Saturday, 14 January 2017 15:45

በጠራራ ፀሐይ፣ በእንፋሎትና በነፋስ የሚወሰድ ብዙ ቢሊዮን ብር የድሃ አገር ሃብት!

Written by  ዮሃንስ . ሰ.
Rate this item
(6 votes)

“የእንፋሎት ሃይል”፣ “አሉቶ ላንጋኖ”... እየተባለ ሲነገርና ሲዘመር …ለስንት ዘመን ሰምተናል? … “ለስንት ዓመትስ ተፅፎለታል?” የሚል ጥያቄ ከጨመርንበትማ... ጉዳዩ የታሪክ ጥያቄ ይሆንብናል፡፡ ነገርዬው፣ ከሃያ ዓመት በላይ፣ ከሩብ ምዕተ ዓመት የዘለለ የረዥም እድሜ “ባለፀጋ” ነው፡፡ ሆኖታል። በመንግስት ቴሌቪዥንና ሬዲዮ ዘወትር የሚዘመርለት፤ በውሃና ኤሌክትሪክ ሚኒስትሩ ቀጥተኛ አመራር የሚካሄድ ፕሮጀክት ነው፡፡ ብዙ የብድርና የእርዳታ ገንዘብም ፈስሶበታል -  በመቶ ሚሊዮን ብሮች የሚቆጠር ገንዘብ!
“ለአሉቶ” ብቻ የተመደበው ተጨማሪ ብድር ደግሞ... 6 ቢሊዮን ብር ይደርሳል። ግን... እስካሁን፣ ለአመል ብልጭ የምትል የኤሌክትሪክ ሃይል አላየንም። አንዲት ብርጭታ እንኳ አይፈነጥቅም?
ዋናው አበዳሪ፣ የአለም ባንክ፣ ስለ አሉቶ ፕሮጀክት፣ እንዲህ ይላል።
1.    ፕሮጀክቱ ቅንጣት ፈቅ አላለም።
2.    ፕሮጀክቱ፣ ከመዘግየት አልፎ… ያለውጤት የመቅረት አደጋው “ከፍተኛ” ነው (High risk project)፡
ምክንያቱንም ሲያስረዳ፣ ጥልቅ ጉድጓዶችን በመቆፈር፣ በእንፋሎት አማካኝነት የኤሌክትሪክ ሃይል ለማመንጨት የሚደረጉ ሙከራዎች፣ በባህርያቸው አስቸጋሪ እንደሆኑ ይገልፃል ባንኩ። አንዳንዶቹ ፕሮጀክቶች፣ ቅንጣት የኤሌክትሪክ ፍንጣሪ እንኳ የማያመነጩ ይሆናሉ በማለትም ባንኩ “እንቅጩን” ተናግሯል፡፡ Ethiopia Geothermal Sector Development project – 2014 (ገፅ 18)።
የዓለም ባንክ፣ አስገራሚዎቹን አደጋዎችና ስጋቶችን ቢዘረዝርም፣ ለአሉቶ ፕሮጀክት ብድር ሰጥቷል። በእንፋሎት አማካኝነት ኤሌክትሪክ ለማመንጨት በማሰብ የተጀመረው የአሉት ፕሮጀክት፣ ቢያንስ ቢያንስ፣ 282 ሚሊዮን ዶላር (አሁን ባለው ምንዛሬ 6.2 ቢሊዮን ብር) እንደሚፈጅ ባንኩ ገልጿል። በእርግጥ ከዛሬ 15 ዓመት በፊት ጀምሮ፣ በአሉቶ አካባቢ ለተለያዩ ስራዎች ብዙ ገንዘብ ወጥቷል። ቀሪውን ለማሟላትም ነው፣ በአለም ባንክ አስተባባሪነት 126 ሚሊዮን ዶላር የተመደበው። ከጃፓን መንግስት ደግሞ 110 ሚሊዮን ዶላር ተጨማሪ ሌላ ብድር ይጠበቃል። (በሌላ አነጋገር፣ ከዚህ በፊት፣ 46 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ሆኗል (1 ቢሊዮን ብር መሆኑ ነው)።
126 ሚሊዮን ዶላር ብድር ከተፈቀደ ወዲህስ ምን ተሰራ? ምን ውጤት ተገኘ?
