Saturday, 14 January 2017 15:33

የሃይማኖት መሪዎች የእርቀ ሰላም ጥሪ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ፤”የሰላም እና የእርቅ ሀገራዊ የምክክር መድረክ”፤ በአፍሪካ የኢኮኖሚ ኮሚሽን አዳራሽ፣ ባለፈው ማክሰኞና ረቡዕ
ተካሂዷል፡፡ በዚህ መድረክ ላይ የተለያዩ የሃይማኖት መሪዎች፣ባለፈው ዓመት የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ፣የተከሰተውን የዜጎች ህልፈትና
የንብረት ውድመት እንዲሁም በህዝቦች መካከል የተፈጠረውን መቃቃር በማስታወስ፣አገራዊ አንድነቱንም ሆነ ህዝባዊ ትስስሩን ወደቀድሞው ቦታው
ለመመለስ እርቀ ሰላም ማውረድ ወሳኝ መሆኑን በስፋት አንጸባርቀዋል፡፡
የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፣በምክክር መድረኩ ላይ ተገኝቶ የሃይማኖት መሪዎቹን የእርቀ ሰላም ሃሳብና ጥሪ እንደሚከተለው አጠናቅሮታል፡፡
ለፖለቲካዊ ችግሮች መፍትሄው ፖለቲካዊ ውይይት ነው፡፡

“ጠባሳው እንዲድን የእርቀ ሰላም ስራዎች
መስራት ይገባል”

ፓትርያርክ አባ ማትያስ (የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ፓትርያርክ)

ጌታችን በትምህርቱ፤”አስታራቂ ሰዎችን ብፁአን ናቸው” ብሎ ከማወደሱም በላይ “የእግዚአብሔር ልጆች ይግባቡ” በማለት የመጨረሻውን አምላካዊ ክብር እንደሚሰጣቸው አረጋግጦአል፡፡ ከዚህ አኳያ የዕርቀ ሰላም ተግባር ምን ያህል ታላቅ እንደሆነ መገንዘቡ የሚከብድ አይሆንም፡፡ በዓለም ዙሪያ ሁሉ እንደሚታየው፣ ጥንትም ሆነ ዛሬ፣ በአማንያንም ሆነ በኢ-አማንያን፣ የችግሮች ሁሉ መቋጫና አስተማማኝ መፍትሄ፣ እርቀ ሰላም ብቻ እንደሆነ ጥያቄ የለውም፡፡ ከአምላካዊ መርህ በመነሳት ስለ እርቀ ሰላም አስፈላጊነት ስናሰላስል፣ ነገሩ ግልፅ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ እግዚአብሔር ሁሉን ማድረግ የሚችልና ምንም የሚሳነው የሌለ ኃያል አምላክ ሲሆን ደካማ ከሆነው ፍጡር ጋር መታረቅ ለምን መረጠ? ብንል፣ እግዚአብሔር ባህርዩ ዕርቀ ሰላምን የሚወድ፣ ጥላቻን የሚጠላ በመሆኑ ብቻ እንደሆነ ቅዱስ መፅሐፍ ይነግረናል፡፡
