Sunday, 08 January 2017 00:00

የአገሪ መሪ ከመሆናቸው በፊት ---?

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 የአገር መሪዎች ወደ ሥልጣን ከመምጣታቸው በፊት ምን ይሰሩ እንደነበር ወይም በምን ሙያ ላይ ተሰማርተው እንደቆዩ አስባችሁት ታውቃላችሁ? እኔ ትዝ ብሎኝም አያውቅም፡፡ ግን እኒህ ሰዎች ሲወለዱ ፕሬዚዳንት ወይም ጠ/ሚኒስትር ሆነው አለመወለዳቸውን ያለ ጥርጥር እናውቃለን፡፡ (የንጉሳውያን ቤተሰብ ካልሆኑ በቀር) ይሄ ማለት ደግሞ ወደ ሥልጣን እስኪመጡ ድረስ ባለው ዕድሜያቸው ሲተዳደሩ የቆዩበት ሙያ እንደሚኖራቸው ይጠቁማል፡፡ አንዳንዴ ታዲያ ተሰማርተው የነበሩበት ሙያ ወይም የሥራ ዘርፍ ከፖለቲካና ከአገር መሪነት ጋር ባለው ከፍተኛ ርቀት የተነሳ መገረምና መደነቅ ሊፈጥርብን ይችላል፡፡ የሚከተሉት መሪዎች ማለፊያ ምሳሌዎች ይመስሉኛል፡፡
                                  
     ሙዚቃ ቀማሪው ፕሬዚዳንት
 -   የክሮኤሽያው ፕሬዚዳንት ኢቮ ጆሲፖቪክ፤ወደ ፖለቲካ  ከመግባታቸው በፊት የክላሲካል ሙዚቃ ቀማሪ ነበሩ፡፡ በደርዘን የሚቆጠሩ ክላሲካል ሙዚቃዎችን የደረሱ ሲሆን የክሮኤሽያን ዋነኛ የሙዚቃ ፌስቲቫል መርተዋል፡፡  
•   ጆሲፖቪክ በፕሬዚዳንትነት የተመረጡት እ.ኤ.አ በ2010 ሲሆን በወቅቱ የሙዚቃ ሙያቸውን እንደማያቆሙ ቃል ገብተው ነበር። በኋላ ላይ ግን የፕሬዚዳንትነት ስራቸው ፋታ የማይሰጥ በመሆኑ ቃላቸውን መፈፀም እንዳልቻሉ አምነዋል፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን አንድ ፒያኖ  ወደ ፕሬዚዳንታዊ ቢሮአቸው ለማስገባት አልሰነፉም፡፡ ኢቮ ጆሲፖቪክ፤ በቅድመ ምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ኪ-ቦርድ መጫወታቸው ተዘግቧል፡፡
    ሰዓሊው ጠ/ሚኒስትር
 -   የአልባኒያው ጠ/ሚኒስትር ኢዲ ራማ ወደ አገር መሪነት ሥልጣን ከመምጣታቸው በፊት ሰዓሊ ነበሩ፡፡ በፓሪስ የሥነ  ጥበብ ት/ቤት ስዕል ያጠኑት ራማ፤ እ.ኤ.አ በ1998 ወደ አልባኒያ ሲመለሱ የባህል ሚኒስትር ሆነው ተመደቡ። ከዚያም የአልባኒያ ከተማ- ቲራና፣ ከንቲባ ሆነው ተሾሙ፡፡ ይሄም ለሥነ ጥበባዊ ውበት ያላቸውን ስሜት ለመወጣት ዕድል የሰጣቸው ሲሆን በሲሚንቶ የተገነቡ የኮሙኒስት ዘመን ግራጫ ህንፃዎች፤ በሮዝ፣ በብጫ፣ በአረንጓዴና ሀምራዊ ቀለማት እንዲዋቡ አስደርገዋል፡፡
•   የቀድሞ የቅርጫት ኳስ ተጫዋችም የነበሩት ራማ፤ እ.ኤ.አ በ2004 ለቢቢሲ በሰጡት  ቃለ መጠይቅ፤ “በእርግጠኝነት ፖለቲከኛ ነኝ ለማለት አልችልም፡፡ እኔ አሁንም ሰዓሊ ነኝ ነው የምለው፤ ፖለቲካን ለለውጥ በመሳሪያነት ለመጠቀም እየሞከርኩ ነው” ብለው ነበር፡፡
•   በ2012 የTED ቶክ ላይ ለመሪዎች ባስተላለፉት ጥሪ፡- “ከተማችሁን በቀለም መልሳችሁ ፍጠሩ” ብለዋል፡፡  
   ገጣሚው ፕሬዚዳንት
 -   የአየርላንድ ፕሬዚዳንት ማይክል ዲ.ሂጌንስ፣ የሥልጣን መንበር ከመቆናጠጣቸው በፊት ገጣሚ ነበሩ፡፡ አራት የግጥም ጥራዞችን (volumes) ለህትመት ያበቁ ሲሆን የአየርላንድ የመጀመሪያው የሥነ ጥበብ ሚኒስትርም ነበሩ። ማይክል ዲ. በሚል ቁልምጫ የሚታወቁት ታጋይ-ገጣሚ ፕሬዚዳንቱ፤ አየርላንድ “የፈጠራ ሪፑብሊክ” እንድትሆን ጠይቀዋል፡፡  
•    የራሳቸው የግጥም ስራዎች ግን ከሃያስያን የሰላ ትችት አላመለጡም፡፡ አንዱ ሃያሲ እንደውም፤ “ፕሬዚዳንቱ በሥነ ፅሁፍ ላይ ለፈፀሙት ወንጀል ክስ ሊመሰረትባቸው ይችላል” ማለቱ ተዘግቧል፡፡

Read 1117 times