Print this page
Monday, 09 January 2017 00:00

የጥበብ ሰዎቹ ምድር ጥያቄ

Written by  ሰሎሞን አበበ ቸኮል solomonabebechekol@gmail.com
Rate this item
(3 votes)

በፊቱም ኢትዮጵያ ይሰግዳሉ፤…
የተርሴስና የደስያት ነገሥታት ስጦታን ያመጣሉ፤
የሳባና ዓረብ ነገሥታት እጅ መንሻን ያገባሉ፡፡     (መዝ 71)
ቻይናና ሞንጎልያ ሳይቀሩ፣ ብዙ ሀገሮች የሰብአነ ሠገሉ ምድሮች እንደኾኑ ይተርካሉ። ስለፋርሳዊነታቸው ዞሮአሰትራዊነቱና በኢራን ይገኛል የተባለው መቃብራቸው ይገኛል፡፡ በህንድና ፓኪስታን ከሐዋርያው ቶማስ ጋር ያለው ንክኪ ዋነኛው ማስረጃ ኾኖ ይቀርባል። አውሮፓም የራሷን ትረካዎች በቱርክ፣ በስፔይንና በፖርቱጋል ይዛለች፡፡ የጣልያንዋ ሚላንና ጀርመን ከዓፅማቸው ማረፍያነት ጋ የተያዙ ትውፊቶች አሏቸው፡፡ ከአፍጋንዋ ካንዳር፣ ከጥንቱዋ ባቢሎን (ኢራቅ)፣ ከሶርያ፣ ከአርመን፣ ከደቡብ ዓረብያና ከኢትዮጵያ ጋ የተያያዙ የሦስቱ ነገሥታት ትውፊቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ የታወቁ ናቸው፡፡
ባለንበት ዘመን ደግሞ ስለ ጥበብ ሰዎቹ እሰከ ዛሬ ሲታወቅ ከነበረው የተለየ፣ ተጨማሪና የተሟላ አዲስ ታሪክ በኢትዮጵያ ውሥጥ ይገኛል። የተቀረው ዓለም ቀርቶ በኢትዮጵያውያንና ቀጥታ በሚመለከታቸውም የታወቀ ባይመስልም.፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደ ጊዜ ስጦታንና እጅ መንሻን ይዘው በመሔድ የሰገዱለት የሦስቱ ጠቢባን ነገሥታት ሀገሮች ውሥጥ የአንደኛው ምድር ተደርጋ በቤትዋም በውጭም የምትታወቀው ኢትዮጵያ የሦስቱ ዕድለኞች ነገሥታት ሀገርነትዋን የሚናገሩ መጻሕፍት አግንኝታለች፡፡ የእነዚህን የጥበብ ሰዎች ማንነት፣ ከየት ተነስተው በየት እንደተጉዋዙ፣ ከመነሻቸው እስከመድረሻቸ ድረስ ያጋጠማቸውን ፈተናና እነዴትና በየት በኩል እንደተመለሱ ኹሉ አሟልተው የሚተርኩ ጽሑፎች ተገኝተው፣ ከግእዝ ወደ አማርኛ ተመልሰው፣ በመጽሐፍ ታትመው ይገኛሉ፡፡
እነዚህን ሦስት ነገሥታት ታሪክም ጨምሮ፣ በአጠቃላይ የኢትዮጵያን ዘመን ታሪክ አዳዲስ ሠነዶች በጥንትዋ ኑብያ፣ የንግሥት ኢትያኤል (የሳባዋ ንግሥት) መናገሻ ከተማ ከነበረችው ናፓታ ባድማዎች ውሥጥ በአንድ ዋሻ በተገኘ ወጥ ኾኖ በተፈለፈለ የድንጋይ  ሣጥን ውስጥ እንደተቀመጡ ተገኝተዋል፡፡ በ1960ዎቹ ኹለተኛ አጋማሽ እነዚህን መዛግብት መሪራስ ኤም በላይ በግል ገንዘባቸው በመግዛት ወደ አማርኛም መልሰው፣ ወደ 10 የሚጠጉ  መጽሐፎች አሳትመው  አቅርበዋል፡፡ከነዚህ ውስጥ ዣን ሸዋ፣ መጽሐፈ ሱባዔ ካልዕ፣ መጽሐፈ አብርሂትና የኢትዮጵያ ትንሣኤ ታሪክ የመሳሰሉት የጥበብ ሰዎቹን ነገር በከፊልም በምልዓትም ይተርካሉ፡፡
