Print this page
Monday, 09 January 2017 00:00

የግርማ ጌታሁንን መዝገበ- ቃላት እኔ እንዳየሁት

Written by  ነቢይ መኮንን
Rate this item
(1 Vote)

 “--- ጥርት ያለ ጥረት ያለው ፀሀፊ ነው፡፡ ልቅም ያለ ሥራ ነው፡፡
             ብጥርጥር አድርጎ የሚፅፍ፣ ዝርዝር-ዳሳሽ (meticulous) ፀሀፊ ነው፡፡---”
          
       ስለ መዝገበ-ቃላት ሳስብ አስቀድሞ በአዕምሮዬ የሚመጡት ገና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሳለን እንጠቀምባቸው የነበሩት ‹‹ያለ አስተማሪ እንግሊዝኛ መማሪያ›› የሚሉ መፃህፍት ናቸው፡፡ እነዚያን ደራሲያን ምስጋና ይግባቸው፡፡ በአጭር አቀራረብ፣. በውስን ገጾች፣ በአንድ ወይም በሁለት ፍቺ መሠረቱን ጥለውልናልና። ከዚያን ጊዜ ጀምረን ምን ያህል የእንግሊዝኛ ቋንቋ እንዳዳበርን እናስብ፡፡ አድገን እነ ዶክተር አምሳሉ አክሊሉና ዎለፍ ሌስላው መዝገበ-ቃላት ዘንድ እስክንደርስ አያሌ ቃላትና ፍቺያቸው በአዕምሮአችን ተከማችተዋል፡፡ ተመላልሰዋል፡፡ ብዙ አገባቦችን አይተናል፡፡ ዛሬም በዕለት ሰርክ ንግግር ውስጥም ሆነ በሙያዊ ፋይዳ ረገድ በርካታ ቃላትን እያስተናገድን ነው፡፡ መግባባታችንም በዚያው መጠን የዳበረ ይመስለኛል፡፡ ህይወት ይቀጥላል፡፡ መግባባታችንም እንደዚያው፡፡ በየሞባይላችን ላይ የጫናቸው መዝገበ-ቃላት ቋንቋችንንና የመግባባት አቅማችንን ምን ያህል እንደሚያግዙ ልብ ይሏል!
በዛሬው ፅሁፌ ስለ አንድ ስለተደመምኩበትና ስለቀናሁበት አዲስ መዝገበ-ቃላትና ስለ ፀሀፊው ላወጋችሁ ነው፡፡ ለናንተም ከፀበሉ ይድረሳችሁ ዓይነት ምኞትም አለበት፡፡ በመጀመሪያ፣ በቃሌ ከረዥም ጊዜ ጀምሮ በማስታወሰው፣ መቼ እንዳጠናሁት ግን ትዝ በማይለኝ፤ ከአንደኛው የጥንት መፃህፍት መግቢያ ላይ ባገኘሁት ግጥም ልባርክ፡፡
ይህቺን ጨቅላ መፅሀፍ የምታነቡ ሁሉ
አደራ ስለእኔ ማሪያም ማሪያም በሉ፡፡
ከሆዴ ያለውን የትምርት ሽል
ያለጭንቅ እንድወልድ እንድገላገል፡፡
ከሀያ ስድስቱ ወንዶች ፊደላት
አርግዣለሁና መዝገበ-ቃላት
ስንት እልፍ አበው ናቸው አርግዘው የሞቱ
ቀኝ እጃቸው አጥሮ ፊደል በማጣቱ፡፡
ለትምክህት አይደለም ይህን መናገሬ
ለማስቀናት እንጂ ሰነፉን ገበሬ
ሃዋርያው ሲናገር ወደ ምዕመናኑ
ለምትበልጥ ፀጋ ይላል ቅኑ አስቀኑ!!
