Monday, 09 January 2017 00:00

ገና በዓሉና ባህሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(8 votes)

 የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የሃይማኖት መምህር መጋቢ ሀዲስ እሸቱ አለማየሁ በተለያዩ መድረኮች በሚያቀርቧቸው ሃይማኖታዊ ትምህርቶችና ንግግሮች ይታወቃሉ፡፡ በገና ታሪካዊ፣ ባህላዊና ሀይማኖታዊ አከባበር ዙሪያ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ አነጋግሯቸዋል፡፡

     የገና በዓል አከባበር በሌላው ዓለምና በኛ በኢትዮጵያ
ወደ አከባበሩ ስንመጣ ጣኦትና ሃይማኖት ክርስትና ከእየሩሳሌም ተነስቶ ወደ አራቱ የዓለም ማዕዘናት ሲስፋፋ፣ ሁለት ዓይነት ነገሮች አጋጥመውታል። ኢትዮጵያንና እስራኤልን የመሰሉ ሀገሮች ከብሉይ ወደ አዲስ ኪዳን ማለትም ከአምልኮተ እግዚአብሔር ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር የመጡ ናቸው፡፡ ሌሎቹ ደግሞ አህዛብ የምንላቸው ከአውሮፓ ጀምሮ ሌላው ዓለም ከአምልኮቱ (ባዕድ ጣዖት) ወደ ክርስትና ነው የመጡት፡፡ ለምሳሌ እኛ ኢትዮጵያውያን ከብሊይ ኪዳን ወደ አዲስ ኪዳን የተሸጋገርን በመሆናችን፣ አብዛኞቹ የበዓል አከባበሮቻችን፣ በዓሉ የሚከበርበት ምክንያት አዲስ ኪዳናዊ ይሁን እንጂ በዓሉ የሚከበርበት ወይም የሚገለፅበት አይነት ደግሞ ከብሉይ ዘመን የሚሸጋገር ነው፡፡ አለባበሳችን፣ አመጋገባችን ቤተ መቅደስ ያለው አገልግሎት፣ ጧፉ እጣኑ፣ መጋረጃው፣ የቤተ መቅደሱ አቀማመጥ፣ የምንበላው፣ የምንጠጣው በሙሉ ቅድመ ልደተ ክርስቶስ ከነበረው የብሉይ ዘመን የተሸጋገረ ነው፡፡ ሌሎች የዓለም ሀገራት ግን ከባዕድ አምልኮ ወደ ክርስትና የመጡ በመሆናቸው፣ እነዚህን ባህል አያውቋቸውም፡፡ እነሱ ከባዕድ እምነቱ ወደ ክርስትናው ያሸጋገራቸው ባህሎች ናቸው ያሉት፡፡ ከጣኦት አምልኮ ወደ ክርስትና ቢመጡም ለጣኦቱ ሲያደርጉ የነበረውን ነገር አልዘነጉም፡፡ ክርስቶስን ቢያመልኩም የቀደመውን ባህላቸውን አልረሱም፡፡ ለምሳሌ ፈረንጆቹ ታህሳስ 25 ቀን የክርስቶስን ልደት የሚያከብሩበት ምክንያት፣ የፀሐይ አምላክ የሚሉት በትልቁ የሚከበር የጣኦት በዓል ነበረ። ጳጳሳቱ ህዝቡ ይሄን ልማድ ሊተውላቸው ባለመቻሉ፣ ለማስተው የዘየዱት መላ፣ ህዝቡ ቀኑን ማክበሩን ያክብር፣ ነገር ግን በጣኦት ስም መሆኑ ቀርቶ በክርስቶስ ልደት ስም ይሁን ብለው፣ በጣኦቱ ቦታ የክርስቶስ ልደት እንዲከበር አደረጉ፡፡