በቅርቡ እነኾ፣ ሊትማንና ክፍሉ መጻህፍት በየወሩ በሚያቀርቡት የመጻሕፍት ኤግዚቢሽን ላይ   ከመጽሐፎቹ የኢትዮጵያ ትንሣኤ ታሪክ ላይ በታሪክ መምህሩና ጸሐፊው ደክተር ሥርግው ገላው ጽሑፍ ቀርቦበት ውይይት ተደርጓል፡፡ የዘመኑ ጥያቄና ጉዳይ ኾኖ ከኢትዮጵያውያን ብሔረሰቦች ኹለቱን ርእስ ያደረገ የታሪክ መጽሐፍ ያቀረቡት ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ እነዚህኑ አዳዲስ ታሪኮች ዋቤ በማድረግ ነው ቀረቡት። ፕሮፌሰር ፍቅሬ የሰብአ ሠገሎቹን ማንነት፣ በተለይም ሦስቱ ከኢትዮጵያ መነሳታቸውን አጽንዖት በመስጠት በተደጋጋሚ አቅርበዋል፡፡
ማጂ (ማጃይ) የሚለውን በሌላው ዓለምም የሚታወቀውን መጠርያቸውን በመያዝ፡-
ማጂዎች ለሕጻኑ ኢየሱስ ስጦታ ለማበርከት ከምሥራቅ ኢት ወደ ቤተ ልሔም ከተጓዙ 12 ብልሆች መካከል ናቸው። (ገጽ45)-የኢትዮጵያ ተወላጆች…. እግዚአብሔር እንዳለው ኢየሱስ ክርስቶስ ሲወለድ ኮከቡ እየመራቸው ወደ ቤተልሔም ሔዱ፡፡
“ንጉሥ አጎድጃ ጃቦን (ከደስያት)፣ ንጉሥ መጋል (ከተርሴስ)ና ንጉሥ ሙርኖ…፣” እያሉ በመዘርዘርም ነው ፍቀሬ ቶሎሳ እነዝያን የኑብያ ሠነዶችን ወይም የመሪራስ በላይን መጻሕፍት ዋቤ በማድረግ ያቀረቡት፡፡
እንደ አዲሱ ታሪክ መሠግላኑ የዛሬ 4000 ዓመት መንግሥተ ኵሽን አጠናክሮ፣ ኢትዮጵያ የሚል መጠርያን ሰጥቶ ከገዛት፣ የመልከ ጼዴቅ ልጅ ከኾነው ቀዳማዊው ኢትዮጵ ልጅ ከኾነው ቢዖሪ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ከተገለጸው ተራጋሚ መሠግል በለዓም የሚወርድ ትውልድ ሐረግ ያላቸው ናቸው። በለኣም የክርስቶስን መወለድም የተነበየ ኾኖ በኦሪት ዘኁልቍ ተጽፏል፡፡ የበለዓም የልጅ ልጅ ከምትኾነዋ፣ በስም ሸምሺል ከተባለች፣ በወንዝ ዳር እየኖረች ትጠነቁል ከነበረች እናት የተወለደው ደሽት (ደስያት) የመሠግላኑን መሪ ኮከብ አስቀድሞ ተመልክቶ ያያውን ሥሎና ጽፎ፣ በቃልም አስተላልፎ አልፏል፡፡        