የመዝገበ ቃላቱን ፀሀፊ ግርማ ጌታሁንን መጀመሪያ ያወቅሁት፤ የአዲስ አድማስ ቢሮ ሴንትራል ሸዋ አካባቢ በነበረ ጊዜ፣ ቢሮዬ መጥቶ ነው፤ በአንድ በጋራ በምናውቃት ወዳጃችን አማካኝነት ወደ እኔ ተልኮ ነው። ብዙ ተጨዋወትን፡፡ ኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ እንዳለና፤ ጥናትና ምርምር ለማድረግና አርትዖትና የትርጉም ሥራ ለመስራት ወደ ጎጃም እንደመጣ፣ የነገረኝ ያኔ ነው፡፡ በማከልም ጎጃም ጥናቱን እያካሄደ ሳለ፣ እዚያ የሚነገረው ቋንቋ ለየት ያለ ሆኖ እንዳገኘው አስረዳኝ፡፡ ከዚያ እነዚያን ልዩ ሆነው ያገኛቸውን የአማርኛ ቃላት መሰብሰብ እንደጀመረ፤ ከዚህ ቀደም ለተፃፉ መዝገበ-ቃላት መጨመሪያ ወይም ማከያ የሚሆን አጋዥ መፅሀፍ ብፅፍስ ብሎ እንዳሰበና ዝግጅቱን እንዳጠናቀቀ አወጋኝ። እኔም ከመፅሀፍ አከፋፋዩ ከጥንቱ ወዳጄ ከክብሩ ክፍሌ ጋር አገናኘሁት፡፡
እነሆ ከዓመታት በኋላ የግርማ ጌታሁን መፅሀፍ፣ የ-ግይጌ ማከያ መዝገበ-ቃላት በሚል ርእስ ዛሬ ብቅ አለ፡፡ በእንግሊዝኛ Giyge’s ADVANCED SUPPLEMENT to Concise Amharic-English Dictionaries ይለዋል፡፡ (ምናልባት የላቀ ወይም የመጠቀ ማኬ ቢባል ADVANCED የሚለውን የእንግሊዝኛ ቃል ይመልስልን ይሆናል ብዬ ማሰቤ አልቀረም፡፡ ይህ የአማርኛ- እንግሊዝኛ መዝገበ-ቃላት በከፍተኛ ደረጃ ጥናት ላይ ላሉ ተማሪዎችና በሥነ-ፅሁፍ-ነክ ሙያዊ  ሥራ ላይ ላሉ ምሁራን መጠቀሚያ ይሆን ዘንድ በላቀ ደረጃ የተዘጋጀ ነው፤ ይለዋል - ግርማ) በዋናነት፤ የአማርኛ-እንግሊዝኛ መዝገበ-ቃላት መፃህፍትን ለማገዝ ወይም እነሱ ላይ ታካይ ሆኖ እንዲያገለግል ነው የፃፍኩት ይላል፤ አዘጋጁ። እኔ ግን ራሱን የቻለ መፅሀፍ ተደርጎ ቢወሰድ ምንም አቅም አያንሰውም፤ ባይ ነኝ፡፡ እንዲያውም በላቀ ደረጃ የተዘጋጀ መሆኑ ትልቅ ትርፍ አለው፡፡ ብዙዎቹ ያካተታቸው ቃላት፣ በታወቁት የዶክተር አምሳሉ አክሊሉ (1976 እ.ኤ.አ) እና የፕሮፌሴር ዎልፍ ሌዝላው (1979 እ.ኤ.አ) ቀዳሚ መዝገበ-ቃላት ውስጥ የሌሉ ናቸውና ለአማርኛ ቃላት ክምችታችን ላሜ ወለደች ነው፡፡ እሱ ማከያ (Supplement ) ማለቱ በመሠረትነት እነሱን ይዞ በመነሳት ነው፡፡
