Monday, 09 January 2017 00:00

የሸገር ደርቢ በኢትዮጵያና ሌሎች ደርቢዎች… በአፍሪካ፤ በአውሮፓና በዓለም ዙርያ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

 በእግር ኳስ ስፖርት ሁለት ተቀናቃኝ ክለቦች የሚገናኙበት ግጥሚያ ደርቢ በሚል መጠርያ ይታወቃል። ደርቢዎች በስፖርቱ ታሪክ እና እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ አላቸው፡፡  በየውድድር ዘመኑ የሚጠበቁ የጨዋታ መርሃ ግብሮች ናቸው፡፡ በህትመት፤ በብሮድካስት፤ በኢንተርኔት የመረጃ መረቦች በሚያገኙት ትኩረትም ይለያሉ፡፡ የደርቢ ጨዋታዎች ስታድዬሞችን በመሙላት፤ ከፍተኛ የትኬት ሽያጭ በማስመዝገብ፤ በማልያ ሽያጭ፤ በቴሌቭዥ የስርጭት መብት በሚያስገኙት ከፍተኛ ገቢ እና ትርፋማነታቸው ይታወቃሉ፡፡ በየደርቢ ጨዋታዎቹ የሚመዘገቡ ውጤቶች በየክለቦቹ በሚገኙ አሰልጣኞች፤ ተጨዋቾች፤ አመራሮች እና ቀንደኛ ደጋፊዎች እጣ ፋንታ ወሳኝነት ይኖራቸዋል። አንዳንድ ደርቢዎች በፖለቲካዊ፤ በኢኮኖሚያዊ እና ሌሎች የውዝግብ አጀንዳዎች የሚታመሱ፤ ሌሎች ደግሞ በየጊዜው በከፍተኛ ውጥረት የሚካሄዱ እና የሁሊጋኒዝም መናሐርያዎች እየሆኑ ይስተዋላል፡፡ የአንድ ከተማ ክለቦችን የሚያገናኙት የእግር ኳስ ጨዋታዎች መደበኛዎቹ የደርቢ ትንቅንቆች ናቸው፡፡  በዘመናዊ የእግር ኳስ ታሪክ ግን ሌሎች የተለያዩ የደርቢ አይነቶች ተፈጥረዋል፡፡ ሁለት ተቀናቃኝ ከተሞች የሚፋጠጡባቸው፤ በየጊዜው በሚመዘገቡ የውጤት ታሪኮች ተፎካካሪዎች የተፈጠሩባቸው፤ በውጤት የበላይነት የሚያስተናንቁ  … ብዙ አይነት ደርቢዎች በመላው ዓለም ይካሄዳሉ፡፡
ይህ የስፖርት አድማስ ልዩ ዳሰሳ  ባለፈው ሳምንት በአዲስ አበባ ስታድዬም የኢትዮጵያ ቡና እና የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለቦች ያደረጉትን ጨዋታ መነሻ አድርጎ የተዘጋጀ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ትልቁ ደርቢ የሚባለው የሁለቱ ክለቦች ፍልሚያ ሸገር ደርቢ በሚለ ስያሜው የሚታወቅ ሆኗል፡፡ የሁለቱ ክለቦች ትንቅንቅ በአፍሪካ፤ በአውሮፓ እና በሌሎች የዓለም ክፍሎች በእግር ኳስ ከሚካሄዱ የአንድ ከተማ ክለቦች የደርቢ ጨዋታዎች ጋር ለማነፃፀር ነው፡፡ በተጨማሪም ሌሎች የእግር ኳስ የደርቢ ጨዋታዎችንም በተለያዩ መለኪያዎች በመቃኘት ያስተዋውቃችኋል፡፡
ሸገር ደርቢ በኢትዮጵያ