ምንጊዜም ከሃይማኖት ቅኝት ርቆ የማያውቀው የሀገራችን ብሂለ አበው፤ “እርቅ ደም ያደርቅ” እያለ ከእግዚአብሔር ቃል ጋር በመተባበር፣ የዕርቀ ሰላም ሰዎች እንድንሆን ያስተምረናል፡፡ ባለፈው የክረምት ወራት በአንዳንድ የሃገራችን አካባቢዎች ያለአስፈላጊ አለመግባባቶች ተከስተው፣ በንፁሃን ወገኖች ላይ የህይወትና የንብረት ጉዳት ከማድረሳቸውም ሌላ በህዝቦች መካከል የመቃቃር ጠባሳ ፈጥረው አልፈዋል፡፡ ይሁንና ይህ መጥፎ ጠባሳ ብዙ እድሜ ሊሰጠው ስለማይገባ፣ ጠባሳው ሙሉ በሙሉ ድኖ፣ በፊት እንደነበረው ጤናማ እንዲሆን፣ተከታታይነት ያላቸው የዕርቀ ሰላም ስራዎች መስራት ይገባናል፡፡
መንግስት ባስቀመጠው ህጋዊ አሰራር ነገሩ ለጊዜው ሰከን ያለ ቢመስልም አበው፤ ‹‹መተው ነገሬን ከተተው›› እንደሚሉት፣ ሁሉም ቅሬታውን በመተው፣ ወደ ፍፁም መግባባት ይደርስ ዘንድ ባለድርሻ ወገኖች ነገሩን በሰከነ መንፈስ ተወያይተውበት፤ እንዲህ ያለ የሃገርን አንድነት የሚፈታተን ጎጂ ድርጊት እንዳይደገም፣የእርማት ስራ ሰርተውበት፣ በሃገራዊና ወንድማዊ መንፈስ ተማምነው፣ በዕርቀ ሰላም ማህተም የሚያትሙበት፣ ለወደፊትም መሰል ችግር ተነስቶ ዜጎች እንዳይጎዱ የሚያስችል አመለካከትና አስተሳሰብ የሚያሳድጉበት የዕርቀ ሰላም ስራ መሰራት አለበት፡፡ ይኸም ተልዕኮ በዋናነት የሃይማኖት አባቶች ኃላፊነትና ግዴታ መሆኑ ስለሚታወቅ፣ እኛ የሃይማኖት መሪዎች፣ ህዝቡን አስተምረን አሳምነንና አስታርቀን፣ ወደ ቀድሞው ሁናቴ ለመመለስ የአንበሳውን ድርሻ ወስደን፣ በሠፊው ለመስራት መትጋት ይኖርብናል፡፡
እኛ ኢትዮጵያውያን፤ ትናንትም ዛሬም ነገም አንድ ነን፡፡ መቼም ቢሆን አንለያይም፡፡ ይህንንም የምናረጋግጠው፣ በህዝቦቻችን መካከል ብቅ ማለት የጀመሩትን ብዥታዎች፣ ስሜታዊ እንቅስቃሴዎች በዕርቀ ሰላም እንዲስተካከሉና፣ በይቅርታ መንፈስ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ፋይላቸው እንዲዘጋ በማድረግ ነው፡፡