ምንም! ባለፈው ታህሳስ ወር የአለም ባንክ ያወጣውን የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ተመልከቱ።
አዎ፤ ተጨማሪ 10 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ተደርጓል (220 ሚሊዮን ብር!)። ሁለት የእንፋሎት ጉድጓዶችም ተቆፍረዋል። ግን፣ ጉድጓዶቹ፣ ኤሌክትሪክ ለማመንጨት የሚችሉ አይደሉም። እናም እስካሁን፣ ውጤታማ ስራ የለም ብሏል። ማን? “የስራ አፈፃፀም ሪፖርቱ”። በአጭሩ፣ ሁለት ጉድጓዶች ተቆፍረው እንደተመረመሩና ኤሌክትሪክ ለማመንጨት እንደማይችሉ መታወቁን ይገልፃል - ሪፖርቱ (Ethiopia Geothermal Sector Development Project Implementation Status & Results Report Seq No: 5: 19-Dec-2016  ገፅ 3)።
እንግዲህ፣ 26 ጉድጓዶች ይቆፈራሉ ተብሎ ነው የታሰበው። ምናልባት ከእነዚህ ውስጥ፣ ግማሾቹ ኤሌክትሪክ የማመንጨት አቅም ይኖራቸው ይሆናል የሚልም ነው - የፕሮጀክቱ ተስፋ። ግን፣ ቀደም ብለው ከተጀመሩት ጉድጓዶች፣ ምንም ውጤት አልተገኘም። ቀሪዎቹን ጉድጓዶች ለመቆፈር ስንት ዓመት እንደሚፈጅም እንጃ። የሚያውቅ የለም።
እንደ እቅዱ ቢሆን ኖሮማ፣ እስካሁን 12 ጉድጓዶች ተቆፍረው፣ 5 ወይም 6 ያህሉ ውጤታማ ይሆኑ ነበር። ፋብሪካ ተገንብቶም፣ በከፊል ኤሌክትሪክ ማመንጨት ይጀምር ነበር። በሁለት ዓመት ውስጥም፣ ሙሉ ለሙሉ ይጠናቀቅ ነበር። ግን፣ ሊሆን አይችልም። እና እስከ መቼ ይቆያል? አይታወቅም። የአለም ባንክም፣ አላውቅም ብሏል፡፡ ግን፣ እውን በሚቀጥሉት አራት እና አምስት አመታት፣ ጉድጓዶቹ ተቆፍረው ሊጠናቀቁ እንደማይችሉ ይታወቃል - የአለም ባንክ እንደሚለው ከሆነ።
ለነገሩ፣ በብዙ ቢሊዮን ብር ወጪ ጉድጓዶቹ ከተቆፈሩ በኋላም፣ “ብልጭ” የሚል ኤሌክትሪክ ላይገኝ ይችላል። ብልጭ ቢል እንኳ፣ ወዲያውኑ ድርግም ብሎ ሊጠፋ ይችላል። ድሮ... ከ20 ዓመት በፊት የተሰራውን የእንፋሎት ማመንጫ ጣቢያ የሚያስታውስ ሰው ይኖር ይሆን? ከጉድጓድ እና ከእንፋሎት ጋር፣... ያው ጠጠርና ዝገት መች ይጠፋል? ብዙም ሳይቆይ ማመንጫው ተበላሽቷል። በእርግጥ፣ ከስንት ዓመታት ጥገናና እድሳት በኋላ፣ እንደገና ስራ ጀመረ ተብሎ ለጥቂት ጊዜ ተዘምሮለታል፡፡ ግን፣ በግማሽ አቅሙ እንኳ፣ ኤሌክትሪክ ማመንጨት አልቻለም። ይህም ከአንድ ከሁለት አመት በላይ እንደማይዘልቅ የአለም ባንክ ሪፖርት ይጠቅሳል።
ነገሩን እናሳጥረውና፣ እስካሁን 1.2 ቢሊዮን ብር የወጣበትና፣ 6.2 ቢሊዮን ብር ይፈጃል ተብሎ የተጀመረው፣ “የእንፋሎት” ፕሮጀክት፣ በእነ ኢቢሲ የተወራለትን ያህል፣ ብዙም ቁምነገር አይታይበትም። አዎ፣ የሚፈጀው ገንዘብ በጣም እጅግ በጣም ከፍተኛ ነው - መሬት ስር ከታመቀው አስፈሪ እንፋሎት አይተናነስም። በእውን መሬት ላይ፣ “ምን ፈየደ?” ተብሎ ሲጠየቅ ግን፣ ... የነፈሰበት እንፋሎት ይሆንብናል - ብን ብሎ የሚጠፋ እንፋሎት።
በጠራራ ፀሐይ የሚጠፋ የድሃ አገር ሃብት!
