Monday, 09 January 2017 00:00

ከ480 ሚ. ብር በላይ የወጣበት ባለ 5 ኮከብ ሆቴል ይከፈታል

Written by 
Rate this item
(2 votes)

የፈረንሳዩ  ሎቨር ግሩፕ፤  ከ480 ሚ.ብር በላይ በሆነ ወጪ በአዲስ አበባ በመገንባት ላይ ያለውን  “ሮያል ቱሊፕ ፕላዛ” ባለ 5 ኮከብ ሆቴል ለማስተዳደር፣ ”በገዝ ቢዝነስ ግሩፕ” ከተሰኘ የኢትዮጵያ ኩባንያ ጋር ተስማማ፡፡ ግንባታው በመጠናቀቅ ላይ የሚገኘው ሆቴሉ፤ 88 የመኝታ ክፍሎች እንዳሉት ታውቋል። ሆቴሉ የሬስቶራንት፣ የስፓ፣ የስብሰባ አዳራሽ (ለቢዝነስና ተጓዦች) አገልግሎቶችን ጨምሮ ሌሎች ደረጃቸውን የጠበቁ፣ የላቁ መስተንግዶዎችንም ያቀርባል ተብሏል፡፡
ሎቨር ሆቴልስ ግሩፕ፤ ሁለተኛውን ባለ 5 ኮከብ “ሮያል ቱሊፕ ፕላዛ” ሆቴል በኢትዮጵያ መክፈቱ፤ ሎቨር በአፍሪካ ያቀደውን ሆቴሎቹን የማስፋፋት ስትራቴጂ ያጠናክርለታል ተብሏል፡፡ በኬንያ፣ ሩዋንዳ እንዲሁም በታንዛንያ የሆቴሎቹን ቁጥር እያሳደገና አገልግሎቱን እያስፋፋ ይገኛል፡፡ በ2017 እ.ኤ.አ ሎቨርስ ሆቴልስ፤ ወደ 15 ተጨማሪ ሆቴሎችን በክልሉ ለመክፈት አቅዷል፡፡  
ሉቨር ሆቴል ግሩፕ ከሚያስተዳድራቸው ሶስት የሆቴል ብራንዶች አንዱ የሆነውን “ጎልደን ቱሊፕ” ከጥቂት ዓመታት በፊት በቦሌ ከፍቶ እያስተዳደረ ሲሆን “ሮያል ቱሊፕ” የተሰኘው ብራንድ በአዲስ አበባ እንዲከፈት ከአንድ ዓመት በላይ የዘለቀ ድርድር መካሄዱ በስምምነት ፊርማው ላይ ተገልጿል፡፡ ሆቴሉ በአዲስ አበባ እንዲከፈት ድርድሩን ያካሄደው በቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ ቢዝነስ ላይ የተሰማራው “አዚ ቢዝነስና ሆስፒታሊቲ ማኔጅመንት ግሩፕ” መሆኑን የ”ኦዚ ቢዝነስ ሆስፒታሊቲ ግሩፕ ማኔጅምነት” ዋና ዳይሬክተር አቶ ቁምነገር ተከተል ገልጸዋል፡፡
የሆቴሉ በአዲስ አበባ መከፈት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣውን የአገሪቱን የጎብኚ ፍሰት ለማስተናገድና አለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ መስተንግዶ ለመስጠት ትልቅ ሚና ይኖረዋል ተብሏል፡፡ ሆቴሉ ተጠናቅቆ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር ለበርካታ ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ የስራ እድል እንደሚፈጥርም ተጠቁሟል፡፡

Read 2453 times