===========================================

“የሰላም ዋጋ የሚታወቀው ሰላም የጠፋ ጊዜ ነው”

ሼህ ሙሃመድ አሚን ጀማል ኡመር (የኢ/እስ/ጉ/ጠ/ም/ቤት ፕሬዚዳንት)

    እርቅና ሰላም፤ ጥልቅ ትርጉም ያላቸው፣ በሁሉም ሃይማኖቶች የሚፈለጉና የሚወደዱ ሀሳቦች ናቸው፡፡ የምክክር መድረኩም በእርቅና በሰላም ላይ በማተኮር መዘጋጀቱ፣ በሀገራችን ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ፣ የሀይማኖት ተቋማት የድርሻችንን ለማበርከት እድል ይሰጠናል፡፡ በተለይም ከሀገራችን ወቅታዊ የሰላም ሁኔታ አንፃር ሲታይ፣መድረኩ ወቅታዊና የጎላ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ጠቅላይ ምክር ቤታችን ይገነዘባል፡፡
ከጥቂት ወራት በፊት በሀገራችን አንዳንድ አካባቢዎች የታየው አለመረጋጋትና የተፈጠረው ግጭት፣ይህንንም ተከትሎ የደረሰው የህይወትና የንብረት ውድመት ሲታይ፣ ሰላም በምንም የማይተመን ዋጋ እንዳለው ያስገነዝበናል፡፡ የሰላም ዋጋ የሚታወቀው ሰላም የጠፋ ጊዜ ነው፣ የሚለውን አባባል በተግባር አይተናል፡፡ ሁላችንም እንደምናውቀው፣ በሀገራችን ባሳለፍናቸው ሁለት አስርት አመታት፣ አንፃራዊ ሰላም በመኖሩ በርካታ ለውጦችን ተመልክተናል፡፡ መልካምና ተስፋ ሰጭ የእድገትና የልማት ጅማሮዎች ታይተዋል፡፡ ይህም አንዱ የሀገራችን ተጨባጭ እውነታ ነው፡፡ በአንፃሩ ከእድገታችንና ከለውጣችን ጋር አብሮ መጓዝ ያልቻለ የኋላቀርነት አመለካከት፣ ድህነት፣ ብልሹ አስተዳደርና አመራር፣ ሙስና እና መሰል ሁኔታዎች በተቃራኒው የእኛ መገለጫዎች ናቸው፡፡
ይህ አይነቱ የተደበላለቀ ሁኔታም፣ አንዱ በሌላው ላይ የበላይነት ለመያዝ በሚደረግ ፍትግያ፣ በሀገራችን በአንፃራዊነት ሰፍኖ የነበረው ሰላማዊ ሁኔታ፣ በአንዳንድ አካባቢዎች ለመታወክና ለግጭት መፈጠር ምክንያት ሆኗል፡፡ በውጤቱም ሁሉንም ወገን ያሳዘነ ክስተት ተፈጥሮ አልፏል፡፡ ይህ አይነቱ ሁኔታ ዳግም እንዳያገረሽና እንዳይከሰት፣ በየደረጃው ያለን የሀይማኖት መሪዎች፣ ምዕመናንን የማስተማር ኃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል፡፡
በሰዎች ማህበራዊ ግንኙነት ውስጥ የሀሳብ ልዩነትና የሀሳብ ግጭት መኖሩ የሚጠበቅና ተፈጥሯዊ ነው፡፡ ይሁንና ዋናው ጉዳያችን መሆን ያለበት፣ ልዩነቱና ግጭቱ ለምን ተፈጠረ የሚለው ሳይሆን፣ ግጭቱ እንዴት እንደሚፈታ ማወቁ ላይ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የሀሳብ ልዩነቶች ላይ ተመስርቶ የሚፈጠር ግጭትና አለመግባባት፣ በሰከነ መንገድ በውይይት፣ በጥበብና በብልሃት መፈታት አለበት፡፡ ይህ ግጭትን በሰላማዊና በሰለጠነ መንገድ የመፍታት፣ የይቅርታና የእርቅ መንገድም በሀይማኖቶች የሚደገፍ ቅዱስ ስራ ነው፡፡ በመካከላችን እርቅና ሰላም እንዲሰፍንም፣ ፍትህ እንዳይጓደል መጠበቅና ፍትሃዊ መሆን ይገባል፡፡ ሁሉም ሃይማኖቶች ፍትህን በመጠበቅ፣ ግጭትንና ጥላቻን በይቅርታ ልብ ማከም እንደሚገባ ያስተምራሉ፡፡ እስልምናም ከዚህ አስተሳሰብ ጋር በእጅጉ ይስማማል፡፡ በብዙ የቁርአን አንቀፆችም ፍትህን፣ ይቅርታን፣ እርቅንና ሰላምን የተመለከቱ ግልፅ መመሪያዎች ሰፍረዋል፡፡

==================================

‹‹ልዩነቶችን በመነጋገር መፍታት የስልጣኔ ም ልክት ነው››

ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሱራፌል (የኢ/ካ/ቤ/ክ ሊቀጳጳስ)