ሸገር ደርቢ ባለፈው ሳምንት በእድሜ ጠገቡ የአዲስ አበባ ስታድዬም  በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 8ኛ ሳምንት  መርሃ ግብር  ኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ያገናኘው ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ትልቁ ግጥሚያ የሆነው  የሁለቱ ክለቦች ትንቅንቅ ከ30 እስከ 35 ሺህ ተመልካቾችን በሚያስተናግደው የአዲስ አበባ ስታድዬም ሲካሄድ ከ3 ነጥቦች በላይ ብዙ ጠቀሜታዎች እንዳሉት በተለያዩ መረጃዎች ማመልከት ይቻላል፡፡ ሸገር ደርቢ ከትኬት ሽያጭ ብቻ 800ሺ ብር የተገኘበት ነው፡፡ ምናልባትም በቀጣይ ዓመታት ከአዲስ አበባ ስታድዬም ባሻገር 60ሺ ተመልካች በሚያስተናግድ ስታድዬም የሚካሄድ ቢሆን የትኬት ገቢው  በ2 እና በ3 እጥፍ ሊጨምር የሚችል ነው፡፡ በሸገር ደርቢ የሚገኘው ጥቅም በስታድዬም የትኬት ሽያጭ ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ ቡናማውን እና ቡርቱካናማውን ማሊያ ለብሰው ባሸበረቁ የሁለቱ ደጋፊዎች የደመቀው ጨዋታ ከሜዳ ውጭም አትራፊ ነው፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስን 1ለ0 ያሸነፈው ኢትዮጵያ ቡና ከጨዋታው ጋር በተያያዘ እስከ ከ4000 በላይ ማሊያዎችን የሸጠ ሲሆን፤ ክለቡ ዘንድሮ ከማሊያ ሽያጭ እስከ 1 ሚሊዮን ብር ማግኘቱን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስም ከጨዋታው ሁለት ቀናት በፊት ጀምሮ ከ3000 በላይ ማሊያዎችና በሺዎች የሚቆጠሩ የአንገት ሻርፖችን በመሸጥ ተሳክቶለታል፡፡ ደርቢው በአገሪቱ የሚዲያ አውታሮችም ሰፊ ትኩረት አግኝቷል፡፡  3 የኤፍ ኤም ራድዮ ጣቢያዎች በቀጥታ ስርጭት ያስተላለፉት ሲሆን ከአራት በላይ የቴሌቭዥን ጣቢያዎችም ቀረፃ አከናውነውበታል፡፡ ምናልባት ለወደፊት ሁለቱ ክለቦች በሚቀይሱት አቅጣጫ በአፍሪካ ደረጃ የቀጥታ ስርጭት የሚያገኝበት እድል ከተፈጠረ የሌሎችአገራት መገናኛ ብዙሃናት ሰፊ ሽፋን ሊሰጡት ይችላሉ፡፡ ይህም ሸገር ደርቢን ከአፍሪካ ምርጥ የእግር ኳስ ደርቢዎች ተርታ በማሰለፍ በቱሪዝም መስህብነቱ ተጨማሪ ውጤት ለማግኘት የሚያግዝ ይሆናል፡፡
የሁለቱ ክለቦች የአንድ ከተማ የደርቢ ትንቅንቅ ባለፈው ሳምንት የተካሄደው ለ36ኛ ጊዜ ሲሆን 20 ጊዜ  ቅዱስ ጊዮርጊስ ሲያሸንፍ ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ 7 ጊዜ ረትቷል፡፡ በ9 ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከተመሰረተ 81ኛ ዓመቱን የያዘ ሲሆን  ከ1950 እኤአ ጀምሮ 28 ጊዜ የሊግ ሻምፒዮን፤ በጥሎ ማለፍ ከ1952 እኤአ ጀምሮ 10 ጊዜ አሸናፊ እንዲሁም በሱፕር ካፕ ከ1994 እኤአ ጀምሮ 8 ጊዜ በማሸነፍ በድምሩ46 ዋንፃዎችን ሰብስቧል። በአፍሪካ የክለቦች ውድድር አስቀድሞ ካፕ ኦፍ ሻምፒዮን ክለብስ በሚባለው ውድድር  ለ10 ጊዜያት፤ በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ 9 ጊዜያት፤ በአፍሪካ ክለቦች ኮንፌደሬሽን ካፕ 1 ጊዜ፤ በካፍ ካፕ 1 ጊዜ እንዲሁም በካፍ ካፕዊነርስ ካፕ 3 ጊዜ ለመሳተፍ ችሏል፡፡ ኢትዮጵያ ቡና ከተመሰረተ 40ኛ ዓመቱን የያዘ ሲሆን የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግን ለሁለት ጊዜያት፤ የጥሎ ማለፍ ለ5 ጊዜያት፤ የሱፕር ካፕ ለ4 ጊዜያት እንዲሁም የራን አዌይ ሊግን ለ1 ጊዜ በማሸነፍ 12 ዋንጫዎችን ሰብስቧል፡፡ በአፍሪካ የክለቦች ውድድር ደግሞ በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ 2 ጊዜያት፤ በአፍሪካ ክለቦች ኮንፌደሬሽን ካፕ 1 ጊዜ፤ በካፍ ካፕ 2 ጊዜ እንዲሁም በካፍ ካፕዊነርስ ካፕ 3 ጊዜ ለመሳተፍ ችሏል፡፡
*   *   *
ሶስቱ  ምርጥ የአንድ ከተማ ክለቦች ደርቢዎች በአፍሪካ
ካይሮ ደርቢ በግብፅ
ኤል አሃሊን ከዛማሌክ የሚያገናኘው የካይሮ ደርቢ በአፍሪካ ትልቁ የደርቢ ጨዋታ ነው ማለት ይቻላል፡፡ የሰሜን አፍሪካ ተመልካቾች በእግር ኳስ አፍቃሪነታቸው ልዩ እና ተስተካካይ እንደሌላቸው ያረጋገጠው ደርቢው፤ በጥንታዊቷ የካይሮ ከተማ ላይ በእግር ኳስ ውጤት ለመንገስ በየጊዜው የሚደረግ ትንቅንቅ ነው፡፡ በቀይና ነጭ ቀለማት ያሸበረቁ ልዩነቶች በከፍተኛ ደረጃ የሚንፀባረቁበት ፍልሚያው በየጊዜው በሚያጋጥሙ ብጥብጦች የተነሳ ከዓለማችን አስፌ ደርቢዎች ተርታ ያስፈረጀው ነው፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት በመቶዎች የሚቆጠሩ የሁለቱ ክለቦች ደጋፊዎች በብጥብጥ ህይወታቸው በማለፉ፤ ዘንድሮ የደርቢ ጨዋታው በካይሮው ዋና ብሄራዊ ስታድዬም ያለተመልካች በዝግ እንዲካሄድ  ተደርጓል፡፡ የግብፅ ክላሲኮ ተብሎ በሚጠቀሰው ግጥሚያ የሚገናኙት ሁለቱ ክለቦች በግብፅ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ደረጃ ከፍተኛ ስኬት አላቸው፡፡ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን የ20ኛው ክፍለ ዘመን የአህጉሪቱ ምርጥ ክለቦች ብሎ የተባሉ ሲሆን ኤል አሃሊን 1ኛ ደረጃ እንዲሁም ዛማሌክ ሁለተኛ ደረጃ ሰጥቷቸዋል፡፡ ክለቦቹ በግብፅ ሊግ በአመት ሁለት ጊዜ ከመገናኘታቸው ባሻገር፤ በግብፅ የጥሎ ማለፍ ዋንጫ እንዲሁም በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ እና በኮንፌደሬሽን ካፕ በየጊዜው መገናኘታቸው የሚያገኙትን ትኩረት ከማሳደጉም በላይ በሰሜን አፍሪካ፤ በመካከለኛው ምስራቅ እና በአረቡ ዓለም  ባለፉት 10 ዓመታትም የቀጥታ ቴሌቭዥን ስርጭት አስገኝቶላቸዋል፡፡
