Saturday, 14 January 2017 15:50

በ31ኛው ቶታል የአፍሪካ ዋንጫ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

• አዘጋጇ ጋቦን በቀውሶች ታጅባ ዋንጫውን ማስቀረት ትፈልጋለች
• ኮትዲቯርና ሴኔጋል ከምእራብ ግብፅና አልጄርያ ከሰሜን አፍሪካ ተጠብቀዋል፡፡
• በቶታል ስፖንሰርሺፕ የሽልማት ገንዘብ አድጓል፡፡
• አፍሪካዊ አሰልጣኞች 4 ብቻ ናቸው፡ሸ
• የ16ቱ ብሄራዊ ቡድኖች ተጨዋቾች በዝውውር ገበያ 992.35 ሚሊዮን ዩሮ ያወጣሉ፡፡
• በአውሮፓ ሊጎች የሚጫወቱ ከ150 በላይ ተጨዋቾች ይገኙበታል፡፡


31ኛው ቶታል የአፍሪካ ዋንጫ በምእራብ አፍሪካዋ  ጋቦን አስተናጋጅነት  ይጀመራል፡፡ በከፍተኛ የኢኮኖሚ እና ፖለቲካ ቀውሶች በመታጀብ መስተንግዶዋን የጨረሰችው ጋቦን ዋንጫውን ለማስቀረት ትፈልጋለች፡፡ በ2017 የአፍሪካ ኮከብ ተጨዋች ሆኖ የተመረጠው ፒዬር ኤምሪክ ኡብምያንግ አገሩን ውጤታማ እንደሚያደርጋት ተስፋ ተጥሎበታል፡፡
ጋቦን በቀውሶች ታጅባ የሰነበተችው ከነዳጅ ዋጋ መውረድ ጋር በተገናኘ ነው፡፡ ይህም የአገሪቱ ህዝብ ለአህጉራዊ ሻምፒዮናው የነበረውን ጉጉት አቀዝቅዞታል፡፡ የአፍሪካ ዋንጫ ሊጀመር አንድ ሰሞን እየቀረው ጨዋታዎችን የሚያስተናግዱት አራት ዋና ዋና ስታድዬሞች በማጠናቀቂያ ስራዎች መጠመዳቸው በሚዲያዎች ሲተች ሰንብቷል፡፡   አስተናጋጆቹ ከተሞች ዋና ከተማዋ ሊበርቪል፤ በሰሜናዊ ክፍል የምትገኘው ኦዬም፤ የደቡብ ምስራቋ ፍራንስ ቪል እና የነዳጅ መዲና የምትባለው ፖርትጄንቲል ናቸው፡፡ በእነዚህ ከተሞች ጋቦን ለአፍሪካ ዋንጫው መስተንግዶ 5 ስታድዬሞች እና 6 መለስተኛ የልምምድ ስታድዬሞችን ያዘጋጀች ሲሆን ሁለት ስታድዬሞች በቻይና ኩባንያዎች አዲስ የተገነቡ እና እያንዳንዳቸው 20ሺ ተመልካቾች የሚያስተናግዱ ናቸው፡፡ 1.8 ሚሊዮን የህዝብ ብዛት ያላት ጋቦን ከምእራብ አፍሪካ አገራት በተለይም ከሴኔጋል፤ ከቡርኪናፋሶ እና ከካሜሮን የሚፈልሱ ስደተኞች መናሐርያ በመሆኗ ትታወቃለች፡፡ በ2012 እኤአ ላይ 28ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ከኢኳቶርያል ጊኒ ጋር በጣምራ ማዘጋጀቷም  ይታወሳል፡፡
ዘንድሮ የአፍሪካ ዋንጫውን ልዩ ከሚያደርጉ ሁኔታዎች ዋንኛው የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ከቶታል ኩባንያ ጋር በፈፀመው ግዙፍ የስፖንሰርሺፕ ውል የሽልማት ገንዘቡን በየደረጃው በማደጉ ነው፡፡ ካፍ እና የፈረንሳዩ የነዳጅ እና ጋዝ አምራች ዓለም አቀፍ ኩባንያ ቶታል ለስምንት የውድድር ዘመናት በ1 ቢሊዮን ዶላር በፈፀሙት ውል መሰረት ነው፡፡ ይህም ቶታል የአፍሪካ ዋንጫ በሚል ውድድሩ እንዲሰየም አድርጎታል። በሽልማቱ ዝርዝር አከፋፈል መሰረት የዋንጫ አሸናፊ 4 ሚሊዮን ዶላር የሚያገኝ ሲሆን፤ ለሁለተኛ 2 ሚሊዮን ዶላር፤ ግማሽ ፍፃሜ ለሚደረሱ አራት ብሄራዊ ቡድኖች ለእያንዳንዳቸው 1.5 ሚሊዮን ዶላር፤ ለጥሎ ማለፍ የሚደርሱት 8 ብሄራዊ ቡድኖች ለእያንዳንዳቸው 800ሺ ዶላር፤ በየምድባቸው በሶስተኛ ደረጃ ለሚያጠናቀቁት ቡድኖች ለእያንዳንዳቸው 575ሺ ዶላር ይታሰብላቸዋል። በአፍሪካ ዋንጫ በመሳተፋቸው ብቻ 16ቱ ብሄራዊ ቡድኖች በነፍስ ወከፍ 475ሺ ዶላር እንደሚከፈላቸውም ታውቋል፡፡