ግርማ በተጨማሪ እንደገለፀው፤ ‹‹በ1990 እ.ኤ.አ የታተመው ቲ.ኤል.ኬን ሌላው የአማርኛ እንግሊዝኛ መዝገበ ቃላት፤ ጥራት፣ምሉዕነትና ምሁራዊ ይዞታ ባለው ደረጃ ቀርቧል፡፡ ለመስኩ ትልቅ ርቀት የጨመረ ነው፡፡ ስለሆነም ለዋንኛው የአማርኛ ሥ-ፅሁፍ ሁነኛ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ ችግሩ፤ መፅሀፉ እጅግ ደጓሳ (በሁለት ዕትም 1088 እና 1263 ገጾች) ታትሞ በመቅረቡ ለትናንሾች የአውሮፓ መፃህፍት ቤቶች እንኳ የማይሞከር ዋጋ ያለው መሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ በትላልቅ መፃህፍት ቤቶች ለዋቢ ብቻ (reference) እንጂ እጅ-ገብቶ ለግል አገልግሎት ሊውል የሚችል አልሆነምም፡፡ የአማርኛ ሥነ ፅሁፍ ዕድገት የማያቋርጥ በመሆኑ፤ የኬን የ1990 ታላቅ ሥራ ኖሮም፤ ቋንቋችን ፍፁም ምሉዕነትና ወቅታዊ ብቃት ኖሮት ገና አልጠናም፡፡››
የግርማ ሥራ አስፈላጊነት እዚህ ጋ ደርዝ ይዞ ይመጣል፡፡ የእኔም ምርኮኝነት እዚህ ጋ ይጀምራል፡፡ እንደ ግርማ አገላለፅ፤ የማከያ ፅሁፉን ሥራ የጀመረው የጎጃምን ዜና- መዋዕል (Chronicle) በመተርጎምና አርትዖት ሥራ በመሥራት ላይ ሳለ ነው - የአለቃ ተክለ እየሱስ ዋቅጅራን መፅሀፍ፡፡ ይህ እንግዲህ እ.ኤ.አ በ1980ዎቹ መሆኑ ነው፡፡ በዚያን ጊዜ ይጠቀምባቸው የነበሩት አጥረው- የተዘጋጁ መዝገበ ቃላት (concise dictionaries) በዓላማም፣ በገጽም ውስንነት፣ በቂ ቃላት ባለመያዛቸው፣ ያንን ለማሸነፍ ከኦርጅናሌ ፅሁፎች፣ ከገድሎችና ከታተሙ ምንጮች.፤ ውድና የማይገኙ ጥንታዊ፣ ምሳሌያዊ አነጋገሮች፤ እንዲሁም ሌሎች አገላለፆችን መጥቀስና ማሰባሰብ ግድ ነበር። ዓመቱ ሲጨምር ስብስቡም እየበዛ ሄደና የግርማን ማከያ መዝገበ-ቃላት ያህል ሆነ፡፡ አደረጃጀቱና አሰነዳደሩ፣ እንዲሁም የቃላት አመራረጡ ዘዴ የዎለፍ ሌዝላው ዓይነት ነው፡፡ ሌዝላው የግዊዲን ዘዴ መጠቀሙ ይታወቃል፡፡ የግዊዲ መዝገበ-ቃላት አጠቃቀም ለማንኛውም ሰው ቀላል ነው የሚባለው ነው፡፡ ግርማ በዚሁ ሳይገታ፣ የግዕዝና የአማርኛ መዝገበ - ቃላት፣ ሀውልት - አከል ሥራ የሠሩትን አለቃ ኪዳነወልድንና የአለቃ ደስታ ተክለወልድን አሰነዳድ ዘዴ ለማከያ ሥራውን ተጠቅሞበታል፡፡ በዚህም፡
ሀ/ መነሻ ድምፃቸው ተመሳሳይ በሆነና በተለያየ ፊደል የሚፃፉ ለምሳሌ ሣለ እና ሳለ፤ አለለ እና ዐለለ፤ ከሠሠ እና ከሰሰ የሚሰጡትን የትርጉም ልዩነት አጉልቶ ለማሳየት፤
ለ. ለአስተዋይ ፀሀፍት እና የምሁራን ቤተሰብ የቃልን ታሪካዊ አመጣጥ፤ ሥርወ-ቃሉን መሠረት ባደረገና ተቀባይነት ባለው መልኩ፤ የሚመረምሩበት ዘይቤ እንዲኖራቸው ለማጠናከር
ሐ. በገጠሩ ህዝብ ለሚነገረው ቋንቋ ተገቢ ትኩረት ለመስጠት፤ አስቤ ተገልግዬበታለሁ ይላል፡፡ (ዞሮ ዞሮ የአማርኛ ተናጋሪው አብዛኛው ህዝብ ያለው እዚያው ገጠር ነው፡፡)