በሃገራችን በተለያዩ የታሪክ ምዕራፎች ውስጥ መጠነ ሰፊ የሆኑ የውጭና የውስጥ ግጭቶችን ያስተናገድን ህዝቦች ብንሆንም የውጭውን ግጭቶች፣ ሃገራዊ ፍቅርን መሰረት ባደረገ፣ ጥበብ በተሞላበት ስልት በመከላከል፣ በአለም መድረኮች እስከ ዛሬ ስማችንን የሚያስጠራ ታሪክ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡ በሌላ በኩል በሃገር ውስጥ የሚነሱ ሃይማኖታዊም ሆነ ፖለቲካዊ ግጭቶች በተለያዩ ደረጃና ሁኔታዎች መፍትሄ እየተበጀላቸው ካለንበት ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡ የሃገራችን ህዝቦች ዘመናት ተሻግሮ እስከ ዛሬ ድረስ ህያው የሆነ ዘላቂ ሰላም ይገኝ ዘንድ የእርቅ ሂደቶች፣ ግጭቶችን የመፍታት ጥበብና ክህሎቶች ጠብቀው በማቆየት አስተላልፈውልናል፡፡ ይህ ጥልቅ የሆነ ሀይማኖትን መሠረት አድርጎ፣ ህዝቦችንና የሃገራችንን ሀብቶች ማክበር፣ የእለት ተእለት ኑሮአችን መርሆ ማድረግ ያለብን መልካም እሴት ነው፡፡
በሃገራችን ካለፈው አመት ጀምሮ የሰላም መደፍረስ አጋጥሞ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ሰላም ያልሰፈነበት ህብረተሰብ፤ ስለ ሁለንተናዊ የሰው ልጅ ብልፅግና፣ ግብረ-ገብነትና መልካም አስተሳሰብ በፅናት የመቆም አቅሙ ይዳከማል። ተያያዥ ውጤቱም ምድራዊና ሰማያዊ ድህነት ይሆናል፡፡
በሃገራችን ህዝቦቿ ምንም አይነት ልዩነት ሳይገድባቸው በጋራ ለሰው ልጆች ክብር፣ ለፍትህ፣ ለእውነት፣ ለነፃነትና ለፍቅር የቆሙ እንዲሆኑ አደራ እንላለን፡፡ በሃገራችን በተከሰተው ሁከትና ጠብ ሰለባ ሆነው ላለፉት ወገኖቻችን ከልብ እናዝናለን፡፡ የጠፋውም የአገር ሃብት የሚያስቆጭና የሚያሳዝን ነው። ለዚሁ ጥፋት ምክንያት የሆኑ ተግባራት ሁሉ ሊወገዙና ሊታረሙ ይገባል፡፡ ለወደፊት ተመሳሳይ ፈተናዎች ቢያጋጥሙን እንኳን ሰላማዊ በሆነ መንገድ፣ በውይይት የመፍታት ልምድ እንድናዳብር ከወዲሁ መሰራት እንዳለበት በታላቅ አፅንኦት አደራ እንላለን፡፡
ልዩነቶችን በሠላማዊ መንገድ በመነጋገር መፍታትም የስልጣኔ ምልክት ነው፡፡ ይህን የሚቃወም ወይም የሚያግድ አካልም መኖር የለበትም፡፡ ልዩነቶች በሰላማዊ መንገድ የማስተናገድ ልምድ እንዲኖረን፣ በት/ቤቶች የግብረገብና ስነምግባር ትምህርት ከመዋዕለ ህፃናት ጀምሮ መሰጠት እንዳለበት እምነታችን ነው፡፡

=================================

‹‹ሰላም የሁላችንንም ስምምነት ትፈልጋለች››

ፓስተር ፃድቁ አብዶ (የኢት/ወ/አ/ክ/ህ/ፕሬዚዳንት)

