Friday, 06 January 2017 12:33

“ስፌትዋ እንዳይከፈት... በኦፕራሲዮን አዋልዷት”

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

  •    ስራ መስራት የሚገባው በተገረዙ ሴቶች ችግር ላይ ብቻ አይደለም። ያልተገረዙ ሴቶችንም ጉዳይ ማየት ያስፈልጋል።
      •  በደቡብ በአንዳንድ አካባቢዎች ግርዛት እንደገና እንደአዲስ ተጠናክሮ ቀጥሎአል። ሳይገረዙ የተዳሩ ሴቶች እንደገና በራሳቸው ፈቃድ እየተገረዙ ነው።
      ለርእስነት የመረጥነው አባባል የአንዳንድ አባወራዎች ውሳኔ ነው። ምናልባትም ከርእሱ የምንገነዘበው በአንዳንድ አካባቢዎች አንዲት ሴት ምንያህል በራስዋ ገላ ላይ ማዘዝ ሊሳናት እንደሚችል እና በባህል ወይንም በልማድ ከዚያም ባለፈ በግለሰብ ፍላጎት የምትኖርበት አጋጣሚ እንደሚኖር ነው። ርእሱ የሚያስረዳን ገና በህጻንነትዋ በቤተሰብ ውሳኔ እንድትገረዝ ከመደረግዋም ባሻገር ትዳር ከመሰረተችም በሁዋላ ለመውለድ እንኩዋን ካለባለቤትዋ ትእዛዝ ሕክምናውም ሊረዳት እንደሚችገር የሚያሳይ ነው። ብልትዋ የተሰፋ ሴት ምጥ በተያዘችበት ወቅት ወንድየው ለሕክምና ባለሙያዎቹ ከሚሰጠው ትእዛዝ አንዱ ነው - “የብልትዋን ስፌት እንዳትከፍቱ። በሆድዋ በኩል ኦፕራሲዮን አድርጋችሁ አዋልዷት” የሚለው። ይህንን የነገሩን እ.ኤ.አ በ2025 የሴት ልጅ ግርዛትን ማስወገድ በሚል ርእሰ ጉዳይ ታህሳስ 6 በአዲስ አበባ ተደርጎ በነበረው የምክክር አውደጥናት ላይ ተሳታፊ የነበሩና ለዚህ አምድ እንግዶች ካደረግናቸው መካከል በአለም የጤና ድርጅት የሚሰሩት ዶ/ር ፍቅር መለሰ ናቸው።
እንደ ዶ/ር ፍቅር ማብራሪያ፣ “ግርዛት የሚለው ቃል ለሁለቱም ማለትም ለወንድም ለሴትም የምንጠቀምበት ቃል ነው። ነገር ግን ግርዛት ማለት የጥሩ ተግባር መገለጫ ነው። ስለሆነም በተለይም ወንዱን በተመለከተ ከመገረዙ በፊት ያለውን ተፈጥሮአዊ ሁኔታ በማገናዘብ ግርዛት ከጤናው አኩዋያ ጠቃሚ ስለሆነ የሚፈጸም ነው። የሴቷን በሚመለከት ግን አስቀድሞወኑ ግርዛት የሚለው ቃል ድርጊቱን አይገልጸውም። ምክንያቱም ምንም ጠቃሚ የሆነ የጤና ነገር ስለሌለውና እንዲያውም ጎጂ ድርጊት ስለሆነ ነው። ድርጊቱም እንደየአካባቢው በደረጃ የተለያየ አፈጻጻም ያለው ነው። የሴት ልጅ ግርዛት በአካባቢው ያሉ ሰዎች ልምድ አድርገው የያዙት እና ካላቸው ልምድ ጋራ አብሮ የሚጉዋዝ ነው። የሴትዋን የግንኙነት አካል አገራረዝ ስንመ ለከት ከላይ ጫፉን ብቻ የሚቆርጡ አሉ። ይህ በእንግሊዝኛው (Female genital mutilation ) የሚባለው ሲሆን ሚቲሌሽን ማለት ቅርፍ አድርጎ ማንሳት የሚል ትርጉዋሜ አለው። ስለዚህም እንደ የህብረተሰቡ ልምድ ከላይ ያለውን ጫፍ አንስቶ እስከመቀርፈፍ ድረስ የሚደርስ ድርጊት ነው። ከዚህ በተለየ ደግሞ የሴትዋን ብልት