Saturday, 14 January 2017 15:28

ግብፃውያኑ የስለላ ተጠርጣሪዎች ከእስር ተለቀው ወደ አገራቸው ተላኩ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(6 votes)

     በስለላ ወንጀል ተጠርጥረው ለወራት በእስር የቆዩ 3 ግብፃውያን፤ ከእስር ተለቀው ረቡዕ ምሽት ወደ ሀገራቸው ተላኩ፡፡የግብፁ ‹‹ናይል ቲቪ›› የሀገሪቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጠቅሶ እንደዘገበው፤ የኢትዮጵያ መንግስት በዲፕሎማሲያዊ ጥረት ግብፃውያኑን ከእስር ለቅቆ ወደ ሀገራቸው መላኩን አስታውቋል፡፡
የህዳሴውን ግድብ በሚመለከት የስለላ ስራ በመስራት ተጠርጥረው ታስረው የነበሩት ግብፃውያን በኢትዮጵያ ለ7 ዓመት የኖረውና በአንድ ሆቴል ግንባታ በተቆጣጣሪ ሲሰራ የቆየው ሃኒ ኡል አካካድ፣ የራዲሰን ብሉ ሆቴል ም/ስራ አስኪያጅ የነበረው ጠሃ መንሱርና በንግድ ስራ ላይ የተሰማራው ሀሰን ራማዳን መሆናቸው ታውቋል፡፡  ተጠርጣሪዎቹ በመንግስት የፀጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ስር የዋሉት ባለፈው ጥቅምት 21  ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃ/ማርያም ደሳለኝና የግብፁ አቻቸው አብዱልፈታ አልሲሲ በቅርቡ በተገናኙበት ወቅት ስለ እስረኞቹ ጉዳይ መነጋገራቸውን ‹‹ናይል ቲቪ›› ዘግቧል፡፡
የግብፃውያኑ ከእስር መለቀቅና ወደ ሀገራቸው መላክ የሁለቱን ሀገራት ወዳጅነት የበለጠ እንደሚያጠናክረው የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማስታወቁም ተዘግቧል።
በጉዳዩ ላይ ከኢትዮጵያ መንግስት ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ተወልደ ሙሉጌታ ማብራሪያ ለማግኘት ያደረግነው ተደጋጋሚ የስልክ ጥሪ ምላሽ ባለማግኘቱ ሊሳካልን አልቻለም፡፡

Read 2763 times