Print this page
Monday, 09 January 2017 00:00

ኢንሹራንሽ ኩባንያዎች ለትራፊክ አደጋ ከፍተኛ ካሳ ይከፍላሉ ተባለ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

ዓቻምና 2.4 ቢ. ብር ከፍለዋል
  ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመጣው የመንገድ ትራፊክ አደጋ ኢንሹራንስ ኩንያዎች በየአመቱ ከፍተኛ መጠን ያለው የካሳ ክፍያ እንደሚከፍሉ የተገለፀ ሲሆን በ2007 ዓ.ም በአደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው አውቶሞቢሎች 2.6 ቢሊዮን ብር መክፈላቸው ታውቋል፡፡
ይና ቢዝነስ ፕሮሞሽን ከትራንስፖርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ባዘጋጀው 1ኛው የትራፊክ ደህንነት ኮንፍረንስ ላይ የተለያዩ ባለ ድርሻ አካላት የተገኙ ሲሆን በጉባኤው መክፈቻ ላይ እንደተገለፀው፤ የመንገድ ትራፊክ አደጋ በየጊዜው እየጨመረ መምጣቱንና አቻምና ብቻ 17ቱ የኢንሹራንስ ኩንያዎች በድምሩ 2.4 ቢሊዮን ብር ለተሽከርካሪ አደጋ የካሳ ክፍያ መክፈላቸው ተገልጿል፡፡
በተለይ የበዓላት ሰሞን ሰዎች ከፍተኛ እንቅስቃሴ የሚያደርጉበትና አሽከርካሪዎችም ሆነ እግረኞች የአልኮል መጠጥ አብዝተው የሚወስዱበት  በመሆኑ አደጋው እንደሚጨምር በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ  ፕሮፌሰር፣ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ከፍተኛ ስፔሻሊስትና የኢትዮጵያ አጥንት ህክምና ማህበር ፕሬዚዳንት የሆኑት ዶ/ር ብሩክ ላምቢሶ ተናግረዋል፡፡፡
ዶ/ር ብሩክ አቻአምና በገና ሰሞን በአንድ ወር ውስጥ 58 የመኪና አደጋዎች ኬዞች እንደተከሰቱ ገልፀው፤ ባለፈው ዓመት በገና ሰሞን በ1 ወር ውስጥ 70 ያህል የመኪና አደጋ ተጎጂዎች ለህክምና መምጣታቸውን ጠቁመው ጥንቃቄ ካልተደረገ የዘንድሮው ከዚህም ሊብስ እንደሚችል አሳስበዋል፡፡
ዶ/ር ብሩክ እደገለፁት ከመንገድ ትራፊክ ጋር በተያያዘ ባለፈው ዓመት 1493 የአደጋ ቀዶ ጥገናዎች መካሄዳቸውን አስታውሰው፣ ዘንድሮ ገና ዓመቱ ሳይጋመስ 1788 የአደጋ ቀዶ ጥገናዎች መሰራታቸውንና በየዓመቱ የአደጋው መጠን 70 በመቶ እየጨመረ መምጣቱን ጠቁመዋል፡፡
የጠብታ አምቡላንስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ክብረት በጉባኤው ላይ ባደረጉት ንግግር፤ “የትራፊክ አደጋን አስመልክቶ የሚዘጋጁ ጉባኤዎች አስፈላጊ ቢሆኑም ለውጥ እስካላመጡ ድረስ ፋይዳቸው አይታየኝም” ብለዋል፡፡ ሹፌርን እንዳልተማረ እየቆጠርን ከትራፊክ አደጋ እንድናለን ማለት ዘበት ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ከሁሉም በፊት የሰውን አመለካከት የመቀየር ስራ አማራጭ የሌለው የሁሉም የቤት ስራ ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ባለፈው አመትና በያዝነው ሩብ አመት ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ከተሽከርካሪ አደጋ ጋር በተያያዘ ስለከፈሉት የካሳ ክፍያ መረጃ ከሰጡን መካከል ቡና ኢንሹራንስ አክሲዮን ማህበር ባለፈው አመት ከ42 ሚ. ብር በላይ መክፈሉንና በያዝነው ሩብ አመት ብቻ እንኳን ከ30 ሚ. ብር በላይ ካሳ መክፈሉን የኩባንያው የገበያ እቅድና ቢዝነስ ልማት ስራ አስፈፃሚ አቶ እንዳልካቸው ተስፋዬ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡

Read 2578 times