Monday, 09 January 2017 00:00

መንግስት በአመራሮቹ ላይ እየወሰደ ያለው እርምጃ ግልፅ አይደለም ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(21 votes)

‹‹በሙስና ተጠርጥረው የሚመረመሩት አብዛኞቹ የመንግስት ባለስልጣናት ናቸው” የፌደራል ጠ/አቃቤ ህግ

መንግስት “በጥልቅ ተሃድሶው” ግምገማ የተለያዩ ጉድለቶች ተገኝቶባቸዋል በተባሉ መካከለኛና  ከፍተኛ አመራሮች ላይ እርምጃ መውሰዱን የገለፀ ሲሆን ተቃዋሚ ፓርቲዎች “እርምጃው ግልፅነት ይጎድዋል፤ በሚፈለገው መጠንም አይደለም” ብለዋል፡፡
የትግራይና የአማራ ክልል መንግስታት በቅርቡ በአጠቃላይ ከ1380 በላይ መካከለኛና ከፍተኛ አመራሮችን ከስልጣን ማባረርና ዝቅ ባሉ መደቦች ላይ የመመደብ እርምጃዎች መውሰዳቸውን ያስታወቁ ሲሆን የኦሮሚያ ክልልና የደቡብ ክልል ግምገማዎች ሲጠናቀቁ ተመሳሳይ እርምጃዎች ይወሠዳሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ለማወቅ ተችሏል፡፡
የአማራ ክልል መንግስት 240 አመራሮችን በሙስና ጠርጥሮ የማጣራት ምርመራ እያካሄደ መሆኑን ገልጿል፡፡
የ‹‹ጥልቅ ተሃድሶው›› አካል ነው በተባለው እርምጃ ከሰሞኑ በአዲስ አበባ  በሙስና የተጠረጠሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ያዋለ ሲሆን ተጠርጣሪዎችን የመመርመር ስልጣንን ከፀረ ሙስና ኮሚሽን የተረከበው የፌደራል ፖሊስ፤ በስም ያልተገለፁ የመንግስት ከፍተኛ ሹማምንትን ጨምሮ 130 ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር አውሎ እየመረመረ መሆኑን ገልጿል፡፡ ቀደም ሲል የአዲስ አበባ አስተዳደርም አመራሮችን ጨምሮ 125 ግለሰቦችን በተመሳሳይ የሙስና ወንጀል ጠርጥሮ እየመረመረ መሆኑን አስታውቋል፡፡ ከነዚህ ውስጥ አብዛኞቹ የመንግስት ባለስልጣናት ናቸው ተብሏል፡፡
‹‹መንግስት አመራሩን መፈተሽ አለበት፤ ሙሰኞችን መቅጣት አለበት›› በማለት በተደጋጋሚ ያሳስቡ ከከረሙ ተቃዋሚዎች መካከል አንዳንዶቹ ሰሞኑን መንግስት በአመራሮቹ ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ ግልፅነት እንደሚጎድለው ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ስራ አስፈጻሚ አባልና የፓርቲው የጥናትና ምርምር ኃላፊ አቶ ዋሲሁን ተስፋዬ፤ ‹‹መንግስት በመገናኛ ብዙሃን እርምጃ መወሰዱን ሲገልፅ በእነማን ላይ እርምጃው እንደተወሰደ? እና በምን ጉዳይ የሚሉትን ጥያቄዎች እንድናነሳ የሚያስገድድ ግልፅነት የጎደለው እርምጃ ነው ብለዋል፡፡
