፡፡ በየጊዜው በሚገነቡ የስፖርት ማዕከላት፣ ስታዲየሞችና ሌሎች የስፖርት መሰረተ ልማቶች በስማቸው መታሰቢያ ያስፈልጋል፡፡ እንደውም እንደምሩፅ አይነት ጀግና አትሌቶች የህይወት ተሞክሯቸውና የሩጫ ዘመናቸው በትምህርት ካሪኩለም ውስጥ ገብቶ ለትውልድ ቢተላለፍ ነው ሀሳብ የምንሰጠው።›› በማለትም አሰልጣኝ ካሱ አለማየሁ መልዕክታቸውን በስፖርት አድማስ አስተላልፈዋል፡፡
‹‹ከምሩፅ የወረስኩት ወኔውን ነው››ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት የሆነው ታላቁ አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ ለስፖርት አድማስ በሁለት ሁኔታዎች ላይ አስተያየት ሰጥቷል፡፡ የመጀመርያው በ7 ዓመቱ የምሩፅ ተምሳሌትነት ስለተረዳበት ልዩ አጋጣሚ ሲሆን ሌላኛው ምሩፅን ተምሳሌት ያደረገበትን ተመክሮ የገለፀበት ናቸው፡፡
‹‹ገጠር ነበርኩኝ፤ የዕለት ተዕለት ስራዬም ከብቶች ማገድ ነበር፡፡ በቤታችን ሬዲዮ ስለምሩፅ እየተሰማ ነው፡፡ ዛሬም ደግሞ ድል አደረገ ይላል ጋዜጠኛው፡፡ የገረሙኝ ዜናውና ሌሎች ዘገባዎች አልነበሩም፤ ጎን ለጎን ለጀግንነቱ ማወደሻ  የሚቀርቡት ሙዚቃዎች እና ግጥሞችን ነበሩ፡፡ ገና 7 ዓመቴ ቢሆንም በአድናቆት ፈዝዤ  ስሰማ እንደነበር አስታውሳለሁ፤  ስሜታዊ ነገር ነበርኩ፡፡ ምሩፅ አሸነፈ ምናምን እያሉ ሲያወሩ ሰው ሁሉ አልመሰለኝም ነበር፡፡ ምንድነው ያሸነፈው አላስጨነቀኝም፡፡ ግን ለሱ እንደተዘፈነው ለእሱ እንደተገጠመው ለእኔስ ብዬ ተመኘሁ፡፡ ከዚያማ በቃ በየቀኑ ምሩፅ ነኝማለት ጀመርኩ፡፡ ከጓደኖቻችን ጋር ወደ ትምህርት ቤት ለመድረስ እየተሯሯጥን ስንፎካከር ‹‹ምሩፅ እኔ ነኝ›› ማንም ሊነጥቀኝ አይችልም ነበር፡፡ ከስሜ ይልቅ ምሩፅ እያሉ ይጠሩኝም ነበር፡፡
‹‹ከምሩፅ ትልቅ የተማርኩት ጠንካራው ልምምዱ፤ ማርሽ ቅየራው ሌላው ሌላው የአሯሯጥ ታክቲክ አልነበረም። ለማንኛውም ውጤት እነዚህ ሁኔታዎች 50 በመቶ ድርሻ ቢኖራቸው ነው፤ ሌላው 50 በመቶ ጀግንነቱና ወኔው ነው። ከምሩፅ የተማርኩትም ይህንኑ አልሸነፍ ባይነትና ወኔው ነው፡፡        
‹‹የምሩፅን ጀግንንት  ዛሬም ልንከተለው ይገባል፡፡›› አትሌት ገ/እግዚአብሔር ገ/ማርያም
ከአዲግራት ከተማ ከተገኘው ምሩፅ በኋላ ከትግራይ ክልል ጠንካራና ውጤታማ አትሌቶች በየጊዜው እየወጡ ቆይተዋል፡፡ አትሌት ገ/እግዚአብሔር ገ/ማርያም፣ ደጀን     ገ/መስቀል እና ሀጎስ ገ/ህይወት ይገኙበታል፡፡ “ምሩፅ ለእኔ የሩጫ ፈር ቀዳጅ፤ ለወርቅ የሚያበቃ የማሸነፍ ታክቲክ ያስተዋወቀ፤ በአፍሪካ፤ በዓለም ሻምፒዮናና በኦሎምፒክ የተሳካለት ምርጥ ተምሳሌት ነው፤ በተለይ አንድ ጀግና ከፊት ለፊት ሲመጣ ከአካባቢህ ሲገኝ ያነሳሳል፡፡ እኛም የዛ ውጤት ነን” በማለት በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት የሆነው አትሌት ገ/እግዚአብሔር ገ/ማርያም ይናገራል፡፡ ‹‹ምሩፅን ሁልጊዜም በሚሰጠኝ ምክር  እንደ አባት ነበር የምቀርበው፡፡ መሸነፍ የሚለው ነገር አዕምሮዬ ውስጥ እንዳይገባ ይነግረኛል። ለማሸነፍ ብቻ ወደ ውድድር እንድገባ ነው የሚያነሳሳኝ።› ሲልም ለስፖርት አድማስ አስተያየት ሰጥቷል፡፡ ምሩፅ በሩጫ ዘመኑ የሰራቸውን ታላላቅ ስራዎችና ታሪኮች እየዘከርን፤  ጀግንነቱን ዛሬም ልንከተለው ይገባል በሚልም መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡                 

Read 496 times