Sunday, 08 January 2017 00:00

የገና ጨዋታ

Written by  ጌታሁን ፋንታው
Rate this item
(3 votes)

አዝመራው ተሰብስቦ፣ ጤፍና የብርዕ እህል (ስንዴና ገብስ) ሁሉ ታጭዶ በእርሻው ላይ ከብት ይሰማራበታል፡፡ ወርሃ ታህሣስ ደግሞ ይህን የሚያበስር ወር ሲሆን እረኞችም ታህሳስ ሲመጣ የገናን ጨዋታ አብረው ያስቡታል፡፡ የእርሻ ቦታዎችና መስኮች ሁሉ ወደ ገና መጫዎቻነት ሜዳ ይቀየራሉ።
የገና ጨዋታ በሀገራችን ባህላዊና ሀይማኖታዊ ይዘት ያለው፣ ከጥንት ጀምሮ የነበረ ጨዋታ እንደሆነ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡ መምህር ካህሳይ ገ/እግዚአብሔር የተባሉ የታሪክ ተመራማሪና ደራሲ፤ ስለ ገና ጨዋታ ታሪካዊ አጀማመር ሁለት ትውፊቶች ተደጋግመው እንደሚነገሩ ይገልፃሉ፡፡ ጌታ ሲወለድ እረኞች ከመላዕክት ጋር አብረው እንደዘመሩና በወቅቱም የገና ጨዋታ መጫወት እንደጀመሩ አንደኛውን ትውፊት በመጥቀስ ያስረዳሉ፡፡
ሁለተኛው ትውፊት ደግሞ ከሰብዓ ሰገሎች ጋር የሚገናኝ ነው፡፡ ንጉስ ሄሮድስ የሚባለው የዘመኑ ንጉሥ አዲስ የሚወለደው ህፃን የበለጠ ዝናና ክብር እንደሚያገኝ የሰማው ትንቢት ስላስደነገጠው በዚያን ጊዜ የተወለዱ ወንድ ህፃናት በሙሉ እንዲገደሉ ትዕዛዝ ሰጥቶ እያሳደደ ያስገድል እንደነበር ይወሳል። ሄሮድስ ታዲያ ጌታ ሊወለድ መሆኑ ተነግሮት ስለነበር የት እንደሚወለድና ስለ አጠቃላይ ሁኔታው በቅርበት ለማወቅ በመፈለጉ አንድ ሰላይ የሰብዓ ሰገሎች ዓይነት ልብስ አስለብሶ፣ ከእነሱ ጋር እንዲቀላቀል ይልካል፡፡ ሰላዩ ከሰብዓ ሰገሎች ጋር ተቀላቅሎ ጌታ ወደሚወለድበት ሥፍራ ሲጓዙ፣ ይመራቸው የነበረው ኮከብ ድንገት ቀጥ ይላል፡፡ ይኼኔ ተጠራርተው መሃላቸውን ሲፈትሹ፣ ሰላዩን እንዳገኙት ይኸው ትውፊት ያስረዳል፡፡ ከዚያም ሰብዓ ሰገሎቹ ሰላዩን ይገድሉና ራሱን ቆርጠው እንደ አሁኑ የገና “እሩር” እየተቀባበሉ ተጫወቱበት ይላል - ሁለተኛው  ትውፊት፡፡ ከዚያም በመነሳት የገና ጨዋታ ተፈጠረ ይላሉ፤ የታሪክ ተመራማሪው፡፡
እነሆ ከዚያን ጊዜ አንስቶ ከትውልድ ትውልድ እየተቀባበለው፣ እስከ አሁን የቀጠለው የገና ጨዋታ፤ በየዓመቱ በታህሣሥ ወር በተለይ በኢትዮጵያ የገጠሩ ክፍል እረኞች በድምቀት ይጫወቱታል። በአብዛኛው ጨዋታው ወሩ እንደገባ የሚጀመር ሲሆን በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ ከታህሳስ ወር አጋማሽ ጀምሮ እንደሚጧጧፍ ይታወቃል፡፡
የገና ጨዋታ ሁለት ቡድኖች ጎራ ለይተው የሚጋጠሙበት ልዩ ባህላዊ ትዕይንት ነው፡፡ ለሁለቱ ቡድኖች እኩል እኩል ቁጥር ያላቸው ተጋጣሚዎች ላይኖራቸው ይችላል፡፡ ያንደኛው ቡድን በርከት ብሎ፣ የሌላኛው ቡድን አነስ ያሉ ተጋጣሚዎች ሊይዝ ይችላል፡፡
አንደኛው ቡድን ከቀኝ ወደ ግራ ከያዘ፣ ሌላኛው ቡድን ደግሞ ከግራ ወደ ቀኝ ያለውን ስፍራ ይይዛል። አቅጣጫውን ያልለየ ተጫዋች ካለ፣ “ሚናህን ለይ›› ተብሎ፣ ካስፈለገም በዱላ ቸብ ተደርጎ፣ ቦታውን ይይዛል፡፡ በአብዛኛው የሰሜኑ በተለይም በአማራ አካባቢዎች “ጥንጓን” ወይም “ሩሯን” የመቱበት የዱላው ራስ “ገና” ይባላል፡፡ ከወደ ራሱ እንደ ከዘራ ቆልመም ያለ ዱላ ነው፡፡
የገና ጨዋታ አሁን በዘመናዊ መልኩ በከተሞች ከምናየው ይለያል፡፡ በስፖርታዊ ውድድር ውስጥ በገባው ዘመናዊ የገና ጨዋታ ህግ መሰረት፤ ዱላውን (ገናውን) ወደ ላይ ማንሳት አይቻልም፡፡ በጥንታዊው ወይም በገጠሪቱ ኢትዮጵያ በሚደረገው የገና ጨዋታ ላይ ግን እንደተፈለገው በማንሳት፣ ሩሯን (ጥንጓን) አክርሮ መለጋት ይቻላል፡፡
ሌላው ደግሞ በዘመናዊው የገና ጨዋታ ስፖርት፣ ሩሯ የምትገባበት (የምትለማበት) ሥፍራ እንደ እግር ኳስ የግብ ሥፍራ ያለው ነው፡፡ በጥንታዊው ጨዋታ ግን የገና ጨዋታው የሚካሄድበት ሜዳ ወይም የእርሻ ማሣ፣ ሁለቱም ጫፎች የግብ ወይም የመልሚያ ቦታዎች ናቸው። ከሜዳው ወይም ከማሳው ስፋት የተነሳም ተጫዋቾቹ እንደ ልባቸው እየሮጡ ይጫወታሉ፡፡ ጨዋታው በውጤት አሊያም በሽንፈት እየታጀበ ይቀጥላል፡፡
አንዱ ቡድን ሩሯን (ጥንጓን) እንዳለማ ወይም እንዳገባ በተቃራኒው ቡድን ላይ የተረብ መዓት ይዥጎደጎዳል፡፡ በገና ጨዋታ ላይ የሚሰነዘሩ ተረቦች ታዲያ እንደ መዝናኛና እንደ ማድመቂያ ነው የሚቆጠሩት፡፡ የሚተርበው ቡድን እንኳን በተረቡ ይዝናናል ይስቃል እንጂ ቂም መያዝ ብሎ ነገር በገና ጨዋታ አይታሰብም፡፡ ተሸናፊውም በእልህ ለማሸነፍ ይነሳሳል እንጂ በጨዋታ አድማቂው ተረብ አይቆጣም፡፡
በጨዋታው ላይ የሚሰነዘሩ ወይም የሚወረወሩ ተረቦች በአብዛኛው በአካላዊ ገፅታ ላይ የተመሰረቱ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ቁመት፣ እርዝመትና እጥረት፣ ውፍረትና ቅጥነት ወዘተ…
“አሲና በል አሲና ጋማዬ
እያሃ … አሲና ጋማዬ”… እያሉ ተጋጣሚዎች ጨዋታውን ያደሩታል፡፡
ለምሳሌ አጫጭሮቹን የቡድን አባላት ለመተረብ አሸናፊዎቹ እንዲህ ይላሉ፡-
‹‹ይህን ወዳጅ ብላ ታስከትለዋለች
አንድ ቀን ጩልሌ ታስወስደዋለች፡፡››
አጭሮቹ በተራቸው ደግሞ፡-
‹‹እረጅም ነህና ሞኝነት አታጣም
እቆርጥልሃለሁ አሳጥሬ በጣም
ይኸን ረጅሙን ጎምዶ ጎማምዶ
ግማሹን በርጩማ ግማሹን ማገዶ›› እያሉ የአፀፋ ምላሹን ያዥጎደጉዱታል፡፡
ወፍራሞች ደግሞ ቀጭኖችን እንዲህ ይሏቸዋል፡-
‹‹ሲሄድ ቅትር ቅትር ሲበላ እንዳንበጣ
ወዘና የሌለው የጨጓራ ቋንጣ››…
የተረብ በትር ያረፈባቸው ቀጭኖችም ከአፀፋ ምላሽ አይቦዝኑም፡-
‹‹እየው አካሄዱን አረማመዱን
እንደ ቃሪያ ሎሚ ወጥሮ ሆዱን››
በጥንቱ የገና ጨዋታና አሁንም በአንዳንድ የገጠር አካባቢዎች ሴቶች ባይጫወቱም በሜዳው፣ ዙሪያ ሆነው የሚደግፉትን ቡድን ያበረታታሉ፤ የሚነቅፉትን ደግሞ በተረብ ይሸነቁጡታል፡፡ …
‹‹ወንድ ነው ብዬ … ብሰጠው ጋሻ
ለናቱ ሰጣት ላመድ ማፈሻ
ወንድ ነው ብዬ ብሰጠው ጦር
ላባቱ ሰጠው ለቤት ማገር›› …እያሉ ተወዳጁን የገና ጨዋታ ያደምቁታል፡፡
በአጠቃላይ “በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ” እየተባለ እንደሚጨፈረው ሁሉ፣ ቂምና በቀል በገና ጨዋታ አይታሰብም፡፡ ከጨዋታው በኋላ መብል መጠጡ ተሰናድቶ፣ ድግሥ ላይ ጌታውም ሎሌውም እኩል ይቀጣሉ፡፡ አብረው ይበላሉ። አብረው ይጠጣሉ፡፡ ይህን ልምድ ደራሲና ጋዜጠኛ መምህር ካህሳይ ገ/እግዚአብሔር፤ ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ውልደት ጋር በማቆራኘት ያብራሩታል፡-
“የኢየሱስ ውልደትም የሰውን ልጅ እኩልነት ለማወጅ፣ ኃጢያተኞችን ይቅር በማለት ከሌላው ጋር ያዋሀደ ክስተት በመሆኑ፣ በገና ጨዋታም አሽከርና ጌታው እኩል ይጫወታሉ፤ ይራገጣሉ”
መልካም የገና በዓል!   

Read 2782 times