ሁለቱ ክለቦች ባለፉት 30 ዓመታት በግብፅ የውስጥ ውድድሮች እና በአፍሪካ ደረጃ 157 ግጥሚያዎች አድርገው 65 ጊዜ ኤል አሃሊ እንዲሁም ዛማሌክ 56 ጊዜ ያሸነፉ ሲሆን በ65  ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል፡፡ በጋራ የሰበሰቧቸው ዋንጫዎች ብዛትም 152 ሲሆን 102 የኤል አሃሊ እንዲሁም 50 የዛማሌክ ናቸው፡፡ ሁለቱ ክለቦች በመካከከላቸው 50 የግብፅ ሊግ እንዲሁም 60 የግብፅ ጥሎ ማለፍ ዋንጫዎችን ሰብስበዋል፡፡   ኤል አሃሊ በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ 8 ጊዜ ሲያሸንፍ ዛማሌክ ደግሞ 5 ጊዜ ሻምፒዮን መሆን ችሏል፡፡ ኤል አሃሊ በ1948 /49 የመጀመርያውን የግብፅ ሊግ ካሸነፈ በኋላ ለ38 ጊዜያት ሻምፒዮን ለመሆን ሲበቃ ዛማሌክ 12 ጊዜ ሻምፒዮን ነው፡፡
ስዌቶ ደርቢ በደቡብ አፍሪካ
ኦርላንዶ ፓይሬትስን ከካይዘር ቺፍ የሚያገናኘው ስዌቶ ደርቢ ከ40 ዓመታት በላይ እድሜ ያለው ሲሆን፤ የመጀመርያው ጨዋታ በ1970 እኤአ ላይ ተደርጓል፡፡በደቡብ አፍሪካ የስፖርት ቁማር ከፍተኛ ትኩረትም የሚስበው  የሁለቱ ክለቦች ትንቅንቅ የተጀመረው ካይዘር ሞቱዋንግ የተባለ የኦርላንዶ ፓይሬትስ ተጨዋች ለረጅምግዜ ክለቡን አገልግሎ ጫማውን ከሰቀለ በኋላ ካይዘር ቺፍን በመመስረቱ ነበር፡፡ በአፍሪካ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ካገኙ ጨዋታዎች አንዱ ከመሆኑም በላይ በክለቦቹ ማልያዎች የተለያዩ አልባሳት፤ በቩቩዜላ እና በህብረ ዝማሬዎች ይደምቃል፡፡ ስዌቶ በጆሃንስበርግ ከተማ የምትገኝ የድሆች መንደር ስትሆን የደርቢ ጨዋታን የሚያስተናግደው ስታድዬሙ ኤፍኤንቢ የሚባል፤ በ2010 እኤአ ሶከር ሲቲ ተብሎ የ19ኛው የዓለም ዋንጫ የፍፃሜ ጨዋታን ያስተናገደና ከ90ሺ በላይ ተመልካች የሚይዝ ነው። ሁለቱ ክለቦች በደቡብ አፍሪካ በሚካሄዱ ሁሉም የክለብ ውድድሮች ለ65 ጊዜያት ተገናኝተው ካይዘር ቺፍ 21 ጊዜ ሲያሸንፍ ኦርላንዶ ፓይሬትስ በ19 አሸንፎ በ22 ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል፡፡ በደቡብ አፍሪካ የሊግ ውድድር ካይዘር ቺፍ 18 ጊዜ ሻምፒዮን የሆነው ካይዘር ቺፍ በሌሎች የአገር ውስጥ ውድድሮች ጋር 40 ዋንጫዎችን ሰብስቧል። በደቡብ አፍሪካ የሊግ ውድድር 8 ጊዜ ሻምፒዮን የሆነው ኦርላንዶ ፓይሬትስ ደግሞ ከሌሎች ውድድሮች ጋር በድምሩ 18 ዋንጫዎችን ሰብስቧል፡፡
ቱኒዝ ደርቢ በቱኒዚያ
ክለብ አፍሪካን ከኤስፔራንስ ስፖርቲቭ ዴስ ቱኒስ የሚያገናኘው የቱኒዝ ደርቢ በብዙ ገፅታው ከካይሮ ደርቢ ጋርም ይመሳሰላል፡፡
