Saturday, 14 January 2017 15:26

የመንግስት ስልጣን በኢህአዴግና በተቃዋሚዎች ቢያዝ ግንኙነታቸውን የሚደነግግ ህግ ተዘጋጀ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

በሀገራዊ ምርጫ ውጤት የክልልና የፌደራል መንግስታት ስልጣን በተለያዩ የፖለቲካ ሃይሎች ቢያዝ፣ በሁለቱ መንግስታት መካከል የሚኖረውን ግንኙነት የሚደነግግ የህግና ፖሊሲ ማዕቀፍ መዘጋጀቱ ተገለፀ፡፡
የህግ ማዕቀፍ ዝግጅቱ 4 አመታትን መፍጀቱ የተገለፀ ሲሆን ሀሳቡ በፌደራልና አርብቶ አደር ጉዳዮች ሚ/ር እና በፌዴሬሽን ም/ቤት ፈልቆ የተዘጋጀ ነው ተብሏል የፖሊሲ የህግ ማዕቀፉ ከዚህ ቀደም በፌደራል መንግስቱና በክልል መንግስታት መካከል የነበረውን ተለምዷዊ የመንግስታት ግንኙነት በህግ የሚያጠናክር ይሆናል ተብሏል፡፡
እስካሁን የነበረው የፌደራልና የክልል መንግስታት ግንኑነት፤ መደበኛ ያልነበረ ሲሆን አሁን የሚዘጋጀው የፖሊሲ የህግ ማዕቀፍ፣ ህገ መንግስቱን መሰረት አድርጎ በህግና በፖሊሲ የተደገፈ ዘላቂነት ያለው መደበኛ ግንኙነት እንዲኖር የሚያደርግ መሆኑን በፌዴሬሽን ም/ቤት የዲሞክራሲያዊ አንድነት የመንግስታት እርስ በእርስ ግንኙነት ማጠናከሪያ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አስቻለው ተክሌ ለአዲስ አድማስ አብራርተዋል፡፡
በህገ መንግስቱ አንቀፅ 51፤ የፌደራል መንግስቱ የሃገሪቱን የኢኮኖሚ ማህበራዊና ልማት ስትራቴጂ የማውጣትና የማስፈፀም ስልጣን እንዳለው የሚደነግግ ሲሆን አንቀፅ 52 ደግሞ የክልል መንግስት የራሳቸውን የኢኮኖሚ፣ማህበራዊና የልማት እቅድ የማውጣት ስልጣን እንዳላቸው ይደነግጋል፡፡
እነዚህን ተግባራት እስካሁን የፌደራልና የክልል መንግስታት ተለምዶአዊ በሆነ መንገድ በምክክር ሲሰሩ ቢቆዩም ህገ መንግስታዊ ድንጋጌያቸውን በዝርዝር የሚያብራራ የህግ ማዕቀፍ በማስፈለጉ ላለፉት አራት አመታት ይኸው ጥናትና ዝግጅት ሲካሄድ መቆየቱ ተገልጿል፡፡
በህንድ ለረዥም አመታት ኮንሰርቫቲቭ ፓርቲ የፌደራሉንም የክልል መንግስቱንም ስልጣን በብቸኝነት ተቆጣጥሮ መቀጠሉንና ኋላ ላይ በክልል ያለው ስልጣኑ በተቃዋሚዎች እየተሸረሸረ መጥቶ የፌደራል መንግስትነት ቦታውንም ማጣቱን በተሞክሮነት የጠቀሱት አቶ አስቻለው፡፡ በኛም ሀገር የምርጫ 97 አጋጣሚ ማሳያ በመሆኑ፣ ለወደፊት የተለያዩ ፓርቲዎች ወደ ስልጣን ቢመጡ ሀገሪቱ ጤናማ በሆነ መልኩ እንድትቀጥል አርቆ በማሰብ የተዘጋጀ የፖሊሲ የህግ ማዕቀፍ መሆኑን ለአዲስ አድማስ አብራርተዋል፡፡ እንደየዘመኑ አዳዲስ ጉዳዮች ሲፈጠሩ የሚስተናገዱበትን መንገድም የፖሊሲ ህግ ማዕቀፉ አስቀምጧል ብለዋል አቶ አስቻለው፡፡

Read 2659 times