ፀሀፊው መዝገበ-ቃላቱን መታሰቢያ ያደረገላቸው ሰዎች ገርመውኛል፡፡ (ምክኔ፤ ከተለመደው ወጣ በማለቱ ይመስለኛል)፡-
ለወንድሞቼ ለከፍያለው ጌታሁን ይመር እና ለተሻለ መርሻ ብሎ ይጀምርና፤ ስልሳ ያህል ጓደኞቹንና ወዳጆቹን ስም ዝርዝር ያሰፍራል፡፡ ከዝርዝሩ ግርጌም እነማን እንደሆኑ ለማመሳከር የሚከተሉትን ማስታወሻ ፅፏል፡፡ በእንግሊዝኛ ነው የፃፈው፡፡ እኔ እንደሚከተለው ተርጉሜዋለሁ፡፡
“እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት አብዛኞቹ፤ የደርግ መንግስት ከ1968 እስከ 1970 (እ.ኤ.አ) ባካሄደው ቀይ ሽብር፤ በአረመኔያዊ ሁኔታ የተገረፉ፣ የተሰቃዩና የተገደሉ ናቸው፡፡ ያን ሲኦላዊ ሰቆቃና የረዥም ጊዜ እስራት ችለው የተረፉቱ ደግሞ በተከታዮቹ ዓመታት ህይወታቸው እስኪያልፍ ድረስ አካላዊና ስነ-አዕምሯዊ ጉዳት ደርሶባቸዋል። ከላይ የጠቀስኳቸው ሁሉ፤ እንዲሁ ሌሎች አያሌ የማላስታውሳቸው ሰለባዎች፤ አዲስ አበባ ከተማ ከፍተኛ ሰባት ውስጥ የነበሩ ናቸው። ብሩሀን፣ ጀግኖች፣ የሚንቀለቀል የሀገር ፍቅር የነበራቸውና ተራማጅ ወጣቶች ነበሩ፡፡ እነዚያ ወጣቶች ለህብረተሰቡ የዚያን ጊዜ ርዕዮተ-ዓለም የተዋጉ ዓይነተኛ የዚያ ትውልድ አባላት ናቸው፡፡ ምናልባት ግዴለሽነት ታይቶባቸው ቢሆን እንኳ፤ ያለጥርጥር ግን፤ ራስ-ወዳድነት ያልታየበት፤ በወጣት ጥኑና ጉጉ ስሜት የተሞላ፤ ተጋድሎ አካሂደዋል፡፡”
ግርማ ቀጥሎ፤ እገዛ ላደረጉለት ባለውለታዎቹ ተገቢውን እውቅና በመስጠት ያመሰግናል፡፡ በማስተማርና በምርምር የረዥም ጊዜ ልምድ ያላቸውን፣ አማርኛና ሌሎች የኢትዮጵያ ቋንቋዎችን ክህሎት የታደሉትን፣ የመዝገበ ቃላቱን አርታኢ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ሄይዋርድን፣ ከነሰጡት ሙገሳ፤ ቦታ ሰጥቶ በትህትና ያመሰግናቸዋል፡፡ አልፎ ተርፎ መፅሀፉ የእኔ የሆነውን ያህል የእሳቸውም  ነው ይላል፡፡ ከዚያም ለቤተሰቡና ለዘመድ-አዝማዱ ከፍተኛ ምስጋናን ይለግሳል፡፡ ከሽፋን ገፅ እስከ ኢንፎርሜሽን ዲዛይን ሥራ በቴክኒክ የረዱትን ሁሉ ያመሰግናል፡፡ (በነገራችን ላይ የሽፋን ገፁ እጅግ ቅልል ያለና ማራኪ ነው፡፡) በከፍተኛ ሰባት የደርግ ሰለባ የሆኑ ጓደኞቹን ስም ዝርዝር በማሰባሰብ የረዱትን ሁሉ እግዜር ይስጥልኝ ይላል፡፡ በመጨረሻ፤ አሳታሚውን አቶ ክብሩ ክፍሌን፣ ለማሳተም ስለነበረው ጉጉትና መፅሀፉን ለማስተዋወቅ ስለሚያደርገው ጥረት፣ስለ ደግነቱና ሰው-ላይ-ጭምር-ሊጋባ-ስለሚችለው-ልባዊ-ታታሪነቱ ታላቅ ምስጋና ያቀርብለታል፡፡ አገር ቤት መታተሙም ሆነ በተመጣጣኝ ዋጋ የመሸጡ ስኬት፤ ክብሩ ባይኖር አይሆንም ነበር፤ ሲል ውዳሴውን ችሮታል፡፡