ለምሳሌ እኛ የጥምቀት በዓልን እናከብራለን፤ የጥምቀት በዓል አከባበራችን ግን የብሉይ ዘመን ትውፊት ያለው ነው፡፡ እስራኤላውያን ከግብፅ የመጡበትን ቀን ሲያከብሩ፣ ወንዝ ዳር ሄደው ዳስ ጥለው፣ ያልቦካ ነገር ማለት ቂጣ እየበሉ ነው፡፡ የእኛም የጥምቀት በአል አከባበር ይሄ አሻራ አለበት፡፡ በተመሳሳይ ፈረንጆቹም ቀድሞ ያመልኩት የነበረው ጣኦት አሻራ ይታይባቸዋል። ስለዚህ እኛ የምናከብረው ገና መነሻው የክርስቶስ መወለድ ይሁን እንጂ ስሩ ሲፈለፈል፣ ወደ ብሉይ ኪዳን ይወስደናል፡፡ በቤተክርስቲያናችን በአሉን ስናከብር፣ መብራት እናበራለን፣ ነጭ በነጭ እንለብሳለን፡፡ እነዚህ ሁሉ ከብሉይ ኪዳን ያመጣናቸው ናቸው፡፡ ነጭ ልብስ፡- የህብርና ነፃ የመውጣት ምልክት ነው፣ የሃዘን መገፈፍና የደስታ መመለስ ምልክት ነው፡፡ በዚህ መንገድ ነው በአሉና ባህሉ የሚደበላለቀው፡፡
የግሎባላይዜሽን አደጋ
ዘመኑ የግሎባላይዜሽን ነው፡፡ የግሎባላይዜሽን አደጋው ምንድን ነው ከተባለ፣ ሁሌም ምዕራባውያኑ አቀባይ፣ የ3ኛው አለም ተቀባይ መሆኑ ነው፡፡ የስንዴ እርዳታ ብቻ ሳይሆን የአስተሳሰብ እርዳታ ያደርጋሉ፡፡ የአለባበስ፣ የአነጋገር፣ የአመጋገብ እርዳታ ያደርጉልናል፡፡ ስለዚህ እነዚህ የገና አባት፣ የገና ዛፍ የሚባሉት በኢትዮጵያ የልደት አከባበር ውስጥ የማይታወቁ፣ በአለማቀፋዊ ተፅዕኖ የመጡ ናቸው እንጂ የኛ አይደሉም፡፡ እኔ ይሄን ለመከላከል ዝግ መሆን አለብን የሚል አቋም የለኝም፡፡ መጥፎ እንዳለ ሁሉ፣ ጥሩ ጥሩ የምንቀበላቸው ነገሮች አሉ፡፡ የኛን የሚያስረሱና የሚያጠፉ ባህሎች ሲመጡ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
የገና ጨዋታ
ውሃ ልኩና መሰረቱ እንዲሁም መደምደሚያና ጉልላቱ፣ በውሃ ልኩና በመደምደሚያው ክርስትናው ነው፡፡ በውሃ ልኩና በመደምደሚያው መካከል ደግሞ ባህል ትዊፊት፣ ታሪክ አለ፡፡ ሃይማኖት አስኳሉ ነው። ባህሉ ደግሞ እንደ እንቁላል የላይኛው ክፍል ነው፡፡ ስለዚህ በአሉም የገና ጨዋታውም ድሮም የነበረ ነው አሁንም ያለ ነው፡፡ እንደውም ከጥንት ያለው አከባበሩ የገና ጨዋታ የሚደረገው የዕለቱ እለት ብቻ አይደለም፤ ጊዜው ሲቃረብ ጀምሮ ነው የሚደረገው፡፡ ጨዋታው ደግሞ ምሳሌያዊ ነው፡፡ አንደኛ በበረት የነበሩ ልጆች ይጫወቱ ነበር፡፡ የዚያ ትውፊት ነው፡፡ “በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ” የሚለውም ለአንድ ቀንም ቢሆን የበላይና የበታች የሚጠፋበት፣ የስልጣን ልዩነት የሚጠፋበት፤ ንጉሱ ከተራው ሰራዊት ጋር እኩል ሆነው የሚጫወቱበት፣ ለምን መታኸኝ፣ ለምን ረገጥከኝ የማይባልበት ነው። እንደው ዛሬም ቢሆን ባለስልጣኖቻችን እንዲህ የሚጫወቱበት፣ አጋጣሚ ቢፈጠር እንዴት ያለ መልካም ነገር ነበር፡፡ መሪዎቹ ከተመሪዎቹ እኩል የሚሆኑበት ቀን ቢኖር መልካም ነበር፡፡ በገና ጨዋታ ሎሌው ጌታውን ድንገት ቢመታው፣ ለምን መታኸኝ ተብሎ አይጠየቅም። ይሄ ትርጉም የተናቁት እረኞች፣ ጠቢባኑ ሰብአ ሰገል፣ ሃያላን፣ የማይዳሰሱ የማይጨበጡ መላዕክት ከእረኞቹ ጋር አንድ ላይ የሆኑበት የክርስቶስ ልደት ነበር፡፡ ትውፊቱ ይሄን ለማመላከት ነው፡፡
የፍቅር በዓል
የልደት በአል በቤተክርስቲያን ካሉት ዘጠኙ አበይት በአላት አንዱ ነው፡፡ የጌታ በአላት የምንላቸው 9 በአላት አሉ፡፡ ከዘጠኙ በሁለተኛ ደረጃ ያለው ልደቱ ነው፡፡ አንደኛው ፅንሰቱ ነው፡፡ ጌታ ባይወለድ ጥምቀት የለም፤ ስቅለት የለም፣ ትንሳኤ የለም፣ እርገት የለም፡፡ ስለዚህ ልደቱ በቤተ ክርስቲያናችን የሁሉም ነገር መሰረት ነውና፤ በትልቅ ደረጃ ነው የሚከበረው፡፡ እግዚአብሔር ሰውን ለማዳን የሰው ስጋ የለበሰበት ነው፡፡ በዘመኑ የህክምና ቋንቋ ለበሽታው ክትባት የሚሰራው፣ ከራሱ ከበሽታው ነው ይባላል፡፡ እግዚአብሔርም በሽተኛውን ሰው ለማዳን የራሱን የበሽተኛውን ሰውነት ነው የተጠቀመበት፡፡ ከገነት የተባረረውን አካል ነው ክርስቶስ የለበሰው፣ የተዋሃደውና ዓለምን ያዳነው፡፡ ይሄ ትልቅ ምስጢረ ስጋዌ፣ ምስጢረ ድህነት፣ ምስጢረ ሰው መሆንና የመዳናችን ሚስጥር ነው፡፡ እግዚአብሄር ለሰው ያለውን ፍቅር እስከ ጥግ የገለፀበት በዓል ነው፡፡
የገና ስጦታ
ስጦታ ሃይማኖታዊ ትውፊት ብቻ ሳይሆን ሀይማኖታዊ ትዕዛዝ፤ መመሪያም ነው፡፡ ትውፊትና ባህል ብቻ ሳይሆን ሃይማኖታዊም ነው!! በመጀመሪያ የስጦታ መነሻ የሆነው የመጀመሪያው ሰጪ እግዚአብሔር ነው። አዝርዕቱን፣ አየሩን፣ ውሃውን፣ አፈሩን፣ ንፋሱን፣ ጨረቃውን፣ ከዋክብትን በጠቅላላ የምናየውን ሁሉ ፈጥሮ፣ በነፃ የሰጠን እግዚአብሔር ራሱ ነው፡፡ የስሜት ህዋሳቶቻችንን በነፃ ፈጥሮ የሰጠን ራሱ ነው፡፡ ይህን ሁሉ ስጦታ ሰጥቶ የልቡ ስላልደረሰ ደግሞ መጨረሻ ላይ ክርስቶስ ራሱን ሰጠን ብለን ነው የምናምነው፡፡ ራሱን ለሠጠን እግዚአብሔር ደግሞ እኛ ራሳችንን መስጠት አለብን፡፡
