Monday, 09 January 2017 00:00

ምሁሩ ለአ.አ.ዩ. ጥንታዊ መፃህፍትን አበረከቱ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

100 ሺ ዶላር የሚገመት የገንዘብ ኖቶችም ለግሰዋል
ታዋቂው የእርሻ ምጣኔ ሀብት እና የገጠር ልማት ባለሙያ ዶ/ር ጌታቸው ተድላ በቀላሉ የማይገኙ ከ100 በላይ ጥንታዊ መፃህፍትንና የኢትዮጵያን ጨምሮ በየዘመኑ የነበሩ የተለያዩ ሀገራት የመገበበያ ሳንቲሞችና የገንዘብ ኖቶችን ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቤተ መፅሀፍትና ሙዚየም አስረከቡ፡፡
ለዩኒቨርሲቲው ቤተ መፃህፍት ከዶ/ር ጌታቸው የተበረከቱት ከ100 በላይ ታሪካዊ መፃህፍት ለጥናትና ለምርምር የሚያገለግሉ፣ በገበያ ላይ በቀላሉ የማይገኙ መሆናቸው ተገልጿል፡፡
መፅሀፍቶቹ በአማርኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተፃፉ ሲሆኑ “ህይወቴና የኢትዮጵያ እርምጃ፣” “የፍትሃ ብሄር ህግ”፣ “የአፈወርቅ ተክሌ አጭር የህወት ታሪክ”፣ “ወንጀለኛው ዳኛ” እና ሌሎች በአማርኛ የተፃፉ ታሪካዊ መፅሀፍትን ጨምሮ የኢትዮጵያና የአፍሪካን ታሪክ ያካተቱ የእንግሊዝኛ የድሮ መፅሀፍት መሆናቸወን ዶ/ር ጌታቸው ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡ መፅሀፍቶቹ ለምርምርና ጥናት ከፍተኛ ተፈላጊነት ያላቸው ሲሆኑ ለዶ/ር ጌታቸው ከቤተ መፅሀፍቱ የእውቅና ሰርተፍኬት ተሰጥቷቸዋል፡፡
ለዩኒቨርሲቲው ሙዚየም ደግሞ ከ100 ሺህ ዶላር በላይ የሚገመት ከበርካታ የዓለም ሀገራት ያሰባሰቧቸውን ሳንቲሞችና የገንዘብ ኖቶች በቅርስነት እንዲያዙ ዶ/ር ጌታቸው አስረክበዋል፡፡
“በእድሜ ዘመኔ ያጠራቀምኳቸውን ሳንቲሞች ለሙዚየሙ ይጠቅማል ብዬ ነው የሰጠሁት” ያሉት ዶ/ር ጌታቸው፤ ከኢትዮጵያ በአፄ ምኒልክ ጊዜ የነበረው “አላድ” የተሰኘው መገበያያ ጨምሮ የአፄ ምኒልክ ፎቶግራፍ ያለባቸውን ሳንቲሞችና ከዚያ በኋላ በየዘመኑ የነበሩ የገንዘብ ኖቶችና ሳንቲሞችን አበርክተዋል፡፡ ዶ/ር ጌታቸው ተድላ የእርሻ ምጣኔ ሀብት እና የገጠር ልማት ባለሙያ ሲሆኑ ከ30 ዓመት በላይ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ውስጥ ከ17 ሀገራት በላይ ተመድበው እየተዘዋወሩ ሲሰሩ መኖራቸውን “የህይወት ጉዞዬና ትዝታዎቼ” የሚለው መፅሀፋቸው ይጠቁማል፡፡

Read 4067 times