የሰላም ሕልውና በተለያዩ ምክንያቶች አደጋ ውስጥ ሊወድቅ ይችላል፡፡ በእግዚአብሔር አምሳል በተፈጠሩ ሰዎች መካከል የሚደረግ አድልዎ፣ ወገንተኝነትና ብሔርተኝነት፣ የመልካም አስተዳደር እጦት እንዲሁም የተለያዩ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መድልዎች የሰላምን እስትንፋስ በአጭሩ ሊቀጩት ይችላሉ፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አደጋ በትውልድ ላይ እንዳይወድቅ፣ የአገር መሠረት ከሆነው ቤተሰብ ጀምሮ ሰላምን በማስፈን፣ እውነቶች ላይ መነጋገርና ወደ ማኅበረሰብ ማዝለቅ ከእያንዳንዳችን ይጠበቃል፡፡
እርስ በርስ መከባበርን፣ መደማመጥንና ለሌላው የሚጠቅመውን ማሰብን፤ ይህንንም መልካም እሴት ኅብረተሰቡ በሃይማኖታዊ ግንኙነት፣ በማኅበራዊ ተራክቦውና በፖለቲካ አስተሳሰቡ ተግባራዊ እንዲያደርገው ማስተማርና ደጋግሞ ማስገንዘብ በብርቱ ይጠበቃል፡፡ በተለይ በአሁኑ ወቅት፣ የዓለማችን ሰላም በተለያዩ ምክንያቶች በመደፍረሱ፣ የሰው ልጆች ሕይወት ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ስጋት ላይ ወድቋል፡፡ ተፈጥሮ በምታስከትለው ቀውስና የሰው ልጆች በሚፈጥሩት ፀረ ሰላም ድርጊቶች፣ ሕዝቦች ሰላማቸውንና ነፃነታቸውን ተነጥቀው፣ ተንከራታችና ምውት ሆነው መመለከት ሲበዛ ኀዘን ላይ ይጥላል፤ ልብንም ይሰብራል፡፡
መቼም ጦርነትን ለመቀስቀስ ብዙ ልፋት አያስፈልግም፡፡ ጥቂት አሉታዊ ቃል መሰንዘር ይበቃል፡፡ ሰላምን ለማስፈን ግን እንደዚያ አይደለም፤ ብዙ ውይይት፣ ብዙ ትጋትና ብዙ መሥዋዕትነትን የሚጠይቅ ሂደት ነው፡፡ ከዚህም የተነሳ፣ ሰላም በአንድ ወገን መልካም ፈቃድ ብቻ የምትገነባ ሳይሆን የሁላችንንም ስምምነት የምትፈልግ ናት፡፡ ስለሆነም ማናችንም አስቀድመን በሰላም አስፈላጊነት ልናምን፣ አስከትሎም እውነተኛ በሆነ የአመለካከትና የሕይወት ለውጥ እምነታችንን ልንተረጉም ያስፈልጋል፡፡
ሰላም በሰው ልጅ ሕይወት ውስጥ መሠረታዊ ጉዳይ በመሆኑ፣ ክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ምድር የመምጣቱ ብሥራት በተነገረ ጊዜ፣ ከመላዕክቱ የምሥጋና ቃል ጋር የተላለፈውና፣ ‹‹ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን፣ ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ›› የተሰኘው መልዕክት፣ በዓለማችን ላይ የሰላም አስፈላጊነት የቱን ያህል ዋጋ እንዳለው ያመላክተናል፡፡ ስለሆነም የሰላም መልዕክተኞች ተብለን የምንጠራ የሃይማኖት አባቶች፣ በዚህ ዐቢይና ዋነኛ ጉዳይ ላይ አብዝተን እንድንሠራ የሰላም አለቃ ከሆነው ከእግዚአብሔር የተሰጠን ሃላፊነት በመሆኑ፣ ለሰላም መስፈን እንቅፋት የሆነውን ጉድፍ ነቅሰን በማውጣት፣ በሕዝባችን መካከል ፍፁም ሰላም የሚሰፍንበትን ጎዳና ልንተልም፣ ሰላምና እድገት በምድራችን ይሠፍን ዘንድም በተግባርና በጸሎት ሃላፊነታችንን ልንወጣ፣ አብዝተን ሰላምን እንደምንሻ ሁሉ የመጠበቅንም ትጋት አጥብቀን ልንፈልግ የእያንዳንዳችን ሃላፊነት መሆኑን ልንገነዘብ ያስፈልጋል፡፡

=================================

“ዘላቂ ሰላም የሚኖረው ሁሉም ለሰላም ሲሰራ ነው”
ፓስተር ተመስገን ቡልቲ (በሰባተኛው ቀን አድቬንቲስት
ቤ/ክ የኢትዮጵያ ዩኒየን ሚሽን ፕሬዚዳንት)