ከመሠረቱ ስለነዚህ ነገሥታት ማንነትና ሌሎች ጉዳዮች ከኋዋላ የነበሩ በመጽሐፍና በትውፊት የሚታወቁ ቃሎች ስላሉ አነጋጋሪነታቸው ብዙም ላይኾን ይችላል። ስለነሡ በዳዊት የተነገሩት ብቻ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያ ከነበሩት ምድሮች ውጭ የሚያሳስቡ ዐይደሉም። - ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር ታነሳለች። - በፊቱም ኢትዮጵያ ይሰግዳሉ፤..- የተርሴስ (በዛሬዋ ምሥራቅ አፍሪካ የቀይ ባሕር ዳርቻ) እና የደስያት (ጣና አካባቢ) ነገሥታት አምኃን ያገባሉ፡፡ - የዓረብና የሳባ ነገሥታት ጋዳን ያመጣሉ፡፡ … የሚሉት ኹሉ  አሁን በሱዳኖቹ ሰነዶች ተጠብቀው ቆይተው ከወጡት ጋር ተስማምተው ነው የሚገኙት፡፡
መሠግላኑን ለየራሳቸው ዜግነት የሚሰጡት በርካታ ሀገሮች ናቸው፡፡ ስሞቻቸውን በየቋንቋው በመጥራት ስለ መሠግላን ነገሥታቱ  የተለያዩ ማንነት ግምቶች ያስከትላሉ፡፡
በምዕራቡ ዓለም በታወቁበት ስሞቻቸው (በጀርመን ላንድስበርግ ሄራድ የተጠሩባቸው) ላይ ዜግነታቸውም አብሮ ይጠራል፡፡ የህንዱ ምሁር ፓቲሳር (ካስፓር ወይም ጋስፓር፣ ጃስፓር፣ ጃስፓስ፣ ጋዛስፓ…)፤ የፋርሱ ምሁር ሜልኪዮር እና በቢሎናዊው ባልታዛር ወይም ባልዛሳር፣ ቢዚሳርያ…። ኢንሳይክሎፔድያ ብሪታኒካም ከየስማቸው ጎን እንዲሁ ሀገሮቻቸውን  ይገልጻል፡- የዓረብያው ንጉሥ ብልታዛር፣ የፋርሱ ንጉሥ ሜልኪዮር፣ የህንዱ ንጉሥ  ጋስፓር፡፡ ሌላውና አይሪሻዊ የትመጣ ያለው የ8ኛው መቶ የግሪክ ሠነድም፣ (ኮሌክታኒያ  ኤት ፍሎሬስ ተብሎ በተጠራ መጽሐፍ የቀረበ)  በሦስቱ ስሞች ላይ ዘርዘር ያለ ገለጻ አቅርቧል፡፡
ጋስፓር  የሚለውን ስም የት መጣ የመረመሩት ደግሞ በሐዋርያው ቶማስ ሥራዎች ውሥጥ ከሚገኘው ጎንዶፋሬስ ከተባለው ንጉሥ ጋ ያገኛኙታል፡፡ ይህ የኢንዶ ፓርትያን የመጀመርያው ንጉሥ ከቶማስ ሐዋርያው ጋር እንደተገናኘ በመጨመር ያቀርቡታል፡፡ ይህን  ስም በመያዝ ኧርነስት ሔርዝፌልድ የተባሉት ምሑር ካንድሀር ከተባለች የአፍጋን ከተማ ስም ጋር አያይዘው፣ ያችን ከተማ  ጉንዶፋሮን በተባለው ስሙ ራሱ እንደቆረቆራት ጠቁመዋል፡፡.
በሶርያ ክርስትያኖች ዘንድ የሦስቱ ስም  ላቫንዳድ፣ ጉሽናሳፍ፣ እና ሆርሚሥዳስ የሚል ነው። እነዚህ ስሞች መጀመርያ የፋርሲ ቋንቋ ቃሎች እነደነበሩ ተገልጾአል፤ ለእውነተኝነታቸው ግን ዋስትና እንደማይኾን ተጨምሮ፡፡
በዓለም ዓቀፍ ደረጃ እንዲኹ የማጂዎቹ ስም ከተጠቀሱላቸው  የምሥራቅ አብያተ ክርስትያናት ውስጥ አርመንያና ኢትዮጵያ ይገኙበታል፡፡ በአርመኖች ካግፋ፣ በዳዳካሪዳና በዳዲልማ ሲኾኑ በኢትዮጵያ ደግሞ ሖር፣ ከርሱዳን እና ባዛንተር መኾናቸው ጠይዟል፡፡