የግርማ ጌታሁን አፃፃፍ እጅግ ምሁራዊ ነው። ምስጋናና ዕውቅና አሰጣጡም ጭምር፡፡ ይሄን ነገር ብንለምደው ደግ ይመስለኛል፡፡ ጥርት ያለ ጥረት ያለው ፀሀፊ ነው፡፡ ልቅም ያለ ሥራ ነው፡፡ ብጥርጥር አድርጎ የሚፅፍ፣ ዝርዝር-ዳሳሽ (meticulous) ፀሀፊ ነው፡፡ እንዲህ ያለውን ችሎታ ለማዳበር ብንጣጣር መልካም ይመስለኛል፡፡
መዝገበ-ቃላቱ 382 ገፆች ያሉት ነው፡፡ የታተመው በፋር ኢስት ትሬዲንግ ነው፡፡ ዋጋው 230 ብር ነው፡፡ ለመዝገበ-ቃላት በጣም መጠነኛ ዋጋ ይመስለኛል፡፡
መቅድሙ ስለ መዝገበ-ቃላቱ ይዘትና ቅርፅ አንኳሩን በማስቀመጥ የአንባቢን ዐይን ይገልጣል፡፡ በእንግሊዝኛ ነው የተፃፈው፡፡ አንዳንዱን ትላልቅ ሀሳብ ተርጉሜ ላካፍላችሁ፡፡ ግርማ ለየቃላቱ ሰፊ ትርጉም ይሰጠናል። በተለይ የተለየ አጠቃቀማቸውንና አገባባቸውን ድንቅ አድርጎ ይደረድርልናል፡፡ አንድ አስረጅ ልጥቀስ፡፡
ለቀቀ የሚለውን ቃል እንደሚከተለው ያቀርባል፡፡ (ገጽ 12)
ለቀቀ laqqaqqa 1. Let go; let out; set free 2.Let loose, unleash. እሳት ለቀቀበት esat leqqaqqabbat- set fire to it. ወታደር ለቀቀባቸው Wattadar laqqaqqabbaccew-he unleashed soldiers on them; (TI-GC 29A/8,15)-3 Move out, vacate; evacuate. ቤቷን ለቀቀች bet w an laqqaqqacc-she move out of her house. ሀገራቸውን ለቀቁ hagaraccawen laqqaqqu- they left their country. -4 fade; lose its color. ቀለሙ ለቀቀ qalamu laqqaqqa-its colour fade- 5. Resign, relinquish. ሥልጣኑ ለቀቀ seltanune laqqaqqa-he resigned from office. _6 grow out of (habit, character, etc). ትዕቢት አለቀው (አለቅቀው (ውም) ብሎ te:ebit al:laq: qaw belo-unable to grow out of his arrogance; (TI-GC 24A/4.)-7 Utter loudly or hysterically. ጩኸቷን ለቀቀችው Cuhatwan laqqaqqaccew- She cried hysterically.. -8. Emit, burst out or discharge involun-tarily. ሽንቱን ሱሪው ላይ እስኪለቀቅ ይስቃል፡፡ Sentun surrie lay eskilaqq yeseqal-he laughs until he wets his trousers.