ኤስፔራንስ በ1919 እንዲሁም ክለብ አፍሪካን በ1920 እኤአ ላይ በአንድ አመት ልዩነት የተመሰረቱ የቱኒዚያ ውጤታማ ክለቦች ሲሆኑ ለደርቢው ጨዋታ ለዓመታት በሜዳነት የተጠቀሙት ስታድዬም ስታዴ ኤልሜንዛህ ይባል ነበር፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ጨዋታቸው 60ሺ ተመልካቾችን በሚያስተናግደው ስታዴ ኦሎምፒኩዌ ዴ ራዴስ የሚደረግ ነው፡፡ ሁለቱ ክለቦች ባሏቸው የደጋፊዎች ብዛት ከሁሉም የቱኒዚያ ክለቦች በእጅጉ የላቀ ደርሻ ሲኖራቸው በሁሉም ውድድሮች በ120 ጨዋታዎች ተገናኝተው 48 ያሸነፈው የቱኒዚያን ዝቅተኛ ማህበረሰብ የሚወክለው ኤስፔራንስ ሲሆን የከፍተኛው ማህበረሰብ ተወካይ የሚባለው ክለብ አፍሪካን በ27 ድል ቀንቶታል፡፡
*   *   *
ሶስቱ  ምርጥ የአንድ ከተማ ክለቦች  ደርቢዎች በአውሮፓ
ደርቢ ዴላ ማዶንያ በጣሊያን
የሚላን ከተማን በሚወክሉት ኤሲ ሚላን እና ኢንተር ሚላን የሚደረገው ይህ ደርቢ ሚላን ደርቢ እና  ሳንሲሮ ደርቢ  በሚል ስያሜዎችም  ይጠራል፡፡ የጣሊያን የክለብ እግር ኳስ ከፍተኛ ትንቅንቅ ሲሆን ሁለቱም ክለቦች በአውሮፓ ከፍተኛ ስኬት ያገኙም ናቸው፡፡
ታዋቂውን ሳንሲሮ ስታድዬምን የጋራ ሜዳቸው አድርገው የሚፋለሙት ሁለቱ ክለቦች በጣሊያንና በአውሮፓ ደረጃ በሁሉም ውድድሮች 217 ጊዜ ተገናኝተዋል፡፡ ኢንተርሚላን 77 ጊዜ ኤሲ ሚላን ደግሞ 75 ጊዜ በደርቢ ጨዋታው ድል ሲቀናቸው በ65 ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል፡፡  እነቫንባስተን፤ ሮናልዶ፤ ካካ፤   ዛኔቲ፤ ኢብራሞቪችና… ሌሎች ታላላቅ ተጨዋቾች የተሰለፉበት ይህ ደርቢ ላይ ብዙ የተጫወተው የኤሲ ሚላን አምበል የነበረው ፓውሎ ማልዲኒ በ56 ጨዋታዎች በመሰለፍ ሲሆን ሌላው የኤስ ሚላን ተጨዋች ዩክሬናዊው አንድሬይ ሼቼንኮ በ14 ጎሎች የደርቢው ከፍተኛ ግብ አግቢ ነው፡፡  ኤሲ ሚላን በሴሪኤ፤ በኮፓ ኢታሊያ፤ በሻምፒዮንስ ሊግ እና በአውሮፓ ሱፕር ካፕ በድምሩ 48 ዋንጫዎችን ሲሰበስብ ኢንተርሚላን ደግሞ 39 ዋንጫዎችን ሰብስቧል፡፡ ሁለቱ ክለቦች በጣሊያኑ ሴሪኤ እኩል 18 ጊዜ ሻምፒዮን ሲሆኑ በአውሮፓ ደረጃ ኤሲ ሚላን 7 ጊዜ እንዲሁም ኢንተርሚላን 4 ጊዜ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫዎችን ተጎናፅፈዋል፡፡
ኤል ደርቢ ማድሪሊያኖ   በስፔን
ሪያል ማድሪድ ከአትሌቲኮ ማድሪድ የሚያገናኘው ይህ ደርቢ የስፔን ዋና ከተማ ማድሪድን የሚወክሉት ሁለት አንጋፋ ክለቦች የሚፋለሙበት ሲሆን ከ220 በላይ ጨዋታዎች ተደርገውበታል፡፡ የሁለቱ ክለቦች የደርቢ ጨዋታን የሚያተናግዱት ስታድዬሞች የሪያል ማድሪዱ ሳንቲያጎ በርናባኦ እና የአትሌቲኮ ማድሪዱ ቪሰንቴ ካልዴሮን ናቸው፡፡ ለመጀመርያ ጊዜ የተካሄደው የማድሪድ ደርቢ በ1928 እኤአ የተካሄደው ኮፓ ዴላሬይ ሲሆን 1ለ0 ያሸነፈው ሪያል ማድሪድ ነበር፡፡ ለመጨረሻ ጊዜ የተገናኙት ደግሞ ከ2 ወራት በፊት በስፔን ፕሪሚዬራ ሊጋ የነበረ ሲሆን አትሌቲኮ ማድሪድን በቪሴንቴ ካልዴሮን ሪያል ማድሪድ 3ለ0 ያሸነፈበት ነው፡፡ የማድሪድ ደርቢ ከፍተኛ ጎል አግቢ የሪያል ማድሪዱ ክርስትያኖ ሮናልዶ በ18 ጎሎች ነው፡፡