ስጦታ ሁለት አይነት ነው፡፡ መልሶ የሚጠበቅ ስጦታ አለ፤ መልሶ የማይጠበቅ አለ፡፡ ለጓደኛ የሚደረግ ስጦታ በተዘዋዋሪ ብድር ማለት ነው፡፡ መልሶ ጓደኛችን ሌላ ስጦታ ይሰጣል፡፡ በሌላ በኩል መልስ የማይፈልገው ደግሞ ለድሆች፣ ለተቸገሩ፣ ለተራቡ፣ ለተራቆቱ የሚደረግ ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ሰብአ ሰገል እጣን፣ ከርቤ፣ ወርቅ … ለክርስቶስ እጅ መንሻ ይዘው መጥተዋል፡፡ ይኸውም እንደመንሻ ተደርጎ፣ ገና የስጦታ በአል ነው ይባላል፡፡ ሰብአ ሰገልን እንደ መነሻ ብንወስደውም፣ አሁንም በረቂቁ የምዕራባውያን ተፅዕኖ አለበት፡፡ እንደሚታወቀው የገና ዛፍ ገበያ የሚደራበት፣ ፖስት ካርድ የሚሸጥበት፣ ከክርስቶስ ልደት ይልቅ አሻንጉሊት የሚከበርበት የፈንጠዚያ በአል ሆኗል፡፡ ሙሽራው ተረስቶ ሚዜዎቹ የሚታጀቡበት በአል ሆኗል፡፡ ይሄ የምዕራባውያን ባህል ወረራ ውጤት ነው፡፡ ስጦታ ግን የሃይማኖት መመሪያ ነው፡፡
ሃይማኖታዊ ትውፊትን ማስቀጠል
እነዚህ ነገሮች ተጠብቀው እንዲቀጥሉ ኃላፊነት መውሰድ የሚገባቸው ብዬ የማስበው በመጀመሪያ ደረጃ የእምነት ተቋማት ናቸው፡፡ የነበረውን ጠብቀው በማስተማር ማቆየት አለባቸው፡፡ ህዝብ ስላልፈለገና ስላልተቀበለ አይደለም፡፡ ሃይማኖታዊ እውነት፣ በሠዎች መልካም ፈቃድ የሚቀጥል ወይም የሚቋረጥ አይደለም፡፡ ስለዚህ የእምነት ተቋማት ባህልና ትውፊቱን የማስጠበቅ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ በመቀጠል ሚዲያዎችም ኃላፊነት አለባቸው፡፡ አሁን ለምሳሌ አዲስ አመትን በተመለከተ፣ ጋዜጣችሁ በዚህ አመት ያጣናቸው ታላላቅ ሰዎች ብሎ አውጥቷል ሲባል ሰምቻለሁ፡፡ 2016 በምን ተቆጥሮ ነው “በዚህ አመት የተባለው? ይሄ መታረም አለበት። በአማርኛ የሚተላለፉ የእንግሊዝ ወይም የፈረንሳይ ሚዲያዎች እስኪባሉ ድረስ ብዙ እየታዘብናቸው ነው፡፡
በሶስተኛ ደረጃ ት/ቤቶቻችን ከመዋዕለ ህፃናት ጀምሮ እስከ መካነ አዕምሮ (ዩኒቨርስቲ) ድረስ እያሰለጠናቸው ያለው ምንድ ነው? ዕውቀቱን ከምዕራባውያን፣ ውስጡን ከኢትዮጵያዊነት መሆን አለበት፡፡ በ4ኛ ደረጃ ፊልሙ ቲያትሩ የምንቀርፃቸው ገፀ ባህርያት፣ የምንጠቀምበት ቋንቋ … ኢትዮጵያዊነትን የምንገልፅበት ነው ወይ? የሚለው መጠየቅ አለበት፡፡ በ5ኛ ደረጃ መንግስት ግዴታ አለበት፡፡ ባህልና ቱሪዝም ምን እየሠራ ነው? እነዚህን መጠበቅና ማስጠበቅ አለበት፡፡

Read 11021 times