(በነገራችን ላይ፤ ከላይ በአነባብ ውስጥ ያስገባቸው ለምሳሌ ‘a’ አናቷ ላይ ሁለት ነጥብ ያላት ሲሆን፤ e ደግሞ እንደ ተገለበጠች ያለች ደግሞም ፊቷን ያዞረች ናት፡፡ እንዲሁም w ባለችበት እንደ እመጫት ተደርጋ የተፃፈች ናት፡፡ ይሄ ሁሉ ድካም ትክክለኛውን ድምፅ ለማምጣት ነው፡፡ ፀሀፊው እንዲህ ያሉትን የድምጸት ወይም የፎኔቲክ ዘዴዎች አሳምሮ ስለሚጠቀም እጀ-ሰባራ እንዳላደርገው ብዬ ነው ልብ በሉልኝ የምለው)
እንግዲህ ‹‹ለቀቀ›› የሚለው ቃል ከመሠረታዊ ትርጉሙ፣ ከአነባበቡ፣ እስከነ ልዩ ልዩ አገባባዊ ፍቺው ምን ያህል ጥረት እንደተደረገበት ልብ እንበል፡፡ ከላይ (TI-GC ) የሚለው ምህፃረ ቃል፤ አለቃ ተክለየሱስ ዋቅጅራን ምንጭ ያደረገ መሆኑን ያመላከተበት ነው። የጎጃም ገድል ላይ ከፃፉት መፅሀፍ የተጣቀሰ ነው። ግርማ ጌታሁን የእሳቸውን መጽሀፍ አርትዖቱንና ትርጉሙን ሰርቷል፡፡
ከዚህ ቀደም አጥረው በቀረቡ መዝገበ- ቃላት ውስጥ በበቂ የተተረጎሙትን ቃላት መግደፍ፣ በበቂ ያልተተረጎሙትን ማከል፣ በታተመም ባልታተመም የአማርኛ ሥነፅሁፍ ውስጥ አዘውትረው የሚጠቀሱ እንዲሁም በትውፊትና በህዝባዊ ዘፈኖች ለምሳሌ (ዐዶ) እንደ የባህላዊና ታሪካዊ ጠቀሜታቸው እንዲገቡ አድርጓቸዋል፡፡ ግርማ ትልቅ ተፅዕኖ አለው ያለው ሌላ ፍሬ ጉዳይ፤ በሚከተሉት ነጥቦች ላይ ትኩረት ማድረግን ነው፡-
ሀ/ ሳይታዩ የታለፉ ግን ዘመናዊ ፅንሰ-ሀሳቦች በቅጡ ሊገልፁ የሚችሉ ቃላትን ለምሳሌ አባደ፣ alienate ወይም ማባድ፤ ከ‹‹ባዳ›› የመጣ ነው፡፡ ‹‹ባዳ›› በየዕለቱ የምንጠቀምበት ስም መሆኑን ልብ በሉ፡፡
ለ. እንደ ቆቦ፣ ቡሬ፣ ብጡል ያሉ እንደ ስም የሚወሰዱ ቃላትን ፍቺ
ሐ. ከዐረቢኛ የተዋስናቸውና በኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች የሚነገሩ ቃላት ለምሳሌ ሱብሒ፣ ውዱእ እና ዱዓ
መ. በምትክነት የሚያገለገሉ ቃላት ለምሳሌ፤ ከአስተዋፅዖና ከታዳጊ ይልቅ ተዋፅዖ እና አዳጊ
ሠ. ረቂቅ ልዩነት ያላቸውን ቃላት ማስተዋል ለምሳሌ መፀው፣ ጥቢ፣ እና ጽጌ ወይም ደግሞ በምሣር እና በጠገራ መካከል ያለውን ልዩነት
ግርማ፤ያለ ቃላት አፈጣጠር ህግ የመጡ ያላቸውን ቃላት ትቷቸዋል፡፡ ለምሳሌ መተግበር፣ ድረ ገጽ ወይም ድኅረ ገጽ፣ ግብረ መልስ፣ እና ፍኖተ ካርታ፡፡ እንደነዚህ ያሉትን ለታሪክ ብንተዋቸው ይሻላል ባይ ነው፡፡ ያም ሆኖ ፀሀፊው ለምን ያን እንዳለ በግርጌ ማስታወሻው  አስፍሮልናል፡፡ አንድ ሁለቱን ምክንያት ልጥቀሳቸው፡-
መተግበር የሚለው አርዐስት ገበረ ከሚለው ይልቅ ተገበረ ከሚለው የመጣ ይመስላል፡፡ ከመሰረታዊ ግንዱ ይልቅ ከተዋለደው መጣ ማለት ነው፡፡ መተግበር ለማለት መሞከር መተግደል ወይም መተፍጠር የማለት ያህል ስህተት ነው፡፡ ሌላው የተለመደ ቃል፡- ድረ ገጽ ወይም ድኅረ ገጽ የሚለው ነው፡፡ website እና webpage ለሚለው የቆመ ነው፡፡ የመጀመሪያው የገጽ ድር ማለት ሲሆን ሁለተኛው ከገጹ ጀርባ ወይም ኋላ ማለት ነው፡፡ ምናልባት ለሁለቱም በአማራጭነት የሚበጀው ድርገጽ ይሆን ይሆናል፡፡