ሜርሲሳይድ ደርቢ በእንግሊዝ
ሊቨርፑል እና ኤቨርተን በሚያዋስነው ሜሪሲ የተባለ ወንዝ  ሜርሲሳይድ ደርቢ ተብሎ የተሰየመው ይህ ትንቅንቅ የወዳጅነት ደርቢ ተብሎ በተለያዩ ዘገባዎች ይጠቀሳል። የሊቨርፑል ከተማን በቀዮቹ ሊቨርፑል በሰማያዊዎቹ ኤቨርተን የከፈለ የደርቢ ጨዋታ ነው፡፡ ሁለቱ ክለቦች የደርቢ ጨዋታዎችን የሚያደርጉባቸውማዶ ለማዶ የሚተያዩ ስታድዬሞች የሊቨርፑሉ አንፊልድ እና የኤቨርተኑ ሜርሲሳይድ ናቸው፡፡ ለመጀመርያ ጊዜ የተገናኙት በእንግሊዝ አንደኛ ዲቪዝዮን በ1894 እኤአ ላይ ሲሆን 3ለ0 ያሸነፈው ኤቨርተን ሲሆን ከወር በፊት ደግሞ በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ የመጨረሻ ጨዋታቸውን አድርገው በጉዲሰን ፓርክ ድል የቀናው 1ለ0 የረታው ሊቨርፑል ነው፡፡  ሁለቱ ክለቦች በሁሉም ውድድሮች ተገናኝተው ሊቨርፑል 90 ጊዜ ኤቨርተን 66 ጊዜ ማሸነፍ የቻሉ ሲሆን በ71 ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል፡፡ የሜርሲሳይድ ደርቢ ከፍተኛ ግብ አግቢ 25 ጎሎች በስሙ ያስመዘገበው የሊቨርፑሉ ኢያን ራሽ ነው፡፡
*   *   *
ምርጥ የአንድ ከተማ ክለቦች ደርቢዎች  በዓለም ዙርያ  
ኦልድ ፊርም ደርቢ  በስኮትላንድ
የስኮትላንድ ታላላቅ ክለቦችን ሴልቲክ  እና ሬንጀርስ የሚያገናኘው ይህ የደርቢ ጨዋታ
በዓለም አንጋፋው የአንድ ከተማ ክለቦች  ትንቅንቅ ሲሆን  ከ125 ዓመታት በላይ ታሪክ አስመዝግቧል። ማህበራዊ፤ ፖለቲካዊ እና ሃይማኖታዊ ልዩነቶች የሚንፀባረቁበት ደርቢው እስከ 125 ሚሊዮን ዶላር ለስኮትላንድ ኢኮኖሚ የሚያስገኝም ነው፡፡ ሁለቱ ክለቦች በስኮትላንድ ሊግ 101  ጊዜ በሻምፒዮናነት የተፈራረቁ ሲሆን 54 በሴልቲክ 47 ደግሞ በሬንጀርስ የተመዘገቡ ናቸው፡፡ በውድድር ታሪካቸው በሁሉም የውድድር ደረጃዎች ከ404 ጊዜ በላይ ተገናኝተዋል፡፡ ሬንጀርስ 159 እንዲሁም ሴልቲክ 148 ጊዜ የደርቢ ጨዋታውን ያሸነፉ ሲሆን 97 ጊዜ አቻ ተለያይተዋል፡፡
ሱፕርክላሲኮ ደርቢ በእርጀንቲና
ቦካ ጁኒዬርስን ከሪቨር ፕሌት የሚያገናኘው ይህ ደርቢ የቦካ ጁኒዬርስ ከተማ አበይት ክስተት ሆኖ ይጠቀሳል። ለመጀመርያ ጊዜ የተደረገው በ1913 እኤአ ሲሆን እጅግ ሃይለኛ ፉክክር የሚታይበትና ቦካ ጁኒዬርስ የወዛደሩ እንዲሁም ሪቨርፕሌት የባለፀጋው ማህበረሰብን በመወከል የሚያደርጉት ትንቅንቅ ነው፡፡  በአርጀንቲና የክለብ እግር ኳስ  ከፍተኛ የውጤት ታሪክ ያስመዘገቡት ሁለቱ ክለቦች ከአገሪቱ የስፖርት አፍቃሪ 70 በመቶ ያህሉን ደጋፊዎቻቸው ያደረጉ ናቸው፡፡ በሁሉም ውድድሮች 362 ጊዜ ተገናኝተው 132 ጊዜ ቦካ ጁኒዬርስ 116 ጊዜ ደግሞ ሪቨር ፕሌት የደርቢ ጨዋታውን ሲያሸንፉ 115 ጊዜ አቻ ተለያይተዋል፡፡ ይህ ደርቢ ማራዶና፤ ኦርቴጋ፤ ክሬስፖ፤ ቴቬዝ…..የመሳሰሉ ተጨዋቾችን ያሳተፈ ነው፡፡
