Monday, 09 January 2017 00:00

‹‹ዋተርጌት ኢንተርናሽናል ሆቴል›› ተመርቆ ተከፈተ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

 ከ25 ዓመት በፊት በእግራቸው በስደት ከአገር በወጡት ትውልደ ኢትዮጵያዊ ኢንቨስተር ጆን አብርሀም የተገነባውና ባለ አምስት ኮከብ ይሆናል የተባለው ‹‹ዋተር ጌት ኢንተርናሽናል ሆቴል የዛሬ ሳምንት ተመርቆ ተከፈተ፡፡ ለ160 ሰራተኞች የስራ እድል የፈጠረውና መስቀል ፍላወር አካባቢ የተከፈተው ይሄው ሆቴል ግንባታው አምስት አመት እንደፈጀና ወጪው ከፍተኛ እንደሆነ የተገለፀ ሲሆን፤ አሁንም መጠናቀቅ የሚገባቸው ነገሮች እንዳሉና ወጪው እንደቀጠለ የሆቴሉ ባለቤት ገልፀው፣ ግንባታው ሲጠናቀቅ ትክክለኛ ወጪውን እንደሚያሳውቁ ተናግረዋል፡፡ 45 ሜትር ከፍታ ያለውና በአጠቃላይ 109 ክፍሎችን የያዘው ዋተርጌት ኢንተርናሽናል ሆቴል ከሌሎች ሆቴሎች ለየት የሚያደርገው የሆቴሉ በሮች፣ መጋረጃዎች ሶፋ ጨርቆችና ሌሎች እቃዎች እሳት በቀላሉ የማያጠቃቸው መሆናቸው እንደሆነ ባለቤቱ ገልጸው የእሳት አደጋ በሆቴሉ ውስጥ ቢነሳ አንድ እንግዳ እሳትናጭስ ሳይነካው የሚያመልጥባቸው ደረጃዎችን የያዘ እንደሆነ በምርቃቱ እለት ተናግረዋል፡፡
ሆቴሉ የተለያየ መጠን ያላቸው የስብሰባ አዳራሾች፣ የመዝናኛ ቦታዎችና ባሮች፣ ሬስቶራንቶችና በቂ የመኪና ማቆሚያን የሚያካትት ሲሆን ሆቴሉን ለመገንባት ፈቃድ ሲያወጡ ባለ 5 ኮከብ ለመገንባት በመሆኑ ካለው ጥራትና የተሟላ አገልግሎትም በደረጃ መዳቢዎች ባለ 5 ኮከብ ሆኖ ይመደባል የሚል እምነት እንዳላቸው አቶ ጆን አብርሃም ተናግረዋል፡፡ በአውሮፓ ላለፉት 25 ዓመታት የኖሩት ኢንቨስተሩ በሚኖሩበት አውሮፓ ላለፉት 15 ዓመታት በቢዝነስ ስራ ላይ ተሰማርተው እንደነበር የሆቴሉም ግንባታ ከዚያ በሚመጣ ገንዘብ መስራቱን ጨምረው ገልፀዋል፡፡ ሆቴሉ በሙሉ አቅሙ ስራ ሲጀምር አሁን ከሚሰሩት 160 ሰራተኞች በላይ ለሌሎችም የስራ ዕድል እንደሚፈጥር አቶ ጆን አብርሀም ጨምረው ገልፀዋል፡፡

Read 803 times