Sunday, 08 January 2017 00:00

የጉራጌ የኪነጥበብ ባለሙያዎች መድረክ ተመሰረተ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 በተለያዩ የኪነ-ጥበብ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ የጉራጌ ተወላጆችን የሚያሳስብና የሚያወያይ የጉራጌ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች መድረክ ባለፈው ሳምንት በዮድ አቢሲኒያ የባህል ምግብ አዳራሽ ተመሰረተ፡፡ በምስረታ ስነ-ስርዓቱ ላይ ድምፃዊያን፣ ተወዛዋዦች፣ የፊልም ባለሙያዎች፣ አንጋፋ ደራሲያን፣ ሰዓሊያን፣ ተዋንያንና ሌሎችም ከመቶ በላይ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ተገኝተዋል፡፡
የጉራጌ ተወላጅ የኪነ- ጥበብ ባለሙያዎች፤ አካባቢያቸውን ባህላቸውንና ታሪካቸውን ለቀሪው ኢትዮጵያዊና ለመላው ዓለም ለማስተዋወቅ፣ በሙያቸው ዙሪያ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ለመፍታትና እርስ በእርስ ለመደጋገፍ የሚያስችል መድረክ እንዳልነበራቸው በምስረታው የተገለፀ ሲሆን የመድረኩ መመስረት ዋና አላማ፤ እነዚህን ክፍተቶች ለመሙላትና የጉራጌን እምቅ ባህልና አብሮነት በጋራ ለዓለም ማስተዋወቅ እንደሆነ፣ የጉራጌ ልማትና ባህል ማህበር ዋና ዳይሬክተርና ደራሲ ተስፋዬ ጉይቴ ተናግረዋል፡፡
የተመሰረተው መድረክ እስኪጠናከርና በራሱ እስከሚቆም የጽ/ቤት፣ የፋይናንስና መሰል ድጋፎችን የጉራጌ ልማትና የባህል ማህበር ድጋፍ እንደሚያደርግላቸው የማህበሩ የባህል ዘርፍ ምክትል ዳይሬክተር አቶ መንግስቱ ኃ/ማሪያም ገልፀዋል፡፡
በምስረታ ስነስርዓቱ ላይ መድረኩን የሚመሩ ሀላፊዎች ምርጫ፣ ስለ መድረኩ የወደፊት ጉዞ ውይይትና የመዝናኛ ፕሮግራሞች የተካሄዱ ሲሆን ድምፃዊያንና ተወዛዋዦች የሙዚቃ ስራዎቻቸውን ለታዳሚው አቅርበዋል፡፡

Read 2395 times