ከምሥራቅ  ወደ ኢየሩሳሌም እንደገቡ የተጻፈውን በመያዝ፣ ከኢየሩሳሌም ምሥራቃዊ አቅጣጫ መግባታቸውን ገላጭ ከመኾን ውጭ ባይኾንም፣ የአቅጣጫ ጥቆማው ብዙዎችን ወደ መካከለኛው፣ ቅርብ እና ሩቅ ምሥራቅ እንዲያስቡ አስገድዶአቸዋል፡፡ ባቢሎናውያንን ፋርሳውያንን ወይም የየመን ይሁዲዎችን ሲያሳስብ የኖረ እንደኾነ ይታወቃል፡፡ በቤተ ክርስትያን በቅድስና ከታወቁት አባቶች አንዱ የኾነው ቅዱስ ዮሃንስ አፈወርቅ ለምሳሌ፣ እነዚህኑ  ሦስቱን ነው ያቀረበው፡፡
የሦስቱ ነሥታት ታሪክ የተባለ መጽሐፍ የጻፉ ጆን ሂልድሻይም የተባሉ የታሪክ ሊቅና ቄስ ከማጂዎቹ አንዱ ኢዝላማባድ አጠገብ በምትገኘው ታክሲላ በተባለች ከተማ ላይ በሚያልፈው የጥንቱ የሐር መስመር በኩል ወደ ቤተልሔም እንደተጓዘ ጽፏል። የክርስትና ታሪክ ምሁሩ ሰባስትያን ብሮክ ደግሞ፣ ከዞራስትርያኒዝም ከተለወጡት ክርስትያኖች ዘንድ  በወንጌላቱ ማጂዎች ዙርያ አንዳንድ የአፍ ታሪኮች ስለመጎልበታቸው ጥርጥር ሌለው ነበር ብሏል፡፡
ከዚህም በመነሳት አንድርያስ ሀልትጋርድ እንደተባሉት ያሉት ጠቅላላ ትረካው ከኢራናዊ ታሪከ አፍ የመጡ እንደኾኑ እስከመግለጽም ደርሰዋል። በፋርሳውያን እምነት የኮከብ መውጣት ከንጉሥ መወለድ ጋር ይያያዛል። በተረታ ተረቶችም ብርሓንና እሳት ከመለኮታዊ አካል ጋር ይያዛሉ፡፡  
አንዳንዶች ደግሞ፣ በ66ኤዲ ቄሳር ኔሮንን እጅ ለመንሳት ወደ ሮም ከመጣው የአርመን ንጉሥ ታሪክ ጋር አያይዘው፣ የወንጌሉን ቃል ከዝያ የተገኘ ነው ብለው ያስባሉ፡፡ ንጉሡ ቲሪዴትስ ይባላል፡፡ የራሱን አርመኔ የጥበብ ሰዎችን አስከትሎ ኔሮን ቄሳርን እጅ ሊነሳና ንግሥናውን ሊያስመርቅ ወደ ሮም ተጉዞአል። እንደዚህ አድርገው በሚያይዙት ዘንድ የማቴዎስ ወንጌል ከመጻፉ ጥቂት ዘመን ቀደም ብሎ ይህ አርመናዊው ንጉሣዊ ጉዞ እንደተደረገ በማሰብም ነው ማቴዎስ ያነን ይዞ የሰብአ ሠገልን ነገር የጻፈው ባይ ናቸው፡፡ እዚሀላይ፣ የትኛው ከየትኛው ቀደመ ተብሎ ሲጠየቅ የሚታይ የታሪክ ዝብነት ብቻ አይኾንም የሚታየው የዘመን ቁጥር ቅየራው የወለደው ስህተትም እንጂ፡፡ ወደ ጥንቱ ታሪክ ሲኬድ በዲዮናስየስ አቆጣጠር መሠረት የተቀየሩም ያልተቀየሩም ታሪኮች አንዳሉ በፈረንጆቹ 2ኛው ሚለንየም ወቅት የተጣፉ የቆጠራ ታሪኮች ያሳወቁ ሲኾን በነዝህ ዘመኖች የተፈጸሙ ታሪክ ዘመኖችን ለሚመለቅምና በተናጠል ለሚያጠና የሚያጋጥሙት ኾና ገኛሉ፡፡ 66 የተባለው በዔዲ ነው ልንል ብንችል እንኩዋ አኹንም ከማትዎስ ወንጌል የቀደመ ታሪክ አይኾንም፡፡ በ፶፮ ዓም የተጻፈ ወንጌል የተለወጠ ነው ቢባል በ12 ዓመት ያልተለወጠ ነው ቢባል ደግሞ የኹለትና ሦስት ዓመት ቅድምያ አለው- ወንጌሉ፡፡