*   *   *
አንድ ከተማን የሚወክሉ ክለቦች ደርቢ
በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ የአንድ ከተማ ክለቦች ከሚቀናቀኑባቸው ሌሎች የደርቢ  ፍልሚያዎች የሰሜን ለንደን ደርቢ የሚባለው የአርሰናል እና የቶትንሃም ክለቦች ፍጥጫ እንዲሁም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ከፍተኛ ትኩረት እያገኘ ያለው የማንችስተር ከተማ ክለቦች ማንችስተር ዩናይትድ እና ማንችስተር ሲቲ የሚያገናኙት ይጠቀሳሉ። በአንድ ከተማ ክለቦች በአውሮፓ ከሚካሄዱ ሌሎች ደርቢዎች መካከል  በጣሊያን ዋና ከተማ ወኪልነታቸው የሚታወቁት ሮማ እና ላዚዮ የሚፋጠጡበት የሮም ደርቢ፤ በጀርመን የሩሃር ግዛትን የሚወክሉት ቦርስያ ዶርትመንድ እና ሻልካ 04 የሚያካሂዱት ሬቭዬር ደርቢ ፤ በፖርቱጋሏ ሊዝበን ተወካዮች ቤነፊካ እና ስፖርቲንግ ሊዝበን መካከል የሚደረገው ደርቢ ዴላ ሊዝቦዎ  እንዲሁም በግሪክ አቴንስ ከተማ የሚገኙትና የአገሪቱ ከፍተኛ ውጤታማ ክለቦች ኦሎምፒያኮስ ከፓነትኒያኮስ የሚያደርጉት የአቴና ደርቢ ይጠቀሳሉ፡፡ በሌላው ዓለም ክፍል በአንድ ከተማ ክለቦች ከሚካሄዱ የደርቢ ጨዋታዎች መካከከል ደግሞ ሁለቱ የሚገኙት በታላቋ የእግር ኳስ አገር ብራዚል ነው፡፡ ሳኦፓውሎ ደርቢ የሳኦፓውሎ ከተማ ተወካዮች በሆኑት ኮረንቲያስ እና ፓልሚሬስ የሚካሄደው ሲሆን በሪዮ ዲጄኔሮ ከተማ ክለቦች መካከል የሚደረገውና ፍላ ፍሉ ደርቢ ተብሎ የሚጠራው የፍላሚንጎ እና የፍሉሚንዜ ክልቦች ጨዋታ ነው፡፡
*   *   *
ሁለት የተለያዩ ከተሞች የሚወክሉ ክለቦች ደርቢ
በሁለት የተለያዩ ከተሞች ተወካዮች የሚደረጉ ታላላቅ የደርቢ ጨዋታዎችም በዓለም ዙርያ ይገኛሉ። በተለይ መጠቀስ ያለበት በመላው ዓለም በሚያገኘው የቲቪ ተመልካች ብዛት፤ በገቢው ከፍተኛነት እና በውጤት የበላይነት የሚካሄደው የሪያል ማድሪድ እና የባርሴሎና ክለቦች ፍልሚያ ነው፡፡ ኤል ክላሲኮ ተብሎ ስያሜ የተሰጠው ይህ የደርቢ ፍልሚያ በመላው ዓለም እስከ 500 ሚሊዮን የቲቪ ተመልካች የሚያገኝ፤ ከ200 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ የሚሆንበትም ነው፡፡  በሆላንድ የሚገኘው ሌላው የሁለት ከተማ ክለቦች ልዩ ትንቅንቅ የአምስተርዳም ከተማን በሚወክለው አያክስ እና የሮተርዳም ከተማን በሚወክለው ፌዬኖርድ መካከከል የሚደረገው ሲሆን ይህ ደርቢ የአምስተርዳም ጥበበኞች የሚባሉትን አያክስና ወዛደሮች  የሚሰኙትን ፌዬኖርድ የሚስተናንቅ ነው፡፡ በሌላ በኩል ወደ ሁለት የተለያዩ አህጉራት በሚዋሰኑ ሁለት የቱርክ ክለቦች የሚካሄደው ደርቢ ፌነርባቼ እና ጋለተሰራይ የሚገናኙበት ነው፡፡ ይህ ፍጥጫ ካታላራሲ ወይም ኢንተርኮንትነንታል ደርቢ የሚል ስያሜ የሚሰጠው ሲሆን ፌነርባቼ ወደ ኤስያ እንዲሁም ጋላተሰራይ ወደ አውሮፓ የሚዋሰኑ ከተሞችን ከመወከላቸው ጋር በተያያዘ ነው፡፡ በዓለም እግር ኳስ እጅግ ትርፋማ በሆነው የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ በግንባርቀደምነት የሚጠቀሰው ደግሞ ከሳምንት በኋላ የእንግሊዝን ሁለት ውጤታማ ክለቦች ማንችስተር ዩናይትድ እና ሊቨርፑል የሚያገናኘው የሰሜን ምዕራብ ለንደን ደርቢ ነው፡፡ የሁለቱ ክለቦች የደርቢ ጨዋታ የሊጉ ትልቁ ጨዋታ ሆኖ ይጠቀሳል። በመካከላቸው የ35 ማይል ርቀት ያላቸውን የሊቨርፑል እና የማንችስተር ከተሞች ወኪሎችን የሚያተናንቀው ይህ ደርቢ በእንግሊዝ ባለከፍተኛ ውጤት ክለብ ማነው የሚለው ጥያቄ ምላሽ የሚያገኝበት እና በየጊዜው ፉክክሩ ተጠናክሮ የሚቀጥልበት ነው፡፡
*   *   *
ምርቃት የደርቢ ጨዋታዎችን በተመለከተ
የስፔኖቹ ክለቦች ሪያል ማሪድ እና ባርሴሎና የሚገናኙበት ኤልክላሲኮ በሁለቱ ክለቦች ስታድዬሞች ድምር የተመልካች መያዝ አቅም 180398 አንደኛ ደረጃ ሲሰጠው ኤሲ ሚላን ከኢንተር ሚላን የሚፋለሙበት ሚላን ደርቢ በ160036 እንዲሁም የሮም ከተማ ክለቦች ላዚዮ እና ሮማ የሚያደርጉት 145395 ተከታታይ ደረጃ አላቸው፡፡
የደርቢ ተፋላሚ ክለቦች በጋራ በሰበሰቡት የዋንጫ ድምር ግንባር ቀደም ሆኖ የሚጠቀሰው የስኮትላንዶቹ ሴልቲክ እና ሬንጀርስ የሚያገናኘው ኦልድ ፊርም ደርቢ ሲሆን 213 ዋንጫዎች ያስመዘገቡበት ነው። በሁለተኛ ደረጃ የሚጠቀሰው የካይሮ ደርቢ ተፋላሚዎች የሆኑት ኤል አሃሊ እና ዛማሌክ በሰበሰቡት 77 ዋንጫዎች ነው፡፡
በጎል ብዛት ከሚንበሸበሹ የደርቢ ጨዋታዎች በአንደኛ ደረጃ የሚጠቀሰው የአምስተርዳም ከተማን የሚወክለው አያክስ እና የሮተርዳም ከተማን የወከለው ፌዬኖርድ የሚገናኙበት ደርቢ በአማካይ 3.6 ጎሎች በአንድ ጨዋታ ስለሚመዘገቡበት ሲሆን የስፔኑ ኤልክላሲኮ በ3.4 እንዲሁም የጀርመኖቹ ዶርትመንድ እና ሻልካ የሚያደርጉት በ3.3 ጎሎች ነው፡፡   
በአፍሪካ የተለያዩ አገራት ከሚካሄዱ የደርቢ ፍልሚያዎች በሚያስገኙት ገቢ በወጣው ደረጃ በአንደኛ ደረጃ የተቀመጠው በአንድ ጨዋታ እስከ 400ሺ ዶላር የሚያስገባው የስዌቶ ደርቢ ሲሆን፤ የቱኒዝ ደርቢ እስከ 240ሺ ዶላር፤ የካዛብላንካ ደርቢ 210ሺ ዶላር እንዲሁም የካይሮ ደርቢ 186ሺ ዶላር በአንድ ጨዋታ በማስገባት ተከታታይ ደረጃ አላቸው፡፡

Read 2853 times