ፈጣሪ አምላካችን የሰላም አምላክ ነው፡፡ እንደዚሁም የፍትህ አምላክ ነው፡፡ ሰላምና ፍትህ ለአንድ ሀገር እድገትና ልማት ወሳኝ መሆናቸው አያጠያይቅም፡፡ በቅርቡ በሀገራችን ተከስቶ የነበረው የሰላም መደፍረስ አስከትሎት የነበረው አለመረጋጋት፣ የሰላም ዋጋ ምን ያህል ውድ እንደሆነ እንደገና እንድናስታውስ አድርጎናል፡፡ ሰላም ለሁሉም አስፈላጊና ጠቃሚ ቢሆንም ዘላቂ ሰላም ሊኖር የሚችለው፣ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በአንድነት ለሰላም ሲሰሩ ብቻ ነው። ሰላም አንድ አካል ብቻ በተናጠል ሊያስጠብቀው የሚችለው እሴት አይደለም። ይልቁንም ሁሉም አካላት የሚጠበቅባቸውን ድርሻ በትጋት፣ በቅንነትና ሌላውን በመረዳት ሲያበረክቱ ዘላቂ ሰላም ይሰፍናል። ስለዚህ የሀገራችንን ሰላም ዘላቂ በሆነ መልኩ ለማስፈን፣ መንግስትም ሆነ ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደዚሁም መላው የሀገራችን ህዝቦች፣ በፍቅርና በመቻቻል፣ ይቅር ተባብለው፣ ወደ ሰላም መድረክ ለመምጣት ዝግጁ መሆናቸው ወሳኝ ነው፡፡
ሰላም የሚወርደው “እኔ ያልኩት ብቻ ይሁን” በማለት እንዳልሆነ፣ ያለፈው ታሪካችን በግልፅ ያሳያል። መቻቻል፣ ተጨማሪ ምዕራፍ መሄድ፣ የመሸነፍ ሳይሆን የበሳልነት፣ የአመራር ብቃት ምልክቶች ናቸው፡፡ ስለዚህ ከመንግስትም ሆነ ከሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደዚሁም ከመላው የሀገራችን ህዝቦች፣ ይሄ ከመቼውም ጊዜ ይልቅ በአሁኑ ወቅት ይጠበቃል። የአመለካከት ልዩነቶች እንደተጠበቁ ሆነው፣ የጋራ ሀገራችንን ለማሳደግና ለማልማት፣ ሁሉን አቀፍ የሆነ ዲሞክራሲን ለማስፈን፣ በመቀራረብ፣ በልበ ሰፊነትና በይቅርታ መንፈስ፣ ሁሉም ወገኖች ለእርቅና ለሰላም እንዲሰሩ ጥሪ እናቀርባለን፡፡    

===============================


‹‹የችግሮቻችን መፍቻ ያለው በእኛው እጅ ነው››
ቄስ ዋቅስዮም ኢዶሣ (ዶ/ር) (የኢ/ወ/ቤ/ክርስቲያን መካነኢየሱስ ፕሬዚዳንት)