ከተለያዩ ሀገሮችን ሕዝብ ጋ አቆራኝቶ ማቅረቡ አውሮጳዊው የፕሬስተር ጆን እሳቤ ርቆ እሳከታሰበበት የሞንጎልያው ንጉሥ ጌንጊስ ክሃን ድረስም ይደርሳል። የማዕከላዊት እስያዊ ኔይማኖች እና ክርስትያን ወገኖቻቸው ማለትም ኬራይቶች ከመጽሐፍ ቅዱሶቹ ማጂዎች የሚመዘዝ ዝርያ ነበራቸው፡፡ ይህ ውርስ ለሞንጎል ሥርወ መንግሥት በጋብቻ ተላልፏል፡፡ ሶርጋግታኒ የተባለው የኬራይት ገዥ፣ የቶግሩል እህት ልጅ ሶርጋግታኒ በኣለም አቀፍ ታሪክ የታወቀ ባታሪክ ጌንጊስ ክሃንን የመጨረሻ ወንድ ልጅ ቶሉይን አግብታ ሞንግኬ ክሃን የተባለውን ገዥ፣ ተከታዩን   ኩብላይ ክሃንንም ወልዳለች፡፡ ቶግሩል በአውሮፓውያን ዘንድ ፕሬስተር ጆን በሚል ስም የማዕከላዊት እስያ ክርስትያን ንጉሥ ተደርጎ ይታሰብ ነበር፡፡   
የሲሲሊያዋ አርመን ንጉሥ ቀዳማዊ ሄቱም ታላቅ ወንድም የሞንጎሊያውን ዐውደ ምኵናን ጎብኝቶ ለቆጵሮሱ ንጉሥ ቀ/ሔንሪና እኅቱ ለምትኾነው ለንግሥት ሰቴፋኒ በ1243 እንደጻፈው-ታንቻት [ታንጉት ወይም ምዕራባዊት ዚያ] ተባለችው ሀገር የሦስቱ ነገሥታት ምድር ናት፡፡ፕሬስተር ጆኑም ከአንዱ የሚመዘዝ ዝር እንዳለው ጠቁማል፡፡
የፕሬስተር ጆኑ ጉዳይ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ መዘጋቱ ይታወቃል፡፡
ህንዳዊው ፓራማሃንሳ ዮጋናንዳ በጻፉት የክርስቶስ ዳግም ምጽአት በተባለ መጽሐፍ ላይ ከክርስቶስ ልደት በፊት ጀምሮ ህንድ ከፍልስጥኤም ጋ ግንኙነት ያላትና የኦርየንት- ሜድትራንያን ንግድ (ግብፅ፣ ግሪክና ሮምን ጨምሮ) መስመር የሚያልፈውም በኢየሩሳሌም መኾኑን ጠቅሰው፣ እነዚህ ጠቢባን  የህንድ ታላላቅ ጠቢቦች   ሊሆኑ እንደሚችሉ ገምተዋል።
 በምዕራቡ ዓለም ያሉ የሥነ ሥዕል ሥራዎችም የበኩላቸውን ድርሻ አዋጥተዋል- በመሠግላኑ የትነት ላይ፡፡ በአሬናዋ የጸሎት ቤት በ1305 በጊዮቶ የተሣለው ሥዕል በዕድሜያቸው ላይ ትኩረት ያደረገ ሥዕል ነው፡፡
ካስፓር የተባለው  የ60 ዓመት ባለዕድሜ፣ ባለ ነጭ ጽህም ሽማግሌ ሲሖን  ወርቁን ያቀረበው ነው። እርሱን  የነጋዴዎች ምድር የኾነችው ተርሴስ ንጉሥ ነው፡፡ ተርሴስ በሜድትራኒያን  ዳርቻ በዛሬይቱ ቱርክ ያለች ደሴት እንደኾነች ጨምረው ያሳውቃሉ፡፡ (ለምን የስፔይንዋን አላሰቡም?)