የላይኛውን ከንፈር በመቀርፈፍ ደም ሲወጣው በማጋጠም ልጅትዋም ሁለቱም ጭኑዋ እንድትታሰር ይደረጋል። በእርግጥ ሕጻን ስለምትሆን ያን ጊዜ የወር አበባዋን አታይም። ብልትዋ እንዲገጥም ሲደረገ በጣም ትንሽ ቀዳዳ ብቻ እንዲኖር ተደርጎ ነው። የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያስረዱት ይህ ድርጊት የሚፈጸመው በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ የአለማችን ክፍሎችም ጭምር ነው። አብዛኛውን ገፈት ቀማሾቹ ግን በምስራቃዊው ኤዥያና በአፍሪካ ውስጥ ያሉ ሴት ልጆ ናቸው። በአፍሪካ ከሚፈጸመው ውስጥ ግማሹን ያህል ድርሻ የሚይዙት ደግሞ ግብጽና ኢትዮጵያ ናቸው። ስለዚህም ጫናው ከፍተኛ ነው።
ዶ/ር ፍቅር አክለውም በአሁኑ ወቅት አለምአቀፉን ትኩረት የሳበውን በተለይም አጽንኦት የተሰጠው የሴት ልጅ ግርዛት ከመንደር ትግበራ ወጥቶ ወደሕክምናው እንዲሄድ የማድረግ አዝማሚያው ነው። በመንደር ውስጥ የሚደረገው ግርዛት ከተለያዩ የጤና ጉዳዮች ጋር ተያይዞ በተለይም እንደኤችአይቪ ኤይድስ ያሉትን ተላላፊ በሽታዎች ለማስወገድ ሲባል የህክምና ባለ ሙያዎች ይስሩት የሚል እምነት ያላቸው አሉ። ምናልባትም ድርጊቱን የሚፈጽሙ የህክምና ባለሙያዎች ካሉ ወይ ከጥቅም አለበለዚያም በእውነተኛው የምትገረዘውን ልጅ ከማዳን አንጻር ሊፈጽሙት ይችሉ ይሆናል። ነገር ግን በፍጹም ስህተት በመሆኑ ሊወገድ ይገባዋል የሚል አለምአቀፋዊ ስምምነት አለ። አንዳንድ ጊዜ ህብረተሰቡም ወንድና ሴት ለሚኖራቸው ግንኙነት በጣም ትልቅና አድናቆት የተሞላው ድርጊት አድርጎ የመመልከት ነገር አለ። ይህም ማለት ወንዱ፣ ‘እኔ የማገባት ሴት ክብረ ንጽሕናዋ ያለ፣ ... እስዋ ብትፈልግ እንኩዋን ማንም ሊደፍራት እንዳይሞክር ተደርጋ የተዘጋጀች የተሰፋች መሆን አለባት’ የሚል እምነት እንዲኖረው አድርጎ የማሳደግ... ይህንን እምነት ለየት አድርጎ ከበሬታ ሰጥቶ የመያዝ ነገር ይስተዋላል። ይህ መጥፎ ነው ለማለት ሳይሆን ነገር ግን የሴትና ወንድ መቀራረብ በመተማ መን መሆን ያለበትን በኃይል እንዲሆን ማድረግ የሴትዋን መብት እስከመዳፈር ያደርሳል ለማለት ነው። ሴትዋ ባልዋን ወደሌላ ሴት እንዳይሄድ ብትፈልግ እንኩዋን ልትይዝበት የምትችልበት ምንም መንገድ የላትም። ባልየው ግን አልፎ ተርፎ ልትወልድ ወደ ሆስፒታል በምትገባበት ወቅት እንኩዋን የተሰፋውን ብልት እንዳትከፍቱ፣ ‘ኦፕራሲዮን አድርጋችሁ ልጁን አዋልዱ’ የሚል ትእዛዛ ለሐኪሞቹ እስከመስጠት የሚደርስበት ሁኔታ ይስተዋላል።