“በሙስና የተጠረጠሩ አመራሮች ጉዳይ በግልፅ ለህዝብ መነገር አለበት” የሚሉት አቶ ዋሲሁን ይህ አይነቱ አካሄድ ህዝብ በሚፈልገው ልክ ከግምገማዎቹ ውጤት እንዳያገኝ ያደርገዋል›› ብለዋል አመራሮችን የማባረርና ከደረጃ ዝቅ የማድረግ እርምጃዎች ተወስደዋል የተባለውም ቢሆን ግልፅነት ይጎድለዋል ብለዋል አቶ ዋሲሁን። የመኢአድ ም/ፕሬዚዳንት አቶ ሙሉጌታ አበበ በበኩላቸው፤ “እርምጃዎች የሚወሠዱት ዝም ብሎ እርምጃ እየወሰድን ነው ለማለት ከሆነ የሚፈለገውን ስር ነቀል ለውጥ ሊያመጡ አይችሉም፤ እርምጃው ሲወሰድም ህዝቡ በግልፅ ያጠፉትን ጥፋት እንዲገነዘብ ተዘርዝሮ ተገልፆ መሆን አለበት ይላሉ፡፡
እርምጃ መወሠዱ መልካም መሆኑን የገለፁት አቶ ሙሉጌታ ግን ግልፅነት የጎደለውና የመንግስትን ቁርጠኛ እርምጃም የማያሳይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
‹‹መንግስት ግለሠቦችን ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ስርአቱንና አሰራሩን ገምግሞ እርምጃ መውሰድ ነበረበት፤ አሁን እየታየ ያለው ስርአቱን የመጠገን ሂደት ነው፤ ብለዋል፤ አቶ ሙሉጌታ፡፡
የመድረክ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ የተከበሩ አቶ ገብሩ ገ/ማርያም  በበኩላቸው የእርምጃ አወሣሠዱ ለህዝብ ግልፅ ያልሆነ፣ በማን ላይ ምን እርምጃ ተወሰደ የሚለውን መሰረታዊ ጥያቄ ያልመለሰ በመሆኑ ተቀባይነቱ እምብዛም ነው ሲሉ ተችተዋል።
የእርምጃ አወሳሰዱ የታችኞቹን ብቻ ሳይሆን እስከ ላይኞቹ መድረስ እንዳለበት ገልፀው አጠቃላይ ግለሰቦች ላይ ከማነጣጠር ባለፈ የስርአትና የፖሊሲ ለውጦች ላይ ማተኮርም እንደሚገባ አቶ ገብሩ አስገንዝበዋል፡፡
የመልካም አስተዳደር ችግሮችን እፈታለሁ በሚል አመራሮችን የማባረር፣ ከስልጣን ዝቅ የማድረግና የመሣሠሉ እርምጃዎች በተከታታይ ሲወሰዱ እንደ ነበር ያስታወሱት የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ (ኢራፓ) ፕሬዚዳንት አቶ ተሻለ ሰብሮ ባለስልጣናትን ግልፅነት በሌለው መንገድ አንዴ መሾም ሌላ ጊዜ ማውረድ ተገቢ አይሆንም ብለዋል። ቁርጠኛ እርምጃ የሚባለው ይሄ ከሆነ ለመቀበል ያስቸግራል የሚሉት አቶ ተሻለ፤ አመራሮችን ዋስትና በማሳጣት በአግባቡ እንዳይሰሩ የሚያደርግና የተባረሩ አመራሮችን የሚያስኮርፍ ተግባር ነው ብለዋል፡፡ የህዝቡም ጥያቄ ባለስልጣናት ይባረሩ የሚል ሳይሆን ስርአቱ እንዲሻሻል የሚሉ እንደሆነ አቶ ተሻለ ጨምረው ገልፀዋል፡፡  በሙስና ተርጥረው በተያዙት ግለሰቦች ጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ፈንታው አምባው ከተጠርጣሪዎቹ አብዛኞቹ በመንግስት አመራር ላይ የነበሩ ግለሰቦች መሆናቸውን ጠቁመው በአሁኑ ወቅት ጉዳዩን ፖሊስ እየመረመረው መሆኑንና እስካሁን የምርመራ መዝገቡ ለአቃቤ ህግ አለመቅረቡን አስታውቀዋል፡፡
ማስረጃ የማሠባሠብና ማስረጃን የመመዘን ስራ ፖሊስና አቃቢ ህግ በጋራ እየሰሩ መሆኑንና መረጃዎች በሚገባ ከተጠናቀሩ በኋላ ለህዝብ ስለጉዳዩ በዝርዝር እንደሚገለፅ ተናግረዋል፡፡



Read 6354 times