የቱርኳ ተርሴስ ቀርቶ የስፔይንዋ ተርሴስ ወደብም “ነገስተ ተርሴስ ወ ደስያት አምኃ የበውኡ፣” የሚለውን ትንቢት በመዝሙሩ የተናገረው ንጉሥ ዳዊት በነበረበት ዘመን አልነበረም፡፡ እነዚሕ ወደቦች ከልደት በፊት 20ኛው ዓመት ወዲህ ጀምሮ ነው ፡፡
በነዳዊት ዘመንም የነበረችው፣ የንጉሥ ሰሎሞን መርከቦች የሚሠሩባትና የሚጫኑባት፣ ዛሬ የአፋር፣ የኢሳዎችና ጉርጉራዎች  ምድር (አፋርን፣ አሰብን፣ ጂቡቲን የሶማልያን ሰሜናዊ የባሕር ዳርቻዎች ላ) በሆነው  ላይ ትገኝ የነበረች ወደብ ናት፡፡ የመርከብ መሥርያ ቦታ እንደነበረች የኑብያዎቹ ሠነዶች ይገልጻሉ። መጽሐፈ ነገሥት  ላይ ስለ ሰሎሞን የንግድ መርከቦች የተገለጸውም ላይም፣ ከላይ ከሰሜን ቀይ ባሕር ወደ ደቡብ ፊታቸውን አዙረው ወደ ተርሴስ  የሚጓዙ መኾናቸውን ነው የሚሳውቀው፡፡ በአዲሱ ታሪክ ንጉሥ መጋል የተባለው የኦሮሞዎች፣ የደርዲ፣ የሰገልና የማጂ ንጉሥ ከተማ የኾነችው ተርሴስ እንደነበረች ተገልቷል፡፡ ንጉሡ ጦር ይዞ በመሔድ በስፔይን ያለችውን ወደብ ይዞ በከተማው ስም ተርሴስ ብሎ እንደሰየማት ተተርኳል፡፡
ሜልኪዮርን ደግሞ ባለመካከለኛ ዕድሜ በማድረግ (40ዓመት)፣ ዕጣኑን እርሱ እንዳቀረበ ተሥሏል፡፡ ከዕጣን ጋ አይተውት ከዓረብያ ብለውታል።
ባልታዛር ወጣት (20ዓመት)፣ ብዙውን ጊዜ ጥቁር ፊት ተደርጎ ይሣልና ከርቤውን ያቀረበው የሳባ (የዛሬይቱ ደቡብ የመን) ሰው ያደርጉታል፡፡ ፔኒን ዋቤ በማድረግ ዕድሜያቸውን የጠቀሰው የዊኪ መስመር ደግሞ፣ ‹‹ይበልጡን ከኢትዮጵያ ወይንም ከሌላው  የአፍሪካ ምድር እንደሔደ ከሚተሰበው ባልታሳር በቀር›› የሰዎጩ ሀገር ምድር የተለያየ እንደኾነ ገልጿል።
በሥነ ሥዕል የባልታዛር ጥቁርኾኖ መገኘት የቅርብ ጊዜ ምሁራን ቀልብ መሳብያ እየኾነ እንደሚገኝ በሺለር ተጽፏል፡፡ ከ12ኛው መቶ ተጀምሮ፣ በሰሜን አውሮጳ ከ15ኛ መቶ ላይ የተለመደ ኾኗል።   
መቃብራቸውቸው ወይም አጽማቸው ይገኛል ያሉአቸውን ቦታዎችም የሰብኣ ሠገሉ ምድር ተደርገዋል። በተለይ በኢራን የምትገኘው ሳባ የተባለች ምድር ዛሬም ድረስ በቱሪስቶች የሚጎበኝ  የመቃብር ቦታ አላት፡፡  የማጂዎቹ ሀገር እንድትኾን  አስችሏታል፡፡ ለመጀመርያ ጊዜ በ1270 ይህን የገለጸው ተጓዡ ማርኮ ፖሎ በደቡብ ቴህራን ሳቬህ በተባለች ቦታ የሦስቱን መቃብር ዐይቶ እንደነበር ገልጧል፡፡
“3ቱ የጥበብ ሰዎች የወጡባት፡ ጎን ለጎን በተሠሩ ሦስት ትላልቅና ውብ ሐውልቶች የተቀበሩባት ሳባ ከተማ በፋርስ ውስጥ ናት፡፡ ከነርሱ በላይ ጥሩ ኾኖ የሚጠበቅ እኩል በኩል የኾነ ዓራት ማእዘን ሕንፃ ይገኛል፡፡  በድናቸው ገና ሙሉ ነው፣ ከጠጉራቸውና ከጽህማቸው በቀር፡፡ (ማርኮ ፖሎ፣ የሚሊዮኖቹ መጽሐፍ፣)