የቃላት ቀጥተኛ አገባብና የፊደሉ ትክክለኛ ቦታን በተመለከተ፣ የኪዳነወልድ ክፍሌንና የደስታ ተክለወልድን ሥርዓት እንደሚከተል ይታያል፡፡ የፊደላቱ ቅደም - ተከተልና የአነባብ ልዩነት ካለ፣ ከነሰዋሰዋዊ አግባቡ በቅንፍ ውስጥ ማስቀመጡ ነገሩን ቀላል አድርጎታል፡፡ አንዳንድ በአነባበብ ልዩነት የሚያመጡ ቃላትንም ለይቶ ያብራራል፡፡ ለምሳሌ፤ አስረሽ ምቺ እና አስርረሽ ምቺ፡- መደበኛ ግሱን እና ስሙን በመጀመሪያ በማስቀመጥ፣ ከዚያ የሚመጣውን ወይም የሚወለደውን ግስ፣ ስም ወይም ቅጽል ያስከትላል፡፡ የቃላት ግብአቶቹን ግንዱንና ተወላጁን እንዴት እንደሰደራቸው አብራርቷል። አንዳንዴ ብቻ የምንጠቀምባቸውን የእንስሳትና ዕጽዋት ስሞችን ግን ገድፏቸዋል፡፡ ሳይንሳዊ ምዳቤያቸው የማይገኝ ሆኖበት ነው፡፡
የፊደል ቅደም - ተከተልን በተመለከተ የተጠቀመው ከአበገደ ይልቅ፡- ሀ-ሐ-ኅ(ኆ)፣ ለ፣ መ፣ ረ፣ ሠ-ሰ፣ሸ፣ቀ (ቁዌ)፣ በ፣
ተ፣ቸ፣ነ፣ኘ፣አ-ዐ፣ -ከ(ኩዌ)፣ ኸ፣ ወ፣
ዘ፣ዠ፣የ፣ ደ፣ ጀ፣ ገ(ጉዌ)፣ ጠ፣ ጨ፣ ጰ፣ ጸ-ፀ፣ ፈ ፐ የሚሉትን ነው፡፡
የአናባቢ ሆሄን የላንቃ፣ የምላስና የጉሮሮ ለይቶ ምልክት አበጅቶላቸዋል፡፡ ለእነ ቁዌ ቁዉ፣ ቁዋ … ሳይቀር በጥንቃቄ ምልክት አበጅቷል፡፡ ቀዳሚ ድምጸት ላላቸው ሆሄ አስቀምጧል፡፡ ለምሳሌ ርኩስ እና እርኩስ፡፡ ለ “እ” ቀዳሚ ድምፅ ምልክት አለው፡፡ የተገለበጠችና ፊቱዋን ያዞረችው የእንግሊዝኛዋ “ኢ” ፣ እንደ “እ” ታገለግላለች - በእርኩስ ውስጥ እንደምናያት፡፡ ለመጀመሪያው ቃል ወኪል እንዲሆነውም ጥምዝ ዳሽ ሰርቷል፡፡ ያ ቃል ሌላ ቦታ ሲገባ ያንን ጥምዝ ዳሽ ያኖራል ማለት ነው - ወኪል ሆኗል እንደማለት፡፡ ቃሉ የሚገኝበትን ገጽና የቃሉ ምንጭ ከየት እንደሆነ በሚገባ ገላጭ ምልከታ ይሰጠናል። ራሱ እንደ ምሳሌ የሰጠንን ልጥቀሰው፡-
ሐኔውን አገንድሮ ከሚለው ሐረግ ጎን (MSWM-EL 10) የሚል አህፅሮተ - ቃል ተቀምጧል፡፡ ይሄ የሚያጣቅሰው ሐረጉ ገጽ 10 ላይ እንደሚገኝና ምንጩ እንቅልፍ ለምኔ የተባለው መጽሀፍ ሲሆን፣ የተጻፈውም በብላቴን ማህተመ ሥላሴ ወልደ መስቀል መሆኑን ነው።
ስለ መዝገበ - ቃላት ጥቅም ለአንባቢ መፃፍ አንድም የዋህነት አንድም ንቀት ይሆናል፡፡ ያም ሆኖ በእኔ እይታ ከአዲሱ የግርማ ጌታሁን መፅሀፍ ያገኘሁትን ፋይዳ ማካፈሉ ደግ መስሎኛል፡፡ ማጠቃለያዬን በጥቂት መስመሮች ቀንብቤ ልጠቁም፡፡ ሌላውን አንባቢ ራሱ በቂ ጊዜ ወስዶ መፅሀፉ ላይ ያገኘዋል፡፡ ሲገለገልበት ደግሞ የበለጠ ዋጋውን ይረዳል፡፡
ማጠቃለያ
ግርማ ጌታሁን ጠንቃቃ ፀሐፊ ነው፡፡ እንደ መዝገበ - ቃላት ያለ ተገልጋዮቹን የማያሳስት ስነ - ፅሁፍ፣ ፍፁም ጥንቃቄን ይጠይቃልና እንደ ግርማ በርትቶ በትዕግስት መትጋት ወሳኝ ነው፡፡ ጥናቱን ይስጠን ጎበዝ!