“ሌላው ነገር...” አሉ ዶ/ር ፍቅር፣ ”የወሲብ ግንኙነት በሚደረግበት ጊዜ ወንዱ እንዲረካ ሲፈቀ ድለት ለሴትዋ ግን ይህ አልተፈቀደም። ምክንያቱም በተለይም እንደ አፋርና ሶማሌ እና ሌሎችም መሰል ግርዛት በሚፈጸምባቸው አካባቢዎች የሴቷን ስሜት ሰጪ አካል በመቁረጥ እስከማ ስወገድ የሚደርስ ትልተላ ስለሚፈጽሙባቸው ሴትዋ እንደባልዋ የመርካት እድል እንዳይኖራት ተደርጋለች። ሴትዋ በግርዛት ምክንያት ተፈጥሮአዊ ገላዋን እንድታጣ እንዲሁም በተለያዩ ወቅቶች ችግር እንዲደርስባት ከመደረግ ባሻገርም የስነልቡና ጫና እንዲደርስባት ስለምትደረግ ይህ በጠቅላላው መወገድ ያለበት ጎጂ ድርጊት ነው። ” ብለዋል
ሰአርቱ ሸምሰዲን ከእስልምና ጉዳዮች ጽ/ቤት በምክክር አውደጥናቱ ላይ የተገኘች ባለሙያ ነች። እስዋ እንደምትለው “በእኛ አገር ደረጃ በጣም የሚያሳዝን ክስተት አለ። እ.ኤ.አ በ2025 ግርዛትን እናስቀራለን ብለን ተነስተናል። ግን በእርግጥ የቀረው ጊዜ በቂ ነውን? የሚለው ነገር አከራካሪ ሊሆን ይችላል። በእኔም አስተያየት ጥያቄ ውስጥ ያለ ጉዳይ ነው። ምክንያቱም በአሁኑ ወቅት ያለውን ሁኔታ ስንመለከት ግብጽና ሞሪሽየስ በጣም በከፍተኛ ደረጃ ድርጊቱን የሚፈጽሙ ሲሆን ቀጣይዋ ደግሞ ኢትዮጵያ ናት። አሁን የሚታዩ ቁጥሮች በእርግጥ በ2025 ማለትም ከስምንት አመት በሁዋላ ሊወገዱ የሚችሉ ናቸውን? በእርግጥ ተስፋ መቁረጥ አይገባም። ነገር ግን በመላ ሀገሪትዋ እጅግ በጣም ከፍተኛ የሆነ ስራ መሰራት ይገባዋል። ይህ ንን ድርጊት በየመድረኩ በመሰብሰብ ብቻ ሳይሆን ወደሕብረተሰቡ ወርዶ እያንዳንዱን ሰው አግ ኝቶ በማነጋገር እና በመመካከር፣ በማሳመን ደረጃ ካልተሰራ ችግሩን መቅረፍ ይቻላል የሚል እምነት የለኝም። ግርዛት ጎጂ ነው የሚለውን ነገር ሁሉም ድርጊቱን የሚፈጽሙም የሚያስፈ ጽሙም ያውቁታል። ነገር ግን ጎጂ ይሁን እንጂ ከባህልና ከልማድ ውጪ መሆን አይቻልም የሚለው እምነታቸው ገዢያቸው ሆኖ የተቸገሩበት ሁኔታ ነው የሚስተዋለው። በሌላም በኩል ህብረተሰቡ ባህልና ልማድን ለመለየት ሲቸገር ይስተዋላል። ግርዛት ጎጂ የሆነ ልማድ እንጂ ባህል አይደለም። ህብረተሰቡ ግን እንደባህል በመውሰድ ባህልን መቀየር ወይንም አለመተግበር አይቻ ልም የሚል የተሳሳተ አመለካከት ስላለ ይህን ለማስተካከል በጣም ጠንካራ ስራ መስራት ይጠይቃል። የሴት ልጅ ግርዛት ጎጂ በመሆኑ ሊቀር እንደሚገባው ሁሉም እንዲያምን ማድረግ ይጠበቅብናል። ”
ከደቡብ ብሔር ብሄረሰቦች ሕዝቦች ክልላዊ መንግስት ጤና ቢሮ ወ/ሮ መስታወት ወልደ አማኑኤል እንደገለጹት በደቡብ በሁሉም አካባቢ ማለት በሚያስችል ሁኔታ አይነቱ ቢለያየም ግርዛት ግን ይፈጸማል። ከዚህ ቀደም ብዙ የማይታይባቸው እንደጌዴኦ ዞን ያሉ ቦታዎችም አሁን አሁን በስፋት ድርጊቱ እየታየ በመሆኑ በሁሉም አካባቢ የሴት ልጅ ግርዛት ይፈጸማል። በ2016 የወጣውሃመ ላይ እንደታየው በሁለት ቦታዎችሐዲያና ወላይታ ከሶ ማሌና ከአፋር ጋር የሚቀራረብ ቁጥር የታየበት ነው። ሐዲያ ላይ ከአሁን ቀደም በጣም ሰፊ ስራ ተሰርቶ የሴት ልጅ ግርዛት ቀርቶ የነበረ ቢሆንም በሚያስገርም ሁኔታ እንደገና ወደሁዋላ ተመልሶ ሁሉንም በሚያዳርስ ሁኔታ እየተተገበረ ነው። አለመገረዝ የጤና ችግር ያመጣል የሚለው የተሳሳተ አባባል በሁሉም ወረዳዎች ስለተዳረሰ ዛሬ እንኩዋንስ ሕጻናቱ ...