ነገር መበላሸት የጀመረው፣ ከ20 ከ30 ዓመት በፊት ቢሆንም፣ ገንኖ የወጣው ግን ባለፉት 10 ዓመታት ነው። በአካባቢ ጥበቃ ቡድኖች ተፅእኖ የተነሳ፣ የአለም ባንክ፣ “ለግድብ ግንባታ፣ ብድር አልሰጥም” ብሎ የወሰነ ጊዜና፤ … ከዚያን ጊዜ ወዲህ፣ ነገሩ ሁሉ ቅዠት እየመሰለ ነው፡፡ ግን፣ ባንኩ፣ ብድር ከመስጠት አልቦዘነም። በግድብ ግንባታ ምትክ፣ ባለፉት 10 ዓመታት፣ ለእንፋሎት ጉድጓድ፣ እና... አዎ ለፀሐይ ኃይል...ብዙ ገንዘብ አበድሯል፡፡
ባለፉት ስድስት ዓመታት፣ ለ44ሺ ቤተሰቦች፣ በፀሐይ ሃይል የሚሰራ ኤሌክትሪክ ገብቶላቸዋል - በ20 ሚሊዮን ዶላር ተገዝቶ። ማለትም በ440 ሚሊዮን ብር (በአማካይ አንድ ቤተሰብ በ10ሺ ብር፣ የኤሌክትሪክ ሃይል ባለቤት ሆነ ማለት ነው)። በቃ፣ ገጠር ሁሉ በመብራት ደመቀ ማለት ነው። ከነስሙ “rural electrification” ተብሎ የለ?
ኢቢሲ ደግሞ “የብርሃን አብዮት” ብሎ እየሰየመው ይመስላል። በቃ፣ አንዴ ኤሌክትሪኩ ከገባ በኋላ፣ “ምንም ወጪ የለበትም” - ኢቢሲ እንደሚለው። እንደተለመደው … በነፋስ ኃይል፣ በእንፋሎት ኃይል፣ … በፀሐይ ኃይል ስለሚሰራ “ምንም ወጪ የለበትም” እያሉ ሌት ተቀን ይሰብካል፡፡
ይሄ አዲስ ነገር አይደለም፡፡ “በአካባቢ ጥበቃ ቡድኖች” የሚራገብ ፕሮፓጋንዳ ነው። ብዙ የኢቢሲ ጋዜጠኞች ደግሞ፣ ከአካባቢ ጥበቃ ቡድኖች ተደጋጋሚ ስልጠና አግኝተዋል። የመንግስት ፕሮፓጋንዳ ሲጨመርበት፣ ... አስቡት። በቃ፣ አንዴ ኤሌክትሪኩ ከገባ በኋላ፣ “ምንም ወጪ የለበትም” የሚል አደንዛዥ ፕሮፓጋንዳ ይግቱናል።
በፕሮፓጋንዳው ለመስከር ሳይሆን፣ እውነታን ለማወቅ ከፈለጋችሁ ግን፣ እውነተኛው መረጃ ይኼውላችሁ።
“የኤሌክትሪክ ሃይል (የSHS) ባለቤት ሆነዋል” የተባሉት 44ሺ ነዋሪዎችን ተመልከቱ። የሃያ ሺ ዎቹ ኤሌክትሪክ፣ ባለ 10 ዋት ነው (በተለምዶ፣ ባለ 10 ሻማ የምንለው ማለት ነው)። የድሮው አይነት አንድ አምፖል እንኳ ማብራት አይችልም። በሌላ አነጋገር “የአንዲት ትንሽ ቆጣቢ አምፖል ኤሌክትሪክ” ነው ለነዋሪዎቹ የደረሳቸው። ግን ይሁን። ከኩራዝ፣ አንዲት “ቆጣቢ” አምፖል ትሻላለች።
ግን፣ እሷም ለብዙ ሰዓት ትበራለች ማለት አይደለም። ሁልጊዜ፣ በቂ ፀሐይ አይኖርም። ጨለማ አለ፤ ዳመና አለ። ፀሐይ ሲኖርስ? … በባትሪ የሚጠራቀመው የኤሌክትሪክ ሃይል፣ ለተወሰነ ሰዓት ብቻ ነው የሚያገለግለው። ይሄም ይሁን፡፡ ነገር ግን፣ በዳመና ሳቢያ፣ በተደጋጋሚ የፀሃይ ሃይል ሲደበዝዝ፣ ባትሪው ለብልሽት ይጋለጣል። ባትሪ ብቻ ሳይሆን፣ በፀሐይ ሃይል የሚመነጨውን ኤሌክትሪክ ወደ ባትሪ የሚያስተላልፈው ተዛማጅ መሳሪያም እንዲሁ ይበላሻል።
ይሄንን እውነት የአለም ባንክም ሊክደው አልቻለም። እንዴት በሉ፡፡ የውሃና የኤሌክትሪክ ሚኒስቴር እንደሚገልፀው፤ በመጀመሪያው ዙር በፀሐይ ኃይል የሚሰራ ኤሌክትሪክ ያገኙ ቤተሰቦች 1100 ናቸው፡፡
ነገር ግን፣ የኤሌክትሪክ ባለቤት ለመሆን ከታደሉት፣ 1100 ቤተሰቦች መካከል፣ የ80ዎቹ ኤሌክትሪክ ወዲያውኑ ተበላሽቷል - በአብዛኛውም በባትሪና በተዛማጅ መሳሪያዎቹ ብልሽት ሳቢያ።
ግን፣ ብልሽቱ የእነዚህ ነዋሪዎች ብቻ አይደለም። እነዚህ፣ “ወዲያውኑ የተበላሸባቸው” ናቸው።
ሌሎች ነዋሪዎችም ተበላሽቶባቸዋል። የስንቶቹ ተበላሸ? የአብዛኞቹ ነዋሪዎች! የአለም ባንክ ራሱ፣ ይህንን አምኗል፡፡ እንዲህ ብሏል።
Indeed, investing in SHS... may not turn out to have been the best use of IDA funds. (የአለም ባንክን ገንዘብ፣ በእንዲህ አይነት ‘ኤሌክትሪክ’ ላይ ማዋላችን፣ በጎ እንዳልነበረ መታየቱ አይቀርም... ነገሩ አላማረኝም እንደማለት ነው።)
እንዴት መሰላችሁ። ለመጀመሪያዎቹ 1100 ቤተሰቦች ከተከፋፈሉት የኤሌክትሪክ መሳሪያዎች መካከል፣ የ1100 ያህሎቹ … ችግር ያለባቸው ናቸው። ይሄ አባባል ግር ይላል። ግን፣ አልተሳሳትኩም። ሁሉም መሳሪያዎች ችግር ነበረባቸው ለማለት ነው።
ባለፈው ዓመት የተለቀቀው የአለም ባንክ ሪፖርት፣ በገፅ 49 እንዲህ ይላል።
Under Solar home system (SHS) for households
• 1108 households electrified
እንዲህ ስኬቱን ከነገረን በኋላ ችግሮችን ይዘረዝራል፡፡
Problems
• Substandard items, especially 1108 households
ለስንት ቤተሰቦች ኤሌክትሪክ እንደተዳረሰ፣ በቁጥር እየተናገረ ስኬቱን አበሰረ። ከጥቂት መስመሮች በኋላ ደግሞ፣ ‘ጉዱን’ ይነግረናል። በፕሮጀክቱ ውስጥ ያጋጠሙትን ችግሮች ሲዘረዝር፣ በስንት ቤተሰቦች ችግር እንደተከሰተ ይጠቅሳል (በሁሉም ቤተሰቦች)።
አሁን፣ ኤሌክትሪክ የደረሳቸው ሰዎች፣ 44 ሺ ሆነዋል። ችግር የገጠማቸው ቤተሰቦች ቁጥርም በዚያው መጠን ጨምሯል። ለዚህም ነው፣ የአለም ባንክ፣ “የፕሮጀክቱ መጨረሻ አላማረኝም” ወደማለት ያዘነበለው።
ግን ችግር የለም። ለምን? የተበላሹትን ቁሳቁሶች ለማስቀየር፣ ሌላ ተጨማሪ ብድር እንደመደበ ባንኩ ባለፈው ሰኔ ወር ገልጿል።
250 ሚሊዮን ብር ብድር!
በ440 ሚሊዮን ብር ብድር ተገዝተው የተበላሹትን ቁሳቁሶች ለመቀየር፣ 250 ሚሊዮን ብር ብድር! ሩብ ቢሊዮን ብር።
ይህም ብቻ አይደለም። በየሶስት ዓመቱ፣ ተመሳሳይ ብድር ያስፈልጋል - እንደገና የሚበላሹ ቁሳቁሶችን ለማስቀየር!
የቅዠት ዘመን አይመስልም? ለእንፋሎት ኃይል … የቢሊዮን ብር ሀብት በከንቱ ይባክናል፡፡ ለፀሐይ ኃይል … የብዙ መቶ ሚሊዮን ብር ሀብት ይባክናል፡፡ 5 ቢሊዮን ብር በማይፈጅ የውሃ ግድብ የሚመነጭ አነስተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት የማይችሉ የነፋስ ተርባይኖችን ለመትከል፣ 17 ቢሊዮን ብር እንደወጣም አስታውሱ፡፡ ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ ሀብት በከንቱ በነፋስ ተወሰደ እንደማለት ነው፡፡
በዚህ መሃል ነው፤ ኢቢሲ “የብርሃን አብዮት” የሚል መፈክር ይዞ የመጣው።
በቃ፣ አንዴ ኤሌክትሪኩ ከገባ በኋላ፣ “ምንም ወጪ የለበትም” - ይላል ኢቢሲ።
አለማወቅ ነው? ደንታ ቢስነት ነው? ቅዠት ነው? ወይስ ወንጀል?



Read 1918 times