ለሁላችንም ትምህርት የሚሆን ኮስታራነት ከፀሀፊው ፍርጥምታ እንማራለን፡፡ እንደዚህ ያለ ኮስታራነት ከኢትዮጵያ ሥነ- ፅሁፍ ድባብ ቆሌ ከራቀ ቆየ፡፡ ስለዚህ እንደግርማ ዓይነት ሰው ብቅ ሲል ቆሌዋ እንድትታረቀን ያግዘናል፡፡
ለአማርኛ ሥነፅሁፍና ፀሀፍት ዕፁብ አስተዋፅዖ አበርክቷል፡፡ ብዙ የድርሰትና የትርጉም ሥራ የምንሠራ ሰዎች ወይ ለጉዳዩ ሁነኛ ትኩረት ባለመስጠት፣ ወይ በቃላት እጥረት ሳቢያ ድግግሞሽና ተራነት እየጎበኘን ተችግረናል፡፡ በአብዛኛው አንድ የውጪ አገር ቋንቋ ቃል ወይም ሐረግ የአማርኛ ተመጣጣኝ ትርጉም የለውም እያልን እንፈጠማለን፡፡ እንዲህ እንደግርማ ያለ መፅሀፍ ከጣጣው ይገላግለናል፡፡ ከድርቁ ያድነናል።
በተለይ ደግሞ ገጣሚያን የቃላት ባንክ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ስለዚህ መዝገበ-ቃላቱ ባለውለታቸው ይሆናል፡፡
ዝርዝር ጉዳይ ውስጥ ገብቶ፣ እልህ አስጨራሽን ጉዞ ተጉዞ፣፣ ፍንትው አድርጎ ማሳየትን ግርማ አስተምሮናል፡፡ ባለውለታችን ነው፡፡
ለአበው ፀሀፍት ልንሰጥ የሚገባንን አክብሮት በትህትና አስተምሮናል፡፡ ከእነሱ የወሰደውን ግብዐትም ከነምክንያቱ አመስግኖ አስቀምጦልናል። ቀዳሚ ሰዎቻችንን እናክብር፡፡ ሥራቸውን የበለጠ ጥልቀትና ስፋት እንችረው፡፡
መዝገበ-ቃላት ማዘጋጀት የዋዛ ሥራ እንዳልሆነና ፅፌ ጨርሼዋለሁ የማይባል ነገር መሆኑን አሳይቶናል፡፡ አለቃ ኪዳነወልድ፣ አለቃ ደስታ፣ ዶክተር አምሳሉ፣ ፕሮፌሴር ዎልፍ ሌዝላው፣ ቲ ኤል ኬን ብዙ መዝገበ-ቃላት ፅፈዋል፡፡ አሁንም ግርማ መከያ ጨመረ፡፡ አማርኛ አሁንም በቃኝ አይልም፡፡ ስለዚህ የግርማን አርአያነት ተከትለን የበለጠ እናበልፅገው፡፡
በጭራሽ ዕውቀት በቃኝ አንበል!! መልካም ንባብ!!
ለአንባቢዎቼ የገና ስጦታ ይሁን!

Read 3675 times