የሦስቱ ነገሥታት መታሰቢያ የኾነ ካቴድራል  በጀርመን ኮለኝ ውስጥ ይገኛል፡፡ በዝያ ውስት በ1164 ቅዱሱ  ሮማዊ ንጉሥ ቀዳማዊ ፍሬደሪክ ከሚላን ያፈለሰው ዓፅማቸው እንዳረፈ ይታመናል፡፡ ከዛሬይቱ ኢስታንቡል (ኮንስታንቲኖፕል) ወደ ሚላን መጥቶ ተቀምጦ ስለነበር ዛሬም በየዓመቱ ጃንዋሪ 6  ሚላኖያውያን በክት አልባሳት ተውበው በጎዳናና በአደባባይ በሠልፍ ያከብሯቸዋል፡፡ (ምዕራባውያኑ የገናን ዕለት ሳይቀይሩት፣ በትክክለኛው ዕለት ይከበርበት በነበረው ቀን ነው የሦስቱን ነገሥታት መታሰብያ የሚያደርጉት፡፡)
ወደ ኮንስታንቲኖጵል ዐጽማቸውን ያስወሰደችው ደግሞ ንግሥት ሔለና ናት ይላሉ፡፡ ይህንን የጻፈው ጆን ሄይልድሸን፣ የ14ኛው መቶ አውሮጳዊ ካህን፣ የሦስቱ ነገሥታት ታሪክ በተባለ መጽሐፉ እንዲህ ከመገኛው ጀምሮ ተርኳል፡፡
ቅድስት ሔለን…  ስለኘዚህ 3 ነነገሥታት ዐጽም በእጅጉ ስታስብ ቆየችና ከአጀቦችዋ ጋ ወደ ምድረ ኢንድ አመራች፡፡… የሜልቾይርን፣ የባልታዛርንና የጋስፓርን ዐጽም ባገኘች ጊዜም በአንድ ሣጥን አስደርጋ በብዙ ውድ ጌጦች አንቆጥቁጣ ወደ ኮንስታንቲኖፐል አፈለሰቻቸው፡፡ በዝያም ቅድስት ሶፍያ በተባለ ቤተ ክርስትያን እንድያርፍ አደረገች፡፡
በቤተ ክርስትያን እንደሚታወቀው በአዲሱ የኑብያ ሰነዶች እንደሚተረከው ሦስቱም ክርስትናን ተቀብለው ከሐዋርያቶችም ጋ ነው ቢሉ፣ ብቻቸውን ነውም ቢሉ፣ ቀይባሕርን በመሻገር ማስተማርና መስበክ ውስጥ ገብተው በቅርብ ምሥራቅ ወይም በሩቁ በሰማዕትነት በማረፋቸው መቃብሮቻቸው ከአፍሪካ ውጭ መኾኑ ግድ ነበር፡፡ የአጽማቸው ፍልሰትም ቢኾን የሚቀይረው ነገር አይኖርም፡፡
በሌላ በኩል  በኢንሳይክሎፔድ ብሪታኒካ እና በኦክስፎርድ መዝገበቃላት (1910፣ 3ኛ ዕትም) እንደተገለጸው በምሥራቅ ክርስትናና በሶርያውያኑ አብያት የማጂዎቹ ቁጥር መጀመርያ 12 ነበር፡፡ ይህም ጭምር ነው በኑብያዎቹ ሠነዶች የተገኘው፡፡ ከየትም ይነሱ፣ የነርሱን ሀረግ ከኢትዮጵያዊነቱ እስካላወጣ ድረስ፣ ከዛሬይቱ ኢትዮጵያ ውጭም ሊኖሩ ይችላሉና ያን ያሕል  የሀገሩ ብዛት አያነጋግር ይኾናል፡፡
የደቡብ የመንና የየዓረብያን ነገር ብናነሳ ከጥንት ጀምሮ በታሪክ የታወቀውን ከኢትዮጵያውያነት የሚመጣውን ነገዳቸውንና የኢትዮጵያ አንዲት ክፍለ ግዛት የነበሩ መኾናቸውን መያዝ እንችላለን፡፡ (ነገር ግን በዳዊት ኘገሥተ ሳባ የተባሉት የየመኖቹ ወይም እዚህ ላይ እንዳየነው፣ በኢራንም ያለቸውን ሳባ እንዳልኾነ መታወቅ አለበት፡፡ የሳባ ንግሥት ተብሎ ከሰሎሞን ጋ የሚያያዘው ጥሪ በነበረበት ዘመን፣ ዳዊት የሚጠራት ሳባ(የቦታ ስም) በኩሽ ልጅ ስም ተሰይማ የኢትዮጵያውያን መንግሥት መዲና የኾነቻትንና በሳባ ስም እየተጠሩ የተቀመጡበትን፣ የሳባውያን ምድር ዛሬም ድረስ በሰሜን ሱዳን የሚገኘውን፣ ቀይባሕር ወሰን የኾነበትን ምድር ነው፡፡)
መልካም የልደት በዓል!

Read 1167 times