በደሴ ሼህ ኑር ይማምን ገድላችኋል የተባሉ ተከሳሾች ትላንትና በዋለው ችሎት ጥፋተኛ የተባሉ ሲሆን የቅጣት ውሳኔ ለመስጠት ለጥር 9 ተቀጥረዋል፡፡
በእነ አህመድ እንድሪስ መዝገብ ክስ የተመሰረተባቸው 12 ግለሰቦች ያቀረቡት መከላከያ በሙሉ ውድቅ የተደረገባቸው ሲሆን፤ ጉዳዩን እየመረመረ የቆየው የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ችሎት፣ በትላንትናው ዕለት ጥፋተኛ ብሏቸዋል፡፡
ተከሳሾቹ መጀመሪያ 14 የነበሩ ሲሆን 9ኛው ተከሳሽ ሙባረክ ይመር፣ ጥር 5 ቀን 2008 ዓ.ም ጉዳዩን በማረሚያ ቤት ሆኖ በመከታተል ላይ ሳለ፣ በድንገተኛ ህመም ህይወቱ ማለፉ ተጠቁሟል፡፡ ተከሳሾቹ በ2004 ዓ.ም በደሴ ከተማ ታዋቂ የሃይማኖት መምህር የነበሩትን ሼህ ኑር ይማምን በጥይት መግደላቸውን ፍ/ቤቱ በማስረጃዎች ማረጋገጡን አመልክቷል፡፡
በሌላ በኩል እስላማዊ መንግስት ለመመስረትና የሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላትን ለማስፈታት ተንቀሳቅሰዋል የተባሉት በእነ ነቢል ሲራጅ መዝገብ የተከሰሱ 7 ተከሳሾች ትናንት፤ እስከ 3 ዓመት ከ11 ወር ቅጣት ተላልፎባቸዋል፡፡
Monday, 09 January 2017 00:00
ሼህ ኑር ይማምን ገድላችኋል የተባሉ 13 ተከሳሾች ጥፋተኛ ተባሉ
Written by ማህሌት ፋሲል
Published in
ዜና