የሰው ልጅ ለዕለት ተእለት ኑሮውና ተግባሩ፣ ለእድገቱና ለደህንነቱ አስተማማኝ ሠላም መኖሩ እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ለግለሰብ፣ ለቤተሰብ፣ ለማህበረሰብ፣ በአጠቃላይ ለህብረተሰብ እንዲሁም ለሃገር እድገትና ብልፅግና ሰላም የሁሉም ነገር መሠረት ነው፡፡ በምንኖርባት ምድር ላይ ለሰላምና ስለ ሰላም ሲባል ትልቅ ዋጋ የሚከፈለው፣ የሰላም መደፍረስ ወይም እጦት የሚፈጥረው ቁስል ጥሎ የሚያልፈው የማይሽር ጠባሳን ለማስቀረት ነው፡፡
ባለፉት ጥቂት ወራት ህዝባችን ለመንግስት ሲያቀርብ ከነበረው የመልካም አስተዳደር ችግር ጋር ተያይዞ በሃገራችን የተለያዩ ቦታዎች የተከሰተው ግጭትና ሁከት ያስከተለው የሰው ልጅ ህይወት ማለፍና የንብረት ጥፋት፣ ምን ያህል የዜጎችን ልብ እንዳሳዘነና እንዳቆሰለ እንዲሁም ምን ያህል የሃገርን ሰላም እንዳወከ በቅርብ የምናስታውሰው ነው፡፡ ሃገራችን ኢትዮጵያ በብዙ አባቶችና እናቶች ያልተቋረጠ ትግልና መስዋዕትነት፣ ሰላሟ ተጠብቆ፣ ከዚህ የደረሰች አኩሪ የሰላም እሴት ያላት ሃገር ነች፡፡ ከእነዚያ አባቶችና እናቶች ጥንካሬና እግዚአብሄርም ከሰጣቸው ስኬት የተነሳ የተረከብናትን ይህቺን ሃገር፣ ለመጭው ትውልድ የማስረከብ ኃላፊነት የተጣለው አሁን ባለን ኢትዮጵያውያን ሁሉ ላይ እንደሆነ ግልፅ ነው፡፡ ይህንን ብርቱ ኃላፊነት ለመወጣት ዛሬም ተቀራርቦ መመካከርና ለጋራ ችግሮቻችን የጋራ መፍትሄ ማፈላለጉ ጊዜ የምንሰጠው ጉዳይ አይደለም፡፡ ሃገሪቱ የእኛ፣ እኛም የእኛ ስለሆንን፣ የራሳችንን ችግር ለመፍታት ከእኛ የተሻለ የምንጠብቀው ሌላ አካል የለም፡፡ የችግሮቻችን መፍቻ ያለው በእኛው በኢትዮጵያውያን እጅ ነው። በተለይም የሃይማኖት መሪዎችም ሆነ ተቋማት ግንባር ቀደም ተግባር ለእርቅና ለሰላም ግንባታ መስራት መሆን ይኖርበታል፡፡
በሁለት ወይም ከዚያ በላይ በሆኑ ግለሰቦች፣ ቤተሰቦች፣ ህዝብና መንግስት መካከል የሃሳብ ልዩነቶች መከሰታቸው የማይቀር ሃቅ ነው። እነዚህን ልዩነቶች የምናስተናግድበትም ሆነ የምንይዝበት መንገድ ግን ሊጠቅመን ወይም ሊጎዳን ይችላል፡፡ ስለዚህ የሃሳብ ልዩነቶችን ይዘን፣ በረጋ መንፈስና በማስተዋል መፍትሄ ካበጀንላቸው፣ ለአብሮነታችን፣ ለሰላማችንና ለእድገታችን መፋጠን ያላቸው ጠቀሜታ ከፍተኛ እንደሚሆን መገመት አያዳግትም።
ለዚህም ስራ ውጤታማነት የሁላችን የሆነችውን የሃገራችንን ሰላም፣ የህዝቦቿን አንድነት ለመጠበቅ፣ አባቶቻችን የተጠቀሙባቸውን የሽምግልና ዘዴዎች መዳሰስና መከተሉ ጠቃሚ ይመስለኛል፡፡ ያለፉ መልካም ምሳሌነት ያላቸው ልምዶቻችን፣ ወደፊት ለምንሰራቸው ስራዎች ኃይል ሆነውን አዲስ ታሪክን ለመስራት የሚቀሰቅሱን መሆን አለባቸው። ስለዚህ አኩሪ ታሪክን ከቀደምት ኢትዮጵያውያን እንደተረከብን ሁሉ፣ የእኛም ልጆች የሚኮሩበትና የሚጠቅሱት መልካም ታሪክ ለመስራት ጊዜው አሁን እንደሆነ አልጠራጠርም፡፡ እኛ በመልካም ነገር ስንነሳ፣ ፍቅር የተሞላው አምላካችን እግዚአብሔር፣ እንደሚረዳንና ስራችንን እንደሚባርክ እርግጠኛ ነኝ።

Read 3049 times