በ16ቱ ብሄራዊ ቡድኖች አፍሪካዊ ዜግነት ያላቸው አሰልጣኞች አራት ብቻ ሲሆኑ፤ እነሱም የዲ ሪ ኮንጎው ፍሎረንት ኢቢንጌ፤ የሴኔጋሉ አሊዩ ሲሴ፤ የጊኒ ቢሳዎው ባኪሮ ካንዴ እና የዚምባቡዌው ካሊስቶ ፓስዎ ናቸው። በሌሎቹ 12 ብሄራዊ ቡድኖች አንዱ ብቻ አርጀንቲናዊ ዜግነት ሲኖራቸው የተቀሩት በአውሮፓዊ አሰልጣኞች የሚመሩ ይሆናሉ፡፡ ከአውሮፓዊ አሰልጣኞች 4 ፈረንሳዊ፤ 2 ቤልጅማዊ እንዲሁም እስራኤል፤ ስፔን፤ ፖላንድ፤ ፖርቱጋልና ሰርቢያ እያንዳንዳቸው በ1 የተወከሉ ናቸው።
ከአፍሪካ ዋንጫው ጋር በተያያዘ ከ150 በላይ ፕሮፌሽናል ተጨዋቾች ከአውሮፓ እና ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች በጋቦን የየአገሮቻቸውን ማልያ በመታጠቅ የሚገኙ ሲሆን 69 ከፈረንሳይ፤ 29 ከእንግሊዝ፤ 25 ከፖርቱጋል፤ 20 ከቱርክ እንዲሁም 19 ከስፔን ክለቦች ናቸው፡፡ በታዋቂው የዝውውር ገበያ ትምና  ድረገፅ ትራንስፈርማርከት መሰረት በ16ቱ ብሄራዊ ቡድኖች የሚገኙት ተጨዋቾች በ992.35 ሚሊዮን ዩሮ የሚያወጡ ናቸው፡፡  ከተጨዋቾቹ በውድ የዝውውር ገበያ የዋጋ ተመኑ አንደኛ ደረጃ የተሰጠው የአዘጋጇ ጋቦን ወሳኝ ተጨዋች የሆነውና በጀርመኑ ክለብ ቦርስያ ዶርትመንድ የሚጫወተው ኦቡሚያንግ በ45 ሚሊዮን ዩሮ ሲሆን፤ የሴኔጋሎቹ ካሊዲዮ ኩሊባሊ እና ሳድዮ ኤማኔ፤ የግብፁ መሀመድ ሳላህ እና የአልጄርያው በ30 ሚሊዮን ዩሮ ይከተሉታል፡፡
በ31ኛው ቶታል የአፍሪካ ዋንጫ የሻምፒዮንነት ግምት ከተሰጣቸው አገራት የምእራብ አፍሪካዎቹ አይቬሪኮስት እና ሴኔጋል እንዲሁም የሰሜን አፍሪካዎቹ ግብፅ እና አልጄርያ ዋናዎቹ ናቸው፡፡ የወቅቱ የአፍሪካ ኮከብ ተጨዋች ፒዬር ኤምሪክ ኡቡምያንግ፤ የወቅቱ የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ አፍሪካዊ ኮከብ ተጨዋች ሪያድ ማህሬዝ እንዲሁም ሴኔጋላዊው የሊቨርፑል ክለብ ጨራሽ አጥቂ ሳዲዮ ኦማኔ ለኮከብነት እጩ ከተደረጉት ይጠቀሳሉ፡፡ አይቬሪኮስት ሻምፒዮንነቷን እንድታስጠብቅ  በአምበልነት የሚመራት ያያ ቱሬ፤ በአሁኑ ግዜ ክለብ የሌለውና ቶጎን በአምበልነት ይዞ የሚሳተፈው ኢማኑዌል አደባዬር እንዲሁም ሁለት የአፍሪካ ዋንጫዎች ካለፏት በኋላ ወደ ውድድሩ የተመለሰችውን ግብፅ በመመራት በ43 ዓመቱ ግብ ጠባቂ የሚሆነው ኦሳም ኤል ሃድሪ  ከአንጋዎቹ ትኩረት የሳቡት ናቸው፡፡
በ31ኛው ቶታል የአፍሪካ ዋንጫ በምድብ 1  አዘጋጇ ጋቦን፣ ቡርኪናፋሶ፣  ጊኒ ቢሳዎ እና ካሜሮን ፤ በምድብ 2 አልጄርያ፣ ሴኔጋል፣ ቱኒዚያ እና ዚምባቡዌ፤ በምድብ 3 ዲ.ሪ ኮንጎ፣ አይቬሪኮስት፣ ሞሮኮና ቶጎ እንዲሁም በምድብ 4 ግብፅ፣ ጋና፣ ማሊና  ዩጋንዳ ተደልድለዋል፡፡








Read 1211 times