ሳይገረዙ ያገቡ እና የወለዱ ሴቶች ሁሉ ሳይቀሩ ስላልተገረዛችሁ ችግር ያመጣባችሁዋል ተብለናል በማለት እንደገና እየተገረዙ ነው። ስለዚህም በደቡብ የሴት ልጅ ግርዛት የከፋ ደረጃ ላይ ይገኛል ብሎ መግለጽ ይቻላል። በእርግጥ ድርጊቱን ለማስቆም የተለያዩ ስራዎች ከጤና ጥበቃ ሚኒስር እና ሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር ተሰርተዋል ቢባልም ችግሩን ግን ቀርፈን እዚህ ደረጃ ላይ አድርሰነዋል ማለት አያስችልም። የህብረተሰቡን ግንዛቤ የማዳበር ስራ መስራት አስፈላጊ ነው። አጠቃላይ ህብረተሰቡን በንቅናቄ መልክ ተደራሽ በማድረግ ማስተማር ይበልጥ ይጠቅማል። ባለድርሻ አካላትም ሁሉም የራሱ ጉዳይ አድርጎ ሊወስደው የሚገባ ነው። ባጠቃላይም ደቡብ ላይ ብዙ ስራዎች መሰራት አለባቸው ብዬ አምናለሁ። ” ብለዋል።
ሰአርቱ ሸምሰዲን ከእስልምና ጉዳዮች ጽ/ቤት በስተመጨረሻ የሚከተለውን ምስክርነት ነበር ለአምዱ አዘጋጅ የሰጠችው።
“በሱማሌ በተለያዩ ስፍራዎች በመሄድ ስልጠናዎች እየሰጠሁ ባለበት ጊዜ አንድ አጋጣሚ አግኝቼ ነበር። አንዲት ልጅ እየተገረዘች መሆኑን መረጃ አግኝቼ ወደስፍራው አቀናሁ። እኔ እዚያ ስደርስ ልጅትዋ ተገርዛለች። ምንም ማድረግ ስለማልችል በጣም ተናደድኩ። ነገር ግን ሌሎች ሶስት ልጆች ደግሞ ገና ሊገረዙ ተራቸውን እየጠበቁ ነበር። እኔም በፍጹም አይሆንም ብዬ ተሟገትኩ። በጊዜው ግን የገረመኝ ነገር ልጆቹ መገረዝ እንደሚፈልጉ ሲገልጹልኝ ነው። ለምንድነው ብዬ ስጠይቃቸው፣ “እኛ በእርግጥ ቤተሰቦቻችን መገረዝ ትክክል አይደለም ብለው አላስገረዙንም። ነገር ግን ከጉዋደኞቻችን ጋር መግባባት አልቻልንም። በምንጫወትበት ይሁን አብረን በምንሄድበት ወቅት አንድ ነገር እንደጎደለን... ባለመገረዛችን ምሉእ እንዳልሆንን ይነግሩናል... ያሽሟጥጡናል... ያገልሉናል... ይጠሉናል” አሉኝ። እንዲሁም ለጋብቻ ቅድሚያ የሚሰ ጣቸው የተገረዙት ስለሆኑ መገረዝ አለብን ብለው ተሟገቱኝ። በማስረዳቸውም ወቅት ሊሰሙኝ አልቻሉም። ተገርዤ ልሙት የሚል ነበር መልሳቸው። ከወሊድ ጋር በተያያዘም ቢሆን ‘ልጄ ይተርፋል...እኔ ግን ችግር የለም ብሞትም’... የሚል አሳዛኝ መልስ ነበር የሰጡኝ። ወላጆቻቸውን አስተምረን በከፍተኛ ድካም አሳምነን እንዳይገረዙ ከተደረጉ በሁዋላ በራሳቸው ጊዜ እንገረዛለን ብለው ድርጊቱ እንዲፈጸም የሚያደርጉ ከሆነ ዞሮ ዞሮ ማዳን አልተቻለም ማለት ነው። ስለዚህ ባልተገረዙት ሴት ልጆች ስነልቡና ላይ ከፍተኛ ስራ መስራት እንደሚጠበቅብን አምናለሁ። ” ብላለች።

Read 3088 times